በዘር የሚተላለፍ የኮሌስትሮል ህመም (የፋሚሊያል ሃይፐርኮሌስትሮሌሚያ, Familial Hypercholesterolemia, FH) በጣም ከፍተኛ የኮሌስትሮል መብዛት የሚያመጣና ለልብ ህመም የሚያጋልጥ የተለመደ በዘር የሚወረስ በሽታ ነው። ሮጠው ያልጠገቡ ልጆችን እና ወጣቶችን በልብ ህመም የሚያሰቃይ ህመም ሲሆን በጊዜ ካልታከመ ገዳይ በሽታ ነው።
በአለም አቀፍ ደረጃ ከ300 ሰዎች አንዱን እንደሚያጠቃ የተረጋገጠ ሲሆን በዘር ከሚወረሱ የሜታቦሊክ ህመሞች በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው። በሃገራችን ኢትዮጵያም ይህ በሽታ እንዳለ ማረጋገጫዎች ቢኖሩም የህመሙን ስፋት ከ100 ሺህ በላይ ሰዎችን ሊይዝ እንደሚችል ከመገመት ውጭ በውል አይታዎቅም።
ይህንን አስከፊ ህመም ለማከም እያንዳንዱ ሰው ማገዝ ይችላል! እንዴት ቢባል የህመሙን ምልክቶች በራስ፣ በቤተሰብ አባላት፣ በጓደኞች ወይም በስራ ቦታ ላይ በመመልከት እና በመለየት ለትክክለኛ ምርመራ እና ህክምና ወደጤና ተቋም እንዲሄዱ በማበረታታት ህይወት አድን ስራ ሊሰሩ ይችላሉ።
ማንም ሰው ሊያያቸው የሚችላቸው የህመሙ ምልክቶች እነዚህ ናቸው፡
- በቆዳና ጅማት ላይ የሚወጡ ቢጫማ እብጠቶች (xanthoma) ዋነኛ የህመሙ ምልክቶች ናቸው። እነዚህ እባጮች በቁርጭምጭሚት አካባቢ የተረከዝ ጅማት (ቋንጃ) ላይ፣ በጉልበት፣ በእጆች ወይም ክርን ላይ ሊወጡ ይችላሉ። በአይን ዙሪያም (xanthelasma) ሊወጡ ይችላሉ። እነዚህ እብጠቶች በቀላሉ የሚታዩ ቀለማቸው ቢጫማ ሲሆን ኮሌስትሮል በቆዳና ጅማት ውስጥ ሲከማች የሚመጡ ናቸው።
- የአይን መስታውት ዙሪያ ላይ የሚወጣ ቀለበቶች (arcus cornealis) ሌላኛው የኮሌስትሮል ህመም መገለጫ ሊሆን ይችላል። ይህ ነጭ ወይም ግራጫ ቀለም ያለው ክብ መሰል ሲሆን ኮሌስትሮል በአይን መስታወት ዳርቻ ላይ ሲከማች የሚፈጠር ነው። በአብዛኛው በአረጋውያን ላይ ከእድሜ ጋር ተያይዞ የሚታይ ሲሆን ከ45 ዓመት በታች በሆኑ ሰዎች ላይ ሲታይ የኮለኢስትሮል ህመም ምልክት ነው።
- ከቤተሰብ አባላት ውስጥ በወጣትነታቸው ከ50 አመት እድሜ በፊት ድንገተኛ የልብ ድካም (heart attack) ወይም ስትሮክ (stroke) ያጋጠመው ካለም እንዲሁ የዚህ የኮሌስትሮል ህመም ምልክት ሊሆን ይችላል።
- ለሌላ አጠቃላይ የጤና ምርመራ ሲሰራ ከፍተኛ የኮሌስትሮል መብዛት ከተገኘም እንዲሁ የፋሚሊያል ሃይፐርኮሌስትሮሌሚያ ሊሆን ይችላል።
ይህን ህመም ማወቅና ተጠቂዎችን በቶሎ መለየት ለምን አስፈለገ?
በቅድመ ምርመራ፣ ትክክለኛ ህክምና እና የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች ይህ በዘር የሚወረስ የኮሌስትሮል ህመም ያለባቸው ሰዎች ረጅም እና ጤናማ ህይወት ሊመሩ ይችላሉ። እነዚህን ቀላል ምልክቶች በማወቅ በማህበረሰባችን ውስጥ የዚህ ህመም ተጠቂዎችን የልብ ድካም ሳይዛቸው አስቀድሞ መታከምና መከላከል ይቻላል።
በዘር የሚተላለፍ የኮሌስትሮል ህመም በመለየት በወጣትነት የሚመጣን የልብ ድካም ለመከላከል የሚደረገውን ሃገራዊ ጥረት እናግዝ። ይህን ማድረግ እንዲያስችለን በሚኖሩበት፣ በሚሰሩበት ከባቢ ውስጥ የፋሚሊያል ሃይፐርኮሌስትሮልሚያ (FH) ምልክቶችን ይወቁ! ለሌሎችም ያሳውቁ።
ይህንን መረጃ ከቤተሰብ፣ ከጓደኛ እና ከጎረቤት ጋር ያካፍሉ።
ማስታወሻ፡ በዚህ ጽሁፍ የተካተቱት ይዘቶች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና የጤና ባለሙያዎን ያማክሩ።
ይህ መረጃ ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኙት ተስፋ አደርጋለሁ! ተጨማሪ ጥያቄዎች ካሉዎት የዚህን መረጃ ያሰናዳዉን ዶ/ር መላኩ ታዬ እና የስራ ባልደረቦቹን በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል ማግኘት ይችላሉ። ውድ የሆነውን ጤናዎትን ለመጠበቅ ምን ማድረግ እንዳለብዎት ለማዎቅ ተጨማሪ ተግባራዊ ምክሮችን በዶ/ር መላኩ ድህረ ገጽ www.melakutaye.com እና ማህበራዊ ሚዲያዎች @hakimmelaku ይከታተሉ!
ሰላም ዶክተር ቤተሰብ ማንም ሰዉ እስከ አያቴ ድረስ ምንም ሰዉ ኮልስትሮል የለባቸዉም እኔ ግን አሁን ላይ ምርመራ ሳደርግ ኮልስትሮል ከመደበኛ በላይ ነዉ አሉኝ ሀኪሞቹ የመከሩ እንቅስቃሴ እንዳረግ ነዉ እና ሁሌም ጠዋትና ማታ ስፖርት እየሰራሁነዉ መመገብ የሌለብኝን ምግብ አቁሚያለሁ ተጨማሪ ምን ማድረግ አለብኝ ትላለህ ዶክተር
በመጀመሪያ የኮሌስትርል መዛባት ህመሙ አይነትና መነሻው ምንድን ነው የሚለውን ማወቅ ይፈልጋል። የኮሌስትሮል ህመም አይነቱ ከተለየ ምን አማራጭ ህክምና እንዳለው መፈለግ ይቻላል። ይህን ማድረግ እችል ዘንድ በአካል መወያየት እ፣እክራለሁ። የሚመችዎት ከሆነ ከዚህ በታች በተጠቀሰው አድራሻ በቀጠሮ መመካከር ይቻላል።
Dr. Melaku’s clinic schedule (October to November 30, 2024)
Private clinic
1. Heal Venture medical center
🕐 Monday, & Wednesday afternoon.
Book at +251926454647
Address: Megenagna 24 area infront of Sidra Hotel.
ከለም ሆቴል ወደ 24 የሚወስደዉን ድልድይ እንደጨረሱ በመጀመሪያው መታጠፊያ ወደ ቀኝ 50ሜ ገባ ብሎ።
📍Location- https://maps.app.goo.gl/1j52DhHCnxQ2bwgm6?g_st=i
2. Gesund Medical & Cardiac center
🕑 Wednesday & Saturday morning.
Book at +251994000095
0955927583
Location: near CMC Michael
https://maps.app.goo.gl/e8XngmFG3EP5U2DDA
Public hospital
1. Tikur Anbessa Specialised Hospital, Addis Ababa University
💚💛❤️
Melaku Taye, M.D.
Let us connect at Blog (https://melakutaye.com/) | TikTok (https://www.tiktok.com/@hakimmelaku) | Telegram (https://t.me/hakimmelaku) | Google Profile (https://g.page/r/CaCoYXX0TnQrEBE/review)