የጤናሙያን ክብር ለማስመለስ የአወንታዊ ታሪኮች ሚና

እስቲ አስቡት ቀን ቀን ህይወትን ለማዳን፣ ማታ ኪራይ ለመክፈል ሲታገል – የጤና ባለሙያው። ለራሱ ተንከባካቢ የሌለው ባለሙያ ከፍተኛ ሙያዊ ጥንቃቄና ብቃት የሚያስፈጋቸውን ታካሚዎችን መንከባከብ አስበው፤ ኑሮ ያቆሰለው ባለሙያ የቆሰለን ሲፈውስ! አሰልፎ መርፌ ሲወጋ የዋለ ባለሙያ ማታ በድካም ስሜት ለአንበሳ ባስ እግሩ እስኪሰል ሲሰለፍ!

 

የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች በአለም ዝቅተኛ ክፍያ ከሚከፈላቸው የህክምና ባለሙያዎች መካከል ይጠቀሳሉ። የምን መካከል ማለት ነው? ማንጆ ነን እንጅ! ከቀደምቶቹ ስመጥር ሃኪሞቻችን ጀምሮ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ለኢትዮጵያዊያን ጤና በማያወላውል ቁርጠኝነት እያገለገሉ ቢሆንም የአሁኖቹ ባለሙያዎች መሰረታዊ የኑሮ ፍላጎትን ማሟላት የማይችሉበት ዘመን ደርሰናል። ጥሪት ማፍራትና ቤተሰብ መርዳትማ ላም አለኝ በሰማይ የማይደረስ ህልም ሆኖ ቆይቷል። በቅርቡ ትዊተር ላይ የሰውን ልብ እንደመዳፉ የሚያገላብጥ የልብ ሰርጅን ‘እኔም ለልጆቼ መቦረቂያ የሚሆን ቤት አንድ ቀን ይኖረኛል’ ብሎ ሲጽፍ እንኳን ለእንደኔ አይነት ለወጣኒዎቹ ለጉምቱዎቹም የማይቻል እንደሆነ አርድቶናል።

 

በዚህ ምክንያት ብዙዎች ብስጭታቸውን በማህበራዊ ድረ-ገጾች እንዲገልጹ አድርጓቸዋል። በአለም ላይ በጣም ደካማ በሆነው የኢትዮጵያ ጤና ስርዓት ውስጥ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚያገለግሉት የጤና ባለሙያዎች ክፍያና የኑሮ ሁኔታ ይሻሻልልን የሚሉ የትግል ድምጾች እየጨመሩ መጥተዋል። ነገር ግን እነዚህ ‘የህዝብ ይወቅልን’ ጩኸቶች ከሰፊው ማህበረሰብ ድጋፍ ከማግኘት ይልቅ ያልተጠበቀ ምላሽ አስከትሏል። ‘ይበላችሁ!’ አይነት መሳለቂያነት ወደመቀየር አሳሳቢ የሆነ አዝማሚያ ታይቷል። ሁሉም የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች የከፈሉትና አሁንም እየከፈሉ ያሉት መስዋዕትነት እና አስተዋጾ የማይናቅ እንደመሆኑ መጠን ይህንን ጸሃይ የሞቀዉን የድህነት ኑሯቸውን ገሃድ አውጥተው በማሳየታቸው መዘባበቻ ማድረግ እንደማህበረሰብ ልክ አይመስልም። እንዲያው በርኅራኄ ‘አይዟችሁ፣ በርቱ፣ ያልፋል’ አንደማለት ባለሙያዉን ዞሮ መውቀስና ማዋረድ በባለሙያዎቹ ዘንድ ያለውን የተስፋ መቁረጥ ስሜት ያባብሰዋል።

 

ይህ የኑሮ ጫና ከደሞዝ ማነስ ጋር ብቻ የተገናኘ አይደለም። ማህበረሰቡ ራሱ ጎረቤትህ ዶክተር ነኝ ስትለው የሌለ ይጠብቅብሃል። አሁን ባለፈው በትርፍ ሰአት የምሰራበት ክሊኒክ ሲታከም የነበረ ደንበኛዬ በህክምና ውይይታችን መሃል ከኪሴ ሶፍት ለማውጣት እጄን ስሰድ ጭርምት ያለች የባስ ትኬት ሲወድቅ አይቶ ‘ወይኔ.. ዶክዬ በጣም ይቸግርሃል እንዴ በባስ የምትጠቀመው? በል በቃ ባይሆን ዛሬ በራይድ ሂድ’ ብሎ ከምርመራ ዋጋ ላይ የተመለሰለትን ብጫቂ ገንዘብ አልወረወረለኝም! በባስ መሄድ አይመጥንህም እያለኝ ነው። የብዙሃን ትራንስፖርት መንገዶች መጠቀም እንደሃገር የሚበረታታ እንጅ የድህነት ምልክት መሆን አልነበረበትም። የሆነ ጊዜ ዲያስፖራዎች ለገና ወደእናት ሃገር ኢትዮጵያ የተመሙ ጊዜ – እንዲያ ቂን ቂን ያረጋቸው ጊዜ! አንዷ ዲያስፖራ ‘ዶክተርዬ አመድህ ቡን ብሏል እኮ? እንካ ይችን ሎሽን ተቀባ’ ብላ የአንድ ዶላር አንባሬጭቃ አልሰጠችኝም! ዶክተር ስትሆን ፊትህን ተወልውለህ ውጣ ማለትም አይደል! ታክሲ ላይማ ስንቱ ‘ለዚያ ጋቢና ላለው ዶክተር ተከፍሏል በለው’ እያሉ ለዴች የተመጻደቁብኝ ቤት ይቁጠራቸው። የራሳቸው ክሊኒክ ወይ ሆስፒታል ያላቸው ጉልበተኛ (bully) ባልደረባዎችማ አይጣል ነው። በቀደም እለት ከመንግስት የስራ ሰአት በኋላ ወደ ‘ሱቅ’ በእግሬ ሰከም ሰከም ስል የራሴው የምለው ጓደኛዬ በኮልኮሌው ጎርፍ አከናንቦኝ አልሄደም?! በዚህ አልበቃ ብሎት ‘ኧረ እግርህ እንዳይሰበር የአጥንት ቫይታሚን ውሰድበት’ ብሎ አስታቀፈኝ።  በእግር መጓዝ አልተቻለምኮ! ማህበረሰቡ ራሱ ደሞዝህን እንድትጠላ፣ እንደቤትህ እንዳትኖር ያደርግሃል ስልሕ።

 

ይህ የኑሮ ጫና ከደሞዝ ማነስ ጋር ብቻ የተገናኘ አይደለም። የችግሩ መነሻዎች ጥልቅና ውስብስብ ናቸው። ኢትዮጵያ ልክ እንደሌሎች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት የጤና ሥርዓቱ በቂ ገንዘብ አይበጀትለትም። መንግሥት ለህክምና ባለሙያዎች ተወዳዳሪ ደመወዝ መስጠት ቀርቶ ለህክምና የሚውሉ አላቂ ቁሳቁሶችን ማሟላት አይችልም። በዚህም ዶክተሮች እራሳቸውን እና ሙያቸውን በሚያሳዝን ሁኔታ ውስጥ ያገኙታል። በእውቀታቸው እና በክህሎታቸው በጣም የተከበሩ ናቸው፤ ነገር ግን የባንክ አካውንታቸው ይህንን አክብሮት አያሳይም። ይህ ችግር ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ ሌሎችን ለማዳን ሕይወታቸውን የሰጡ ባለሙያዎችን ሞራልና የስራ ተሳሽነት ላይ ከባድ የስነ-ልቦና ጫና አለው። ወደፊት የህክምና ሙያተኛ መሆን ለሚፈልጉ ልጆችና ታዳጊዎችም ‘ኧረ ይሄስ ይቅርብኝ፣ ቲክታክ ላይ ብሸቅል ይሻላል’ እንዳይሉ ያስፈራል። አሁን የህክምና ትምህርት ላይ ያሉት የወደፊት ተስፋዎቻችንን ወኔና ሞራል አንዳይነካ መጠንቀቅ ያሻል።

 

ዶክተሮች ስለሚሠሩበት አስቸጋሪ ሁኔታ ‘የስልጣን ባለቤት ለሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ’ ማሳወቅ አስፈላጊ ቢሆንም ድህነትን በይፋ ማውጣት አደጋዎች አሉት። የሕዝቡ ምላሽ በተለይም ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚወራው አሳሳቢ ሆኗል፣ ራሱን ተጎዳሁ ባይውን መልሶ መውቀስ እየበዛ መጥቷል። የጤና ባለሙያዎች ለችግሮቻቸው ተጠያቂ እራሳቸው ብቻ ናቸው ባዮች በዝተዋል።

የጤና ባለሙያዎቹ ችግሮቻቸውን ሲገልጹ ለራሳቸው ለግል ጥቅማቸው ብቻ ሳይሆን ችግር ውስጥ ስለወደቀው አጠቃላይ የጤና ሥርዓት የሚናገሩ ቢሆኑም ብዙውን ጊዜ የህዝብ ምላሽ ወደ ተጎጂውን አዙሮ ወቀሳ (Victim blaming and shaming) ይመራሉ። ‘አውቀህ የገባህበት ነው፣ ዋናው ‘እርካታ ነው’ ብሎሃል ጠሚው፣ ህክምና የቅድስና ስራ እንጂ ገንዘብ መስሪያ አይደለም …’ የመሳሰሉ ማህበረሰባዊ ምላሾች በአጠቃላይ የጤናው ስርአት ጉድለቶችን ችላ ይሉ እና በመጨረሻም ዶክተሮችን ወደሌላ አቅጣጫ የበለጠ ይገፋሉ።

እኛም ድምጻችንን የምናሰማበት መንገድ መቀየር አለበት። እውነተኛ ለውጥ ለመፍጠር ትርክቱ ድህነትን ከማስጣት ወደ ስኬትን ብሮድካስት ማድረግ መሸጋገር አለበት። ተጽእኖ ፈጣሪ አዎንታዊ የስኬት ታሪኮች ላይ በማተኮር የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎችን ብርና ክብር መመለስ ይቻላል።

 

ትርክታችንን እንዴት እንቀይር? አወንታዊ ታሪኮችስ ምን ፋይዳ አላቸው?

 

የስኬት ታሪኮችን ማካፈል መተማመንን ይገነባሉ። ህብረተሰቡ ዶክተሮችን እንደ ጎስቋላ ተቀጣሪዎች ሳይሆን እንደ ታታሪ ለውጥ የሚያመጡ ባለሞያዎች ሲያያቸው ህይወቱን በመረዳት የሃኪሙን ድምጽ ይደግፋሉ። ተግዳሮቶችን ተሻግረዉ ያሸነፉ፣ የማህበረሰብ ጤና ቀያሪ ፕሮጀክቶችን ያስመረቁ ወይም ጉልህ የሆነ የጤና እመርታ ያስመዘገቡ ዶክተሮችን ታሪክ ማካፈል ተስፋን ያበራል፤ በዶክተሮች እና በህዝቡ መካከል ያለውን ግንኙነት ዳግም ያድሳል። ስለዚህ በማህበራዊም ይሁን ሜይንስትሪም ሚዲያ የሚንሸራሸሩ የህክምና ዜናዎች የባለሙያዉን ስኬት የሚያጎላ ይሁን። ከግለሰብ ስኬቶች እስከ ማህበረሰብ አቀፍ የጤና ቱሩፋቶች ሲዘገቡ የህዝቡን ግንዛቤ ለማስተካከል ይረዳሉ። በስኬት ትርክታችን ውስጥም ታካሚዎችን እና አጠቃላይ ህዝቡን ያሳተፉ ይሁኑ። ከሐኪሞች እንክብካቤ ተጠቃሚ ከሆኑ ታካሚዎች የተሰጠ ምስክርነቶች ይታዩ። ፓስተርና የባህል ሃኪም ብቻ ነው እንዴ ምስክርነት የሚቀርብለት!

 

የታሪካችን አወራር ከማጣት ወደ ስኬት መሸጋገር አለበት። የስኬት ታሪኮች የወሬውን መልክ ለመለወጥ ኃይለኛ መሳሪያዎች ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ። የኢትዮጵያውያን ዶክተሮችን አለም አቀፋዊና ሃገራዊ በጎ አስተዋጾ በማጉላት የበለጠ አዎንታዊ የህዝብ ግንዛቤን ማዳበር እንችላለን። የጤና ባለሙያዎች ፈተናዎችን በማሸነፍ በማህበረሰባቸው ውስጥ ያስመዘገቡትን የድል ታሪኮችን ሲያካፍሉ ሌሎችን ማበረታታት ብቻ ሳይሆን ሙያውን ሰብአዊና የህዝብ ለማድረግም ይረዳል። እነዚህ ትረካዎች ርህራሄ እና መግባባትን ሊያዳብሩ ይችላሉ፤ የህዝቡን አመለካከት ከወቀሳ ወደ ድጋፍ ሰጪነት ይለውጣሉ።

በአዎንታዊ ትረካዎች የተደገፈ ድምጽ ከችግር ትረካዎች የበለጠ ውጤታማ የማስተጋባት አቅም አለው። ሰዎች ከችግር ታሪክ ይልቅ ወደ አዎንታዊነት ይሳባሉ። የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ስኬቶቻቸውን እና ያበረከቱትን አስተዋጾ በማጉላት ከህዝብ፣ ከመንግስት እና ከአለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ትስስር መፍጠር ይችላሉ። ሁሉም ህዝብ የጤና ሴክተር አጋርና ጠበቃ እንዲሆን ያደርጋል።

 

በተጨማሪም በሁሉም ኢትዮጵያዊ ላይ የመጣ የኑሮ ጫናን ከማስተጋባት ይልቅ የሥርዓት ለውጥ ተሟጋች እንሁን። ታሪካችንን ስንናገር ከመሰረታዊ የጤና ሴክተር ለውጥ ፍላጎቶቻችን ጋር ብናጣምረው ከፍተኛ ተሰሚነት ያተርፋል። ዶክተሮች በአስከፊው የፋይናንስ ሁኔታ ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ ድምጻቸውን ለተሻለ የስራ ሁኔታ እና ለታካሚዎቻቸው የላቀ አገልግሎት ለመስጠት አስቻይ ስርአት ለማምጣት ያላቸውን ቁርጠኝነት ከሚያሳዩ ታሪኮች ጋር ማዳመር ይችላሉ። ይህ አካሄድ የሚያሳየው ኑሮ ቢፈትናቸውም ለዜጎች የተሻለ የጤና እንክብካቤ መስጠታቸውን እንደሚቀጥሉ ያረጋግጣል።

ዶክተሮች ለፍትሃዊ ደሞዝ፣ ለተሻለ የስራ ሁኔታ እና ለሁሉን አቀፍ የጤና ስርአት ለውጥ መሟገታቸውን መቀጠል አለባቸው። ነገር ግን ይህ ተሟጋችነት እነዚህ ለውጦች ለዶክተሮች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጤና ወሳኝ እንደሆኑ አጽንኦት በሚሰጡ ታሪኮች ሊጠናከር ይችላል።

ለማጠቃለል ያህል ማጣትን ይፋ ማድረግ ሳይሆን ስኬትን ማሳወጅ ያዋጣል። የማይካድ የኑሮ ጫና ቢኖርብንም የማጣት ታሪኮችን ማጋራት ላይ ብቻ ማተኮር ወደሚፈለገው ውጤት አያደርስም። ትኩረቱን ወደ አወንታዊ ታሪኮች በመቀየር ዶክተሮች የህዝቡን አመለካከት መቀየር፣ ህብረት መፍጠር እና በመጨረሻም የመንግስትን ድጋፍ መጠምዘዝ ይችላሉ። በተጨማሪም ለስር ነቀል የጤና ሥርዓት ለውጦች መሟገታቸውን በመቀጠል የራሳቸውንም ህይወት ለማሻሻል የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ማግኘት ይችላሉ።

 

በቅርቡ የጀመረው HAKIM ፖድካስት ‘ከጀግኖቻችን እንማር፣ አዋቂዎችን ታዋቂ እናድርግ’ አዲስ አቀራረብ ይበል የሚያስብል ነው። ህክምናችን አኩሪ ታሪክና ባለ ታሪኮች እንዳሉት ማሳወቁ የህዝቡን አመለካከት ይቀይራል፣ እንማማርበታለን፣ ህክምናውን እናሻሽልበታልን፣ እንሸላለምበታለን። የለቅሶ መድረክ ከመሆን ወደ ስኬቶቻችን የሚወደሱበት፣ የትብብር ማእቀፎች የሚዳብሩበት፣ የለውጥ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበት፣ ፋና ወጊ ጥናቶች የሚቀርቡበት፣ ፈጠራ የሚፈልቅበት ሚዲያ መሸጋገር ያሻል። ይህን ለማድረግ ጊዜው አሁን ነው።

1 thought on “የጤናሙያን ክብር ለማስመለስ የአወንታዊ ታሪኮች ሚና”

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top