ውፍረት (obesity) በአለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ የጤና አጀንዳ ሆኗል። የስነ ተዋልዶ ጤናን ጨምሮ ለበርካታ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እንደወረርሽኝ መስፋፋት ቀንደኛ ተወቃሽ ምክንያት ነው። ከመጠን ያለፈ ውፍረት ተጽእኖ ከተለመዱት ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞች ለአብነትም ስኳር ህመም፣ ኮሌስትሮል ችግር፣ የልብና ደም ስር ህመሞች ወዘተ ባሻገር የወንዶች የስነ ተዋልዶ እክሎችን ያመጣል።
ይህ ትምህርታዊ ጽሁፍ ከመጠን ያለፈ ውፍረት በተለይም ቦርጭ በወንዶች የስነ ተዋልዶና ጾታዊ ጤና መካከል ያለውን ውስብስብ ግንኙነት በጥልቀት ያስረዳል ፣ የተለመዱ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ለማስወገድ ያብራራል በተጨማሪም የተሟላ ጤናን ለማሻሻል ተግባራዊ ምክሮችን ይሰጣል ።
ይህንን ጽሁፍ እንዳሰናዳ ያነሳሳኝን የአንድ ደንበኛ የስኬት ታሪክ ቀንጭቤ ላካፍላችሁ። ይህ ባለታሪክ የ45 አመት ጎልማሳ ነው። ባለትዳርና የ15 አመት ልጅ አባት ነው። ከስራና ኑሮ ጫና ጋር ተያይዞ አመጋገብ ማስተካከልና ስፖርት መስራት አልሆን ብሎት ከጥቂት አመታት ወዲህ ክብደቱ ከመጠን በላይ እየጨመረ መጥቶ አሁን ከቁጥጥር ውጭ ሆኖበታል። አልፎ አልፎም ቢራ አይጠላም። ይባስ ብሎ ላለፉት ሶስት አመታት ትዳሩን የሚረብሽ ስንፈተ ወሲብ አጋጠመው። ይህን ግላዊ የሆነ ጭንቀት የሚያወጋው ሰው አጥቶ በሃፍረት ዋጥ አድርጎት ቆይቷል። ለማውራት የማይመች ጉዳይ ሆኖበት የህክምና እርዳታ ከመፈለግ ይልቅ በድብቅ የባህል መድሃኒቶችና እንክብሎችን ከጥቁር ገበያ እየሸመተ ይሞክራል። የሚፈልገውን አመርቂ ለውጥ ግን ማግኘት አልቻለም። ቀስ በቀስ የሞቀ ትዳሩን ማናጋት ጀመረ። ከአመት በላይ ሌላ ልጅ ለመጸነስ ፈልገው ቢሞክሩም አልታዘዝ ብሎታል። የብልት መስነፍ ብቻ ሳይሆን የቴስቶስቴሮን ሆርሞን አነስተኛ እንደሆነና የዘር ፍሬ ምርመራዎችም የስፐርም መጠንና ጥራት ማሽቆልቆሉን አረጋገጡ። አሁን ለዚህ ሁሉ ችግር ዋና መንስኤ የሆነውን ውፍረትና ቦርጭ ለማጥፋት ጉዞ ለመጀመር ወሰነ።
የዚህን ጊዜ ነው የውፍረትና ሆርሞን ህክምና ለማግኘት ቀጠሮ የያዝነው። ሰፊ ውይይት አድረገን የሚያስማማ እቅድና ግብ ካስቀመጥን በኋላ ለመሃንነትና ስንፈተ ወሲብ ችግር መነሻ የሆነውን ውፍረት ለማጥፋት የሚረዳውን የረዥም ጊዜ የቤት ስራ በአንድ እርምጃ ሃ ብሎ ጀመረው። ጤናማ አመጋገብና መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማጣመር የክብደት መቀነስ ጉዞን ቀጠለ። አልኮል የሚባል ነገረ ድጋሜ ዞሮ ላያይ ምሏል። የሚፈለገው የክብደት ለውጥ እስኪመጣ በጊዜያዊነት ሻል ያለ የብልት ማጠንከርያ መድሃኒትም አልፎ አልፎ እንዳስፈላጊነቱ ይውጣል። ከባለቤቱ ጋር ስለጾታዊ ግንኙነታቸው በግልጽ መነጋገርና መተጋገዝ ጀመሩ። ይህም ትዳራቸውን ድጋሜ እንደአዲስ አደሰ። በ4 ወር ውስጥ ከእልህ አቆራጭ ግብ ግብ በኋላ ከፍተኛ ክብደት ቀንሶ ቦርጩንም ድራሹን ማጥፋት ቻለ። አሁን በራስ መተማመኑ ወደቀደመ የወንድነት ስሜቱ ተመልሷል። ወደጋለ የትዳር ግንኙነት ለምልሟል። የቴስቶስቴሮን መጠኑ ተምልሶ እንደጎረምሳ ወጣት ቆንጆ ደረጃ ደርሷል። የዘር ፍሬ ምርመራውም የስፐርም ቁጥርና ጥራት ምርጥ ሆኖ ተስተካክሏል። ብዙም ሳይቆይ የሁለተኛ ልጃቸውን በደስታ አቅፈው ለመሳም በቅተዋል።
ውፍረት በወንዶች ስነ ተዋልዶ ጤና ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ምንድን ነው?
ውፍረት የወንድ መሃንነት ሊያስከትል ይችላል። የሆርሞን መጠንን በመቀነስ በተለይም የቴስቶስትሮን ምርት እንዲያሽቆለቁል በማድረግ የወንድ የዘር ፍሬን ይጎዳል። ይህ የሆርሞን መዛባት የስፐርም ቁጥር እንዲቀንስ፣ የማይንቀሳቀሱ ወይም የተኮላሹ ስፐርም ቁጥር እንዲበዛ እና በአጠቃላይ የስፐርም ጥራት እንዲቀንስ ስለሚያደርግ ወንዶች አባት የመሆን ተስፋቸውን አስቸጋሪ ያደርገዋል።
የወንድ የብልት መቆም ችግርም ሌላኛው የውፍረት ተያያዥ ችግር ነው። ከመጠን በላይ የሆነ ውፍረትና ስብ የብልትን የደም ስር በመዝጋት የደም ዝውውሩን ያሰናክላል፤ ብልት በደም እንዳይወጠር ስለሚያደርግ የወንዱ ብልት በግብረ ስጋ ግንኙነት ጊዜ እንዲሰንፍ ያደርገዋል። በተጨማሪም ከውፍረት ጋር የተያያዙ እንደ የደም ግፊት፣ የስኳር በሽታ እና የልብ ሕመም ካሉ ሁኔታዎች ጋር የተቆራኘ በመሆኑ ለስንፈተ ወሲብ በከፍተኛ ሁናቴ ያጋልጣል።
ከዚህ ባሻገር ከመጠን በላይ ውፍረት ሌሎች በርካታ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት እክሎችን ሊያስከትል ይችላል። ጾታዊ ግንኙነት ፍላጎት ማጣትና ስሜት እንዲቀንስ ሊያደርግ ይችላል። የወንድነትን በራስ የመተማመን ስሜት በማኮሰስ እና የተክለ ሰውነት የስነ-ልቦና ተፅእኖ ውስጥ በመክተት የስንፈተ ወሲብ ችግሮችን የበለጠ ሊያባብሰው ይችላል።
በዚህ ረእሰ ጉዳይ ዙርያ የሚሰሙ የተለመዱ የተሳሳቱ አመለካከቶች ምንድን ናቸው?
በዚህ የወንዶች ጤና ዙርያ ከተለመዱት የተሳሳቱ አመለካከቶች መካከል አንዱ ውፍረት ከስነ ተዋልዶ ጤንነት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም የሚል ይገኝበታል። ብዙ ወንዶች ውፍረትና ቦርጭ በጾታዊ ጤንነታቸው ላይ በቀጥታ ተጽዕኖ የማያሳድር እንደሆነ ያምናሉ። እውነታዉ ግን በርካታ ጥናቶች እንዳረጋገጡት ከመጠን በላይ ውፍረት ዋነኛው የስንፈተ ወሲብ አጋላጭ ጠንቅ ነው። ይህን በውፍረትና የስነ ተዋልዶ ችግሮች መካከል ያለውን ጠንካራ ትስስር መገንዘብ አስፈላጊ መንስኤዎችን እና ተገቢውን ህክምና ለማድረግ ወሳኝ ነው።
ሌላኛው ስጋት ደግሞ ስለዚህ ጉዳይ በግልጽ ለመነጋገር መሸማቀቅ እና የመገለል ስሜት ነው። በጾታዊ ጤና ጉዳዮች ላይ መወያየት ለብዙ ወንዶች አሳፋሪ ሊሆን ስለሚችል እርዳታ ከመጠየቅ ወደ ኋላ እንዲሉ ያደርጋል። ይህንን ፍርሃት ማሸነፍ እና እነዚህ ጉዳዮች ውጤታማ የህክምና አማራጭ ሊታከሙና ሊድኑ የሚችሉ መሆናቸውን መገንዘብ በጣም አስፈላጊ ነው።
በሌላ በኩል ክብደት መቀነስ ብቻውን ሁሉንም ነገር ሊፈታ ይችላል ብሎ በማሰብ በተለይም አመርቂ ለውጥ ማምጣት ሳይቻል ቢቀር ብስጭትና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ሊፈጥሩ የሚችሉ ከእውነታው የራቁ ግቦች ማስቀመጥም ሌላኛው የተሳሳተ አመለካክት ነው። ክብደትን ማስተካከል በተለይም ቦርጭ ማጥፋት የስነ ተዋልዶ ጤናን እንዲሁም ወሲባዊ ብቃትን በእጅጉ ሊያሻሽል ቢችልም ብቸኛ መፍትሄ ግን አይደለም። ለበለጠ ውጤት አጠቃላይ የአኗኗር ዘይቤ ለውጦችን፣ የስነልቦና ድጋፍን እና የመድሃኒት ህክምናዎችን የሚያጠቃልል ሁሉን አቀፍ መፍትሄ ማፈላለግ አስፈላጊ ነው።
ውፍረት እና የወንዶች የስነ ተዋልዶ ጤናን ለማሻሻል መደረግ የሚገባቸው ተግባራዊ እርምጃወች
የአኗኗር ዘይቤ ማሻሻያዎች ማድረግ ለስነ ተዋልዶ ጤናን በእጅጉ ያስተካክላሉ። መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አዘውትሮ ማድረግ የሰውነት አላስፈጊ ስብን ክምችት በመቀነስ የደም ዝውውርን ያሻሽላል፤ የቴስቶስትሮን ሆርሞን መጠንን ይጨምራል። ጤናማና የተመጣጠነ አመጋገብ ማዘውተር በተለይም አትክልት፣ ፍራፍሬና ገንቢ ፕሮቲኖች የበለጸገ ምግብ መመገብ ቁልፍ መፍትሄ ነው። በተቃራኒው ደግሞ ከመጠን በላይ የሆነ ጤናማ ያልሆኑ ቅባቶችን እና ስኳራማ ጣፋጭ ምግቦችን ማስወገድ የጾታዊ ህይወትን ያጣፍጣል። በቂ እንቅልፍ አለማድረግም የሆርሞን ስርኣትን ስለሚረብሽ በቂና ጥራት ያለው እንቅልፍ ይኑርዎት። አልኮል መጠጥን ይገድቡ ከተቻለ ከአልኮል ይታቀቡ፤ ሲጋራ ከማጨስ ይቆጠቡ።
የስነልቦና ድጋፍም በርካታ የጾታዊ ህመሞችን ለማሻሻል ይረዳል። የስነ ልቦና ሕክምና ማግኘት ወንዶች ከጾታዊ ግንኙነት ብቃት ዙርያ ያላቸውን በራስ መተማመን ያሻሽላል፤ ‘ጓደኛዬ እንደምታስበኝ ጎበዝ ባልሆንስ’ የሚል ጭንቀትና ፍርሃት ያክማል፤ ከውፍረትና ስንፈተ ወሲብ ጋር የተገናኙ ድብርትና መሰል የአእምሮ ጭንቀት ህመሞችን ያድናል። በርካታ የስነልቦና ድጋፍ አይነቶች ቢኖሩም ሁሉም አይነት የስነ ልቦና ህክምናዎች የጾታዊ አፈጻጸም ጭንቀትን (performance anxiety) ይቀንሳሉ፤ በአጠቃላይ የጾታዊ ጤንነት ላይ በጎ ተጽዕኖ ያመጣሉ።
የስንፈተ ወሲብ (erectile dysfunction) እና መሰል የወንዶች የስነ ተዋልዶ ህመሞች በመድሃኒት (Medical Treatment) ይታከማሉን?
አዎ! የወንዶች የስነ ተዋልዶ ችግሮች እንደማንኛውም ህመም ውጤታማ ህክምና አላቸው። ይታከማሉ። ሊድኑም ይችላሉ።
ዋናውና ቀዳሚው ሜዲካል ህክምና የችግሩን መነሻ የሆነውን ውፍረትና ቦርጭ ማስተካከል ነው። ይህን ማድረግ ካልቻልን መድሃኒቶች ሁሉ ከጊዜያዊ ማስታገሻ ያለፈ ዘላቂ መፍትሄ አያመጡም። ስለዚህ በምግብም ይሁን በስፖርት አሊያም በክብደት መቀነሻ መድሃኒቶች ቦርጭ ማጥፋት ይፈልጋል።
የብልት ማጠንከሪያ መድኃኒቶችም አሉ። PDE5 inhibitor የሚባሉ መድሃኒቶች ከጾታዊ ግንኙነት ትንሽ ሰዓታት ቀደም ብለው ሲወሰዱ ወደ ወንዱ ብልት የሚሄደውን የደም ፍሰትን በማሻሽል ብልት በደንብ እንዲጠነክርና እንዲገተር ይረዳሉ። በምርመራ የተረጋገጠ የቴስቶስትሮን ማነስ ላላቸው ወንዶች የሆርሞን ሕክምና ያስፈልጋል።
ለማጠቃለል ያህል ውፍረትና ቦርጭ በወንዶች የስነ ተዋልዶ ጤና ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው። ከስንፈተ ወሲብ እስከ መሃንነት በርካታ ችግሮችን ሊያመጣ ይችላል። ይሁን እንጂ ይህን የውፍረት አስከፊ ጉዳት በመረዳት እና ንቁ እርምጃዎችን በመውሰድ ወንዶች የስነ ተዋልዶ ጤንነታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ማሻሻል ይችላሉ። የአኗኗር ማሻሻያዎችን፣ የስነ-ልቦና ድጋፍን እና የህክምና ህክምናዎችን ማጣመር እነዚህን ተግዳሮቶች ለማሸነፍ ያስችላል።
አስታውስ፣ ለማንኛውም የስነ ተዋልዶ ችግር እርዳታ መፈለግ የጥንካሬ ምልክት እንጅ የሚያሸማቅቅ ጉዳይ አይደለም። ክብደትን በማስተካከል የስነ ተዋልዶ እንዲሁም አጠቃላይ ጤናን በማበልጸግ የበለጠ ጣፋጭ ህይወትን መምራት ይቻላል።
ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ይዘቶች ወይም ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና የጤና ባለሙያዎን ያማክሩ።
ተጨማሪ ምክር፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት በኢሜል፦ contact@melakutaye.com እና ስልክ፦ +251921720381 ማግኘት ይችላሉ። ለግል ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር መመካከር ይችላሉ። ይህን መረጃ ጠቃሚ ሆኖ ካገኙት ለሌሎች ያጋሩ።