በዚህ ሳምንት በቲክቶክ ትሬንዲንግ ከሆኑት የጤና መረጃዎች መካከል አንዱ ሩዝን አቀዝቅዞ መመገብ ስኳር ያስተካክላል፤ ቦርጭ ያጠፋል የሚል መረጃ እየተተራመሰ እንደሆነ አስተውለናል። በዚህ ትምህርታዊ መጣጥፍ ይህን ጉዳይ የምናብራራ ይሆናል።
በአለም ላይ በከፍተኛ መጠን ከሚመረቱት የምግብ እህል ምርቶች መካከል ሩዝ ሶስተኛውን ደረጃ ይይዛል – በቆሎንና ስንዴን ተከትሎ። ከአጠቃላይ ፍጆታ አንፃር ግን ሩዝ በበለጠ በብዛት ይበላል። በተለይም በእስያ፣ በአፍሪካ እና በደቡብ አሜሪካ ያሉ ብዙ ሀገራት ዋና ምግብ ሩዝ ላይ የተመሰረት ነው። እንዲህ መላው አለም እያጣጣመ የሚሰለቅጠው ሩዝ ለስኳር ታካሚዎች ግን እንዳሻቸው እንዲመገቡት የሚመከር አይደለም። ይህ ሲባል ግን ሩዝ መብላት ለስኳር ታካሚ የማይቀመስና የተገዘተ ምግብ ነው ማለት አይደለም።
ሩዝ 80% ያህል ይዘቱ ስታርች (starch) የሚባለው ካርቦሃይድሬት ነው። በዚህ ከፍተኛ የካርቦሃይድሬት ይዘቱ ምክንያት ሩዝን በተመገብን ከመቅጽበት የደም ስኳር መጠን በከፍተኛ መጠን እንዲያሻቅብ ሊያደርግ ይችላል። ከፍተኛ ግላይሴሚክ ኢንዴክስ (high glycemic index) አለው ማለት ሩዝ እንደበላን በፍጥነት አንጀት ወስጥ በቀላሉ በመፈጨትና ወዲያውኑ ወደ ደም በመስረግ ስለሚዋሃድ ድህረ ምግብ (post-meal) የግሉኮስ መጠን በድንገት እንዲጨምር ያደርጋል ማለት ነው።
ትኩስ የበሰለ ሩዝ (freshly cooked rice) በቀላሉ ሊፈጩና ሊዋሃዱ በሚችሉ ስታርቾች የበለፀገ በመሆኑ ወዲያውኑ እንደበላን የደም ውስጥ የግሉኮስ መጠን ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ያስከትላል። ትኩስ የበሰለ ሩዝ ጣፋጭ መሆኑ በፍጥነት ደም ውስጥ ወደ ግሉኮስ እንደሚቀየር ማሳያ ነው። ለጤነኛ ሰው ይህ የሩዝ ባህሪ ብዙ አሳሳቢ ላይሆን ይችላል። የስኳር ህመም ላለባቸው ሰዎች ግን ይህ አደገኛ የደም ስኳር መጠን መጨመር (post-prandial hyperglycemia) ያስከትላል። ለረጅም ጊዜ ሲቆይ ደግሞ ለበርካታ የስኳር ህመም ተያያዥ ችግሮች ያጋልጣል።
በሌላ በኩል፣ የበሰለ ሩዝ ከ12 እስከ 24 ሰዓት ፍሪጅ ቀዘቅዞ ከመበላቱ በፊት እንደገና የሚሞቅ ከሆነ የተለየ ባህሪ ይይዛል። ሩዝ በሚቀዘቅዝበት ጊዜ የተወሰኑት ስታርቾች ወደ የማይልም የስታርች ዓይነት (resistant starch) ይለወጣሉ። የማይልም ስታርች አንጀት ውስጥ በከፊል የማይፈጭ ና የማይሰባበር ስለሆነ ወደ ደም ውስጥ አይሰርግም። ይህም ማለት የስኳር መጠናችን ቶሎ አይጨምርብንም ማለት ነው። ቢፈጭ እንኳ በጣም በዝግታ ስለሚሆን የፈጠነ የስኳር መጨመር አያስከትልም።
ሩዝ አፍቃሪ የሆኑ የስኳር ታካሚዎች ስኳር በሃይል ሳይጨምር እንዴት ሩዝን መመገብ የሚያስችሉ ተግባራዊ ምክረ ሃሳቦች እነሆ።
የመጀመርያው ሩዝን በብልሃት የመብላት ጥበብ የበሰለ ሩዝዎን አቀዘቅዞ አድሮ ክዚያ እንደገና አሙቆ መብላት ነው። ሩዝን ካበሰሉ በኋላ ወዲያውኑ አይበሉት። ይልቁንም ለብዙ ሰዓታት እስከ 24 ሰዓት ፍሪጅ ውስጥ በ 4 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ እንዲቀዘቅዝ ያድርጉት። መብላት ሲፈልጉ በሚቀጥለው ቀን እንደገና ያሙቁ እና ይብሉት። ይህን በማድረግ ሩዝን መመገብ የስኳር ልኬታችን እንዳያሻቅብ ለመገደብ በመጠኑም ቢሆን ይረዳል። ከላይ እንደተጠቀሰው የበሰለ ሩዝ በሚቀዘቅዝበት ጊዜ የሩዝ ስታርች ባህሪ ስለሚቀይር አንጀት ውስጥ ምግብ የሚያደቁ ኤንዛይሞችን በመቋቋም በቀላሉ የማይልምና የማይፈጭ ጸባይ ይይዛል። ስለሆነም የደም ስኳር መጠን ቶሎ እንዳይጨምር ይከላከላል።
ሌላኛው ወሳኝ ዘዴ ደግሞ መጠናችንን መገደብ ነው። ቀዘቀዞ የተሞቀ ሩዝም አንኳ ቢሆን አብዝተን ከበላን የስኳር መጠን ከፍ ያደርጋል። ያው በዝግታም ቢሆን ተፈጭቶ ወደ ስኳር መቀየሩ አይቀርማ! ሁሌም ቢሆን የምግባችንን መጠን መመጠን (Portion control) ይገባል። የስኳር ታካሚ ቢበዛ ቢበዛ ከግማሽ አነስተኛ ጭልፋ በላይ ሩዝ በቀን ቢመገብ ስኳር ከቁጥጥር በላይ እንዲወጣ ሊያደርገው ይችላል። በሌላ አነጋገር ሩዝን እንደግዝት ከምግብ ምርጫችን ሙሉ በሙሉ መሰረዝ አስፈላጊ ባይሆንም ከበዛ ግን መዘዙ አይለቀንም። ከትኩስ የበሰለ ሩዝ ከመጠቀም ይልቅ የበሰለ ሩዝን አቀዝቅዞና እንደገና አሙቆ መመገብ በንጽጽር የተሻለ ነው ለማለት ነው እንጅ የቀዘቀዘ ሩዝ ለስኳር መጠን መጨመር በጭራሽ አስተዋጽኦ አያደርግም ተብሎ መተርጎም የለበትም። በዝግታና በአነስተኛ ደረጃም ቢሆን ስኳር ይጨምራል። በተለይ አብዝተን ከበላን ስኳር ከፍ ማለቱ አይቀርም። [It does not mean that cooled-reheated rice does not contribute to the rise in sugar levels, but it contributes less and very slowly to the rise in blood sugar levels compared to freshly cooked rice].
ሶስተኛው የሩዝ አመጋገብ ምክረ ሃሳብ ደግሞ ሩዝን ብቻውን ሙሉ ማዕዳችን ከማድረግ ይልቅ ከሌሎች ፕሮቲን እና በፋይበር የበለጸጉ ምግቦች ጋር አብሮ መብላት ነው። እንዲህ ከከፍተኛ ፋይበር ያላቸው አትክልትና ገንቢ ምግቦች ጋር አብሮ ሲበላ የምግብ እንሽርሽሪት ሂደት እንዲረጋጋ ስለሚያደርጉ የደም ስኳር መጠን በፍጥነት እንዳይጨምር ያዝ ያደርገዋል።
በቀላሉ ለማጠቃለል ያህል የበሰለ ሩዝ በትኩሱ ወዲያውኑ ከመመገብ ይልቅ አቀዝቅዞና እንደገና አሙቆ መብላት የሩዝ ስታርቾች ወደ የማይልም የስታርች ዓይነት (resistant starch) ስለሚለወጡ አንጀት ውስጥ በከፊል የማይፈጭ ና የማይደቅ ከሆነ ወደ ደም ውስጥ እንዳይሰርግ ይሆናል። ስለሆነም የስኳር መጠናችን ቶሎ አይጨምርብንም። ቢፈጭ እንኳ በጣም በዝግታ ስለሚሆን የፈጠነ የስኳር መጨመር አያስከትልም። ይህ ማለት ግን የቀዘቀዘ ሩዝ ምንም ካሎሪ የለውም ስኳርም በፍጹም አይጨምርም ማለት አይደለም።
ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ይዘቶች ወይም ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና የጤና ባለሙያዎን ያማክሩ።
ተጨማሪ ምክር፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት በኢሜል፦ contact@melakutaye.com እና ስልክ፦ +251921720381 ማግኘት ይችላሉ። ይህን መረጃ ጠቃሚ ሆኖ ካገኙት ለሌሎች ያጋሩ።