A Tale of Kaldi’s Dancing Goats at Emory University

በሃገረ አሜሪካ የጆርጅያ ግዛት አትላንታ የሚገኘው ዝነኛው የኤሞሪ ዩኒቨርሲቲ ቅጽር ግቢ ዋነኛ ካፌዎች መካከል በሮሊንስ የማህበረሰብ ጤና ት/ቤት የሚገኘው ‘Dancing Goats’ እና በተማሪዎች መዝናኛ ማእከል ያለው ‘Kaldi’ ቡና ይጠቀሳሉ።


የካፌዎችን ስም እንዳየሁ የኢትዮጵያ የቡና መፍለቂያ ምድርነት ታሪክ ልቤን አሞቀው።


እረኛው ካልዲ (Kaldi) በከፋ አምባዎች ላይ ፍየሎቹን በለመለመ መስክ ሲያሰማራ ቡና ላይ የመጀመሪያዉን ጥናታዊ ምርመር ጀመረ። የቡና ቁጥቋጦዎችን የሚቀጣጥፉ ፍየሎቹ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በጣም ንቅት (Dancing Goats) እንደሚሉ አስተዋለ። የመመራመር ጉጉት ስላደረበት ካልዲ የቡና ፍሬዎችን በራሱ ሞክሮ ማየት ፈለገ። ፍሬዉን ሲበላ ሃይለኝነት ተሰማው፣ ፏ ፍክት አለ። የዚህን ‘አስማተኛ ፍሬ’ የምርመር ግኝት አሰራጨ። ዜናው የደረሳቸው ገዳማዊያኑም ረጅም ጸሎት በሚያደርጉበት ጊዜ ነቅተው እንዲቆዩ እንዲረዳቸው ቡናን ማጣጣም ጀመሩ። ይህ የቡና መወለድ የኢትዮጵያዊያን አኩሪ የምርምር ግኝት ነው።


የ Dancing Goats እና Kaldi ካፌዎች በኢሞሪ የመጠቀ የምርምር ባህልና እና በቡና አብቃይት ኢትዮጵያ ልጅ ካልዲ ቀደምት ተመራማሪነት መካከል ያሉ አገናኝ የታሪክ ድልድይ ይመስላሉ። ይህን ታሪካዊ የቡና አመጣጥ ለማጠየቅ ምልክት ሆነዋል። የኢትዮጵያን የቡና መፍለቂያነት እየዘከሩ ነው። የካልዲን ትሩፋት፣ አስተዋይነትና ተመራማሪነት እያከበሩ ነው። ከኢሞሪ ባሻገር በአለም በመላ Kaldi Coffee፣ Kaldi’s Coffee፣ Dancing Goat እና Wandering Goat የመሳሰሉ የቡና መሸጫ ሱቆችና ካፌዎች ስያሜዎች በስፋት የተለመዱ ናቸው።


ባልተያያዘ ዜና የካፌው አስተናጋጅ የሆነች አንዲት መለሎ ኢትዮጵያዊ ቀለሜን ስላስተዋለች የዳንሲንግ ጎትስ ብራንድ ያለው ኮፍያ ለአትላንታ ብርድ ይሁንህ በማለት ጀባ ብላኝ ከቡናው እኩል እያሞቀኝ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። ስለቡና እና ኢትዮጵያ ያላት እውቀት ገራሚ ነው። ቡና በሰው ዘር መካከል የፈጠረው ትስስር ጥልቅ እንደሆነ ተሰማኝ። የትም ብትሆን የቡና ኢትዮጵያዊ ታሪክ ከሁሉም አለም ጋር ያቆራኛል።


ከካልዲ የምንማራቸው ቁልፍ ትምህርቶች

የኢትዮጵያን ወቅታዊ ፈተናዎችን በመፍታት የበለጸገች ሃገር ለመፍጠር የአሁን ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ከካልዲ መማር አለብን። በጥንት ክፍለ ዘመን የኖረ የፍየል እረኛ አስተዋይነትና ተመራማሪነት ኢትዮጵያን የቡና መገኛ ሆና እንድትከበር፣ ስሟ እንዲጠራ ከማድረግ ባሻገር ዋና የገቢ ምንጫችን የሆነ ውድ ሃብት ፈጥሯል።


የካልዲ ታሪክ ቡናን ከማግኘት በላይ የማወቅ ጉጉት፣ ሳይንሳዊ አሳቢነት እና ተመራማሪነት ስነ ልቦና ያዘለ ጊዜ የማይሽረው ትምህርት ነው። ዛሬ እነዚህ ባህሪያትን በመላበስ ያሉንን ሀብቶች በመለየት ወደ ሃብት መቀየር እንደሚቻል ጥልቅ ግንዛቤን ይሰጣል።


ሳይንሳዊ ምልከታን (Scientific Curiosity) ማዳበር

የካልዲ ግኝት የሚጀምረው የሚያግዳቸውን የፍየሎቹን ባህሪ በትኩረት በመከታተል ነው። የካልዲ ፍየሎች የቡና ፍሬዎችን ከበሉ በኋላ ያሳዩትን ያልተለመደ ጸባይ እንደ አጋጣሚ ብቻ አላየውም። ይልቁንም በጥልቀት በመመልከት ሊያጠናው ፈለገ። የማወቅ ጉጉት ስለወሰወሰው በራሱ ለመሞከር አልዳዳም። በፍየሎች ያየዉን ተሞክሮ experiential research ዘዴን በመጠቀም ራሱ ላይ አጠና። ካልዲ የቡና ፍሬዎች አበረታች የሆነ ነገር እንዳላቸው በመፈልሰፉ ዛሬ ቡና ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ እምርታው የትና የት ደርሷል።


በተመሳሳይ እኛም አካባቢያችንን፣ የምንሰማውን፣ የምናየዉን ነገር በሙሉ በጥልቀት በመመርመር፣ በሳይንሳዊ መንገድ በማጥናት ያሉንን ጸጋዎች ወደ ሃብት መቀየር እንችላለን። ኢትዮጵያ በብዝሀ ህይወት፣ ባህል፣ ቅርስ እና ተፈጥሯዊ ሃብት የበለፀገች ናት። እነዚህን ሃብቶቻችንን በመተንተን እና በመመርመር የምንመኛትን የበለጸገች ኢትዮጵያ ማሳካት ይቻላል።


ችግር ፈቺ አዳዲስ እሳቤዎችን (Critical Thinking) ማዳበር

ካልዲ ጥያቄዎችን የመጠየቅ እና ሳይንሳዊ መልስ የመፈለግ መሻት ነበረው። የዛሬዎች የትምህርት ተቋማትም ከሽኩቻና ጥላቻ ተፋተው የምርመር እሳቤን እና ባህልን ማዳበር ይኖርባቸዋል። ተማሪዎች እና ተመራማሪዎች እንዲጠይቁ ማብቃት፣ የተለመዱ ልምዶችን እንዲፈትሹ ማገዝ፣ ያተደረሰብትን እንዲያስሱ መፍቀድ፣ የፈጠራ መፍትሄዎችን እንዲያቀርቡ ማመቻቸት ግድ ይላል።


ቡና አዲስ ተክል አልነበረም። ጥንትም በከፋ ደን ነበረ። ነገር ግን ዋጋውን ለአለም ለመግለጥ የካልዲን ማስተዋል እና ተመራማሪነት መጠበቅ ነበረበት። የከፋ ተክል ወደ ዓለም አቀፋዊ ምርት አደገ።


የአሁኒቷ ኢትዮጵያም እንዲሁ ሀብቶቿን፣ ትርክቷን በአዲስ መንገድ ማጤን አለባት። በምርምር ግኝት ላይ ኢንቨስት በማድረግ ያልተገለጠልንን ተክል ወደ ወሳኝ ፈዋሽ መድሃኒት መቀየር ይቻላል።


የካልዲ ታሪክ ምልከታ፣ ሙከራ እና ምርምር ህይወትን ወደሚቀይሩ ግኝቶች እንደሚያመራ ያስረዳል። እነዚህን መርሆች በመተግበር፣ ኢትዮጵያ አንገብጋቢ ፈተናዎችን መፍታት ትችላለች።


የካልዲ ቡና ግኝት ለአለም ሁሉ ንቃትና ፍካት እንዳጎናጸፈ ሁሉ ዘመናዊት ኢትዮጵያም በምርምር ላይ የተመሰረተ የፈጠራ ስራ በመስራት ለአለም አዲስ በረከት ልታበረክት ትችላለች።


እኔስ ምን ትምህርት ቀሰምኩ?

እኔም እንደ አንድ ኩሩ ኢትዮጵያ የህክምና ባለሙያ በአገራችን ያሉ የጤና ችግሮችን ለመፍታት እንደካልዲ ማስተዋል፣ በአዲስ እይታ መመልከት፣ መመራመር እና አዳዲስ ሃገራዊ መፍትሄዎችን የማሰስ ፍላጎቴ ከፍ ብሏል። ሃገራዊ ልምዶችን እና የህዝቡን ብሂል በቅርበት በመመልከት የጤና ችግሮችን ለመፍታት እንደሚቻል ተምሬያለሁ።


አሁን እየሰራሁበት ያለውን የጤና ስርዓት እንደገና እንደአዲስ  በማጤን የኢትዮጵያዊያንን ጤና ለማሻሻል እና ግንዛቤን ለማስፋት በአዲስ እይታ እሰራለሁ። የበለጠ ጤናማ የሆነች ኢትዮጵያ እንድትፈጠር የበኩሌን አስተዋፅዖ አደርጋለሁ።

2 thoughts on “A Tale of Kaldi’s Dancing Goats at Emory University”

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top