ትክክለኛ ቅድመ እርግዝና የስኳር ህክምና እና ክትትል ማድረግ እርግዝና ጤናማ እንዲሆን ያስችላል፤ ልጅም ደህና እንዲወለድ ይረዳል። ጤናማ እርግዝና የሚጀምረው ከመፀነስሽ በፊት ነው። የቅድመ እርግዝና እንክብካቤ በጣም አስፈላጊ ነው።
የስኳር ህመም ያለባቸው ሴቶች አስቀድመው ማቀድና ማስተካከያ ማድረግ ለተሻለ ውጤት ወሳኝ ነው። የጽንስ ጤና ችግሮች እንዳይከሰቱ ይረዳል። ስለሆነም የእርግዝና ጊዜን በደንብ ማሰብ ያስፈልጋል። የስኳር መጠኑ አሪፍ ቁጥጥር ደረጃ እስኪደርስ ድረስ አስተማማኝ የእርግዝና መከላከያ መጠቀም ይመከራል።
ስለዚህ ለማርገዝ እያሰብሽ ከሆነ እና የስኳር ህመም ካለብሽ ይህን ወሳኝ የቅድመ እርግዝና እንክብካቤ ምክር እናካፍልሽ።
የግሉኮስ ቁጥጥርን ማሻሻል
ከማርገዝ በፊት በተቻለ መጠን የስኳር ቁጥጥር ደረጃን በደንብ ማስተካከል ይገባል። በተቻለ አቅም ስኳሩን ወደ ጤናማ መጠን ማድረስ ይመከራል። ለአብዛኛዎቹ ሴቶች የሶስት ወር ስኳር ክምችት መጠን (A1c) ከ6.5% በታች ቢሆን ይመረጣል። በርካታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ይህንን የስኳር ግብ ማሳካት በእርግዝና እና ወሊድ ወቅት የሚፈጠሩ የጤና ችግሮችን፣ ውርጃ እና ሌሎች ችግሮችን በእጅጉ ይቀንሳል።
ይህን ለማድረግ ከሌላው ጊዜ በተለዬ ቶሎ ቶሎ ክትትል ማድረግ ጥሩ ነው። የደም ውስጥ የግሉኮስ መጠንን በየጊዜው መከታተል (በባዶ ሆድ እና ከምግብ በኋላ) ቆንጆ የግላይሴሚክ ቁጥጥር ለማምጣት አስፈላጊ ነው።
መድሃኒቶችን፣ አመጋገብን፣ ክብደትን ወዘተ ማስተካከልና ማሻሻል ያስቀመጥነውን ግብ በቶሎ ለመድረስ ይረዳል። ከስኳር ባለፈ አጠቃላይ ጤንነት ለማረጋገጥ ከስኳር ሃኪም፣ የማህፀን ሐኪም ወይም ሌሎች ባለሙያዎች ጋር ይወያዩ።
የመድኃኒት ማስተካከያዎች ማድረግ
አንዳንድ መድሃኒቶች ለእርግዝና ላይመጥኑ ይችላሉ። ስለሆነም ሁሉንም የሚወስዷቸውን መድሃኒቶች መቀየር ወይም ማቆም ይፈልግ እንደሆነ ከሃኪም ጋር ይወያዩ።
ለአብነትም የስኳር መድሃኒቶች ለእርግዝና የማይመከሩ ክኒኖች ከሆኑ ወይም ስኳሩን በደንብ እየተቆጣጠሩት ካልሆነ ወደ ኢንሱሊን ሊቀየርልዎት ይችላል።
ጽንስ የሚጎዱ አንዳንድ የግፊት መድሃኒቶች፣ የኮሌስትሮል መድሃኒት፣ ደም ማቅጠኛዎች፣ ማስታገሻዎች፣ የሚጥል ህመም መድሃኒቶች ወዘተ መቋረጥ ወይም ለእርግዝና በሚመጥኑ አቻ መድሃኒቶች መቀየር ሊያስፈልግ ይችላል።
የፎሌት ቫይታሚን መውሰድ (Folic Acid Supplementation)
ይህ ቫይታሚን ለሽል አፈጣጠርና ጽንስ እድገት ይጠቅማል። በተለይም የአንጎልና ህብለ ሰረሰር ቱቦዎች አፈጣጠር እክሎችን ይቀንሳል።
የአኗኗር ዘይቤ ማሻሻያዎች ማድረግ
ማህጸን ለእርግዝና ዝግጁ እንዲሆን የአኗኗር ዘይቤን አስቀድሞ ማስተካከል ይመከራል። የተመጣጠነ እና ጤናማ አመጋገብ ማዘውተር ለእርግዝና ጤና ወሳኝ ነው። የተረጋጋ እና የማይዋዥቅ ስኳር እንዲኖረን የተሻሻለ አመጋገብ ስርዓት ማዳበር ይገባል።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የስኳር ቁጥጥርን እና አጠቃላይ ጤናን ያሻሽላል።
ሌላው ወሳኝ ነገር ከእርግዝና በፊት ክብደት ማስተካከል ነው።
አልኮል፣ ሲጋራ እና ሌላም ጎጂ ሱስ ካለ እርግፍ አርጎ ማቆም ይመከራል።
የስኳር ተያያዥ ችግሮችን ለመለየት ቅድመ ምርመራዎች ማሰራት
- የአይን ምርመራ ማድረግ፡ እርግዝና ከስኳር ጋር የተያያዘ የአይን ነርቭ ችግርን (Diabetic Retinopathy) ሊያባብሰው ስለሚችል አጠቃላይ የአይን ምርመራ በተለይም የአይን ነርቭ ምርመራ ያድርጉ
- የኩላሊት ምርመራ ማድረግ፡ በሽንትና ደም ናሙና የሚሰራ የኩላሊት ክትትል ያስፈልጋል።
- ሌሎችም እንደ ልብ ህመም ያሉ የደም ሥር ችግሮችን (cardiovascular conditions) መታዬት ጥሩ ነው።
- እንዳስፈላጊነቱ የእንቅርት ሆርሞን ምርመራ ሊያስፈልግ ይችላል።
መደበኛ የእርግዝና ክትትል ወዲያውኑ መጀመር
እርግዝና እንደታዎቀ ወዲያዉኑ የእርግዝና ክትትል ጀምሪ። እንደአስፈላጊነቱ የስኳር መድሃኒቱን ቶሎ ቶሎ ማስተካከል ስለሚያስፈልግ ከሃኪምሽ ጋር በቅርብ መመካከር ቀጥይ።
እነዚህን ምክሮችን በመተግበር የስኳር ህመም ያለባቸው ሴቶች ጤናማ እርግዝና እንዲኖራቸው ማድረግ ይቻላል። ጤናማ ልጅ መውለድ ያስችላቸዋል።
ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል ወይም የግል ሆስፒታሎች መመካከር ይችላሉ።
ተጨማሪ ምክር፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት በኢሜል፦ contact@melakutaye.com ማግኘት ይችላሉ።
በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ Telegram, YouTube & TikTok ይከታተሉ። እነዚህን የተረጋገጡ መረጃዎች ለሌሎችም እንዲያጋሩ በትህትና እጋብዛለሁ።