ቡና ለጤና

አይ ቡና! ‘የገቢ ምንጫችን ቡና ቡና ..’ እያልን የዘመርንለት፣ ‘ቡና ደሜ ..’ እያልን ስታዲየም የጨፈርንለት፣ ከከፋ ተነስቶ አለምን ያጥለቀለቀ መጠጥ! ያለ ቡና መዋል ለብዙዎች የማይቻል ነው። ቡና በብዙዎች የሚወደድ የየለት መጠጥ ሆኗል።


ቀኔ የሚጀምረው የጧት ቡናየን ስቀምስ ነው የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም። መልካም ዜና! ቡና በመጠኑ ሲጠጣ ከማነቃቃት ባሻገር በርካታ የጤና ጥቅሞች ይሰጣል። በመልካም መኣዛና ጥኡም ጣእም ከመደሰት በላይ ቡና ጤናን ይጠብቃል።


በዚህ ጽሁፍ የቡናን የጤና ጥቅሞች እናብራራልዎት ።


ቡና እድሜን ያረዝማል (Longevity)

እንደ ጆን ሆፕኪንስ ተቋም መረጃ መሰረት ቡናን የሚያጣጥሙ ሰዎች በልብ ህመም፣ ስትሮክ፣ ስኳር ህመም፣ ኩላሊት ህመም ወዘተ ያሉ ገዳይ በሽታዎችን ስለሚቀንስ ጤናማ ረጅም እድሜ ለመኖር ይረዳል። ስለሆነም ቡና ከመጠጥነት በላይ የሆነ እድሜ የሚያረዝም የህይወት መድህን ነው ማለት ይቻላል።


የዘረመል (ዲ ኤን ኤ) ጤናን ይጠብቃል

ቡና ተፈጥሯዊ የዲኤን ኤ ጠባሳ እና ብልሽት ሊቀንስ ይችላል የሚሉ ጥናቶች አሉ።


ለጉበት ጤና ይረዳል

ቡና ጉበት ላይ የአደጋ እንዳይደርስ ይከላከላል።


የካንሰር ተጋላጭነትን ይቀንሳል

በተለይም የአንጀት ካንሰር የመያዝ እድልን ይቀንሳል።


የደም ስኳር መጠን እንዳይጨምር ይረዳል

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ቡና በትንሹም ቢሆን የደም ስኳር መጠን እንዳያሻቅብ ይረዳል። ቡና የሚጠጡ ሰዎች የተሻለ የግሉኮስ ሜታቦሊዝም ስላላቸው በአይነት ሁለት ስኳር የመያዝ እድልን ይቀንሳል።


ለልብ ጤና ይጠቅማል

በቀን ከአንድ አስከ ሶስት ስኒ ቡና መጠጣት ለልብ ጤንነት ይጠቅማል የሚሉ ማስረጃዎች አሉ። በልብ ድካም የመያዝ እድልን ይቀንሳል።


የአእምሮ/አንጎል ጤናን ይጠብቃል (Neuroprotective Effects)

በቀን ከአንድ አስከ ሶስት ስኒ ቡና መጠጣት የመርሳት በሽታ (አልዛይመር) ስጋትን ይቀንሳል። በተጨማሪም ከእድሜ ጋር የሚመጣ የእጅ መንቀጥቀጥ (Parkinson’s disease) ለመቀነስ ይረዳል። ሰውነት ፓራላይዝ የሚያደርገው የአንጎል መታዎክ (Stroke) በእጅጉ ይቀንሳል።


የእነዚህ በርካታ የጤና ጥቅሞች ተካፋይ ለመሆን ምን ላድርግ?

ቡና በመጠኑ መጠጣት አስፈላጊ ነው። የቡና ጤና ትሩፋቶችን ለማግኘት ከልክ ያለፈ ቡና መጋት አይፈልግም። በቀን ከሶስት ስኒ ያልበለጠ በቂ ነው።


ጸረ ተባይ መድሃኒት ርጭቶች የበዛበት ከሚሆን ይልቅ ኦርጋኒክ የተፈጥሮ ቡናን ይምረጡ። በጣም አምሽተው ቡና ከመጠጣት ይልቅ በመክሰስ ሰአት በፊት ቢሆን እንቅልፍ እንዳይረብሽ ይረዳል።


ቡናን ማብዛት የልብ ምት ሊያዛባ ይችላል። የእንቅልፍ መዛባትና ተያያዥ ጭንቀት ሊያስከትል ይችላል። በተጨማሪም የቡና ጥቅሞችን ለማጣጣም ቡና ሲጠጡ ማጣፈጫ (ስኳር፣ ክሬም፣ ጨው ወይም ሌላ ጤናን ሊጎዳ የሚችል) አይጨምሩ።


ያስታውሱ ቡና ለጤናማ አኗኗር አንዱ አካል ያድረጉት። ሙሉ ጤናን ለመጠበቅ እና ደስተኛ ህይወት ለመምራት የተስተካከለ አመጋገብ፣ መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ በቂ እንቅልፍ መተኛት፣ ጭንቀት አለማብዛት እና ከሱስ የጸዳ አኗኗር ዘይቤ ወሳኝ ነው።


ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል ወይም የግል ሆስፒታሎች መመካከር ይችላሉ።


ተጨማሪ ምክር፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት በኢሜል፦ contact@melakutaye.com ማግኘት ይችላሉ።


በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ Telegram, YouTube & TikTok ይከታተሉ። እነዚህን የተረጋገጡ መረጃዎች ለሌሎችም እንዲያጋሩ በትህትና እጋብዛለሁ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top