በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የስኳር ህመም (Gestational diabetes, GDM) ሲባል በእርግዝና ጊዜ በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ከሚገባው በላይ ከፍ ብሎ ሲገኝ የሚከሰት የጤና ችግር ሲሆን ነፍሰ ጡር እናቶችን ከሚያጠቁ የጤና ችግሮች በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው።
በአብዛኛው በ24 እና 28 ሳምንታት መካከል ባለው የእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የስኳር ህመም አይነት ነው። ይህ የስኳር አይነት ብዙውን ጊዜ ከወሊድ በኋላ የሚጠፋ ቢሆንም በትክክል ካልታከመ በጽንስና እናት ላይ ጊዜያዊና የረጅም ጊዜ የጤና ችግሮች ሊያስከትል ይችላል።
ይህንን የእርግዝና ጊዜ የጤና ችግር በአስተማማኝ ሁኔታ ለማከምና ለመከላከል የስኳር ቅድመ ምርመራ ለሁሉም እናት (universal screening for GDM) አስፈላጊ ነው። ሁሉም ነፍሰ ጡር እናቶች የስኳር ምርመራ ማድረግ አለባቸው።
ይህ ትምህርታዊ ጽሁፍ የእርግዝና ጊዜ የስኳር ቅድመ ምርመራ አስፈላጊነትን፣ አለም አቀፋዊ መመሪያዎችን እና ማስረጃዎችን ይዳስሳል።
የስኳር ቅድመ ምርመራ ለሁሉም እናት ለምን አስፈለገ?
እያንዳንዷ ነፍሰ ጡር እናት የስኳር ምርመራ ማድረግ ይገባታል። የስኳር ህመም ተጋላጭነት ምክንያቶች ቢኖሩም ባይኖሩም የስኳር ምርመራ ማድረግ ለሁሉም እርጉዝ ሴት የሚመከር ነው። ይህ አካሄድ በብዙ አስረጅዎች የሚደገፍ ነው።
-
- የእርግዝና ጊዜ ስኳር ህመም ምልክት አልባ ስለሆነ፡ ብዙ የእርግዝና ጊዜ ስኳር ህመም ያለባቸው እናቶች ምንም አይነት የህመም ምልክት አያሳዩም። ስለሆነም የህመም ስሜት የለኝም በሚል ብቻ ምርመራ የማናደርግ ከሆነ አብዛኛው ስኳር ሳይታዎቅ ጽንስ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።
-
- ለውጤታማ እርግዝና አወንታዊ አስተዋጽ ያደርጋል፡ የጂዲኤም (GDM) ቅድመ ምርመራ መተግበር እና በጊዜ መታከም በርካታ የእናትና ጽንስ ጤና ችግሮችን ለምሳሌ የጽንስ መፋፋትና መተለቅ (macrosomia)፣ ያለጊዜው መውለድ፣ የእርግዝና ጊዜ የደም ግፊት፣ የጽንስ መታፈን፣ የአራስ ህጻን የመተንፈስ ችግርና የጨቅላው የደም ስኳር ማነስ (neonatal hypoglycemia) ወዘተ ያሉ ችግሮችን ይቀንሳል።
-
- የረጅም ጊዜ የጤና ስጋቶችን ለመከላከል ያግዛል፡ እናት እና ልጅ ወደፊት ለአይነት 2 የስኳር በሽታ የመጋለጥ እድላቸው ከፍ ያለ ስለሆነ የስኳር ቅድመ ምርመራ ለሁሉም እናት ማድረግ እነዚህን ተጋላጭነቶች ለመቀነስ በጊዜ የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ ያስችላል።
የእርግዝና ጊዜ የስኳር ቅድመ ምርመራ መቼ ይሰራል?
የስኳር ቅድመ ምርመራ ለሁሉም ነፍሰ ጡር እናት የሚሰራው በ24 እና 28 ሳምንታት መካከል ባለው አማካኝ የእርግዝና ወራት ነው። ይህ ጊዜ የተመረጠው ስኳር አምጭ የሆኑት የእርግዝና ሆርሞኖች (the diabetogenic placental hormones) የሚበዙበት ወቅት ስለሆነ ነው።
ነገር ግን ከፍተኛ የስኳር ተጋላጭነት ያላቸው ሴቶች (ለምሳሌ ከዚህ በፊት በነበረው እርግዝና ስኳር የታየባቸው፣ ከፍተኛ ውፍረት፣ ወይም ሌላ የሆርሞች መዛባት ችግር) ከ24 ሳምንትም ቀደም ብለው እርግዝና እንደታወቀ ወዲያውኑ ሊመረመሩ ይችላሉ።
የስኳር ቅድመ ምርመራ ለሁሉም እናት እንዴት ይሰራል?
ለእርግዝና ጊዜ የስኳር ቅድመ ምርመራ ለመስራት በጣም የተለመደው የምርመራ ዘዴ የሚበጠበጥ 75 ግራም ግሉኮስ ፈሳሽ/ሽሮፕ በመጠጣት (Oral Glucose Tolerance Test, OGTT) የሚሰራው ነው። በጣም ቀላል የደም ምርመራ ሲሆን እንደሚከተለው ይሰራል።
-
- በመጀመሪያ በባዶ ሆድ (ለስምንት ሰአት ያክል ምንም ምግብ ሳይበላ) ያለውን የደም ግሉኮስ መጠን ለማወቅ ክንድ ላይ ካለው የደም ሥር የደም ናሙና ተወሰዶ ይመረመራል።
-
- ቀጥሎ የሚጠጣ 75 ግራም ግሉኮስ የያዘ ጣፋጭ ሽሮፕ/ፈሳሽ ይወሰዳል።
-
- ከዚያም ግሉኮሱን ከጠጡ በኋላ ከአንድ ሰአት እና በድጋሜ ከሁለት ሰአት በኋላ ክንድ ላይ ካለው የደም ናሙና ተወስዶ የደም የስኳር መጠን ይለካል።
እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ጉዳይ ቢኖር ለዚህ የስኳር ምርመራ (OGTT) የደም ናሙናው መወሰድ ያለበት ከደም ሥር በሚቀዳ ደም እንጂ ከጣት ላይ ከሚወሰድ ናሙና አይደለም። ክንድ ላይ ካለው የደም ስር የሚወሰደው የደም ናሙና በትክክለኛነቱና አስተማማኝነቱ ተመራጭ ነው። በሁሉም የጂዲኤም ህክምና መመሪያዎች እንደተገለፀው የእርግዝና ጊዜ ስኳር ህመም ለማወቅ የምንጠቀምበት መስፈርት በደም ፕላዝማ ውስጥ ባለው የግሉኮስ መጠን ላይ የተመሰረተ ነው።
የጣት ላይ ደም በመውሰድ የሚደረግ ምርመራ በየቀኑ የስኳር መጠንን በራስ ለመከታተል ጠቃሚ ቢሆንም የስኳር ህመም አለብኝ ወይስ የለብኝም ብሎ ለመለየት ግን ተስማሚ አይደለም። ስለሆነም ከጣት ላይ የሚደረገው ምርመራ ስኳር ህመም ከታወቀ በኋላ ለክትትል እንጅ መጀመሪያ ላይ ስኳር ህመም ለማወቅ (ዲያግኖስ ለማድረግ) መጠቀም የለብንም። ( Finger pricks are used for daily self-monitoring of blood glucose levels, not for diagnostic purposes).
የእርግዝና ጊዜ ስኳር መለያ መስፈርቶች (Diagnostic Criteria for GDM)
በብዛት ጥቅም ላይ የሚውሉት የምርመራ መመዘኛዎች ከሚከተሉት የስኳር ምርመራዎች ውስጥ አንዱ ከተሟላ ስኳር አለ ለማለት ያስችላል።
-
- የባዶ ሆድ የደም ስኳር መጠን፡ ≥92 mg/dL
-
- ግሉኮስ ከተጠጣ ከ1-ሰዓት በኋላ ያለው የደም ስኳር መጠን፡ ≥ 180 mg/dL
-
- ግሉኮስ ከተጠጣ ከ2-ሰዓት በኋላ ያለው የደም ስኳር መጠን፡ ≥ 153 mg/dL
እነዚህ መመዘኛ መስፈርቶች የወጡት በእናቶች የስኳር መጠን እና በእርግዝና ጤና መካከል ያለውን ቀጥተኛ ግንኙነት አጥንቶ ያረጋገጠው የHyperglycemia and Adverse Pregnancy Outcome (HAPO) ምርምር ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ይህ ትልቅ ጥናት ከ23,000 በላይ ነፍሰ ጡር እናቶችን ያሳተፈ አለማቀፋዊ ምርምር ሲሆን የደም ስኳር ከፍ ማለት ከእርግዝና ጤና እክሎች ጋር ያለውን ጠንካራ ግንኙነት አረጋግጧል። እንኳን በደንብ የጨመረው ስኳር በትንሹም ከፍ ያለውን ስኳር መመርመር እና ማከም በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት አመላክቷል።
ሌሎችም በርካታ ጥናቶች በተደጋጋሚ እንደሚያሳዩት የስኳር ቅድመ ምርመራ ለሁሉም እናት ማድረግ ወጭ ቆጣቢና ውጤታማ ህክምና ነው። በርካታ የንጽጽር ጥናቶች እንዳሳዩት የስኳር ቅድመ ምርመራ ለሁሉም እናት መስራትን ከተጋላጭነት ላይ ብቻ ያተኮረ ምርመራ ጋር በማነፃፀር እንዳሳዩት የስኳር ቅድመ ምርመራ ለሁሉም እናት መስራት የላቀ የጤና ጥቅሞች አሉት (universal GDM screening is superior to selective risk-based screening)። የኢኮኖሚ ትንታኔዎችም እንዳረጋገጡት ያልታወቀ ስኳር የሚያመጣቸው የጤና ችግሮችን ለማከም የሚውል ከፍተኛ የጤና ወጪን ለመቀነስ በአነስተኛ ወጪ ምርመራውን አስቀድሞ ማሰራት የተሻለ ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እኤአ ከ2013 ጀምሮ የስኳር ቅድመ ምርመራ ለሁሉም እናት እንዲሰራ ባወጣው መመሪያ አጽድቋል። ይህ መመሪያ ሁሉም ነፍሰ ጡር እናቶች በ24-28 ሳምንታት እርግዝና ወቅት 75 ግራም የግሉኮስ ምርመራ በማድረግ ሁሉም እናቶች እንዲመረመሩ ይመክራል። ይህ መመሪያ የስኳር ቅድመ ምርመራ ለሁሉም እናት በአለም አቀፍ ደረጃ እንዲዳረስ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።
ከወሊድ በኋላ የሚደረግ የስኳር ክትትል
የእርግዝና ጊዜ ስኳር የተገኘባት ሴት የስኳር ክትትል ከወሊድ በኋላም መቀጠል አለባት። ድህረ ወሊድ ከ6 እስከ 12 ሳምንታት ባለው ጊዜ ውስጥ እንደገና የስኳር ምርመራ በማድረግ ስኳሩ መስተካከሉን ማረጋገጥ ይገባል። ከዚያም በኋላ የስኳር ቅድመ ምርመራዎችዎን ቢያንስ በየሶስት አመቱ መመርመር ያስፈልጋታል።
የጂዲኤም ምርመራን ለሁሉም እናቶች ለማዳረስ የሚረዱ ምክሮች
የጂዲኤም ምርመራን ለሁሉም እናቶች ማሰራት የተረጋገጡ የጤና ጥቅሞች ቢኖረውም በኢትዮጵያ በስፋት እየተተገበረ አይደለም። ስለሆነም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነፍሰ ጡር ሴት ለጂዲኤም ምርመራ ማድረግ እንድትችል ከቤተሰብ፣ ከጤና ባለሙያዎች እና ከጤና መሪዎች የተቀናጀ ጥረት አስፈላጊ ነው።
ሁሉም የቤተሰብ አባል ስለ ጂዲኤም ምርመራ፣ የጤና ችግሮች እና አስቀድሞ የማወቅን አስፈላጊነት መገንዘብ አለባቸው። እያንዳንዱ ቤተሰብ ስለጂዲኤም ያላው እውቀት ሲዳብር ሃገራዊ ጥረቱን ያግዛል።
ሁሉም ነፍሰ ጡር እናቶች እና የትዳር አጋሮቻቸው የስኳር ቅድመ ምርመራ ማድረግ የመደበኛ የቅድመ ወሊድ እንክብካቤና ክትትል አንድ አካል አድረገው ማየትና ምርመራው እንዲደረግላቸው የጤና ባለሙያዎቻቸውን አበክረው መጠየቅ አለባቸው። የስኳር ምርመራ የመደበኛ ቅድመ ወሊድ ክትትል አካል እንዲሆን መሟገት ያስፈልጋል።
የጤና ባለሙያዎች በበኩላቸው ስለጂዲኤም ግንዛቤን ማስጨበጥ ይገባቸዋል። በተለይም የቅድመ ወሊድ ክትትል አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች የስኳር ቅድመ ምርመራ ለሁሉም እናት እንዲሰራ ማድረግ አለባቸው። የአለም የጤና ድርጅት እንዳስቀመጠው ደረጃውን የጠበቀ የጂዲኤም ምርመራ ማሰራት ይገባቸዋል። ለዚህ እንዲረዳ ባለሙያዎችን ማሰልጠን ሊያስፈልግ ይችላል።
የጤና ተቋማት እና መሪዎችም የጂዲኤም ምርመራን በሀገር አቀፍ መመሪያዎች ውስጥ ማካተትና መተግበር አለባቸው። የጂዲኤም ምርመራ ለሁሉም እናቶች እንዲዳረስ በሀገር አቀፍ መደበኛ የቅድመ ወሊድ ክትትል ፕሮቶኮሎች ጋር በማቀናጀት ሁሉም የጤና ተቋማት አስገዳጅ ፓኬጅ አካል መሆን አለበት። ባለሙያዎችን ማሰልጠን፣ የግሉኮስ መመርመሪያ አቅርቦቶች ማሻሻል፣ እና ተግባራዊነቱን መከታተል ይገባል። ስለጂዲኤም ምርመራ አስፈላጊነት ለማስረጽ የህዝብ ግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻዎችን መጀመርና መደገፍ ያስፈልጋል።
ማጠቃለያ
የስኳር ቅድመ ምርመራ ለሁሉም ነፍሰ ጡር እናት ይገባታል። በእናት እና ጽንስ ጤና ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት አድርጎ ማየት ያስፈልጋል። ጂዲኤምን ቀድሞ በመለየት እና በመቆጣጠር የሚያመጣቸውን የጤና መዘዞች መከላከል፣ የረጅም ጊዜ የጤና ችግሮችን መቀነስ ያስችላል።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ በመስራት ነፍሰ ጡር እናቶች በሙሉ የጂዲኤም ምርመራ እንዲደረግላቸው የሚያስችል ደጋፊ የጤና ስርአት መፍጠር ይችላሉ።
እያንዳንዷ እናት ጤናማ እርግዝና እንዲኖራት ለማረጋገጥ የሚያግዘውን የስኳር ምርመራ እንዲያደርጉ በማገዝ ጤናማ ማህበረሰብን ለመገንባት አስተዋጽኦ እናድርግ።
የስኳር ቅድመ ምርመራ ለሁሉም እናት ማዳረስ ጤናማ ትውልድን ማረጋገጥ ነው።
ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል ወይም የግል ሆስፒታሎች መመካከር ይችላሉ።
ተጨማሪ ምክር፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት በኢሜል፦ contact@melakutaye.com ማግኘት ይችላሉ።
በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ Telegram, YouTube & TikTok ይከታተሉ። እነዚህን የተረጋገጡ መረጃዎች ለሌሎችም እንዲያጋሩ በትህትና እጋብዛለሁ።
Wow an essential platform Dr
Thanks so much