በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የስኳር ህመም ለመጀመሪያ ጊዜ በእርግዝና ወቅት በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ከሚገባው በላይ ከፍ ብሎ ሲገኝ የሚከሰት የጤና ችግር ነው። በአብዛኛው ከ5-7 ወር ባለው የእርግዝና ጊዜ የሚከሰትና ከወሊድ በኋላ የሚጠፋ ነው።
የስኳር ህመም በእርግዝና ወቅት ሲመጣ በነፍሰ ጡር እናቶች እና በጽንስ ጤና ላይ ተጽዕኖ ያስከትላል። ነገር ግን የስኳር ህመም በተገቢው መንገድ ከታከመ እናትም ልጅም ደህና እንዲሆኑ ይረዳል።
ከሌሎች የስኳር አይነቶች የሚለይባቸው መገለጫዎቹ
- ከእርግዝና በኋላ የሚጠፋ ጊዜያዊ መሆኑ
- የሚያስከትላቸው የጤና ችግሮች ከሌሎች ቋሚ የስኳር አይነቶች አነስ ያለ መሆኑ
- የራሱ የሆነ ምልክቶች የሉትም
ስርጭቱ በአለም አቀፍና በአገራችን ደረጃ ምን ይመስላል?
የስኳር ህመም በእርግዝና ወቅት ከሚከሰቱ የጤና እክሎች ውስጥ ቀዳሚው ነው። በአለም አቀፍ ደረጃ ከአምስት እናቶች አንዷ ለዚህ የስኳር ህመም ተጋላጭ ነች። የአለም የስኳር ፌደሬሽን (IDF) እኤአ በ2021 ባወጣው ሪፖርቱ 15% የሚደርሱ ነፍሰ ጡር እናቶች በዚህ ህመም ይጠቃሉ። ስርጭቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል።
መንስኤዎቹ ምንድር ናቸው?
ይህ ህመም የሚከሰተው በሆድ እቃ ውስጥ የሚገኘው ቆሽት (pancreas) የተባለው የአካል ክፍላችን ከእርግዝና ፍላጎት ጋር ተመጣጣኝ የኢንሱሊን ሆርሞንን ማመንጨት ሲቀንስ ወይም ሆርሞኑ ቢመነጭም የሰውነት ህዋሶቻችን ይህንን በአግባቡ መጠቀም ሲያቅት ነው። ከእንግዴ ልጁ የሚመነጩ ሆርሞኖች ኢንሱሊን እንዳይሰራ በማድረግ ረገድ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ።
ተጋላጭነት ያላቸው ሴቶች እነማን ናቸው?
- ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያለባቸው
- አካላዊ እንቅስቃሴ የማያዘወትሩ ከሆኑ
- ባለፈው እርግዝና ወቅት ስኳር የታየባቸው ሴቶች
- ከ4 ኪሎ ግራም በላይ ክብደት ያለው ትልቅ ልጅ የወለዱ ሴቶች
- በቤተሰብ የስኳር ህመም ያለባቸው ሴቶች
- ተደጋጋሚ ውርጃ ያጋጠማቸው ሴቶች
ምልክቶች ምንድር ናቸው?
በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የስኳር ህመም አብዛኛወን ጊዜ ምንም አይነት ምልክት አያሳይም። በዚህ ምልክት አልባነቱ ምክንያት ሁሉም ነፍሰ ጡር እናቶች የእርግዝናው አጋማሽ ላይ የስኳር ምርመራ እንዲያደርጉ ይመከራል። በተለይ የስኳር መጠኑ በጣም ከፍ ሲል የሚታዩ ምልክቶች ለመጥቀስ ያህል ከፍተኛ የዉሃ ጥም፣ ቶሎቶሎና አብዝቶ መሽናትና ሃይለኛ የድካም ስሜት ይገኙበታል።
ምርመራዎች ምንምን ናቸው?
በአብዛኛዎቹ ነፍሰ ጡር እናቶች ላይ የስኳር ምርመራ የሚደረገው ከ6 እስከ 7ኛ ወር ላይ ነው። ለስኳር ህመም ያላቸው ተጋላጭነት በጣም ከፍ ያለ ከሆነ ግን ቀደም ብሎ እርግዝናው እንደታወቀ መመርመር ይኖርባቸዋል። ምርመራው የሚደረገውም 75 ግራም ስኳር ያለው ፈሳሽ ተወስዶ የሚሰራ የደም የስኳር ምርመራ ሲሆን በእርግዛና ጊዜ ከሚጠበቀው ስኳር መጠን በላይ ከፍ ያለ ከሆነ የስኳር ህመም መኖሩን ያሳያል።
በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የስኳር ህመም የሚያስከትላቸው የጤና ችግሮች
በበቂ ሁኔታ ክትትልና ቁጥጥር ካልተደረገ በጽንስና እናት ላይ በርካታ የጤና እክሎች ሊያስከትል ይችላል።
በእናት ላይ የሚያስከትላቸው የጤና ችግሮች
- ውርጃ፣ የጽንስ መጥፋት
- የደም ግፊት መጨመር
- በኦፕሬሽን የመውለድ እድል ይጨምራል
- በቀጣይነት በስኳር ህመም የመያዝ ተጋላጭነት ይጨምራል
በጽንስ ላይ የሚያስከትላቸው የጤና ችግሮች
- ከመጠን በላይ ክብደት ያለው ትልቅ ልጅ መውለድ
- ካለቀኑ መወለድ
- የመተንፈሻ ችግር
- የአፈጣጠር ችግሮችና አካልዊ ጉድለቶች
እንዴት ይታከማል?
ለእናት ጤንነት እና ለጽንስ ደህንነት ለማረጋገጥ ስኳርን በጥብቅና በጊዜ መቆጣጠር አስፈላጊ ነው። የስኳር ህመም በተገቢው መንገድ ከታከመ እናትም ልጅም ደህና እንዲሆኑ ይረዳል።
በመጀመርያ የስኳር ህመም የተገኘባት ሴት ስለ ህመሙና ህክምናው ጠንቅቆ ማወቅና መረዳት ይፈልጋል። የስኳር ቁጥጥር እቅድና ግብ ማስቀመጠም አስፈላጊ ነው።
ጤናማ የአኗኗር ስልት መዘየድ ለስኳር ህክምና ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። ጤናማ አመጋገብ ማዘውተር ይፈልጋል። ነገር ግን ለሁሉም የስኳር ታካሚዎች የሚመች የአመጋገብ መመርያ ማውጣት አዳጋች ነው። ዋናው መሰረታዊ ቁምነገር ግን የምንመገበው ምግብ የስኳር መጠናችንን እንዳያበዛ እና እንዳያንስ መጠንቀቅ ነው።
ከዋናዋናዎቹ የአመጋገብ መርሆች መካከል በእየለቱ መደበኛ የምግብ ሰአት ማበጀት፣ ሃይል ሰጪ ምግቦችን ሲበሉ አሰርነት ያላቸዉን ምግቦች መምረጥ በተለይ ቅጠላ ቅጠሎችን ማዘውተር፣ ቀላል ስኳርነት ያላቸዉን ጣፋጭ ምግቦች አለመጠቀም ያካትታል።
ሌላው መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስራትም ወሳኝነት አለው።
ጤናማ የአኗኗር ስልት ከመከተል በተጨማሪ ከጤና ባለሙያዉ ጋር በመመካከር እንዳስፈላጊነቱ የስኳር መድሃኒት ሊታዘዝ ይችላል። የስኳር ህመም ላለባት ነፍሰጡር እናት የስኳር መጠን ለመቆጣጠር የተወሰኑ የመድሃኒት አማራጮች ቢኖሩም በጣም ተመራጭ የሆነው ሕክምና በመርፌ በሚሰጥ ኢንሱሊን ነው።
ከሌሎች የሚዋጡ መድሃኒቶች ይልቅ ኢንሱሊን የሚመረጥባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፡
- የመጀመርያው ምክንያት ኢንሱሊን ለእናትም ለጽንስም ደህንነት ሲባል ነው። ኢንሱሊን በእርግዝና ወቅት የስኳር በሽታን ለመቆጣጠር በጣም አስተማማኝ መድሃኒት ነው። የእንግዴ ልጁን ማለፍ ስለማይችል በማደግ ላይ ያለውን ጽንስ በቀጥታ አይጎዳውም።
- ኢንሱሊን የስኳር መጠንን በተሻለ ለመቆጣጠር ያስችላል። በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን መዋዥቅ በጽንሱ ላይ አደጋን ሊፈጥር ይችላል፣ነገር ግን ኢንሱሊን ስኳሩን በታለመለት ግብ ውስጥ የተረጋጋ መሆኑን ያረጋግጣል።
- በተጨማሪም ኢንሱሊን እንደእርግዝናው ጊዜያት (gestational age) የእናትየዋን ተለዋዋጭ ፍላጎቶች ለማሟላት ኢንሱሊን ከአፍ ከሚወሰዱ መድኃኒቶች በበለጠ ይመቻል።
በነዚህ ዋነኛ ምክንያቶች ኢንሱሊን በእርግዝና ለሚከሰት ስኳር ተመራጭ፣ ደህንነቱ የተረጋገጠ እና ውጤታማነቱ የተመሰከረለት ሊሆን ችሏል።
ድህረ ወሊድም እንዳስፈላጊነቱ ዘላቂ ክትትልና ምርመራ ማድረግ ይመከራል።
በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የስኳር በሽታ ወደ ሕፃን ሊተላለፍ ይችላል?
በእርግዝና ወቅት ስኳር ሲከሰት የሚወለዱት ልጆች በጉልምስናና በበኋለኛው የአዋቂነት እድሜያቸው በስኳር የመያዝና ለከፍተኛ ውፍረት የመያዝ እድል በትንሹ ሊጨምረው ይችላል። በእርግዝና ወቅት ጥሩ የስኳር ቁጥጥር ከተደረገ ልጅ ላይ የሚያሳስብ ዘላቂ ችግር አያመጣም።
መከላከያ መንገዶች?
በዋናነት በቅድመ እርግዝና ወቅት (ከማርገዝ በፊት) ያለንን የአኗኗር ስልት ጤናም ማድረግ ያስፈልጋል። የሰውነት ክብደትን መቆጣጠር ጠቃሚ ነው።
የማህበረሰቡ ግንዛቤ ምን ይመስላል
የእርግዝና የስኳር በሽታ መረዳትና መከላከል ትውልድ ተሻጋሪ ስኳርን ለመቀነስ ጥሩ እድል ስለሚፈጠር ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል በቂ ግንዛቤ መያዝና የየራሳችንን ድርሻ መወጣት ይኖርብናል። ሁሉም ነፍሰ ጡር እናቶች የስኳር ቅድመ ምርመራ በማድረግ ሊያደርስ የሚችለዉን የጤና ችግር መቀነስ ይገባል።
ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል ወይም የግል ሆስፒታሎች መመካከር ይችላሉ።
ተጨማሪ ምክር፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት በኢሜል፦ contact@melakutaye.com እና ስልክ፦ +251921720381 ማግኘት ይችላሉ። በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ ብሎግ www.melakutaye.com ፣ ቴሌግራምና ቲክቶክ ይከታተሉ። እነዚህን የተረጋገጡ መረጃዎች ለሌሎችም እንዲያጋሩ በትህትና እጋብዛለሁ።
በጣም የተመጠነ እና አስተማሪ ጽሁፍ ነው እናመሠግናለን።