ለስኳር ታካሚዎች የፍራፍሬ አመጋገብ መመሪያ

የስኳር ታካሚዎች ከሚያነሷቸው መጠይቆች መካከል ‘ፍራፍሬ መመገብ እችላለሁ ወይ?’ የሚለው የተለመደ ጥያቄ ነው። የስኳር ታካሚዎች ፍራፍሬዎችን እንዴት መመገብ እንደሚችሉ በርካታ እርስ በእርስ የሚጣረሱ መረጃዎች ስለሚሰሙ ግራ መጋባት ይፈጥራሉ። ይህን ፍራፍሬ ብላ፣ ያንን ፍሬ እንዳትነካ፣ ይህ የተፈቀደ ነው፣ ያኛው ግዝት ነው ወዘተ የሚሉ ውዥንብር የሚፈጥሩ ያልተረጋገጡ የአመጋገብ ምክሮች አሉ። አንዱ ሃኪም አዎ ያለውን ሌላኛው አይ ብሎ ሊያወዛግበን ይችላል። በተለይ በሃኪምና በስነ ምግብ ባለሙያ የሚሰጡ ምክሮች አራምባና ቆቦ መሆን  ከኑሮ ውድነት ባልተናነሰ የብዙዎቻችንን ቆሽት እያሳረረ ነው። በቅርቡ በአንድ ሲኒዬር ሃኪምና ወጣኒ ሃኪም መካከል በጣም የተለያዬ የአመጋገብ ምክር የተሰጣት አንዲት ታካሚ ከመበሳጨቷ የተነሳ ‘በቃ አንድ ላይ ተነጋግራችሁ ስትስማሙ ንገሩኝ’ ብላ ተቆጥታኛለች።


ይህ ጽሁፍ የስኳር ታካሚዎች ፍራፍሬዎችን በማእዳቸው እንዴት ማካተት እንደሚችሉ ያስረዳል። ለስኳር ታካሚዎች የሚመከሩትን የፍራፍሬ አይነቶችና ልከኛ መጠን ያብራራል። የስኳር ቁጥጥርን ሳያበላሹ በፍራፍሬዎች ለመደሰት የሚያስችል  ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ስልቶችን ያመላክታል። እርስዎ እራስዎ የስኳር ታካሚ ከሆኑ ወይም የሚያውቁት ስኳር ያለበት ሰው ካለ ይህ መረጃ መነበብ አለበት። ይህን መረጃ ለሌሎች ሼር ማድረግ አይርሱ!


ፍራፍሬዎችን በስኳር ህክምና አመጋገብ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ያስፈልጋል?

በስኳር ህመም እና በፍራፍሬ አመጋገብ ላይ በጣም ከተለመዱት ሳይንሳዊ ያልሆኑ መረጃዎች መካከል አንዱ ‘የተወሰኑ ፍራፍሬዎች ሙሉ በሙሉ የተከለከሉ ናቸው’ የሚል ይገኝበታል። ይህንን በሳይንሳዊ ጥናቶች ያልተረጋገጠ መረጃ ከእውነታ መለየት ይገባል። እንደ እውነቱ ከሆነ አብዛኛዎቹ ፍራፍሬዎች በስኳር ህመም አመጋገብ እቅድ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።


የስኳር ህመም ላለባቸው ሰዎች ሙሉ በሙሉ የተገዘተ ምንም አይነት ፍራፍሬ የለም። ዋናው ቁምነገር የፍራፍሬ አጠቃቀም መመጠን እና በቶሎ ስኳር ከፍ የማያደርጉትን አይነቶች መምረጡ ላይ ነው። ፍራፍሬዎች ለጤና አስፈላጊ የሆኑ ቪታሚኖች፣ ማዕድናት እና ፋይበር ምንጭ ናቸው። በማስተዋል መጥነን ከተጠቀምንባቸው ለስኳር ታካሚዎች ተስማሚ የሆነ ምግብ አንድ አካል ሊሆኑ ይችላሉ።


ለስኳር ታካሚዎች የፍራፍሬ አመጋገብ መመሪያ ምን ይመስላል?

የስኳር ህመም አለብን ማለት ፍራፍሬዎችን ዞር ብለን ማየት የለብንም ማለት አይደለም። ነገር ግን የደም ስኳር መጠን በጣም ከፍ ሳይል እንዴት ፍራፍሬዎችን በጥበብ መመገብ እንዳለብን ማወቅ ይገባል።


ዝቅተኛ የስኳር መጠን ያላቸውን ፍራፍሬዎች መምረጥ

አብዛኛዎቹ ፍራፍሬዎች በውስጣቸው ተፈጥሯዊ ስኳር ቢኖራቸውም ከፍተኛ ፋይበር ይዘት ስላላቸው በተመገብን ከመቅጽበት የደም ስኳር መጠን በድንገት እንዳያሻቅብ ያደርጋል (low glycemic index)። ዝቅተኛ ግላይሴሚክ ኢንዴክስ ማለት ፍራፍሬ እንደበላን ወዲያውኑ የግሉኮስ መጠን በድንገት እንዲጨምር አያደርግም ማለት ነው።


አብዛኞቹ ፍራፍሬዎች ለስኳር ህመም ተስማሚ በሆነ አመጋገብ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ። ከፍራፍሬዎች መካከል ለስኳር ታካሚዎች የተሻሉ ምርጫዎች የሚከተሉትን ያካትታል።

  • አቮካዶ፡- በጤናማ ቅባት የበለፀገ ሲሆን የደም ስኳርን ለማረጋጋት ይረዳል።
  • ፖም (አፕል): ፋይበር እና ፖሊፊኖል (polyphenols) ስለሚሰጥ የደም ስኳርን በጣም ከፍ እንዳይል ያደርጋል።
  • ሲትረስ ፍራፍሬዎች (ብርቱካን፣ ሎሚ፣ ወይን ፍሬ): በቫይታሚን ሲ እና ፋይበር የበለፀጉ ናቸው።
  • እንጆሪ (Strawberries)፡ በአንቲ ኦክሲዳንት እና ፋይበር የተሞሉ ስለሆኑ በደም ስኳር መጠን ላይ ያለቸው ተጽእኖ እጅግ አነስተኛ ነው።
  • ፕሪም (Cherries)፣ ኮክ (Peaches)፣ ሸክኒት (Pears)፡ ከፍተኛ የፋይበር ይዘት ስላላቸው የግሉኮስ መጠን በአንዴ እንዳያሻቅብ ያደርጋል።

እነዚህ የዘረዘርናቸው ፍራፍሬዎች የስኳር መጠናቸው ዝቅተኛ ስለሆኑ በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን እንዳይጨምር ይረዳሉ። ብዙ ሳንሰጋ ተፈጥሯዊ ጣፋጭ ጣእም ለማጣጣም ያስችላሉ።

‘ከፍተኛ-ስኳር’ ያላቸው ጣፋጭ ፍራፍሬዎችስ? እንደ ማንጎ፣ አናናስ፣ ሙዝ እና መሰል በጣም ጣፋጭ ፍራፍሬዎች ብዙውን ጊዜ በጭራሽ እንዳትወስዱ የሚል ወሬ ይነዛባቸዋል። ከፍ ያለ የተፈጥሮ የስኳር ይዘት ቢኖራቸውም ቅሉ በግዝት የተከለከሉ አይደሉም። ይልቁንስ መጠናቸውን ከሌሎች ፍራፍሬዎች የበለጠ በማሳነስ መጠቀም ይቻላል። ለምሳሌ ማንጎን ከፍለን ትንሽ ክፍል፣ አናናስ ትንሽየ ቁራጭ፣ የሃብሃብ አነስተኛ ቁራጭ ወዘተ አድረገን መብላት እንችላለን።


መጠናችንን መገደብ

ፍራፍሬ ስንመገብ ዋና ቁልፉ ልከኝነት ነው። ምንም እንኳ ፍራፍሬዎች ለጤናችን ጠቃሚ ቢሆኑም ቢሆን አብዝተን ከበላን የስኳር መጠን ከፍ ያደርጋሉ። ስለሆነም ፍራፍሬዎችን በተመጣጣኝ መጠን መጠቀም አስፈላጊ ነው። ሁሌም ቢሆን የምንመገበውን ፍራፍሬ መጠን መመጠን (Portion control) ይገባል።


በግርድፉ ከፍራፍሬ የምናገኘው ካርቦሃይድሬት ከ15 ግራም በላይ እንዳይሆን ይመከራል። ይህ ማለት በግምት ከአንድ አነስተኛ ብርቱካን፣ አንድ ትንሽ ፖም፣ አንድ እፍኝ እንጆሪ፣ ግማሽ መካከለኛ ሙዝ እና ተስተካካይ ሌሎች ፍራፍሬዎች ጋር እኩል ነው። የስኳር ህመም ያለበት ሰው በቀን ከተጠቀሰው በላይ ቢመገብ ስኳር ከቁጥጥር በላይ እንዲወጣ ሊያደርገው ይችላል። በሌላ አነጋገር ፍራፍሬን እንደግዝት ከምግብ ምርጫችን ሙሉ በሙሉ መሰረዝ አስፈላጊ ባይሆንም ከበዛ ግን ችግር መፍጠሩ አይቀርም።


ሌላው ደግሞ በአንድ ጊዜ ትልቅ ወይም ብዙ ፍራፍሬ ከመብላት ይልቅ የፍራፍሬ ፍጆታን በሰአታት መከፋፈል ይገባል። ድንገተኛ የደም ስኳር መለዋወጥን ለማስወገድ የፍራፍሬ ፍጆታን ለተለያዩ የምግብ ጊዜያት በእኩል መጠን ያከፋፍሉ።


በተጨማሪም ፍራፍሬዎችን ስንበላ ከሌላ ካርቦሃይድሬት ምንጮች ጋር ሳይሆን ከፕሮቲን ጋር ማጣመር የግሉኮስ መጠንን ለመቀነስ ይረዳል። ለምሳሌ ፍራፍሬን ከእንጀራ ወይም ዳቦ ጋር ከመብላት ይልቅ ከእንቁላል፣ ስጋ፣ ለውዝ ወይም ሌሎች የፕሮቲን ወይም ጤናማ ቅባት ምግቦች ጋር ቢሆን አጠቃላይ የስኳር አወሳሰድ መጠንን ለመገደብ ይረዳል።


ከጭማቂ ይልቅ ሳይጨመቅ ሙሉ ፍራፍሬዎችን መብላት

የፍራፍሬ ጭማቂ መጠጣት በጤና እና የደም ስኳር ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ ሙሉ ፍሬውን ከመብላት በተቃራኒ ነው። የፍራፍሬ ጭማቂ መጠጣት ሙሉ ፍሬውን ከመብላት በበለጠ ፍጥነት በደም ውስጥ ያለው የግሉኮስ መጠን እንዲጨምር ያደርጋል።


ጠቃሚ የፍራፍሬው ክፍል ተራግፈው ስለሚቀሩ ንጹህ የፍራፍሬ ጭማቂ የፍራፍሬውን ስኳርና ውሃ ብቻ የያዘ ነው። ጭማቂ ውስጥ የሚቀረው የፋይበር መጠን በጣም ትንሽ ነው። በተጨማሪም ጣዕምን ለማሻሻል ሲባል የፍራፍሬ ጭማቂ ውስጥ ስኳር የመጨመር እድላችን ሰፊ ነው። መጠኑም ቢሆን አንድ ብርጭቆ ጭማቂ ብዙ ፍራፍሬ ሊይዝ ይችላል። ጭማቂ ፈሳሽ ስለሆነ  ከአንጀት በፍጥነት ሰርጎ ወደ ደም ይገባል።


ሙሉ ፍራፍሬ ፋይበር፣ ቫይታሚንና ማዕድኖችን ይዟል ይህም ለአጠቃላይ ጤና ጠቃሚ ነው። ፋይበሩ የፍራፍሬው ተፈጥሯዊ ስኳር ወደ ደም ውስጥ የሚገባበትን ፍጥነት እንዲቀንስ እና ረዘም ላለ ጊዜ የጥጋብ ስሜት እንዲኖር ያደርጋል። በተቃራኒው ጭማቂ ወይም የታሸገ ጁስ ከሆነ ግን አብዛኛው ፋይበር በጭማቂ ማዘጋጀት ሂደት ይወገድና ስኳር ብቻ ይቀራል። ጭማቂ ስንጠጣም ፍራፍሬ እንደማኘክ ጊዜ ስለማይወስድ ሳናስተውለው በአንድ ትንፋሽ ብዙ ስኳር ለመጠጣት ይዳርጋል።


ለዚህም ነው በጁስ (ፍሬሽ ጭማቂም ይሁን የታሸገ) መልክ ካለው ፍራፍሬ ይልቅ ሙሉ ፍራፍሬን መብላት የሚበጀው።


ምንም እንኳን የፍራፍሬ ጭማቂ ከመጠጣት ሙሉ ፍራፍሬን መብላት የተሻለ ቢሆንም የተወሰነ ጭማቂ መውሰድ ከፈለጉ በቀን ከአንድ ትንሽ ብርጭቆ (150 ሚሊ ሊትር) የማይበልጥ ሆኖ በውሃ በደንብ በማቅጥን መጠቀም ይችላሉ።


ለአጠቃላይ ጤንነት የሚረዳ የተመጣጠነ አመጋገብ ላይ ማተኮር

አብዛኛው ሰው ስለጤናማ አመጋገብ ሲያስብ ይሄን ልብላ፣ ያኛው ይቅርብኝ፣ ይሄኛው ይሻል ይሆን? እያለ መብሰልሰልና መጨነቅ ያበዛል። ነገር ግን በእያንዳንዱ ማእድ ምን ልብላ ብሎ አብዝቶ ከማሰብ ይልቅ የጤናማ ኑሮ ትልቁ ምስል ላይ ማተኮር ይገባል። ተስማሚ የሆነ የምግብ እቅድ የጤናማ ኑሮ አንድ አካል ብቻ ነው።


ከፍራፍሬ አመጋገብ በተጨማሪ የተመጣጠነ አመጋገብ ፕሮቲኖች (ዶሮ፣ ቀይ ስጋ፣ አሳ፣ ቶፉ እና ለውዝ ወዘተ)፣ አሰርነታቸው ያልወጣ ያልተፈተጉ ሙሉ እህል ምግቦች፣  አረንጓዴ አትክልቶች ወዘተ ያጠቃልላል።


ስኳር ሳይጨምርብን የፍራፍሬ አምሮታችንን ማርካት ይቻላል!

ከላይ በሙሉ ጽሁፉ እንዳየነው ስኳር አብዝቶ ሳይጨምር በፍራፍሬ ጣፋጭ ጣእም አምሮታችንን ለመወጣት የሚረዱ መርሆዎችን መከተል ይገባል። በተጨማሪም ሁሌም ፍራፍሬ ስንጠቀም በትኩሱ ፍሬሽ እያለ ይሁን። እየበሰለ በሄደ ቁጥር ስኳርነቱ እየጨመረ ይሄዳል። በጣሳ ታሽጎ ወይም ደርቆ የታሸገ ከሚሆን ከጓሮ/ማሳ እንደወጣ በትኩሱ መብላት ይመረጣል።


ሳያበዙ በየእለቱ እየቀያየሩ የተለያዩ አይነት ፍራፍሬዎችን ይመገቡ። ‘በገዛ እጄ ስኳሬን አበላሸሁት’ እያሉ የጥፋተኝነት ስሜት ሳይሰማዎት በፍራፍሬዎች መደሰት ይችላሉ። አጠቃላይ የስኳር ቁጥጥር የሚወስነው አንድ የምግብ አይነት ብቻ ስላልሆነ ዋናው የተመጣጠነ አመጋገብ ሚዛን መጠበቅ ነው።


ሌላው ማስተዋል ያለብን እንደ ድግስ በአንዴ አግበስብሰን የፍራፍሬ መአት ከመብላት ይልቅ በልክ መጥኖ በመደበኛ ምግቦች እና መክሰስ ውስጥ በመጠኑ ከፋፍሎ ማካተት ይመረጣል። የተለያዩ የፍራፍሬ ዓይነቶችን በመጠኑ መጠቀም ጠቃሚ ነው። ዋናው ነገር አለማብዛት ነው።


የተለያዩ ፍራፍሬዎች የደም ስኳር መጠን ላይ ያላቸው ተጽእኖ የተለያዬ ስለሆነ የደም ስኳር ልኬትን በቅርበት መከታተል ይመከራል። ከምግብ በኋላ ያለን የደም ግሉኮስ መጠንዎን በመፈተሽ የትኛው ፍራፍሬ እና ምን ያህል መጠን ስኳሬን ከፍ ያደርገዋል የሚለውን መረዳት ይቻላል። ሁልጊዜም የደም ስኳር መጠንን መከታተል እና ከጤና ባለሙያ እና የስነ ምግብ  ባለሙያ ጋር በመመካከር ግለሰቡን ያማከለ የምግብ እቅድ ማዘጋጀት ይመከራል።


ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል ወይም የግል ሆስፒታሎች መመካከር ይችላሉ።


ተጨማሪ ምክር፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት በኢሜል፦ contact@melakutaye.com እና ስልክ፦ +251921720381 ማግኘት ይችላሉ። በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ ብሎግ www.melakutaye.com ፣ ቴሌግራምና ቲክቶክ ይከታተሉ። እነዚህን የተረጋገጡ መረጃዎች ለሌሎችም እንዲያጋሩ በትህትና እጋብዛለሁ።

1 thought on “ለስኳር ታካሚዎች የፍራፍሬ አመጋገብ መመሪያ”

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top