ክብደት መቀነስ በጣም ከባድ የሆነው ለምንድነው?

(ከዶ/ር ካትሪን ሳንደርስ TED Talk የተወሰደ)


ክብደት መቀነስ ዳገት እንደመውጣት ለምን ከባድ እንደሆነ ጠይቀው ያውቃሉ? አንዴ ለፍተው የቀነሱት ክብደት ምንም ያህል ቢሞክሩ ተመልሶ የሚመጣውስ ለምን ይሆን?


በያዝነው ሳምንት በታዋቂው ቴድ ቶክ ላይ በአሜሪካ የውፍረት ሃኪም የሆነችው ዶ/ር ካትሪን ሳንደርስ ክብደት ለመቀነስ ከሚደረግ ግብግብ በስተጀርባ ያለውን ሳይንስ ገልጣ አብራርታለች። ይህ ትምህርታዊ ንግግር ክብደትን በዘላቂነት ለመቀነስ ፈታኝ የሚያደርጉትን ፊዚዮሎጂያዊ እና ስነ ልቦናዊ ሁኔታዎችን ይዳስሳል።


ዶ/ር ሳንደርስ በቅርቡ ስለውፍረት ህክምና በወሰድኩት ስልጠና ላይ አስተማሪየ የነበረች የዘርፉ ዝነኛ ባለሙያ ነች።  ተናገረችውን ሃሳብ በተረዳሁት ልክ እንደሚከተለው እተርከዋለሁ።


ክብደት ሲቀንስ የሰውነታችን ተፈጥሯዊ ምላሽ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ሳንደርስ እንዳለችው በምግብ እጥረት ጊዜ በሃይል ቁጠባ የረሃብ ዘመንን እንድንሻገር ታስቦ በዝግመተ ለውጥ ሂደት ሰውነታችን ስብን ማከማቸት ይወዳል። ይህ ንድፈ ሃሳብ The Thrifty Gene hypothesis ተብሎ ይጠራል። ሰውነታችን ራሱን ከረሃብ ስጋት ለመከላከል ክብደት እንዳይቀንስ የሚጠብቅ ተደርጎ ከጥንተ ፍጥረቱ የተነደፈ ነው። በዚህም ሰውነታችን ክብደት የመጨመር ዝግመተ ለውጣዊ ዝንባሌ እንዲኖረው አድርጓል።


አድነውና ለቃቅመው በሚበሉት የቅድመ አያቶቻችን (ረሃብ በተደጋጋሚ በሚከሰትበት) ዘመን ይህ የቆጣቢነት ባህሪ ሕይወት አድን ነበር። በዚያ ጊዜ ካሎሪን በስብ መልክ ማከማቸት የሚታደን እና የሚጫር በጠፋ ቀን በረሃብ ከመሞት መትረፊያ መንገድ ነበር። ነገር ግን ምግብ በተትረፈረፈበት እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አነስተኛ በሆነበት በዛሬው ዓለም ይህ አብዝቶ ስብ ማከማቸትና ቆጣቢነት ባሕርይ ለውፍረት ወረርሽኙ አስተዋጽኦ አድርጓል።


ዘመናዊው አለም ውፍረት አምጪ (Obesogenic) ነው።

የአሁኑ የምንኖርበት አካባቢያችን ከፍተኛ የካሎሪ ይዘት ያለው ምግብ የበዛበት፣ የተመጣጠነ ምግብ የራቀው፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አነስተኛ የሆነበት ክብደት ጎታች ዘመን ነው። በአሁኑ ጊዜ መግዛት እስከቻልን ድረስ በየቦታው ምግብ በብዛት ስላለ እድኖ መብላት አይደለም በቅጡ አብስሎ መብላት ቀርቷል። ምግብ በቀጥታ ሶፋችን ላይ ሆነን ማዘዝ እንችላለን። ድንገት ምግብ ጠፍቶ ቢርበኝስ የሚል ስጋት ያለቀቀው ተፈጥሯችን የምግብ እጥረት በሌለበት ዘመንም ስብ ማከማቸት አላቆመም። እነኚህ ሁሉ ምክንያቶች ሰውነታችንን ከመጠን በላይ ወደ መወፈር አስከፊ ዑደት ይገፋፉታል።


ክብደት መቀነስ የማይቻል የሚመስለው ለምንድነው?

‘ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያለባቸው ሰዎች ክብደታቸውን ለመቀነስ ሲሞክሩ ሰውነታቸው አጥብቆ ይቃወማቸዋል’ ትላለች ዶ/ች ሳንደርስ። ክብደት ትንሽ ሲቀንስ ሰውነት ይደነግጣል፣ ረሃብ እንደመጣበት ያስባል። የረሃብ ሆርሞኖች ይጨምራሉ፣ የጥጋብ ስሜት የሚያመጡት ሆርሞኖች ግን ይቀንሳሉ። ይህም ምግብን በልክ ለማቆም ከባድ ያደርገዋል። የሜታቦሊዝም ፍጥነትም ይቀንሳል። ሰውነት የበላነውን ምግብ ሁሉ ሳያቃጥል እየተስገበገበ ማከማቸት ይጀምራል። እነዚህ ባዮሎጂካል ለውጦች ክብደትን በቀላሉ መቀነስ አዳጋች ያደርጉታል።


ክብደት መቀነስ የቻሉትም ቢሆን የቀነሱትን ክብደት አስጠብቆ ማቆየት ይከብዳቸዋል። በርካታ ጥናቶች እንዳረጋገጡት በምግብና ስፖርት ክብደት ከቀነሱ ሰዎች መካከል ግማሹ በሁለት አመት፣ 80 በመቶ የሆኑት በአምስት አመት ውስጥ ውፍረቱ በሂደት ይመለሳል።


ክብደት መቀነስ አለመቻል የአንተ/ቺ ጥፋት/ስንፍና አይደለም!

ዶ/ር ሳንደርስ ‘ውፍረት ውስብስብ በሽታ እንጅ የፍላጎት ማነስ አይደለም’ ስትል አጽንኦት ሰጥታለች። ውፍረት ከመጠን በላይ መብላት ወይም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ ብቻ አይደለም። እንደ ጄኔቲክስ፣ የተለያዩ መድሀኒቶች፣ የእንቅልፍ መዛባት እና የአእምሮ ህመሞች ያሉ አጋላጭ ሁኔታዎች ጉልህ ሚና ይጫወታሉ። ስለሆነም እንደሌሎቹ ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞች ሁሉ ግለሰቡን ያማከለ ህክምና እና ክትትል በማድረግ ሊታከም ይገባል።


እንደ ዶ/ር ሳንደርስ ገለጻ ውፍረት ያለባቸውን ግለሰቦች ስናክም ፈራጅና አግላይ የሆነ አቀራረብን ማስተካከል ይፈልጋል። ወቃሽና ነቀፋ የበዛበት አስተሳሰብ መቆም አለበት። ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን የህክምና እንክብካቤ እንዳይፈልጉ በመከልከል ነገሮችን ያባብሳሉ።


በተቃራኒው ውፍረትን እንደ አንድ የሆርሞን መዛባት በሽታ መረዳት የተሻሉ ህክምናዎችን በመፍጠር የተሻለ መፍትሄ ሊያመጣ ይችላል።


ለውፍረት ህክምና አዳዲስ ተስፋዎች

ለበርካታ ሰዎች እንደ አመጋገብ ማስተካከል እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያሉ የአኗኗር ዘይቤ ማሻሻያ ዘዴዎች ብቻውን በቂ አይደሉም።


የምግብና ስፖርት ለውጦች የክብደት ለውጥ ካላመጡ የጸረ ውፍረት ህክምና መጀመር ይገባል። የጸረ ውፍረት መድሃኒቶች ለብዙዎች ማርሽ ቀያሪ ሆነዋል። በርካታ ታካሚዎች ከፍተኛ ክብደት እንዲቀንሱ እና ክብደት ተመልሶ እንዳይጨምር ይረዳሉ።


ዶ/ር ሳንደርስ የጸረ ውፍረት መድሃኒቶች ውፍረትን በአንዴ የሚያጠፉ ‘አቋራጭ ፈውሶች’ ሳይሆኑ የረጅም ጊዜ ህክምናና ክትትል የሚፈልግ ጉዳይ እንደሆነ አፅንዖት ሰጥታለች።


ይህ የቴድቶክ ፕሮግራም መታየት ያለበት ነው።

የዶ/ር ሳንደርስ ንግግር ስለውፍረት ሳይንስ እና ክብደት ለመቀነስ ያለው ፈተና በሚጣፍጥ አቀራረብ ያብራራል። ውፍረት የግለሰቡ ደካማነት እና ወኔ ማጣት እንዳልሆነ የሚያስታውስ ነው። ውፍረትን ስናስብ በርካታ የሆርሞን እና ማህበራዊ ጉዳዮችን እንድንመረምር የሚያጠይቅ ጥሪ ጭምር ነው።


ከክብደት መቀነስ ጋር ተያይዘው ስላሉት ተግዳሮቶች አጠቃላይ ግንዛቤ ለማግኘት የዶ/ር ሳንደርስን ሙሉ ንግግር በቴድ ቶክ ኦፊሻላዊ ድረ-ገጽ ላይ መመልከት ይችላሉ።


ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል ወይም የግል ሆስፒታሎች መመካከር ይችላሉ።


ተጨማሪ ምክር፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት በኢሜል፦ contact@melakutaye.com እና ስልክ፦ +251921720381 ማግኘት ይችላሉ። በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ ብሎግ www.melakutaye.com ፣ ቴሌግራምና ቲክቶክ ይከታተሉ። እነዚህን የተረጋገጡ መረጃዎች ለሌሎችም እንዲያጋሩ በትህትና እጋብዛለሁ።

1 thought on “ክብደት መቀነስ በጣም ከባድ የሆነው ለምንድነው?”

  1. I see your effort and knowledge and also skill on Diabetes Mellitus during Diabetes Week ,conducted before one month at Addis ,Capital hotel. You are great scholar ever i see in my career. thank you Dr for your continous update

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top