አቮካዶ ለስኳር ህክምና ተስማሚ የሆነ ምግብ

ስለአቮካዶ የሚነሱ የተሳሳቱ ወሬዎች

በየእለቱ የስኳር ታካሚዎችን አመጋገብ ስገመግም ከምሰማቸው ልማዶች ውስጥ አንዱ ‘አቮካዶ ለኮሌስትሮል ጎጂ እንደሆነ ስለሰማሁ አቮካዶ መብላት ካቆምኩ ዘመናት አልፈዋል‘ የሚል በሳይንስ ያልተደገፈ መረጃ ይጠቀሳል። አቮካዶ በያዘው የቅባት ይዘት ምክንያት ‘ለልብ ጤና ጎጂ ነው’ የሚል ከእውነት የራቀ መረጃ በስፋት ይሰማል።


በአቮካዶ ውስጥ ያለው ቅባት ኮሌስትሮል ይጨምራል የሚባለው ወሬ ትክክለኛ አይደለም። ይህ የተሳሳተ ግንዛቤ ጊዜው ያለፈበት እንደሆነ ማስተዋል ይገባል። በሌሎች ምግቦች ውስጥ ያሉ ጤናማ ባልሆኑ የስብ/ቅባት አይነቶች እና በአቮካዶ ውስጥ የሚገኙትን ጤናማ ቅባቶችን መለየት በጣም አስፈላጊ ነው።



የአቮካዶ የጤና ጥቅሞች

አቮካዶ ሸካራ ቆዳ፣ ክሬም መሰል ለስላሳ ፍሬ እና አንድ ትልቅ ዘር ያለው የፍራፍሬ አይነት ነው። አቮካዶ ጥሩ የፋይበር ምንጭ እንዲሁም ከፍተኛ ቅባት ያለው ለጤና ተስማሚ ከሆኑ ምግቦች አንዱ ነው። አቮካዶ ዝቅተኛ የካርቦሃይድሬት ይዘት አለው። በበርካታ ለጤና ተስማሚ የሆኑ ተመራጭ የአመጋገብ ዘይቤዎች ውስጥ አቮካዶ አይጠፋም።


አቮካዶ በከፍተኛ ፋይበር የበለጸገ ነው። አንድ መካከለኛ መጠን ያለው አቮካዶ ወደ 10 ግራም ያህል ፋይበር ይይዛል፤ ይህም በየቀኑ ከሚመከረው የፋይበር መጠን ግማሽ ያህሉን የሚሸፍን ነው።


አቮካዶ ጤናማ በሆኑ ቅባቶች (monounsaturated fats) የበለፀገ ነው። አቮካዶ ውስጥ የሚገኙ ቅባቶች ጎጂ ኮሌስትሮል እንዲቀንስ ያግዛሉ። ጥሩ ኮሌስትሮል መጠንን ደግሞ እንዲጨምር ይረዳሉ።


በተጨማሪም በበርካታ ቫይታሚኖችና ንጥረ ምግቦች የበለጸገ ነው።


አቮካዶ ከኮሌስትሮል ነፃ ነው።


ስለሆነም አቮካዶ ለልብ ተስማሚ ከሆኑ ምግቦች አንዱ ነው።


አንድ መካከለኛ አቮካዶ 240 ካሎሪ፣ 3 ግራም ፕሮቲን፣ 22 ግራም ስብ (15 ግራም ሞኖአንሳቹሬትድ፣ 4 ግራም ፖሊአንሳቹሬትድ፣ 3 ግራም ሳቹሬትድ) እና 10 ግራም ፋይበር ያለው ሲሆን በጣም አነስተኛ ካርቦሃይድሬት እና ጨው (13 ግራም ካርቦሃይድሬት፣  11 ሚሊግራም ሶዲየም) ይይዛል።


አቮካዶ በጣም ምርጥ የምግብ አይነት ነው።

አቮካዶን በማእዳችን ውስጥ ማካተት ጤናን ያሻሽላል። አቮካዶ በተለይ የስኳር ህክምና ለሚከታተሉ ታካሚዎች ለስኳር ቁጥጥር፣ ለልብ ጤና እና ለአጠቃላይ ሜታቦሊዝም መሻሻል የሚረዳ ምርጥ ምግብ ነው። አቮካዶ ለስኳር ህመም በፍፁም አይከለከልም። አቮካዶን መመገብ የኮሌስትሮል መጠንን አይጨምርም።


አቮካዶ የያዘው ፋይበርና ጤናማ ቅባት ይዘት ምክንያት የጥጋብ ስሜት ይጨምራል፣ ይህም ግለሰቦች ረዘም ላለ ጊዜ የመጥገብ ስሜት እንዲሰማቸው ስለሚያደግ ክብደትን ለመቆጣጠር ይጠቅማል።


ለልብ ጤና እና ለስኳር ህመም ተስማሚ የሆነ ምግብ ሲሆን የልብና  የሜታቦሊክ ጤናን ለማሻሻል አስተዋፅኦ ያደርጋል። ለጤና መሻሻል በሚያደርገው ቁልፍ ሚና ምክንያት በበርካታ የህክምና መመሪያዎች የሚደገፉት እንደ ሜዲትራኒያን (Mediterranean diet) እና ዳሽ ምግቦች (DASH diets) ያሉ ዋና ዋና የአመጋገብ ዘይቤዎች አካል ነው።


አቮካዶን በአመጋገብዎ ውስጥ ማዘውተር ይገባል

አቮካዶ ሁለገብ ምግብ ሲሆን በተለያዩ ምግብ አዘገጃጀቶች ውስጥ ሊካተት ይችላል። አቮካዶ ከሰላጣ ጋር ሊበላ ይችላል። ለሰላጣ ማጣፈጫም/መቀመሚያም ይሆናል። አቮካዶ ለሳንድዊች መስሪያ የሚረዳ ጤናማ አማራጭ ሊሆን ይችላል። ከሌሎች ምግቦች ጋር ቢጣመር አቮካዶ ለማንኛውም የተመጣጠነ ምግብ ተጨማሪ በረከት ይሆናል። ብቻውንም ቢሆን በቀላሉ በማንኪያ ሊበላ ይችላል።


በከፍተኛ ፋይበርና ጤናማ ቅባት  የበለጸገ ሲሆን ዝቅተኛ የካርቦሃይድሬት ይዘት አለው። ስለሆነም የደም ስኳር ቁጥጥርን፣ የልብ ጤናን እና ክብደትን ለመቆጣጠር ወሳኝ የምግብ አማራጭ ነው።


በተሳሳተ መረጃ አቮካዶን ተከልክለው ከነበረ እንደገና በማጤን አቮካዶን መመገብ ለመጀመር ጊዜው አሁን ነው። ዛሬው የምግቦች ሁሉ አንጸባራቂ ኮኮብ ባለብዙ ንጥረ ነገር የሆነውን አቮካዶ መመገብ ይጀምሩ። 


ያስታውሱ – አቮካዶ በፍጹም ኮሌስትሮል የለውም!


ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል ወይም የግል ሆስፒታሎች መመካከር ይችላሉ።


ተጨማሪ ምክር፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት በኢሜል፦ contact@melakutaye.com እና ስልክ፦ +251921720381 ማግኘት ይችላሉ።


በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ ብሎግ ፣ ቴሌግራምና ቲክቶክ ይከታተሉ። እነዚህን የተረጋገጡ መረጃዎች ለሌሎችም እንዲያጋሩ በትህትና እጋብዛለሁ።

3 thoughts on “አቮካዶ ለስኳር ህክምና ተስማሚ የሆነ ምግብ”

  1. Hello doctor is it my misunderstanding from lipidiology lecture given at Elily Hotel.I was attending that lecture and was against the above content and idea.Thank you.

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top