ውፍረት እንደ አንድ ህመም ይታወቅ (diagnose obesity as a disease)

በአለም አቀፍ ደረጃ እየተስፋፉ የሚገኙትን የስኳር ህመምና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በፍጥነት መጨመር ዋነኛ ተቀዳሚ ምክንያት ከመጠን ያለፈ ውፍረት ነው። እንደወረርሽኝ ስርጭታቸው እየጨመረ የመጡት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሁሉ ከጀርባ ያለው ግንባር ቀደም ድብቅ ምክንያት ውፍረት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ውፍረት የበሽታዎች ሁሉ እናት ነው ብለው የሚጠሩትም አሉ።


ውፍረት ዓለም አቀፍ የጤና ቀውስ ነው። በአጠቃላይ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሰዎችን ይጎዳል። በሰሜን አሜሪካ ሃገራት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ውፍረት ከሲሶ በላይ የሚሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ያጠቃል። የበለጠ የሚያሳስበው ደግሞ በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ውስጥ ከእጥፍ በላይ አንደሚጨምር ይገመታል። ውፍረትን የሃብታም ሃገሮች ብቻ ችግር እንደሆነ ተደርጎ ይታሰባል። ነገር ግን የታዳጊ ሃገሮችንም በር እያንኳኳ ነው።


የውፍረት ህመም ስርጭት የተቀናጀ አለም አቀፋዊና ሁለንተናዊ ምላሽ መስጠት የሚፈልግበት አስጊ ደረጃ ላይ የደረሰ ቢሆንም  አሁንም ለጉዳዩ ቅድሚያ መስጠት አልቻልንም። አንዱ የቸልተኝነት ምንጭ ስለ ውፍረት ያለን የተሳሳተ አረዳድ ነው። ውፍረትን እንደ አንድ ራሱን የቻለ በሽታ አድርጎ ያለመቁጠር ግዴለሽነት የህክምና ባለሙያዎች ውጤታማ እርምጃ መውሰድ አንዳይችሉ እንቅፋት ይሆናል።


ብዙዎቹ ውፍረትን እንደ አንድ ህመም ቆጥሮ ስም ሰጥቶ (diagnosing obesity) ከማከም ይልቅ የውፍረት ምልክት የሆኑትን ስኳር ህመምና ሌሎችንም በሽታዎች ብቻ ማከም ያተኩራሉ። ውፍረት በራሱ በሽታ ሳይሆን ወደ ሌሎች በሽታዎች የሚመራ አጋላጭ ሁኔታ (risk factor) ብቻ አድረገው አቅለው ያዩታል።


ውፍረት ራሱን ችሎ ክሊኒካል እውቅና ህክምና የሚያስፈልገው የሰውነት ስብ ከመጠን በላይ መብዛት ጋር የተያያዘ ስር የሰደደና የሚያገረሽ ውስብስብ በሽታ (Adiposity Based Chronic Disease) ነው።


ውፍረት ራሱን የቻለ ህመም ተደርጎ መታየት ያለበት ለምንድን ነው?

  1. የውፍረት በሽታ መነሻ ውስብስብነት፤

ውፍረት በበርካታ ምክንያቶች መስተጋብር የሚመጣ የረጅም ጊዜ ሂደት ውጤት ነው። ውፍረት በሰውነታችን ሃይል አጠቃቀም እና የስብ ህዋሳት አሰራር መዛባት እንዲሁም የነርቭና ሆርሞኖች ስራ መስተጓጎል ያካትታል። በአኗኗር ዘይቤ አለመስተካከል ብቻ የሚመጣ የስንፍና በሽታ አይደለም። ክብደትን መቆጣጠር የምናስገባው እና የምናስወጣው ካሎሪ ምጥጥን ጉዳይ ብቻ አይደለም።


2. የውፍረት የጤና መዘዞች፡  

ውፍረት “የሁሉም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እናት” ነው። ለስኳር ህመም፣ ለልብ ህመም እና ካንሰርን ጨምሮ ከ200 በላይ በሽታዎች የመጋለጥ እድልን ይጨምራል። ለአእምሮ ጤና መታወክ ተቀዳሚ መንስኤ ነው። ከግለሰብ ጤና ባሻገር የወፍረት ወረርሽኙ አጠቃላይ የጤና ስርአቶችን እና ኢኮኖሚን በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳል።


3. ቀጣይነት ያለቸው ህክምናዎች አስፈላጊነት፡

ውፍረትን እንደ አንድ በሽታ መገንዘብ ውጤታማ የሕክምና ዘዴዎችን ለማቀድና ለመተግበር ያስችላል። የጤና ባለሙያዎች ውፍረትን እንደ አንድ ህመም ቆጥሮ መጻፍ፣ መነሻውን መፈለግ፣ ቀጣይነት ያለው ህክምና አማራጭ መስጠት፣ ምርምር ማድረግ ይገባቸዋል።


እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሃገሮች ረሃብና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ገና ባልተቀረፈበት ውፍረት አሳሳቢ የማህበረሰብ ጤና ፈተና ደቅኗል። ይህ የጤና ችግር ሳይቃጠል በቅጠል ሃይ ካልተባለ ከባድ የጤና፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ መዘዞችን ያስከትላል።


ውፍረት ለሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞች ተቀዳሚ አጋላጭ ምክንያት እንደመሆኑ ውፍረትን እንደ አንድ ህመም/በሽታ በመቁጠር ለችግሩ እውቅና መስጠት የመጀመሪያው እርምጃ ነው።


በዘመቻ መልክ ከሚደረግ የጎዳና ላይ እርምጃ በተጨማሪ የጤና አገልግሎት ተቋማት ውፍረትን በብቃት እንዲመረምሩና እንዲያክሙ ማድረግ ለነገ የማይባል የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆን አለበት።


ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል ወይም የግል ሆስፒታሎች መመካከር ይችላሉ።


ተጨማሪ ምክር፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት በኢሜል፦ contact@melakutaye.com እና ስልክ፦ +251921720381 ማግኘት ይችላሉ።


በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ ብሎግ ፣ ቴሌግራምና ቲክቶክ ይከታተሉ። እነዚህን የተረጋገጡ መረጃዎች ለሌሎችም እንዲያጋሩ በትህትና እጋብዛለሁ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top