ብዙ ሰው የአንድ ሰአት ጂም ሰርቶ ቀሪውን ሃያ ሶስት ሰአት ስለሚዘናጋ ጤናውን እንደሚፈለገው ማሻሻል አዳጋች ያደርገዋል። ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ በመስራት ከምናሳልፈው አጭር ጊዜ ባሻገር በሙሉ ቀን ውሎአችን የምናደርገው እንቅስቃሴ፣ እረፍትና እንቅልፍ ሁሉ ጤናን ይነካል። በታቀዱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ወቅት ብቻ ሳይሆን በቀሪው ቀናችን የምንሰራው ስራ አጠቃላይ ጤና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር መገንዘብ ይገባል።
የአሜሪካ የስኳር ማህበር (ADA) በአዲሱ የስኳር ህክምና መመሪያው ላይ ለአይነት 2 የስኳር ህመም ህክምና የ24 ሰአት ክንዋኔያችን ሁሉ ለጤና አስፈላጊ እንደሆነ በማጉላት አጽንኦት ሰጥቷል። በሙሉ ቀን ውስጥ የምናደርገው ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴያችንን ስለማስተካከል ቅድሚያ መስጠት ለጤና ወሳኝ እንደሆነ አስፍሯል።
የተመጣጠነ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ማውተር ለጤና ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያስገኙ መረዳት ያስፈልጋል።
የ24-ሰአት የጤናማነት ወሳኝ ባህሪያት ምንድን ናቸው?
‘የ24 ሰአት የጤናማነት ወሳኝ ባህሪያት ባህሪያት (24-hour physical/health behaviors)’ የሚከተሉትን ያጠቃልላል፡
- የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፡ ማንኛውንም የታቀደ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ያካትታል።
- እረፍት ማድረግ፡ ይህ ደግሞ መቀመጥ፣ ቲቪ መመልከት ወይም ሌሎችን የእረፍት ጊዜያት ያጠቃልላል። ይህ ጊዜ በተቻለው መጠን መገደብ በተለይም ከአንድ ሰአት በላይ አብዝቶ አለመቀመጥ ያስፈልጋል።
- እንቅልፍ መተኛት: ጥራት ያለው በቂ እንቅልፍ ለአካላዊ እና አእምሮአዊ ጤና አስፈላጊ ሲሆን ሰውነታችን ከቀን ድካም እንዲያገግም የሚያስችል ሂደት ነው።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ
ማንኛውንም የታቀደ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያካትት ሲሆን ለአጠቃላይ ጤና መሰረት ነው። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሲባል በእግር መጓዝ፣ መሮጥ ወይም ሌላ ስፖርት መስራት፤ የጓሮ አትክልት መኮትኮት እና ሌሎችም የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችን ያካትታል።
በሁሉም የጤና መመሪያዎች ውስጥ የማይቀር ምክር ነው። ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ሁሉ በሩቅ የሚመክት ምርጥ መድሃኒት ነው። ማንኛውም ሰው ለጤናው ሊያደርገው የሚችለው ትልቅ ኢንቨስትመንት ነው።
ተዘርዝሮ የማያልቅ የጤና ጥቅሞች ያሉት ሲሆን ጥቂቶቹን እነኚሁና፡
- የውፍረትና ስኳር ህመም ለመከላከል፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተር የሰውነታችንን የኢንሱሊን አሰራር እንዲሳለጥ ስለሚያደርግ የደም ስኳር መጠንን ያስተካክላል። ለውፍረት፣ ስኳር ህመምና ተያያዥ በሽታዎች የመያዝ እድልን በእጅጉ ይቀንሳል።
- የልብ ጤና ለመጠበቅ፤ አዘውትሮ እንቅስቃሴ የደም ግፊትን ያስተካክላል፣ የኮሌስትሮል መጠን ያሻሽላል፣ የልብ በሽታ ተጋላጭነትን ይቀንሳል።
- የአእምሮ ጤና ለማሻሻል፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጭንቀትን፣ እና ድብርትን ይቀንሳል።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ለማዘውተር ተግባራዊ ምክሮች:
- በሳምንት ቢያንስ ለ150 ደቂቃ ያክል ከመጠነኛ እስከ ከባድ የኤሮቢክ እንቅስቃሴን መስራት ለአብነትም ፈጣን እርምጃ፣ ብስክሌት መንዳት፣ መሮጥ፣ መዋኘት ወዘተ።
- በሳምንት ሶስቴ የጥንካሬ ስፖርት መስራት።
- በየቀኑ ቢያንስ አስር ሺህ እርምጃ (steps) ማድረግ ከፍተኛ የጤና መሻሻል ያመጣል።
- የትኛውም አይነት ስፖርት ይሁን እስከሚያልብ ቢሰራ የተሻለ የጤና ጥቅም ያስገኛል።
- በትንሹ ይጀምሩ። ከዚያም ጥንካሬዎ ሲሻሻል ቀስ በቀስ ስፖርቱን ይጨምሩ።
የእረፍት ጊዜን በመጠን ማድረግ
ብዙዎቻችን ስፖርት የምንሰራበትን ትንሽ ጊዜ አጋነን ማሰብ እና ካለእንቅስቃሴ በእረፍት ተቀምጠን የምናሳልፈውን ረዥም ጊዜ አለማስተዋል ይታይብናል።
የትኛውም አይነት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለጤና ወሳኝ ነው። ነገር ግን ረዘም ላለ ጊዜ ካለእንቅስቃሴ መቀመጥ የሚያስከትለውን የጤና ጉዳት በግማሽ ሰአት ስፖርት ማካካስ አይቻልም። ለአንድ ሰአት ስፖርት ሰርተን ቀሪዎን 23 ሰአት በመቀመጥ ካሳልፍነው የምንፈልገውን ጤና ማምጣት አያስችልም። ለዚህም ነው በርካታ የጤና መመሪያዎች አብዝቶ መቀመጥን ማስወገድ የሚመክሩት። በየሰአቱ ንቁ አኗኗር (the “active every hour” approach) መምራት ይመከራል።
ረዘም ላለ ጊዜ መቀመጥ (prolonged sitting) ካለእንቅስቃሴ በተቀመጥንበት ወይም ጋደም ባልንበት ለአንድ ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ መቆየት ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። ይህ አብዝቶ መቀመጥ ወደባህሪ እድጎ ልማድ ሲሆንብን ውዝፍነት (sedentary behavior) ይባላል።
ለረዥም ሰዓት መቀመጥ የሚያስከትለው የጤና መዘዝ ተዘርዝሮ አያልቅም። ከመጠን በላይ ውዝፍነት ለውፍረት፣ ቦርጭ፣ ስኳር ህመም፣ ልብ ሕመም፣ ካንሰር እንዲሁም ሌሎች እልቆ መሳፍርት የሌላቸው ስር የሰደዱ የበሽታ አይነቶች አጋልጦ የሚሰጥ ክፉ ልማድ ነው። ካለእድሜ ያሰረጃል ያጃጃል። በተጨማሪም አብዝቶና አዘውትሮ መቀመጥ ካለአድሜ የመሞትን እድል በእጅጉ እንደሚጨምር በዋና ዋና የህክምና መጽሄቶች ላይ የሚወጡ አያሌ ጥናቶች ያረጋገጡት ሁኗል። አብዝቶ መቀመጥ በሽታ ጎታች ነው።
አብዝቶ መቀመጥን ሰብሮ አካላዊ እንቅስቃሴን ልማድ ለማድረግ ዋናው ነገር በትንሽ መጀመር ነው። ለምሳሌ በየሰዓቱ ለትንሽ ደቂቃ ያህል ለመንቀሳቀስ (ከወንበር ተነስቶ ለመቆም፣ ቢሮ ውስጥ ለመራመድ፣ አንድ ሁለት ደረጃ ወጣ ወረድ ብሎ ወደስራ ለመመለስ…) በመወሰን ይጀምሩ። ይህን ማድረግ አውቶማቲክ ልማድ ሲሆን ቀስ በቀስ የእነዚህን የእንቅስቃሴ ሰዓታት እያረዘሙና የስፖርቱን ክብደት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመሩ መሄድ።
በዕለት ተዕለት ስራችን ውስጥ ማዘውተር የሚገቡን የተወሰኑ ምሳሌዎች ለመጥቀስ ያህል፤
- ከሊፍት ይልቅ በደረጃ እንውጣ እንውረድ፣
- ስልክ ስንይዝ ቁጭ ከምንል እየተራመድን እናውራ፣
- ለሻይ ቡና ስንወጣ መኪና አስነስተን ጭስ ከምንምግ በእግራችን እንሂድ፣ መኪናችንን ራቅ ያለ ቦታ አቁመን ትንሽ ብሎኮች እንራመድ።
- ወደቤታችን ስንመለስ ከባስ ወይም ታክሲ ቢያንስ አንድ ፌርማታ ቀደም ብለን ወርደን ግማሽ ሰዓት በእግር እንጓዝ፣
- ቢሯችን ውስጥ ዱብ ዱብ ማለት፣ ፑሽ አፕ መውረድ ይቻላል።
- በተቀመጣችሁበት ወይም ተነስታችሁ ሰውነታችሁን ማፍታታት፣ እጅ እግርን በማጠፍ በመዘርጋት እንቅስቃሴ ማድረግም ይቻላል።
- እንቅስቃሴን ‘ስናክ’ ማድረግ (exercise snacks)
- በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እንቀሳቀስ!
እነዚህ ትናንሽ ለውጦች ከጊዜ በኋላ ከፍተኛ የጤና ጥቅሞችን ያመጣሉ። እንቅስቃሴን በህይወትዎ ውስጥ ቅድሚያ በመስጠት አጠቃላይ ጤናዎን በእጅጉ ማሻሻል ይቻላል። አብዝቶ በመቀመጥ የሚመጣ ለከባድ በሽታዎች ተጋላጭነትን መቀነስ ይችላሉ።
የእንቅልፍ ሚና
እንቅልፍ ብዙ ጊዜ የሚረሳ የጤና ዋልታ ነው።
የእንቅልፍ ማነስ (በቂ ያልሆነ ወይም የማያረካ) የሆርሞን መዛባት ያመጣል፤ የመላ ሜታቦሊዝምን ስርአት ሊያስተጓጉል ይችላል። እንቅልፍ ማጣት ከጥጋብ በላይ መብላት ስለሚገፋፋ ውፍረት ያመጣል። በቂ እንቅልፍ አለማግኘት የስኳር ህክምና ቁጥጥርን ያበላሻል።
ለጤናማ እንቅልፍ የሚከተሉትን ይተግብሩ፤
- በቂ የእንቅልፍ ሰአት (quantity): በየቀኑ ከ6-8 ሰአታት ጥራት ያለው የማታ እንቅልፍ ይኑርዎት።
- የእንቅልፍ ጥራት (quality): የሚያረካ እንቅልፍ እንዲኖረዎት በየቀኑ የማይቆራረጥ ተመሳሳይ የእንቅልፍ ሰአት ማበጀት። ለእንቅልፍ አመቺ መኝታ መፍጠር ለአብነትም እንቅልፍ የሚረብሽ ድምጽ፣ ብርሃን እና ትኩረትን የሚከፋፍሉ ነገሮችን በማስወገድ ለእንቅልፍ ምቹ የሆነ መኝታ ቤት ይኑዎት። ከመኝታ በፊት ከባድ ምግብ እና አነቃቂ ነገሮችን (ለምሳሌ ቡና) ያስወግዱ።
- የመተኛ ሰአት (Sleep Chronotype)፡ የመተኛ እና መነሻ ጊዜ ጤና ላይ ተጽእኖ አለው። ተፈጥሯዊው የሰውነት የመተኛ ሰዓት በጊዜ ተኝቶ (ማታ ከ3 እስከ 4 ሰአት) በጠዋት መነሳት (ጠዋት ከ11 እስከ 12 ሰአት) ነው። ከዚህ በተቃራኒው የሆነ የእንቅልፍ ልማድ ያላቸው ሰዎች ወይም የማታ ሺፍት ስራ የሚሰሩ ጤናቸው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል።
ማጠቃለያ
የሙሉ ቀን ጤናማ ልማድ በማጎልበት የእንቅስቃሴ፣ የእረፍት እና የእንቅልፍ ጊዜን ማመጣጠን ተገቢ ነው። እነዚህን ልምምዶች ከዕለት ተዕለት ኑሮ ጋር በማቀናጀት የተሻለ የጤና ቱሩፋቶችን ሊያገኙ ይችላሉ።
ጤናዎን እና አጠቃላይ ደስተኛ ህይወት የሚያመጣ ዘላቂ የሆነ አኗኗርን ቀስ በቀስ ይገንቡ።
ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል ወይም የግል ሆስፒታሎች መመካከር ይችላሉ።
ተጨማሪ ምክር፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት በኢሜል፦ contact@melakutaye.com እና ስልክ፦ +251921720381 ማግኘት ይችላሉ።
በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ Blog, Telegram, YouTube & TikTok ይከታተሉ። እነዚህን የተረጋገጡ መረጃዎች ለሌሎችም እንዲያጋሩ በትህትና እጋብዛለሁ።
Insightful article. Thank you for sharing actionable tips!