የአሜሪካ የስኳር ማህበር (ADA) የስኳር ህመም ያለባቸው ግለሰቦች አወንታዊ የጤና ልምዶችን ማሳደግ ጤናን ለማሻሻል እንደ አንድ የህክምና ትኩረት አድርጎ አጽንዖት ይሰጣል። በየአመቱ የሚሻሻለው የስኳር ህክምና መመሪያ በምእራፍ አምስት የሚተነትነው ስለዚሁ ጉዳይ ነው። ይህም ግለሰቡን ያማከለ ሁለንተናዊ የባህሪ ለውጥ ማምጣት እንደሚያስፈልግ ያብራራል። ጤናማ ልማዶችን መገንባት እና የተሟላ ደህንነትን ያማከለ እንክብካቤ መስጠት የስኳር ህክምና ግቦችን ለማሳካት እንዲሁም የህይወት ጥራት ለማሻሻል ወሳኝ ነው።
ሙሉ ስብእና እና ሁለንተናዊ ደህንነት በስኳር ህክምና እውን ለማድረግ አስፈላጊ የሆኑ ስድስት መሰረታዊ መርሆዎችን መተግበር ይፈልጋል። እነዚህም
- የስኳር ህመምን በራስ የማስተዳደር ትምህርት እና ድጋፍ (Diabetes self-management education and support, DSMES)/ የስኳር ትምህርት (diabetes education)
- ሳይንሳዊ የስነ ምግብ ህክምና (Medical nutrition therapy)
- መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ (Regular physical activity)
- የትምባሆ ማጨስ ማቆም (Smoking cessation)
- ጤናማ ልማዶችን መገንባት (Supporting positive health behavior)
- የስነ-ልቦና ድጋፍ (Psychosocial care)
ስኳርን በራስ የማስተዳደር ትምህርት እና ድጋፍ
ራስን ለመንከባከብ አስፈላጊ የሆኑትን እውቀት፣ ክህሎቶች እና ጥበብ የማበልጸግ ቀጣይነት ያለው ተከታታይ ትምህርት ነው። ስኳርን ለመቆጣጠር የሚረዱ ስልቶችን በማስተማር ጤናማ ህይወት እንዲኖር የሚያስችን የስኳር ህክምና እንክብካቤ የማዕዘን ድንጋይ ነው።
አጠቃላይ ዓላማው የስኳር ህክምና ግቦችን እና አጠቃላይ ሙሉ ጤንነትን ለማሻሻል ታካሚዎች በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ ብቁ የጤና ውሳኔ እንዲወስኑ መደገፍ ነው። የስኳር ህክምናን ለማሻሻል አስፈላጊ የሆኑትን እውቀት፣ ክህሎት፣ በራስ መተማመን እና ውሳኔ አሰጣጥ ብቃት ለማስረጽ ይረዳል።
ይህ ትምህርት የግለሰቡን ልዩ ፍላጎት፣ እሴት፣ ምርጫ፣ ባህልና ማህበራዊ ከባቢ ያማከለ እና በመረጃ የተደገፈ ራስን የማስተዳደር ስልቶች ማስቻል ላይ ያተኩራል። አግላይና ፈራጅ ያልሆነ፤ መግባባትን እና ትብብርን የሚያጎለብት ጥሩ የባለሙያና ታካሚ ግንኙነት መፍጠር ይመከራል። ለሁሉም የስኳር ታካሚ ባህል እና የእውቀት ደረጃ ተስማሚ የሆነ እና የእያንዳንዱን ግለሰብ ፍላጎት ያማከለ ሆኖ መዘጋጀት አለበት። ተደራሽነቱም መስፋት አለበት።
በየእለት ህይዎትና ተለዋዋጭ ህክምና ውስጥ የሚያጋጥሙ አዳዲስ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ቀጣይነት ያለው መሆንም ይኖርበታል።
ሳይንሳዊ የስነ ምግብ ህክምና
የስነ ምግብ ምክርና ህክምና ማግኘት ለስኳር ቁጥጥር መሻሻል እና ለአጠቃላይ ጤና በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ የስኳር ህክምና አካል ለብዙ አሳሳች መረጃዎችና አሳች ባለሙያዎች የተጋለጠ ስለሆነ የታወቀ የሙያ ፈቃድ ባላቸው ሃኪሞች (doctors)፣ አስተማሪዎች (diabetes educators) ወይም የምግብ ባለሙያዎች (dieticians) በትብብር እንዲሆን ይመከራል።
ቁልፍ ምክሮች የሚከተሉትን ያካትታሉ፡
- የአመጋገብ እቅድ ማዘጋጀት (Individualized Meal Planning)፡- ከግለሰብ ባህል፣ ፍላጎት፣ ምርጫ እና የህይወት ግቦች ጋር የሚመጣጠን የምግብ ምርጫዎችን ማበጀት
- በሳይንስ የተደገፉ የአመጋገብ ምርጫዎች (Evidence-Based Dietary Patterns): እንደየሃገሩ ባህል የተለያዩ ጤናማ የአመጋገብ አይነቶች ያሉ ሲሆን በተለይም በዕፅዋት ምግቦች ላይ ያተኮሩ ሜዲትራኒያን አመጋገብ ያሉት አለማቀፋዊ ተቀባይነት አላቸው።
- የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን በዘላቂነት መፍታት፤ ‘ይህን አትንካ፣ ያኛው አይበላም’ በሚል ክልከላ የበዛው የአመጋገብ ምክርን አርሞ በተቃራኒው ጤናማ ምግቦችን ለሁሉም ማዳረስን ማረጋገጥ ላይ ማተኮር ተገቢ ነው።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የስኳር ህክምና አንዱ ምሰሶ ሲሆን በርካታ የጤና ጥቅሞችን ይሰጣል ።
የኤሮቢክ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በሳምንት ቢያንስ ለ150 ደቂቃ ከመካከለኛ እስከ ጠንካራ እንቅስቃሴ እስኪያልብ መስራት ይመከራል። በተጨማሪም የጥንካሬ ስፖርት በሳምንት ሶስቴ ማዘውተር ይገባል።
የእንቅስቃሴ አይነትና መጠን ሁሌም የታካሚዉን እድሜ፣ የጤና ሁናቴ፣ ምርጫ ወዘተ ግምት ውስጥ ያስገባ እና ተመጣጣኝ መሆን አለበት።
ትምባሆ ማጨስ ማቆም
ሲጋራ ማጨስ ማቆም የስኳር ህመም የሚያመጣቸውን የጤና ችግሮች ለመቀነስ እና አጠቃላይ ጤናን ለማሻሻል ወሳኝ ነው። በእያንዳንዱ የህክምና ክትትል ወቅት የሚያጨሱትን ግለሰቦች መለየትና እንደአስፈላጊነቱ የምክር አገልግሎትና የመድሃኒት ህክምና መስጠት ይገባል። ሲጋራ ማጨስን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የትምባሆ ዓይነቶችን ማስወገድ አጽንዖት ተሰጥቶታል።
አወንታዊ የጤና ባህሪያትን ማበልጸግ
ለጤና ተስማሚ የሆነ ዘላቂ የባህሪ ለውጥ ማምጣት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ መስጠትና እና ውጤታማ ስልቶችን መንደፍ ይፈልጋል። ጤናን ለማሻሻል መፈለግ፣ ለለውጥ ተነሳሽነት እና ለተግባራዊነት ያለው ቁርጠኝነት ከሰው ሰው ስለሚለያይ ግለሰቡን ያማከለ ትምህርትና ድጋፍ ማቅረብ ይገባል። ለመጀመር የማይከብድ እና ቀጣይነት ሊኖረው ከሚችል ግብ መጀመር ይመከራል።
ባለሙያዎች ታካሚዎችን በማብቃት እና ድጋፍ ሰጪ አስቻይ ሁኔታን በመፍጠር ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።
የስነ-ልቦና እና ማህበራዊ ድጋፍ መስጠት
የስኳር ህክምና ዘርፈ ብዙ የአኗኗር ለውጥ ማድረግ (ጤናማ አመጋገብ፣ መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ)፣ የደም ስኳር በየቀኑ መለካት እና መድሃኒቶችን ከመውሰድ ባሻገር የስራና የቤተሰብ ኃላፊነቶችን ማመጣጠን ይፈልጋል። ይህ ቀላል አይደለም። በዚህ ምክንያት የስኳር ህክምና በርካታ የስነ ልቦና ጫናዎች ያመጣል።
ይህን ጫና ለማቃላል ያለመ የስነ ልቦና እና ማህበራዊ ድጋፍ ማድረግ ትኩረት የሚሻ የስኳር ህክምና ዘርፍ ነው። የስኳር ታካሚዎችን በእያንዳንዱ ክትትል ወቅት የአእምሮ ጤናቸውን ሁኔታ መገምገም ይገባል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የአእምሮ ጤና ባለሙያዎች ጋር እንዲቀርቡ በማድረግ ሁሉን አቀፍ እንክብካቤን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው።
ማጠቃለያ
አወንታዊ የባህሪ ለውጥ ማምጣት ለስኳር ህክምና እና አጠቃላይ ጤንነት ያለው ጠቀሜታ የጎላ ነው። ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት የአሜሪካ ስኳር ማህበር አዲሱ መመሪያ ልዩ ትኩረት ሰጥቶታል።
በዚህ ጽሁፍ የተጠቀሱትን ስድስቱ መሰረታዊ መርሆዎችን በዝርዝር በቀጣይ ክፍል የምናያቸው ይሆናል።
ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል ወይም የግል ሆስፒታሎች መመካከር ይችላሉ።
በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ Blog, Telegram, YouTube & TikTok ይከታተሉ። እነዚህን የተረጋገጡ መረጃዎች ለሌሎችም እንዲያጋሩ በትህትና እጋብዛለሁ።