በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የስኳር ህመም ለመጀመሪያ ጊዜ በእርግዝና ወቅት በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ከሚገባው በላይ ከፍ ብሎ ሲገኝ የሚከሰት የጤና ችግር ሲሆን ነፍሰ ጡር እናቶችን ከሚያጠቁ የጤና ችግሮች በቀዳሚነት ይጠቀሳል። በአብዛኛው ከ5-7 ወር ባለው የእርግዝና ጊዜ የሚከሰትና ከወሊድ በኋላ የሚጠፋ የስኳር ህመም አይነት ነው።
የእናት ጤንነት እና የጽንሱን ደህንነት ለማረጋገጥ ጥንቃቄ የተሞላበት የስኳር ህክምና እና እንክብካቤን ይፈልጋል። ስኳርን በጥብቅና በጊዜ መቆጣጠር አስፈላጊ ነው። የእናትዋን አጠቃላይ ጤና ያማከለ እንክብካቤ የስኳር መጠንን ከመቆጣጠር ባሻገር ሙሉ ጤናማ እርግዝና እንዲኖር ያስችላል።
ይህን ለማድረግ ስለህክምናው ግቦች ጠንቅቆ ማወቅና መረዳት ይፈልጋል። ውጤታማ ህክምና የስኳር ቁጥጥር እቅድ ማውጣት እና ግልጽ የሕክምና ግቦችን በማዘጋጀት ይጀምራል።
የእርግዝና ጊዜ ስኳር ሕክምና ግቦች ምንድን ናቸው?
የደም ስኳር መጠንን ጤናማ በሆነ ክልል ውስጥ መቆጠጠርን ያካትታል። በአለም አቀፋዊ የሕክምና መመሪያዎች የሚደገፉት የስኳር ግቦች እንዲህ ናቸው፡-
- የባዶ ሆድ የስኳር መጠን፡ ከ70 እስከ 95 mg/dL
- ከምግብ ከአንድ ሰዓት በኋላ የስኳር መጠን፡ ከ140 mg/dL በታች
- ከምግብ ከሁለት ሰአት በኋላ የስኳር መጠን፡ ከ120 mg/dL በታች
እነዚህን ግቦች ማሳካት ለእናትም ሆነ ጽንስ ጤና ወሳኝ ነው። የጽንስ መፋፋትና ክብደት ከፍ ማለት (macrosomia)፣ ከምጥ ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ ህጻኑ እንደተወለደ መተንፈስ መቸገር፣ ወዘተ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመቀነስ ስኳርን እስከመጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ማስተካከል ይገባል።
እነዚህ ግቦች ለእያንዳንዷ እናት በሚመች መልኩ በትንሹ ሊለያዩ ይችላሉ። የእያንዳንዷን እናት ጤና፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ የአመጋገብ ምርጫዎች እና ለመድሃኒት ያላትን ምላሽ ከግምት ያስገባ መሆን ይገባዋል። ይህን ከጤና ባለሙያው ጋር በመመካከር ማስተካከል ይችላሉ።
የስኳር መደበኛ ክትትል ማድረግ
የህክምናን ግብ ለማሳካት በየቀኑ የደም ስኳር ክትትል ማድረግ አስፈላጊ ነው። በባዶ ሆድ እና ከእያንዳንዱ ምግብ በኋላ ያለውን የስኳር መጠን በየቀኑ (ወይም በሃኪም እንደታዘዘው) መለካት ይገባል። የለካነውን የስኳር መጠን ካወጣነው ግብ ጋር በማነጻጸር የመድሃኒት፣ አመጋገብና ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ማስተካከል ይመከራል። የለካነውን የስኳር መጠን በማስታወሻ መዝገብ ላይ በመመዝገብ በክትትል ወቅት ከጤና ባለሙያዎ ጋር በማጋራት መመካከር ይገባል።
የስኳር መድሃኒቶችን መውሰድ፣ መርፌ መወጋት፣ ስኳር ደጋግሞ መለካት፣ የሚበላ እና የማይበላ ምግብ መምረጥ ወዘተ ቀላል ስራ አይደለም። ስለሆነም ሁሉም የቤተሰብ አባል እና ጓደኞች ሁሉ የጋራ ጥረት በማድረግ መደገፍ ይገባል። ይህ አይነት እገዛና ድጋፍ ማግኘት የደም ስኳር ቁጥጥርን በማምሻሻል ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
በትክክለኛ ህክምና ስኳር ያለባቸው ነፍሰ ጡር እናቶች ጤናማ እርግዝና እንዲኖራቸው እና በሰላም እንዲወልዱ ማስቻል ይቻላል። እያንዳንዷን እናት ያማከለ ግልጽ የሕክምና ግቦችን በማበጀት ስኳርን መቆጣጠር እና አወንታዊ የእርግዝና ወራት መፍጠር ይችላሉ።
ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል ወይም የግል ሆስፒታሎች መመካከር ይችላሉ።
ተጨማሪ ምክር፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት በኢሜል፦ contact@melakutaye.com ማግኘት ይችላሉ።
በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ Telegram, YouTube & Tiktok ይከታተሉ። እነዚህን የተረጋገጡ መረጃዎች ለሌሎችም እንዲያጋሩ በትህትና እጋብዛለሁ።