አብዝቶ መቀመጥ – ሲጋራ ከማጨስ ያልተናነሰ የጤና ጠንቅ!

በመላኩ ታዬ (ዶ/ር)


ለሰው ልጆች ሁሉ ደህንነትና ጤና ትልቅ ስጋት ከጋረጡ ፈተናዎች አንዱ ዘመናዊነትና ከተሜነት ያመጣብን የአብዝቶ መቀመጥና ውዝፍነት አደገኛ ልማድ ነው ብንል ማጋናን አይሆንም። ከቀደሙ አያቶቻችን ጋር ሲነጻጸር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኑሯችን የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በሚገድቡ ብቻ ሳይሆን ረዘም ላለ ጊዜ መቀመጥ በሚጠይቁ ሁኔታዎች ውስጥ መኖር አስገዳጅ እየሆነ መጥቷል። በቤት ውስጥ፣ በስራ ቦታ፣ የመጓጓዣ መንገዶች፣ ማህበራዊና ሌሎችም የአኗኗር ለውጦች በባህሪያችን ላይ ተጽእኖ አምጥተዋል – እንዳንቀሳቀስና ቁጭ እንድንል! የቢሮ ወንበራችን ላይም ይሁን መኪና ውስጥ አሊያም ቤታችን ሶፋ ላይ ሲብስም ገንዘባችን አውጥተን ጊዜ ለመግደል በየቡና ቤቱ ዘለግ ላለ ሰዓት መዘርፈጥ የየእለት ህይወታችን አንዱ አካል ሆኗል።


ለመሆኑ ለረጅም ጊዜ መቀመጥ (prolonged sitting) እና ውዝፍነት (sedentary lifestyle) ሲባል ምን ማለት ነው? በዚህ የጤና ዘርፍ ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራው Sedentary Behavior Research Network (SBRN) የተባለው አለምአቀፍ የምርምር ተቋም እንደሚለው ረዘም ላለ ጊዜ መቀመጥ ካለእንቅስቃሴ በተቀመጥንበት፣ ጋደም ባልንበት ወይም በተኛንበት ለአንድ ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ መቆየት ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። ውዝፍነት የሚባለው ደግሞ ይህ አብዝቶ መቀመጥ ወደባህሪ እድጎ ልማድ ሲሆንብን ነው።


ልክ ሲጋራ እንደ ማጨስ፣ ከመጠን በላይ ውዝፍነት ለውፍረት፣ ቦርጭ፣ ስኳር ህመም፣ ልብ ሕመም፣ ካንሰር እንዲሁም ሌሎች እልቆ መሳፍርት የሌላቸው ስር የሰደዱ የበሽታ አይነቶች አጋልጦ የሚሰጥ ክፉ ልማድ ነው። ውዝፍነት ካለእድሜ ያሰረጃል ያጃጃል። በተጨማሪም አብዝቶና አዘውትሮ መቀመጥ ካለአድሜ የመሞትን እድል በእጅጉ እንደሚጨምር በዋና ዋና የህክምና መጽሄቶች ላይ የሚወጡ አያሌ ጥናቶች ያረጋገጡት አሌ የማይባል ሃቅ ሁኗል። ለዚህም ነው ለረዥም ሰዓት መቀመጥ በሚያስከትለው መዘዝ ምክንያት ‘the new smoking’ ተብሎ እየተጠራ ያለው።


‘ውይ የኛ ሃኪሞች! ሟርተኞች እኮ ናቸው! እንደናንትስ ወሬ ቢሆን ስንት መዓት በመጣብን ነበር! እሁን ደሞ ማን ይሙት መቀመጥ በምን ሳይንስ ነው ጎጂ የሆነበት ምክንያት?’ ለምትሉ እንደሚከተለው ነው። የሰውነታችንን ተፈጥሯዊ ስርዓተ እንሽርሽሪት (ሜታቦሊዝም) ሂደት ስለሚረብሽ ነው! ለረዥም ሰዓት በምንቀመጥበት ጊዜ ጡንቻዎቻችን እንቅስቃሴ-አልባ ይሆናሉ፣ የበላነው ምግብ (ካሎሪ) አይቃጠልም፣ የደም ዝውውራችንም እንደኤሊ ያዘግማል፣ ሙሉ የሰውነት ህዋሶቻችን ዱዝ ይሆናሉ። ይህ ውፍረት ያመጣል፤ የኢንሱሊንን ስራ ያስተጓጉላል (Insulin resistance)። በሂደትም ለብዙ ከባድ የጤና ችግሮች ያመቻቸናል። ስለዚህ ወዳጄ ሟርት አይደለም – መቀመጥ በሽታ ጎታች መሆኑ ያፈጠጠ ያገጠጠ እውነት ነው።


ይህንን ‘ማስፈራሪያ አዘል’ ጽሁፍ እንድከትብ ያነሳሳኝን የሁለት ታካሚዎቼን ታሪክ የህክምናን ምስጢር የመጠበቅ ስነምግባር በማይጥስ መልኩ በትንሹ ላካፍላችሁ።


የመጀመሪያዋ ባለታሪክ ኢትዮጵያ ሃገሯን ለድፍን አራት አስርት አመታት በመንግስት መ/ቤት ያገለገልች ደርባባ እመቤት ናቸው። ‘ከለውጡ በፊት’ የመስሪያ ቤቱ የአንድ ክፍል ሃላፊ ስለነበሩ በቢሮ መደበኛ ስራ ብዙ ጊዜዋን ተቀምጣ እንደምታሳልፍ አወጋችኝ፣ ከቤት ወደ ስራ ከስራ ወደቤት የሚያደርሳቸው ምድብ መኪና ስላላቸው በእግር መንቀሳቀስ ብሎ ታሪክ የለም። ቤትም ገብተው ወይ ቀሪ የቢሮ ስራ ለመከወን ኮምፒውተር ላይ ማፍጠጥ ነው አሊያም ሶፋ ላይ ተደላድሎ ቲቪ መኮምኮም ነው። ታዲያ እኒህ ሱስ የሚባል የሌለባቸው፣ አመጋገባቸው ሲፈጥራቸው ጠንቃቃ፣ ጣፋጭ ጭራሽ የማይወዱ ኩሩ ሴት ከጥቂት አመታት በፊት ‘ስኳርና ኮሌስትሮል ያሳያል’ ተባሉ። ሆኖም ግን ከድካም ያለፈ ምንም የበሽታ ምልክት ስለሌላት ችላ አለችው። ከአመት በፊት እድሜ ሲደርስ በጡረታ ተገለሉ። በሚያሳዝን ሁኔታ ከጡረታ ማግስት ጤንነታቸው እያሽቆለቆለ ሄደ እና በመጨረሻም የልብ ድካም አጋጠማት። አሁን ላይ የስኳር፣ የኮሌስትሮል፣ የልብ መድሃኒቶችና ሌሎችም ማስታገሻ መድሃኒቶች በየቀኑ ይወስዳሉ። እንዳለመታደል ሆኖ ለዘመናት ያገለገለቻት ሃገሯ ነጻ ህክምና ልትሰጣት አልቻለችም። የጡረታ ደሞዝም ከራስ ምታት ማስታገሻ መድሃኒት ያለፈ ዋጋ አይሸፍንም። እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን እኒህ ሴት አሁን ላለባቸው ህመም ዋነኛ ተወቃሽ አጋላጭ ምክንያት አብዝቶ የመቀመጥ ጦስ (prolonged sitting, sedentary life style) መሆኑን ልብ ማለት ነው።


ሁለተኛዋ ባለታሪክ ገና ሮጣ ያልጠገበች ወጣት ነች። ዩኒቨርስቲ እያለች ሁል ጊዜ ንቁ እና ብርቱ ሴት ነበረች፣ በምትወደው የቴክ ሙያ ተምርቃ የህልሟን ስራ ማግኘት ስላልቻለች ወደዱባይ ተጉዛ ራይድ ታክሲ መሸቀል ጀመረች። ገንዘብስ ተገኘ ግን የአኗኗር ዘይቤዋ በአንድ ጀምበር አስደናቂ ለውጥ ያዘ። በቀን ለ 8-10 ሰአታት በምትሾፍረው መኪና ውስጥ መቀመጥ፣ እረፍት ስታገኝ ብቸኝነትን ለመሸወድ በስልክ ስክሪን ላይ መጣድ በአንዴው የተለመደ ህይዎቷ ሆነ። የምታዘወትረው አመጋገብም በቀላሉና በርካሽ የሚገኝ ፋስት ፉድ (fast food) ነው። ለስላሳ መጠጦችም ከጎንዋ አይለዩም። ብዙም ሳይቆይ በማይታመን ፍጥነት ክብደቷ ሌላ ሰው አስመሰላት። ሳታውቀው የድካም እና የድንዛዜ ስሜት እየወረራት ከህመም ጋር ስትታገል አገኘችው። ስንት ዩኒቨርሲቲ አንዳልበጠሰች በቅጡ ማሰብና ማስታዎስ እየከበዳት ነገሮችን መርሳት፣ ትኩረት ለማድረግ መቸገር እና እንቅልፍ ማጣት አሰቃያት። አእምሮዋን እንደጭጋግ እየጨገጋት ግራ ያጋባት ከረመ። ለውጦቹ በአካላዊ ጤንነቷ ላይ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ደህንነቷ እና በራስ መተማመን ላይም ጎድቷታል። በዚህ የተነሳ ከማህበራዊ ህይወት እራሷን ማራቅ ጀመረች። የሰውነቷ ግዝፈት እያሳቀቃት ቤተሰብና ፍቅረኛዋ ጋርም በቪድዮ ኮል መገናኘት አስጠላት። የበለጠ እራሷን ባገለለች ቁጥር የባሰ ድባቴ ውስጥ ገባች። ይባስ ብሎ በዚህ እድሜዋ በቤተሰቧ ታሪክ ኖሮ የማያውቅ ስኳር ተያዘች። ለሶስት ቀን የተኛችበት ሆስፒታልም ለአመታት የለፋችበትን ጥሪት አራገፋት። ይህ ለእርሷ የማንቂያ ደወል ነበር። አሁን ለውጥ ማድረግ እንዳለባት ወሰነች። ያለማቋረጥ የመቀመጥ ልማዷን ሰብራ ቀስ በቅስ እንቅስቃሴ ማዘውተር ጀመረች። ስልክ ላይ የምታሳልፈውን የስክሪን ሰዓቷን እያስተዋለች መቀነስ ያዘች። ምግቧንም አስተካክላለች። በወራት እልህ አስጨራሽ ትግል በመልክ እና ስሜቷ ላይ አስደናቂ መሻሻል አሳካች። ስኳር ነሽ ኮሌስትሮል አዳፍና መድሃኒቷን በሂደት እየቀነሰች አሁን ላይ ማቆም ችላለች። ወደ ኋላ መለስ ብላ ስታሰላሰል እንቅስቃሴ-አልባ የሆነ አኗኗር በሁሉም ህይወቷ ላይ ምን ያህል ከባድ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ተገነዘበች። ጤናዋን ለመመለስ የወሰደቻቸው አንዳንድ እርምጃዎች ምን ያህል ቀላል እንደሆኑ ስታስብ ይገርማታል። እናም ወደፊት ለጤንነቷ ቅድሚያ ለመስጠት ቆርጣለች።


ጆሮ ያለው ይስማ እንዲል የባለታሪኮቹ ህይወት የሚያስተምረን ውዝፍነት ምን ያህል ካንሰር እንደሆነ ነው። ደስ የሚለው ነገር ግን የመቀመጥን አሉታዊ ተጽእኖ ለማሸነፍ የሚያስችል መፍትሄ በእጃችን ያለ መሆኑ ነው። በእለት ተእለት ህይወታችን ውስጥ ትናንሽ ለውጦችን በማድረግ አጠቃላይ ጤንነታችንን እና ደህንነታችንን በከፍተኛ ሁኔታ ማሻሻል እንችላለን።


በደራሲ ጄምስ ክሊር የተጻፈው ከፍተኛ አድናቆትን ያገኘው ‘Atomic Habits’ መጽሃፍ ላይ የተጠቀሱት ምክረ ሃሳቦች ከመጠን በላይ የመቀመጥን ክፉ ልማድ አስወገዶ በምትኩ አካላዊ እንቅስቃሴን የዘወትር ቀለብ ለማድረግ ጠቃሚ መርሆዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ መጽሃፍ የሚመክረው ልማዶችን ለመቀየር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ የሚሄዱ ትናንሽና ቀላል የማያቋርጡ ለውጦችን በማድረግ ነው። አካላዊ እንቅስቃሴንም ልማድ ለማድረግ ዋናው ነገር በትንሽ መጀመር እና በተቻለ መጠን አሁን ካለዎት የስራ ጸባይ የማይጋጭ ማድረግ ነው። ለምሳሌ፣ አጠቃላይ የስራ ሰዓትዎን ሙሉ በሙሉ ለመቀየር ከመታገል ይልቅ በየሰዓቱ ለትንሽ ደቂቃ ያህል ለመንቀሳቀስ (ከወንበር ተነስቶ ለመቆም፣ ቢሮ ውስጥ ለመራመድ፣ አንድ ሁለት ደረጃ ወጣ ወረድ ብሎ ወደስራ ለመመለስ…) በመወሰን ይጀምሩ። ይህን ማድረግ አውቶማቲክ ልማድ ሲሆን ቀስ በቀስ የእነዚህን የእንቅስቃሴ ሰዓታት እያረዘሙና የስፖርቱን ክብደት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመሩ መሄድ። ለአብነትም ለምሳ ራቅ ያለ ሬስቶራንት በእግር ተጉዞ መብላት ሊሆን ይችላል።


መንቀሳቀስ እንዳይረሳን የሚመች ከባቢን መፍጠርም ይገባል። ለምሳሌ በስልካችን የሚያስታውሰን አላርም መሙላት፣ የስፖርት ጫማን በቀላሉ የሚታይ ቦታ ማስቀመጥ፣ የስራ ባልደረቦቻችን እንዲያስታውሱን ማድረግ ሊሆን ይችላል። እንዲህ እነዚህን ትንንሽ ልምምዶች እያሳደግን እንደነባር ልማዶች በዘላቂነት የህይወታችን አካል ሆነው ሲዋሃዱን ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ ይኖረናል ማለት ነው።


ኧረ እባክህ ተወኝ! ምንም የጂም ሰዓት የለኝም ባተሌ ነኝ! ለምትሉም ከላይ የተጠቀሰው ስትራቴጂ ውጤታማ ነው። እንቅስቃሴን ‘ስናክ’ ማድረግ (exercise snacks) እና በዕለት ተዕለት ስራችን ውስጥ ማዘውተር ትልቅ ለውጥ ያመጣል።


በዕለት ተዕለት ስራችን ውስጥ ማዘውተር የሚገቡን የተወሰኑ ምሳሌዎች ለመጥቀስ ያህል፤


እስኪ ከሊፍት ይልቅ በደረጃ እንውጣ እንውረድ፣ ስልክ ስንይዝ ቁጭ ከምንል እየተራመድን እናውራ፣ ለሻይ ቡና ስንወጣ መኪና አስነስተን ጭስ ከምንምግ በእግራችን እንሂድ፣ መኪናችንን ራቅ ያለ ቦታ አቁመን ትንሽ ብሎኮች እንራመድ። ወደቤታችን ስንመለስ ከባስ ወይም ታክሲ ቢያንስ አንድ ፌርማታ ቀደም ብለን ወርደን ግማሽ ሰዓት በእግር እንጓዝ፣ የቤት ሰራተኛችንን ‘አንቺ ማነሽ ስንዱ ቶሎ በይ ውሃ አምጭልኝ!’ ከምናዝዝ እራሳችን ተነስተን ውሃ እንቅዳ። ጸሃፊያችንን አሁንም አሁንም ሂጂ-ውሰጅ-አምጭ ከምንነተርክ እራሳችን ከተኮፈስንበት ወንበር ተነስተን ወረቀት እናምጣ። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እንቀሳቀስ!
ቢሯችን ውስጥ ዱብ ዱብ ማለት፣ ፑሽ አፕ መውረድ ይቻላል። ጠረጴዛ/ወንበር ተደግፈን ቁጭ ብድግ መስራትም ሌላ አማራጭ ነው። ደሞ የህዝብ ንብረት አንድ ነገር ቢሆንብኝስ … ሆ! ካሰጋችሁ በተቀመጣችሁበት ወይም ተነስታችሁ ሰውነታችሁን ማፍታታት፣ እጅ እግርን በማጠፍ በመዘርጋት እንቅስቃሴ ማድረግም ይቻላል። ይህን ለማዘውተር ስልካችን ላይ በየሰዓቱ የሚያስታውሰን አላርም በመሙላት በየአንድ ሰዓቱ የ5 ደቂቃ ስፖርት መስራት እንድንችል ሊያግዘን ይችላል። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እንቀሳቀስ!


በአንጻሩ ለረጅም ሰዓት መጎለትን የሚያበረታቱ ልማዶችን ለመቀነስና ለማስወገድ መታገልም ይፈልጋል። ለምሳሌ ለመወዘፍ የሚዳርገንን አብዝቶ የስልክ፣ ኮምፒይተር ወይም ቲቪ ስክሪን ላይ ማፍጠጥ መቀነስ ይገባል። አብዛኞቻችን በየእለቱ ምን ያህል ጊዜ እንደምናጠፋ እንኳን ሳናውቅ ስልካችንን ካለደቋና ‘በዞምቢ ሞድ’ ስንነካካ እናሳልፋለን። ይህንን ልማድ የስክሪን ሰዓት ገደብ በመጣል ማረም ይፈልጋል። ውርድ እንውረድ ተጠራርተን ‘ካፌ እንቀመጥ’ ከሚሉን ጓደኞች ይልቅ ‘ወደተራራ እንውጣ’ የሚሉትን ወዳጆች ማብዛት ይሻላል።


እነዚህ ትናንሽ ለውጦች ከጊዜ በኋላ ከፍተኛ የጤና ጥቅሞችን ያመጣሉ። እንቅስቃሴን በህይወትዎ ውስጥ ቅድሚያ በመስጠት አጠቃላይ ጤናዎን በእጅጉ ማሻሻል ይቻላል። አብዝቶ በመቀመጥ የሚመጣ ለከባድ በሽታዎች ተጋላጭነትን መቀነስ ይችላሉ።


ያስታውሱ፣ ለሁሉም ሰው የሚሰራ አንድ የአኗኗር ቀመር ማስቀመጥ አይቻልም። ዋናው ነገር እርስዎ የሚወዷቸውን እና ሊዘወተሩ የሚችሉ እንቅስቃሴዎችን መጀመር ነው። እንቅስቃሴዎችን በቀላሉ በቀን ውሎአችን መካተት የሚችሉበት መንገዶችን ይፈልጉ። የእንቅስቃሴው አይነት ይነስም ይብዛ መንቀሳቀስን በጽናት ማስቀጠል። እያንዳንዱ እርምጃ ለጤና ጠቃሚ ነው። በትንሹ ይጀምሩ እና ቀስ በቀስ የእንቅስቃሴዎን ደረጃዎች በጊዜ ሂደት ይጨምሩ።


ማስታወሻ፡ በዚህ ጽሁፍ የተካተቱት ይዘቶች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና የጤና ባለሙያዎን ያማክሩ።


ይህ መረጃ ጤናዎትን ለመጠበቅ አንድ ግብዓት ሆኖ እንዳገኙት ተስፋ አደርጋለሁ! ስለጤናማ የአኗኗር ስልት ተጨማሪ ጥያቄዎች ካሉዎት የዚህን መረጃ ያሰናዳዉን ዶ/ር መላኩ ታዬ እና ሌሎች ባለሙያዎች በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል ማግኘት ይችላሉ። 


ተጨማሪ ምክር፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት በኢሜል contact@melakutaye.com እና ስልክ +251921720381 ማግኘት ይችላሉ።

4 thoughts on “አብዝቶ መቀመጥ – ሲጋራ ከማጨስ ያልተናነሰ የጤና ጠንቅ!”

  1. This is a very powerful insight. It’s ironic our mothers never let us sit for a single second in the olden generations we always had chores to complete, specially waking up early in the morning at 5:00 AM. It is so sad we came to drop all those and get to where we are today. True sitting is a bad habit. Thank you Dr. Melaku for opening my eyes to how my childhood life was busy, energetic, non resting and most of all having the courage to redo them all over again.

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top