የስኳር ህክምና ግቦች (therapeutic goals of diabetes care) ምንድን ናቸው?

በሁሉም የህይዎታችን ዘርፎች አሸናፊ እንድንሆን ማቀድና ግብ ማስቀመጥ አንዱ የስኬት ቁልፍ ነው። ማቀድና ግብ ማውጣት ህይዎታችንን በተቻለ መንገድ ለመመራት ያግዛል። ከሁሉም የሚበልጠው ደግሞ ጤናችን ነው። ስለሆነም ጤናችንን ለመጠበቅ ማቀድ፣ ግብ ማስቀመጥና በጽናት ዘወትር ራሳችንን መንከባከብ ይፈልጋል። በተለይም የስኳር ህመም ያለባቸው ሰዎች ጤናቸውን ለማሻሻል አበክረው መትጋት ያስፈልጋቸዋል። ይህን ለማድረግ ይረዳ ዘንድ ለዛሬ ውይይታችን የመረጥነው ርዕስ የስኳር ህክምና ግቦች ምንድን ናቸው የሚለውን ነው።

እንደሚታዎቀው የስኳር ህመም ያለባቸው ሰዎች የደም ስኳር መጠን ለመቆጣጠርና የስኳር ተጓዳኝ የጤና እክሎችን ለመቀነስ መደበኛ ክትትል እና ቀጣይነት ያለው ሕክምና ያስፈልጋቸዋል። ሕክምናው የአኗኗር ለውጦችን ማድረግ፣ በጤና ባለሙያ የታዘዙ መድሃኒቶችን በአግባቡ መውሰድና ዘወትር ራስን የመጠበቅ እርምጃዎች ማድረግን ያጠቃልላል። ይህም የስኳር በሽታ የሚያስከትላቸውን የልብና የደም ቧንቧ ውስብስብ ችግሮች ስጋት ይቀንሳል። ነገር ግን ስኳርን ብቻ በማስተካከል ችግሮችን ማጥፋት አይቻልም።

ይልቁንም ዘርፈ ብዙ የተቀናጀ የአደጋ ተጋላጭነት ቅነሳ ማድረግ ይፈልጋል። ይህም ሲባል ስኳር ማተካከል፣ የደም ግፊት በተገቢ ሁናቴ ማከም፣ የጎጅ ኮሌስትሮል መጠን መቀነስ እንዲሁም የሰውነት ክብደት በተለይም ቦርጭን መቀነስ ያካትታል። እነዚህን አራት የስኳር ህክምና ግቦች ማሳካት አዳጋች ነው። በአለም አቀፍ ደረጃ ሁሉንም ግቦች መምታት የቻሉት ከ10% ያነሱ ታካሚዎች ብቻ ናቸው። በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተሰሩ ጥናቶችም የሚያሳዩት የህክምና ግቦቹን ያሳኩት ታካሚዎች ቁጥር ከ3% የማይበልጥ እጅግ አነስተኛ መሆኑን ነው።

የስኳር እንክብካቤን የሕክምና ግቦች ለማሳካት ከሚያግዙ መሰረታዊ መፍትሄዎች ውስጥ የታካሚን ያማከለ የስኳር ትምህርትና ግንዛቤ ማስጨበጫ እውቀትን ማሻሻል እና ራስን መንከባከብ ይገኙባታል።

የታካሚዎች ስለ እነዚህ የስኳር ህክምና ግቦች ያላቸው እውቀት ማነስ ራሳቸውን እንዳይጠብቁ፣ የስኳር ቀጥጥሩ እንዲባባስ፣ እንዲሁም የስኳር ተጓዳኝ የጤና እክሎች ስር እንዲሰዱ ያደርጋል። በተቃራኒው ደግሞ የታካሚዎች ስለ የስኳር ሕክምና ግቦች እውቀት መሻሻል እራስን መንከባከብን ፣ የመድኃኒት አወሳሰድን እና የስኳር ቁጥጥርን እንደሚያሻሽል በርካታ ጥናቶች ያሳያሉ።

የስኳር ህክምና ግቦች ዋና ዋናዎቹ አራት ናቸው።

የመጀመርያውና ዋናው ግባችን በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን መቆጣጠር ነው። ይህም ማለት በባዶ ሆድ የሚሰራው የደም መጠን ከ80 እስከ 130 mg/dl ከምግብ በኋላ የሚለካው የስኳር ልኬት ከ180 mg/dl በታች እንዲሁም የ3 ወር አማካኝ የስኳር ክምችት መጠን ከ7% በታች እንዲሆን ይመከራል።
ነገር ግን የግሉኮስ መጠን በጣም መቀነስ በሁሉም ታካሚዎች ውስጥ የተሻለው ስልት ላይሆን ይችላል። የምናስቀምጠው ግብ ታካሚውን ያማከለ መሆን ይኖርበታል። እድሜያቸው በጣም የገፋ ከሆነ፣ የልብና የደም ሥር ሕመም ከፍተኛ ተጋላጭነት ካላቸው፣ ጥሩ ማህበራዊ ድጋፍ ማግኘት የማይችሉ ከሆነ እየታዬ የስኳር ግባችንን ማላላት ሊያስፈልግ ይችላል። ምክኛቱስ ቢባል አሳሳቢ የሆነ የስኳር ማነስ በራሱ ችግሮች ስለሚያመጣ ነው።
በተጨማሪም ግሉኮስን ብቻ መቆጣጠር በቂ አይደለም። የስኳር ተያያዥ እክሎችን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመቀነስ ሌሎች በርካታ ማስተካከያዎችን ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው።
ሁለተኛ የስኳር ህክምና ትኩረት የደም ግፊትን በተገቢው ሁናቴ ማከም ነው። የደም ግፊትን መቆጣጠር ልክ እንደ የደም ስኳር መጠን ሁሉ አስፈላጊ ነው። ከፍተኛ የደም ግፊት በተለይም ከስኳር ህመም ጋር አብሮ ሲመጣ ለልብ ድካም፣ ለስትሮክ እና ለኩላሊት በሽታዎች ያጋልጣል። ለአብዛኛዎቹ ሰዎች ግፊታቸው ከ130 በ80 ባይበልጥ ይመከራል።
ሶስተኛው ወሳኝ ግባችን ኮሌስትሮል ማስተካከል ነው። ኮሌስትሮልም ማከም ብዙ ጌዜ የሚዘነጋ ቢሆንም ግን ጠቀሜታው ስኳርንና ግፊትን ከማከም አይተናነስም። በተልይም ጎጅ ኮሌስትሮል የሚባለውን LDL-C በደንብ መቀነስ ቢቻል ከ70 በታች ማውረድ ይፈልጋል።
አራተኛው ግባችን የሰውነት ክብደትን በተለይም ቦርጭን መቀነስ ነው። ክብደትን ማስተካከል ስኳርን ግፊትንና ኮሌስትሮልን ለማከም ወሳኝ ሚና ይጫዎታል። በተለይም ቦርጭ ማጥፋት እና ክብደቱ እንዳይመለስ በጽናት መስራት ስኳሩን በከፍተኛ ደረጃ በማሻሻል የስኳር መድሃኒት የሚቀነስበት ለሚቻላቸውም ማቆም ሊያስችል (diabetes remission) ይችላል።
በአጠቃላይ እነዚህና ሌሎች ግቦችን ለመምታት ቀላል ባይሆንም ማሳካት ይቻላል። ይህን ማድረግ ከቻልን ጤናም፣ ስኬታማና አምራች ዜጋ መሆን እንችላለን።
ማስተዋል ያለብን ነገር ቢኖር እነዚህ የህክምና ግቦች አጠቃላይ ምክርና መመሪያዎች ይሁኑ እንጅ ለሁሉም ሰው ይሆናሉ ማለት ግን አይደለም። እንደየ ታካሚው የጤና ሁናቴ እን የህመሙ ደረጃ ሊቀየሩና ሊሻሻሉ ይችላሉ። ከሃኪምዎት ጋር በመመካከር ለእያንዳንዱ ግለሰብ የሚመመጥኑ ግቦች ማስቀመጥ ይፈልጋል።

2 thoughts on “የስኳር ህክምና ግቦች (therapeutic goals of diabetes care) ምንድን ናቸው?”

  1. …… በተለይም ቦርጭ ማጥፋት እና ክብደቱ እንዳይመለስ በጽናት መስራት ስኳሩን በከፍተኛ ደረጃ በማሻሻል የስኳር መድሃኒት የሚቀነስበት ለሚቻላቸውም ማቆም ሊያስችል (diabetes remission) ይችላል….. kemitl lemn defer bileh ‘sikuar ydnal’ atilm.. bizu yebahil awaqiwoch eko sikuar eyadanu new eyetebale new

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top