የስክሪን ጊዜ ገደብ ለልጆችና ታዳጊዎች
ከልክ በላይ የስክሪን ጊዜ በልጆች አካላዊ እንቅስቃሴያቸው፣ በማህበራዊ ግንኙነታቸው እና ጤናማ የእንቅልፍ ስርዓታቸው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያመጣል። የአእምሮ እደገትም ያዘገያል። የአይንና እይታቸው እድገት ላይም ተጽእኖ አለው። አሁን አሁን በርካታ ልጆች የእይታ መነጽር እምዲጠቀሙ ያስገደደው አንዱ ምክንያት ከልክ ያለፈ በልጅነት ኤሌክትሮኒክስ ስክሪን ላይ ማፍጠጥ እንደሆነ የሚጠቁሙ ጥናቶች እየተሰሙ ነው። ስለሆነም በተልቻለ መጠን ልጆች ስክሪን ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜ መገደብ ይገባል።
ለልጆችና ታዳጊዎች የስክሪን ጊዜ ገደብ መመሪያ ምን ያህል ነው?
ከሁለት አመት በታች ያሉ ህጻናት ምንም አይነት ኤሌክትሮኒችስ ስክሪን ፈጽሞ ማየት የለባቸውም።
ከሶስት እስከ አስራ ስምንት አመታ ያሉ ልጆች ደግሞ የስክሪን ጊዜያቸው ከሁለት ሰዓት መብለጥ የለበትም።
የልጆቻችንን የስክሪን ጊዜ ለመቀነስ ምን እናድርግ?
ህጻናት ለአጠቃላይ እድገታቸው መሳለጥ መጫወት፣ ማንበብ እና ከቤተሰብ ጋር ማህበራዊ መስተጋብር መፍጠር እንጅ ስልክ፣ ቴለቪዥን እንዲሁም ቪዲዮ ላይ እንዲያሳልፉ መፍቀድ የለብንም። የልጆችን ስክሪን ጊዜ ገደብ (screen time curfew) በማበጀት ልጆችን መቆጣጠር ያስፈልጋል። ነገር ግን ልጆችን በመከልከል መቆጣጠር ከባድ ነው። በዋናነት የሚማሩት ወላጆችን በማየት ስለሆነ ወላጆች ህጻናት ባሉበት ስልክ ባለመነካካት፣ ቴሌቪዥን በማጥፋት ለልጆቻቸው አርዓያ መሆን ይኖርባቸዋል።
የስክሪን ጊዜ ገደብ ለአዋቂዎች
ስክሪን ላይ አፍጦ ረዘም ላለ ጊዜ መቀመጥ ለውፍረት፣ ስኳር ህመም፣ ለልብ እና የደም ቧንቧ በሽታዎች እና ለአንዳንድ የካንሰር አይነቶች ተጋላጭነት በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል። ከመጠን ያለፈ የስክሪን ጊዜ አካላዊ የጤና ችግሮች ያስከትላል ለምሳሌ የዓይን ድካም፣ ራስ ምታት፣ የአንገት ህመም (texting neck syndrome), የጀርባ ህመም እና የፖስቸር መዛባት ያመጣል። በተጨማሪም ከስክሪኖች የሚወጣው ሰማያዊ ብርሃን እንቅልፍ ሊያስተጓጉል እና አጠቃላይ የእንቅልፍ ጥራትን ሊጎዳ ይችላል። ጤናን ብቻ ሳይሆን በጊዜ አጠቃቀም ላይም ጣልቃ ሊገባ ይችላል። በዋና የህይወት ተግባራችን ላይ ያለንን ትኩረትን ስለሚሰርቅ ስራችንን በጊዜ እንዳናጠናቅቅ እንቅፋት ይሆናል። ባስ ሲልም ከትዳር ጓደኛ፣ ቤተሰብ እና ከጓደኞች ጋር የምናሳልፈውን ጊዜ በመሻማት አለመግባባትና ጠብ ያመጣል።
የስክሪን ጊዜን ለመቀነስ ምን እናድርግ?
- የስክሪን ማያ ጊዜያችንን መከታተልና ስንት ሰዓት እንደምናቃጥል ማወቅ የመጀመርያው እርምጃ ነው። ይህን ለማድረግ ስልኮቻችን ላይ ያሉ መከታተያ መተግበሪያዎችን በመጠቀም በየቀኑ ስልክ ላይ ምን ያህል ጊዜ እናጠፋለን የሚለውን ማወቅ ይቻላል።
- የስልክ መጠቀሚያ ጊዜ ገደብ ማስቀመጥ። ለምሳሌ የመዝናኛ ማያ ጊዜን መገደብ። ጊዜ ገደቡ ሲያልቅ አላርም እንዲጮህ ወይም ስክሪኑ እንዲጨልም በማድረግ ከስክሪን እረፍት እንድናደርግ ሊያስታውሰን ይችላል።
- ስክሪን ስንጠቀም በማስተዋል ይሁን (Mindful Screen Use): ስክሪን እንዴት እና ለምን እንደምንጠቀም ማስተዋል ይገባል። በልማድ ወይም ከመሰላቸት እንዲሁ ጊዜ ለማቃጠል (mindless scrolling) ሳይሆን ፈልገን አስበንና ፈቅደን እየተጠቀምን እንደሆነ እራስን መጠየቅ ይገባል። ስናይም እንዲሁ የመጣልንን ሳይሆን እራሳችን የምንፈልገውን መረጃ ብቻ መርጠን ማየት ያስፈልጋል።
- አንዳንድ የቤት ክፍሎቻችንን ከኤሌክትሮኒክስ ነጻ ዞን ማድረግ ለምሳሌ መመገቢያ ክፍሎች፣ አልጋ ክፍሎች ወይም ማንበቢያ ክፍሎች ውስጥ ምንም አይነት ኤሌክትሮኒክስ ይዞ አለመግባት።