ስለውፍረት ህክምና ያለን አረዳድ ብዙውን ጊዜ የተሳሳተ ሲሆን ይታያል። ውፍረትን በጣም አቅሎ ማየትም አለ። አልፎ ተርፎም ወቃሽና አግላይ ሊሆን ይችላል። ለብዙዎች ውፍረት ሲባል በስንፍና ምክንያት የሚመጣ፣ ከግለሰቡ የግል ፍላጎት ማጣት ወይም ክብደትን ለማስተካከል አለመፈለግ ይመስላቸዋል።
አብዛኛውን ጊዜ ግለሰቦች ብዙ ወራት በራሳቸው ሞክረው የተለያዬ ምግብ አንስተው ጥለው፤ ጂም ደክሞው አልሳካ ሲላቸው ነው ለውፍረት ህክምና ወደባለሙያ የሚያቀኑት። ሞክረው ስላልተሳካላቸው ብዙዎች የተሸነፉ ይመስላቸውና ይሸማቀቃሉ፣ ይበሳጫሉ። ‘ምግብ በማየት ብቻ ክብደት እጨምራለሁ‘ እያሉ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ያንፀባርቃሉ። ራሳቸውን አብዝተው ይወቅሳሉ።
ነገር ግን ስለ ውፍረት ሳይንስ በጥልቀት ለሚመረምሩ አንድ ግልፅ እውነታ አለ። ይህም ውፍረት የሰውነት ስብ ከመጠን በላይ መብዛት ጋር የተያያዘ ስር የሰደደ፣ ለህክምና አስቸጋሪ፣ የሚያገረሽ እና መልከ ብዙ ውስብስብ በሽታ (Adiposity Based Chronic Disease) እንደሆነ ነው።
ስለ ውፍረት አንዳንድ እውነቶች
ሰዎች በተለያየ ምክንያት ክብደት ይጨምራሉ።
ውፍረት አምጭ ምክንያቶች በጣም ብዙ ናቸው። ውፍረት በአኗኗር ዘይቤ አለመስተካከል ብቻ የሚመጣ የስንፍና ህመም አይደለም። ክብደትን መቆጣጠር የምናስገባው እና የምናስወጣው ካሎሪ ምጥጥን ጉዳይ ብቻ አይደለም። ውፍረት ማለት ‘ብዙ መብላት እና ትንሽ እንቅስቃሴ ማድረግ’ ብቻ አይደለም። ውፍረት መልከ ብዙ ነው።
ከአኗኗር ዘይቤ በተጨማሪ ጄኔቲክ፣ ሆርሞኖች፣ የስነ ልቦና / አእምሮ ውጥረትና ጭንቀት ወዘተ በርካታ ተጽእኖዎች የሚያመጡት በሽታ ነው – ውፍረት። ለሌላ ህክምና የምንወስዳቸው መድኃኒቶች ሊያወፍሩን ይችላሉ። የምንኖርበት አካባቢ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ለክብደት መጨመር አስተዋጽኦ ያደርጋል።
ውፍረት ራሱን የቻለ ህመም ነው።
የውፍረት ህክምናዎች ብዙውን ጊዜ የሚያተኩሩት ውፍረትን ከምንጩ ከመፍታት ይልቅ እንደ የስኳር በሽታ እና የደም ግፊት ያሉ የውፍረት ተያያዥ በሽታዎችን በማከም ላይ ነው። ብዙዎቹ ውፍረትን እንደ አንድ ህመም ቆጥሮ ስም ሰጥቶ ከማከም ይልቅ የውፍረት ምልክት የሆኑትን ስኳር ህመምና ሌሎችንም በሽታዎች ብቻ ማከም ያተኩራሉ። ውፍረት በራሱ በሽታ ሳይሆን ወደ ሌሎች በሽታዎች የሚመራ አጋላጭ ሁኔታ (risk factor) ብቻ አድረገው አቅለው ያዩታል።
ውፍረት እንደ አንድ ራሱን የቻለ ህመም/በሽታ መታወቅ፣ መታከም አለበት። ውፍረት ልክ እንደ የስኳር ወይም የደም ግፊት ህመም ያለ የረጅም ጊዜ ህክምና የሚፈልግ በሽታ ነው።
ክብደት መቀነስ ይቻላል ግን ቀላል አይደለም።
ክብደት መጨመር በጣም ቀላል ሂደት ሲሆን አንድ ኪሎ ለመቀነስ እና የተቀነሰውን ማስጠበቅ ግን ራስ ዳሽን እንደመውጣት ዳገት ነው። ክብደት መቀነስ ‘ትንሽ ብላ፣ ብዙ ተንቀሳቀስ‘ የሚባለውን ያህል ቀላል አይደለም።
ሰውነታችን ክብደት ከተወሰነ ቁጥር በላይ እንዳይቀንስ ጥርሱን ነክሶ መዋጋት ዋና ሰዋዊ ባህሪው ነው። ክብደት በሚቀንስበት ጊዜ ሰውነታችን ያጋጠመውን የካሎሪ እጥረት ለመቋቋም በተለያዩ መንገዶች አዳዲስ የሜታቦሊክ አሰራር ይላመዳል (Metabolic adaptation)። ምግብ ስንቀንስ ሰውነታችን መአት እንደመጣበት በማሰብ ማካካሻ መንገድ ይዘይዳል። የሜታቦሊዝም ፍጥነት ዝግ እንዲል በማድረግ ከበፊቱ ያነሰ ካሎሪ ያቃጥላል። ሰውነት የሃይል ቁጠባ ያበዛል፤ ለክፉ ቀን እያለ ማከማቸት ይጀምራል። የረሃብ ሆርሞኖች እየጨመሩ ምግብ አምጣ አምጣ ይወተውታል። ይህ ኢ-ጠቃሚ (mal-adaptive) የፊዚዮሎጂ ለውጥ ክብደት እንዳይቀንስ ይሞግታል። የራሳችን ሰውነት የሚያመነጫቸው ሆርሞኖች በድብቅ ይታገሉናል። ታግለን የቀነስናትን ክብደትም መልሶ በመጨመር ወደነበረበት ይመልሳል።
ለሁሉም ሰው ሊሰራ የሚችል አንድ ፍቱን ቀመር የለም።
ለሁሉም ሰው ተመሳሳይ ህክምና በማዘዝ የውፍረት መንስኤዎችን እና ችግሮችን መፍታት አይችልም። ለምን ቢባል ምክንያቱ ይህ ነው፡
ውፍረት አምጭ ምክንያቶች የተለያዩ መሆን፤
ለአንድ ሰው ክብደት እንዲጨምር ያደረገው ምክንያት ከሌላው ሰው ፈጽሞ የተለየ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ አንድ ሰው በሆርሞን መዛባት ምክንያት ሊወፍር ይችላል። ሌላኛው ደግሞ ክብደትን የሚያመጡ መድሃኒቶችን እየወሰደ ሊሆን ይችላል።
ክብደት ለመቀነስ ያለን ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት የተለያየ መሆን፤
አንዳንድ ሰው ክብደት መቀነስ የፈለገው ስኳር ለማስተካከል ሊሆን ይችላል፣ ሌላኛው ለውበት ሸንቀጥ ለማለት፣ የመገጣጠሚያ ህመሙን ለማስታገስ ወዘተ የተለያዬ ፍላጎት ነው ያለን። ሌሎች ደግሞ አጠቃላይ የጤና መሻሻልን ሊፈልጉ ይችላሉ። ምን ያህል ክብደት መቀነስ እፈልጋለሁ የሚለውም የተለያየ ነው። ተነሳሽነቱና ቁርጠኝነቱም እንደዚያው ለየቅል ነው።
ክብደት እንዳንቀንስ የሚያሰናክሉን እንቅፋቶች የተለያዩ መሆን፤
ክብደት ለማስተካከል ስንሞክር እንዳንቀንስ የሚያሰናክሉን በርካታ ጋሬጣዎች ያሉ ሲሆን ከሰው ሰው በስፋት ይለያያሉ። የአንዱ ሰው ችግር ገንዘብ ነክ ሊሆን ይችላል። ሌላኛው ግለሰብ ጤናማ ምግቦች ካለማግኘት ወይም ጊዜ ከማጣት ሊሆን ይችላል። የጓደኛና ማህበረሰብ ከባቢ ጫናዎችም እንዲሁ አይጠፉም።
ከላይ በዘረዘርናቸው እና ሌሎችም ምክንያቶች ለሁሉም ሰው ሊሰራ የሚችል አንድ ፍቱን የውፍረት ህክምና መስጠት አይቻልም። ውፍረትን በተሳካ ሁኔታ ለማከም የታካሚውን ኑሮ፣ አቅም፣ ፍላጎት እና ጽናት ያማከለ ለእያንዳንዱ ግለሰብ ተመጥኖ የተዘጋጀ አቀራረብን ይጠይቃል።
ግለሰቡን ያማከለ የውፍረት ህክምና
የተሳካ ውፍረት ህክምና የሚጀምረው በግለሰቡ አጠቃላይ ፍላጎት፣ ግብ፣ አቅምና ጽናት ግምገማ በማድረግ ነው።
ለክብደት መጨመር አስተዋፅዖ የሚያደርጉ ክብደት አምጭ ሁኔታዎችን መለየትና ማስተካከል ይገባል። የክብደት ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፉ እንቅፋቶችንም መረዳትና ማረቅ ያስፈልጋል። የታካሚ ግቦችን ማክበር ግድ ነው። የግለሰቡን ተነሳሽነትና ጽናት በመገምገም ለዚያ የሚሆን የሚመጥን ከቀላል ለውጦች መጀመር ይሻላል። እንዲህ ጥልቅ ግምገማ ከተደረገ በኋላ ሊተገበር የሚችል የሕክምና እቅድ ማውጣትና ወደስራ መግባት ይቻላል።
የግለሰቡን ኑሮና አቅም ያገናዘበ የአኗኗር ዘይቤን ማሻሻል ማድረግ። እንደታካሚው ምርጫ እና ልማድ ሁኔታ የተዘጋጀ በዘላቂነት ሊቀጥል የሚችል የአመጋገብ ስልት ማውጣትን ሊያካትት ይችላል። ለማዘውተር የማይከብድ እና ግለሰቡ የሚወደው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ልምምድ መጀመርና በየጊዜ ማሻሻል በጣም ጥሩ አማራጮች ሊሆኑ ይችላሉ።
ወደሚፈልጉት ክብደት ልክ ለመድረስ እና ለረጅም ጊዜ ክብደት ሳይመለስ ለማቆየት ቀጣይነት ያለው ተነሳሽነት፣ ትዕግስት እና ጽናት የሚጠይቅ የዕድሜ ልክ ጥረት ግድ ነው። የበለጠ አመጋገብ በማስተካከል የሙጥኝ መጽናት ይገባል። የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ከበፊቱ ጨመር አድርጎ በመስራት (በተለይ የጥንካሬ ስፖርት በማካተት የጡንቻን ጥንካሬ መጠበቅ) ክብደትን ማስተካከልና ጤናን የበለጠ ማበልጸግ ይቻላል።
ውፍረት ሊያመጡ የሚችሉ የአእምሮ ጤና ጫናዎችን ለመቀነስ የስነ ልቦና ድጋፍ ማግኘት ይመከራል። እንቅልፍ ማስተካከል፣ ጭንቀት መቀነስ፣ ድባቴን መታከምም እንዲሁ ጠቃሚ ነው።
እንዳስፈላጊነቱ በተለይም በአመጋገብና ስፖርት ክብደት ማስተካከል እምቢ ያለቸው ግለሰቦች በሃኪም የታዘዙ ፀረ-ውፍረት መድሃኒቶችን (Anti-obesity medication) በመውሰድ ሊታከሙ ይችላሉ። እነዚህ መድሃኒቶች መታዘዝ ያለባቸው በውፍረት ህክምና ስፔሻላይዝ ያደረገ ይህ ካልሆነ በውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሃኪም ቢሆን ይመከራል።
መርሳት የሌለብን ነገር ቢኖር የፀረ-ውፍረት መድሃኒት በሚጠቀሙበት ጊዜ ጤናማ አመጋገብን፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን እና ሌሎችንም የአኗኗር ለውጦች ማስቀጠል ያስፈልግዎታል። መድሃኒቱ ተጨማሪ አጋዥ እንጅ የሻተንን አብዝተን ለመብላትና ስፖርት ላለመትጋት ሰበብ ይሁን ማለት አይደለም።
በተቃራኒው ብዙ የጤና ባለሙያዎች እነዚህን ፀረ-ውፍረት መድኃኒቶች የመጨረሻ አማራጭ ብቻ አድረገው ማየት አለ። የጸረ ውፍረት መድሃኒቶች ውፍረትን ለመቆጣጠር በጊዜ መጠቀም አስፈላጊ ነው። በግለሰቡ ጤና እና መድሃኒት የመግዛት አቅም ላይ በመመስረት በርካታ አማራጮችን መወያየትና መወሰን ተገቢ ነው። ሌላው ደግሞ ጸረ ውፍረት መድሃኒቶች ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚሰጡና ቶሎ የሚቋረጡ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ መቀጠል ይኖርባቸዋል። አለዚያ ብዙ ወጪ አውጥተን የሞከርናቸው መድሃኒቶች ሲቆሙ ክብደት ወዲያዉኑ ተመልሶ ይጨምራል።
ከመድሃኒቶች ባሻገር የሜታቦሊክ ቀዶ ጥገና (metabolic/bariatric surgery, weight loss surgery) በተለይ መጠነ ክብደታቸው በጣም ከፍተኛ ለሆነ ሰዎች ሊሰራ ይችላል።
ማጠቃለያ
ውፍረት የስንፍና ወይም የፍላጎት ማነስ ጉዳይ አይደለም። ግለሰቡን ያማከለ፣ ሳይንስን መሠረት ያደረገ የሕክምና ዘዴን የሚፈልግ ውስብስብ በሽታ ነው።
ስለሆነም የእያንዳንዱን ታካሚ ፍላጎትና ልዩ ጸባይ ያገናዘበ ህክምና እና እንክብካቤን ማቅረብ ያስፈልጋል። ውጤታማ የውፍረት ህክምና ለመስጠት ለእያንዳንዱ ታካሚ ጥልቅ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ለክብደት መጨመር አስተዋጽኦ የሚያደርጉትን እያንዳንዱን ምክንያቶች እና የክብደት መቀነስን የሚያደናቅፉትን እያንዳንዱ እንቅፋት መረዳት ይገባል። ይህን ካላደረግን የምንፈልገውን ያክል ክብደት መቀነስና የቀነስነውን ክብደት አስጠብቆ ማቆየት አንችልም።
ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ይዘቶች ወይም ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና የጤና ባለሙያዎን ያማክሩ።
ተጨማሪ ምክር፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት በኢሜል፦ contact@melakutaye.com እና ስልክ፦ +251921720381 ማግኘት ይችላሉ። ለግል ህክምና ዶ/ር መላኩ ወይም የስራ ባልደረቦቹ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ።