ከአርቲፊሻል ስኳር ይልቅ በተፈጥሯዊ ማጣፈጫዎች ላይ እናተኩር

አርቲፊሻል ስኳር ማጣፈጫዎች ብዙውን ጊዜ እንደ ጤናማ አማራጭ ይቆጠራሉ። ሆኖም ግን  ስኳር ፍጆታን ለመቀነስ ቢረዱም ለተሻለ ጤና ዋስትና አይደሉም። የታሰበውን ጥቅም ላይሰጡ እንደሚችሉ አሊያም የጤና ጉዳት ሊያመጡ እንደሚችሉ የሚጠቁሙ በርካታ የምርምር መረጃዎች እየወጡ ነው። አርቲፊሻል ስኳር ማጣፈጫዎች ምንም አይነት ምግብነት ወይም አልሚነት ጥቅም የላቸውም።


አርቲፊሻል ስኳር ማጣፈጫዎችን እያስወገድን የበለጠ ጤናማ በሆኑ ተፈጥሯዊ ማጣፈጫዎች መቀየር በአጠቃላይ ጤና ላይ ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ተፈጥሯዊ ጣፋጮች ጥሩ ጣዕም ብቻ ሳይሆን ሙሉ ምግብነት ስላላቸው ሰውነትን ይመግባሉ። ተፈጥሯዊ ጣፋጭ ምግቦች በቪታሚኖች፣ ማዕድናት፣ አንቲኦክሲደንትስ እና ፋይበር የተሞሉ ናቸው። ጣፋጭ ፍላጎታችን ከማርካት ባሻገር በንጥረ-ምግብ የበለጸጉ ስለሆኑ ለጤና ተስማሚ ናቸው።


አርቲፊሻል ስኳር ከመጠቀም ይልቅ በተፈጥሮ ማጣፈጫዎች ላይ ትኩረት ለማድረግ እንዲያስችለን የሚከተሉትን ጤናማ አማራጮች እነሆ።


‘ከስኳር-ነጻ’ የሚባሉ ጣፋጭ ምግብና መጠጦችን እንፈትሽ

አርቲፊሻል ስኳር ‘ስኳር የሌለው’ ተብለው የሚሸጡ ለስላሳ መጠጦች ወይም ጣፋጭ ሻይ  (sugar free ‘diet’ or ‘light’ ኮካ) ውስጥ ይገኛሉ። ‘ከስኳር-ነጻ’ የሚባሉ ጣፋጭ ምግብና መጠጦች በሙሉ አርቲፊሻል ስኳር የታጨቀባቸው ‘ከስኳር ነጻ ያልሆኑ’ ምግቦች ናቸው። እነዚህን በድብቅ ስኳር የሌለው እየተባሉ የሚሸጡ ምግብና መጠጦችን በመፈተሽ ይለዩዋቸው።


ፍራፍሬዎችን እንደ መክሰስ መጠቀም

ለፈጣን እና ጣፋጭ መክሰስ ፍሬሽ ፍራፍሬ መጠቀም ይቻላል። ፍራፍሬዎች ተፈጥሯዊ ስኳር ስላላቸው ጣእምን ይሰጣሉ፣ ከስኳር ጎን ለጎን በጣም አሪፍ ፋይበር ስለተሞሉ የስኳር መጠንን ይገድባል። የሙሉ ፍራፍሬ ንጥረ ነገሮች አጠቃላይ ጤናን ለመጠበቅ ይረዳል። 

ለምሳሌ፡ ሙዝ፡ በፖታስየም እና ቫይታሚን B6 የበለፀገ ሲሆን የልብ ጤና እና የኢነርጂ ሜታቦሊዝምን ይደግፋል። ቴምር፡- ለሃይል እና ለምግብ መፈጨት ጥሩ የተፈጥሮ የብረት እና የፋይበር ምንጭ ነው።


ተፈጥሯዊ ጣፋጮችን ለማጣፈጫነት መጠቀም

ከዕፅዋት የተቀመሙ ቅመሞች ለሻይ ማጣፈጫ መጠቀም እንችላለን።

ኦርጋኒክ ፍራፍሬዎችን እንደ ማጣፈጫ ይጠቀሙ። ለምሳሌ የተፈጨ ሙዝ ለኦትስ ‘ተፈጥሯዊ’ ማጣፈጫ ማድረግ ይቻላል። እንዲጣፍጥ የፈለግነው ምግብ ላይ በተከተፈ ቤሪ ወይም የተፈጩ ፍራፍሬዎች እንደ ዘቢብ እና ቴምር ይሙሉ።

ለስላሳ መጠጦች ከመጠቀም ይልቅ የተጣራ ኖርማል ውሃን በሎሚ፣ ናና ወይም መሰል ማጣፈጫዎች አጣፍጠን መጎንጨት እንችላለን።


ከአርቲፊሻል ስኳር ማጣፈጫዎች ይልቅ በተፈጥሮአዊ ማጣፋጫዎች ላይ እናተኩር

አብዝቶ አርቲፊሻል ስኳር መጠቀም ሊያመጣቸው የሚችለውን የጤና ችግሮች በመረዳት የተሻሉ አማራጮችን ያድርጉ። ከአርቲፊሻል ስኳር ይልቅ የተፈጥሮ ማጣፈጫዎችን መጠቀም ለጣዕም እና ለጤና የተሻለውን ጣፋጭነት ይሰጣል።


እንደ ፍሬሽ ፍራፍሬ ባሉ ተፈጥሯዊ ጣፋጭ ምግቦች ላይ በማተኮር ብዙ የጤና ጥቅሞችን እያገኙ በጣፋጭ መደሰት ይችላሉ። ተፈጥሯዊ ጣፋጭ ምግቦችን በአመጋገብ ውስጥ በማካተት የጣፋጭ ፍላጎት ማርካት ብቻ ሳይሆን ሰውነታችን በሚያስፈልጋቸው ንጥረ ነገሮች ያንበሸብሹታል።


ማሳሰቢያ፡ ፍራፍሬዎች ጤናማ አማራጭ ቢሆኑም በተለይ የስኳር ህመም ለሚታከሙ ሰዎች አጠቃቀማቸውን መገደብና መመጠን ስኳርን ለመቆጣጠር ቁልፍ ነው።


ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና የጤና ባለሙያዎን ያማክሩ።


ተጨማሪ ምክር፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት በኢሜል፦ contact@melakutaye.com እና ስልክ፦ +251921720381 ማግኘት ይችላሉ። በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ ብሎግ www.melakutaye.com ማንበብ ይችላሉ። ለግል ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top