የአርቲፊሻል ስኳር ጣፋጭነት እና መራራ የጤና ስጋቶች

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የጤና ባለሙያዎች ‘ይሄን እንዳትበላ፣ ያንን እንዳትነካ’ የምግብ ክልከላዎች የምግብ አማራጮችን ወስነው የጣመ እንዳንመገብ እየገዘቱ ዉሃ ዉሃ የሚል ምግብ ብቸኛ ምርጫችን እንዲሆን እያስገደዱን ነው። ምላሳችን የሚቀምሰው ምግብ ሁሉ ጣእም አልባ እየሆነበት ነው። 


ይሄንን ጣእም የራቀው ማእድ ወደለመድነው ጣፋጭነት ለመመለስ እንዱ እማራጭ ካሎሪዎችን ሳይጨምሩ ጣፋጭነትን ማጣጣም የሚያስችሉ የስኳር ምትክ የሆኑ አርቲፊሻል ስኳር መዘውተር ጀምረዋል። አርቲፊሻል ስኳር ማጣፈጫዎች በጣም ተወዳጅነት አግኝተዋል። ስኳር አወሳሰድን ለመቀነስ አንደአማራጭ ገበያውን ሞልተውታል። ‘ከስኳር-ነጻ’ የሚባሉ ጣፋጭ ምግቦች በሙሉ አርቲፊሻል ስኳር የታጨቀባቸው ‘ከስኳር ነጻ’ ምግቦች ናቸው።


እውነት ግን ክብደት ለመቀነስ እና የደም ስኳር ለመቆጣጠር ይረዳሉ? ወይንስ የተደበቀ የጤና ስጋት ያመጣሉ?


አርቴፊሻል ስኳር ምንድን ነው?

አርቲፊሻል ስኳር ሲባል እንደ ስኳር ጣፋጭነት ያላቸው የምግብና መጠጥ ማጣፈጫነት ጥቅም ላይ የሚዉሉ የስኳር ምትክ ናቸው። የካሎሪ መጠናቸው ዜሮ አሊያም እዚህ ግባ የማይባል እጅግ በጣም ዝቅተኛ ስለሆነ ለስኳር ታካሚዎች ስኳርን የሚተኩ ምርቶች ሆነው ያገለግላሉ።


የተለመዱ የአርቲፊሻል ስኳር አይነቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ፤ አስፓርቴም፣ አድቫንቴም፣ ኒዮቴም፣ ሳካሪን፣ ሱክራሎዝ፣ ዛይሊቶል፣ ኢሪትሪቶል፣ ሶርቢቶል ወዘተ ናቸው። ጣፋጭነታቸው ከስኳር እኩል ወይም የበለጠ ሊሆን ይችላል።


አርቲፊሻል ስኳር ለምን ጥቅም ላይ ይውላል?

የስኳር ፍጆታ ለመቀነስ

ከአመጋገብ ልማድ መዛባት ጋር የተያያዙ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስርጭት መስፋፋት ጋር ተያይዞ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የስኳር አወሳሰድ መጠንን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ይመክራል። የስኳር መጠንን ለመቀነስ እንደአንድ አማራጭ ተደርገው የተወሰዱት አርቲፊሻል ስኳር ማጣፈጫዎችን መጠቀም ነው። ውፍረት ወይም ስኳር የሚታከሙ ሰዎች ጣእምን አስጠብቀው ክብደትና ስኳር እንዳይጨምር ለማድረግ ይጠቀሙበታል።


ለምግብ/መጠጥ ማጣፈጫነት

የምግብ አምራቾች የስኳር መጠናቸው አነስተኛ የሆኑ ጣፋጭ ምግቦችን ለማዘጋጀት ይጠቀሙባቸዋል። አሪቲፊሻል ስኳር ‘ስኳር የሌለው’ ተብለው የሚሸጡ ለስላሳ መጠጦች ወይም ጣፋጭ ሻይ  (sugar free ‘diet’ or ‘light’ ኮካ) ውስጥ ይገኛሉ። በተጨማሪም ጣፋጭ ዲዘርት ምግቦች፣ ኬኮች፣ አይስ ክሬም፣ ከረሜላ፣ ማስቲካ እና የጥርስ ሳሙና ወዘተ ባሉ ምርቶች ውስጥ ይገኛሉ። ከአፍ ጣእምነት ማስጠበቅ ያለፈ ምንም አይነት የምግብነት ጥቅም የላቸውም (አልሚነት የላቸውም)።


ለጥርስ ጤና

ብዙ ጊዜ ስኳር የሚያበዙ ሰዎች የጥርስ መቦርቦርና ሽህላ ያስቸግራቸዋል። አሪቲፊሻል ስኳር እንደተለመደው ስኳር ሁሉ ጥርስ ላይ ጉዳት አያመጡም። በተለይም ዛይሊቶል የተባለው አርቲፊሻል ስኳር የአፍ ባክቴሪያዎች ጥርስ ላይ እንዳይጣበቁ ስለሚከላከል ለጥርስ ጤንነት ይረዳል ተብሎ ይታሰባል። ነገር ግን አብዛኛዎቹ ጥናቶች እንዳሳዩት አርቲፊሻል ስኳር መጠቀም ለጥርስ ጤና የሚሰጠው ጥቅም የለም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።


የአርቲፊሻል ስኳር የጤና ጉዳቶች

አርቲፊሻል ስኳር ያለተጨማሪ ካሎሪ ጣዕምን ስለሚያጣፍጡ የስኳር ፍጆታን በመቀነስ ውፍረት እና ተያያዥ በሽታዎችን ለመከላከል ይረዳሉ ተብለው ቢታሰቡም በተቃራኒው የጤና እክል አደጋን ሊጨምሩ እንደሚችሉ አዳዲስ ጥናቶች ይጠቁማሉ።


በዚህ ዙሪያ ያለውን ግርታ ለማጥራት የዓለም ጤና ድርጅት እኤአ በ2019 አጥኚ ኮሚቴ አዋቅሮ ሰፊ ምርምር እንዲሰራ አድርጓል። በዋናነት ትኩረት የተሰጣቸው የጤና መለኪያዎች መካከል ክብደት፣ የሰውነት ስብ መጠን፣ የስኳር ህመም፣ የደም ግፊት፣ የኮሌስትሮል መጠን፣ የልብና ደም ስር ህመሞች፣ የኩላሊት ህመም፣ ካንሰር፣ የምግብ ፍላጎትና ረሃብ ስሜት ወዘተ ናቸው። ይህ የጥናት አማካሪ ቡድን የአርቲፊሻል ስኳር አጠቃቀም በጤና ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ያጠኑ 370 ወሳኝ ምርምሮችን ገምግሞ የሚከተለውን ውጤት ይፋ አድርጓል።


ለክብደት መቀነስ ይረዳሉ የሚለው ወሬ የተረጋገጠ እንዳልሆነ ነው በጥናቶች የታየው። በተለምዶ እንደሚታሰበው እነዚህን አርቲፊሻል ስኳር ጣፋጮችን መጠቀም ክብደትን ለመቀነስ ላይረዳ ይችላል። እንዲያዉም የምግብ ፍላጎታችንን ሊጨምሩ ስለሚችሉ ተጨማሪ ምግብ በመመገብ ክብደታችን ሊጨምር ይችላል።


የልብ ህመም እና የደም ቧንቧ ችግሮች ያመጣሉ። በቅርቡ የወጡ ጥናቶች እንዳሳዩት ከፍተኛ መጠን ያለው አርቲፊሻል ስኳር መጠቀም ለልብ ህመም ብሎም የሞት ስጋት ተዛማጅነት አላቸው።


የሆድ ህመም ሊያመጡ ይችላሉ። በአንዳንድ ሰዎች ላይ እንደ ጋዝ ወይም ተቅማጥ ያሉ የጨጓራና አንጀት ህመም ሊያስከትሉ ይችላሉ። በተጨማሪም ለምግብ መፈጨት፣ በሽታ መከላከልና አጠቃላይ ጤና ጠቃሚ የሆኑ የአንጀት ባክቴሪያዎችን በመጉዳት ስራቸውን ያስተጓጉላሉ። የጠቃሚ የአንጀት ባክቴሪያዎችን ቁጥር እንዲመናመን በማድረግ በሽታ አምጭ ጎጂ ባክቴሪያዎች እንዲነግሱ ያደርጋሉ የሚሉ በርካታ ማረጋገጫዎች በታዋቂ የህክምና መጽሄቶች ላይ እየታተሙ ነው።


በእነዚህና ሌሎችም ምክንያቶች በመመርኮዝ የአለም ጤና ድርጅት ምግብና መጠጥ ማጣፈጫ አርቲፊሻል ስኳሮችን መጠቀም አይመክርም። ከዚህ ባሻገር አርቲፊሻል ስኳሮች ለክብደት ህክምና እንደማይረዱ ብሎም የልብ ህመምን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የረጅም ጊዜ የጤና ችግሮችን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አፅንዖት ሰጥቷል።


አርቲፊሻል ስኳር የሚጠቀሙ ከሆነ ተግባራዊ ማሻሻያዎች እነሆ

  • በድብቅ ስኳር የሌለው እየተባሉ የሚሸጡ ምግብና መጠጦችን በመፈተሽ ይለዩዋቸው።
  • አርቲፊሻል ስኳርን በየዕለቱ መጠቀምን ይቀንሱ። የአጠቃቀም መጠን መገደብ ወሳኝ ነው።
  • ከአርቲፊሻል ስኳር ማጣፈጫዎች ይልቅ በተፈጥሮአዊ ማጣፋጫዎች ላይ እናተኩር።
  • ከዕፅዋት የተቀመሙ ቅመሞች ለሻይ ማጣፈጫ መጠቀም እንችላለን።
  • ኦርጋኒክ ፍራፍሬዎችን እንደ ማጣፈጫ ይጠቀሙ። ለምሳሌ የተፈጨ ሙዝ ለኦትስ ‘ተፈጥሯዊ’ ማጣፈጫ ማድረግ ይቻላል።

ማጠቃለያ

አርቲፊሻል ስኳር ማጣፈጫዎች ብዙውን ጊዜ እንደ ጤናማ አማራጭ ይቆጠራሉ። ሆኖም ግን  ስኳር ፍጆታን ለመቀነስ ቢረዱም ለተሻለ ጤና ዋስትና አይደሉም። የታሰበውን ጥቅም ላይሰጡ እንደሚችሉ አሊያም የጤና ጉዳት ሊያመጡ እንደሚችሉ የሚጠቁሙ በርካታ የምርምር መረጃዎች እየወጡ ነው።


አብዝቶ አርቲፊሻል ስኳር መጠቀም ሊያመጣቸው የሚችለውን የጤና ችግሮች በመረዳት የተሻሉ አማራጮችን ያድርጉ። ከአርቲፊሻል ስኳር ይልቅ የተፈጥሮ ማጣፈጫዎችን መጠቀም ለጣዕም እና ለጤና የተሻለውን ጣፋጭነት ይሰጣል።


ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና የጤና ባለሙያዎን ያማክሩ።


ተጨማሪ ምክር፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት በኢሜል፦ contact@melakutaye.com እና ስልክ፦ +251921720381 ማግኘት ይችላሉ። በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ ብሎግ www.melakutaye.com ማንበብ ይችላሉ። ለግል ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ።

1 thought on “የአርቲፊሻል ስኳር ጣፋጭነት እና መራራ የጤና ስጋቶች”

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top