የአለም የስኳር ህመም ሳምንትን እያከበርንበት ባለበት ሁኔታ ላይ በላንሴት የህክምና መጽሄት ላይ ዛሬ ታትሞ የወጣ አንድ ጥናት በስኳር ህመም ዙሪያ በቸልታ የማይታለፉ አሳሳቢ እውነታዎችን አስነብቧል። ይህ ሰፊ ጥናት ብዙ አስደንጋጭ መረጃዎችን ይዟል። በ200 አገሮች ውስጥ የሚገኙ ከ141 ሚሊዮን በላይ ወካይ ተሳታፊዎችን የሚያካትት ሆኖ ከ1,000 በላይ ጥናቶች የተውጣጡ መረጃዎችን የሚሸፍን ጥልቅ ትንታኔ ስለሆነ እስከዛሬ ከተሰሩ የዳሰሳ ጥናቶች በተሻለ ሁኔታ ስለስኳር ህመም ስርጭትና አዝማሚያዎች አለም አቀፋዊ ምስል ምን እንደሚመስል አሳይቷል።
የዚህ ጥናት ቁልፍ ግኝቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ፤
የስኳር ህመም ስርጭት መጨመር፡ በዚህ ጥልቅ ትንታኔ የያዘ ጥናት መሠረት በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ800 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች (እንቅጩን ለመናገር 828 ሚሊዮን) በስኳር ህመም እንደሚሰቃዩ ያሳያል። በሚያስገርም ሁኔታ ይህ ቁጥር እኤአ በ1990 ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ከአራት እጥፍ በላይ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል። ትናንት ከግማሽ ቢሊዮን አይበልጥም እያልን ስንዘናጋ በጥቂት አመታት ወደ አንድ ቢሊዮን እያሻቀበ ይገኛል።
የስኳር ሕክምና ሽፋን ዝቅተኛ መሆን፡ ከስኳር ስርጭት ባለፈ ይበልጥ አሳሳቢ የሆነው ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ስኳር ያለባቸው ሰዎች በቂና ጥራት ያለው ሕክምና አያገኙም። የህክምና እጦት በሚታይባቸው ሃገራት በስኳር ምክንያት የሚመጣ ልብ ህመም እና የኩላሊት መድከም ጨምሮ ለከባድ ችግሮች ስጋት ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል። ይህ የሕክምና ክፍተት በተለይ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሃገሮች ይብሳል።
የስኳር ህመም ስርጭትና ህክምና ኢፍትሃዊነት፤ በስኳር ህመም ስርጭት እና ህክምና ላይ ጉልህ የሆነ የጂኦግራፊያዊ ልዩነቶች አሉ። ሪፖርቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት በስኳር በሽታ ስርጭት ላይ ከፍተኛ ጭማሪ እያጋጠማቸው መሆኑን አጉልቶ ያሳያል። በቀደሙት ጊዜያት በዋነኛነት የበለጸጉ አገሮችን ብቻ የሚያጠቃ የሃብታሞች በሽታ ተደርጎ ይታይ እንዳልነበር አሁን ግን በሁሉም የገቢ ደረጃ ላይ ያሉ ሃገሮችን እንደወረርሽኝ እየጎዳ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት ሆኗል።
የስኳር ህመም መብዛት ምክንያቶች፡ ይህንን ወረርሽኝ እያባባሱት ናቸው ተብለው የተለዩ በርካታ ተያያዥ ምክንያቶች አሉ። ዋነኛው መንስኤ ከመጠን ያለፈ ውፍረት መጨመር እንደሆነ ተጠቅሷል። ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤዎች የሚያመጡት ከፍተኛ ካሎሪ ያላቸው ምግቦች ፍጆታ መጨመር ለውፍረት እና ለስኳር ህመም መስፋፋት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። በቀላሉ የሚገኙ የተቀነባበሩ ምግቦች እየተዘወተሩ መጥተዋል። ፈጣን የከተማ መስፋፋት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚገድብ ስለሆንም እንዲሁ አንዱ ተጠቃሽ ምክንያት ነው። የስኳር ህመም የመያዝ እድል ከእድሜ ጋር ስለሚጨምር የእድሜ ጣሪያ ከፍ ማለትም ለስኳር ህመም መጨመር አስተዋፅዖ ያደርጋል።
የጉዳዩ አሳሳቢነት፤ የስኳር ህመም ስርጭት በዚህ ፍጥነት መጨመር በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የጤና ጉዳት የሚያመጣ አስቸኳይ ጉዳይ እንደሆነ አመላክቷል። በተለይም የስኳር ህመም ክንድ እየበረታባቸው ላሉ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች የማንቂያ ደወል ሆኖ ያገለግላል ተብሎ ይታሰባል። ጥናቱ አክሎም የጤና ፖሊሲዎች የስኳር ህመምን ለመከላከል የሚረዱ የአኗኗር ዘይቤዎችንና ሌሎችም መከላከያ መፍትሄዎች ለማበረታታት የስኳር ቅድመ ምርመራ፣ የተሻሉ ህክምናዎችና የማህበረሰብ ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች በስፋትና በጥራት መስራትን በአጽንኦት መክሯል።
የስኳር ህመም ስርጭት ለመግታት የግለሰብ ሚና
የስኳርን ህመም መስፋፋት ለመቀነስ በየደረጃው የጋራ እርምጃ መውሰድን ይጠይቃል። እያንዳንዱ ግለሰብ የስኳር ህመምን በመዋጋት ረገድ ወሳኝ ሚና አለው።
መደበኛ የጤና ምርመራዎች በተለይም ለበሽታው ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች አስፈላጊ ነው። ይህም ስኳር ህመምን ስር ሳይሰድ በጊዜ ለመለየት ያስችላል። ጤናማ የአኗኗር ዘይቤዎችን መከተል የስኳር በሽታ ተጋላጭነትን በእጅጉ ይቀንሳል።
ስለስኳር ህመም ትምህርታዊ ግንዛቤን በማህበረሰብ ውስጥ ማሰራጨት ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣል። በማህበረሰባቸው ተሰሚነት ያላቸው ሽማግሌዎች፣ ተጽእኖ ፈጣሪዎች እና የማሀበረሰብ አንቂዎች ጤናማ የአኗኗር ዘይቤዎችን የሚያበረታቱ ትምህርታዊ ዝግጅቶችን በማዘጋጀት እነዚህን ጥረቶች ማጠናከር ይችላሉ። በተለይም ማህበራዊ ሚዲያን ለጤና መሻሻል እንዲያግዝ ጤናን የሚያበለጽጉ ባህሪያትን ለማስተዋወቅ እና ስለስኳር ህመም ትክክለኛ መረጃን ለማካፈል ይረዳል።
የስኳር ህመምን ስርጭት ለመግታት የሚረዱ ቁልፍ የፖሊሲ ምክሮች፡
በመጀመሪያ የስኳር ቅድመ ምርመራ ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ለስኳር ህክምና ከሚወጣው ወጪ ጋር ሲወዳደር ቅድመ ምርመራ ማድረግ በጣም አዋጭና ወጪ ቆጣቢ ዘዴ ነው። በተለይም ከፍተኛ ተጋላጭነት ባላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ አተኩሮ በጊዜው ምርመራ እንዲያደርጉ የሚያበረታታ ስራ በጤና ጣቢያና ጤና ኬላ ደረጃ መሰራት አለበት።
በተጨማሪም የስኳር ህመም ተያያዥ የሆኑ የጤና ጠንቆችን የሚቀንሱ ጥራት ያላቸው መድሃኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ማድረግ ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ ነው። ለዚህም የስኳር ህክምና ወደታችኛው የጤና ተቋማት እንዲወርድ በማድረግ ለሁሉም ማህበረሰብ እንዲዳረስ መደረግ አለበት።
የስኳር ህመም ዙሪያ የሚሰጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች በስፋትና በጥራት መስጠት ይመከራል። በተቀናጀና በተደራጀ የጤና ትምህርት የስኳር ህመም አስቀድሞ ለመከላከል የሚረዱ የአመጋገብ ማሻሻል፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተርን አስፈላጊነት ላይ መስራት ይጠቅማል። እንዲህ አይነት የጤና ትምህርቶች የማህበረሰቡን ባህልና አኗኗር ልማድ ያማከሉ መሆን አለባቸው።
በስኳር ህመም ዙሪያ የሚሰሩ ጥናትና ምርምሮችን መደገፍ ለነገ የማይባል ኢንቨስትመንት ነው። እጃችን ላይ ያለውን ያለንን የጤና መረጃ በመመርመር ወደትክክለኛ ውሳኔ እንዲመራን ለስኳር ምርምር የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። በመረጃ የተደገፈ ስልታዊ መከላከል ዘመቻ ለማድረግ ያስችላል።
ብሄራዊ ፖሊሲዎች ጤናማ አመጋገብን፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን እና ሌሎች ጤናማ ልማዶችን ለማዳበር የሚያበረታቱ መሆን አለባቸው። ጤናማ አኗኗር ዘይቤን ለማበረታታት ጤናማ ያልሆኑ ምግቦች አቅርቦት መቆጣጠር እና መቅረጥ ይገባል።
ማጠቃለያ
ይህ አዲስ የጥናት ውጤት የስኳር ህመም አስቸኳይ ንቅናቄ መፍጠር እና የተጠና እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ አጉልቶ ያሳያል።
የአለም የስኳር ህመም ሳምንትን ስናከብር የስኳር ህመም ዓለም አቀፍ ፈተና መሆኑን ተረድተን ግንዛቤን ወደ ተግባር ለመቀየር እንስራ። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ወረርሽኝ የተቀናጀ ምላሽ በመስጠት ለመግታት እንሞክር።
ይህንን ዓለም አቀፍ የጤና ፈተና ለመቅረፍ ከግለሰቦች፣ ከጤና ባለሙያዎች እና ፖሊሲ አውጪዎች የተቀናጀ ጥረት ይጠይቃል። ጤና ላይ በመረባረብ ጤናማ ሃገርን ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ እንችላለን። አስቀድሞ መከላከልን በግለሰብ ደረጃ ቅድሚያ በመስጠት፣ የጤና ማሻሻያ ህግና ፖሊሲዎችን በመደገፍ እና አስፈላጊዉን ግብአት በማሟላት እየጨመረ የመጣውን የስኳር ህመም በጋራ መዋጋት እንችላለን።
ይህ የስኳርን እንግታ ጥሪ የጤናው ሴክተር ጉዳይ ብቻ አይደለም። ከሊቅ እስከ ደቂቅ ለሁሉም የቀረበ የአብረን ታግለን እንጣለው ጥሪ ነው።
ዋቢ
Zhou, Bin et al. Worldwide trends in diabetes prevalence and treatment from 1990 to 2022: a pooled analysis of 1108 population-representative studies with 141 million participants. NCD Risk Factor Collaboration (NCD-RisC). Lancet, 2024.
ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና የጤና ባለሙያዎን ያማክሩ።
ተጨማሪ ምክር፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት በኢሜል፦ contact@melakutaye.com እና ስልክ፦ +251921720381 ማግኘት ይችላሉ። በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ ብሎግ www.melakutaye.com ማንበብ ይችላሉ። ለግል ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ።