ህዳር 5 የአለም የስኳር ህመም ቀን፡ ምሉእ ደህንነትን ያስቀደመ የስኳር ህክምና እንክብካቤ

በዶ/ር መላኩ ታዬ (በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳርና ሆርሞን ህክምና ስፔሻሊስት)


‘የስኳር ህመም አለብህ/ሽ’ መባል በብዙዎች ልብ ውስጥ አስፈሪ ስሜት የሚፈጥር ሲሆን በአለም አቀፍ ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ያለ ተላላፊ ያልሆነ በሽታ ነው። በተለይም የዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች የስኳር ህመም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል። በሃገራችን ኢትዮጵያ የተሰሩ ጥናቶች የሚያረጋግጡት ቁጥራቸው ላቅ ያለ የስኳር ህመም ተጠቂዎች እንዳሉ ነው። በተለይም የጤና ሚኒስቴር ከጥቂት አመታት በፊት ያስጠናው አገር አቀፍ የዳሰሳ ጥናት ከ3.2 በመቶ በላይ ኢትዮጵያዊያን የስኳር ህመም እንዳለባቸው አሳይቷል። የአለም የስኳር ፌደሬሽን በ2021 ባወጣው የኢትዮጵያ ግምታዊ ሪፖርቱም ከ1.9 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን የስኳር ህመም ተጠቂ እንደሆኑ ሲገልጽ ወደ 30 ሺህ ኢትዮጵያዊያን በስኳር ምክንያት ይሞታሉ። ይህም ማለት በእያንዳንዷ ደቂቃ ሶስት ኢትዮጵያዊያን ህይወታቸውን በስኳር ምክንያት ይነጠቃሉ።


የስኳር ህመም በጊዜ በቂ ህክምና ካልተደረገ ለበርካታ የጤና ጠንቆች ይዳርጋል። ሆኖም ግን ከአመት አመት የተሻለ ህክምና እየተገኘለት ስለሆነ የስኳር ህመም በተገቢው መንገድ ከታከመ ታካሚው እንደማንኛውም ሰው ለጅም እድሜ መኖር፣ ጤናማና አምራች ህይወት መኖር ይቻላል።


እኤአ በ1921 ኢንሱሊን የተባለውን የስኳር መድሃኒት ያገኙትን ካናዳዊውን ዶ/ር ፍሬድሪክ ባንቲንግ (1891 – 1941) የልደት ቀን ለማዘከር ህዳር 5 ቀን የስኳር ቀን ሆኖ ይከብራል። ህይወት አድን የሆነውን ኢንሱሊን ከሙያ አጋሮቹ ጋር በመሆን በካናዳው የቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ ላቦራቶሪ ውስጥ በማግኘቱ እኤአ በ1923 በህክምና ዘርፍ የኖቤል ሽልማት (ከስኮትላንዳዊው የፊዚዮሎጂ ባለሙያ ጆን ማክሊውድ ጋር በጋራ) ተሸልሟል። ዶ/ር ባንቲንግ ከትንሽዬ የገጠር መንደር የተገኘ ሲሆን አብዛኛውን የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈው በእርሻ እና ከብቶች ማገድ ህይወት ነው። ከዚህ ተነስቶ ነው ለስኳር ህክምና ፈር ቀዳጅ ፈጠራ የሰራው፤ በዚህም ገና በ32 አመት እድሜው ለሰው ዘር በሙሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱት የተመረጡ ምርጦች የሚሰጠውን የኖቤል ሽልማት ማሳካት የቻለው። በአውሮፕላን አደጋ በ49 አመቱ ከዚህ አለም ድካም እስካረፈበት ጊዜ በርካታ የስኳር ህክምና ታሪክ ውስጥ ማርሽ ቀያሪ የሆኑ ስራዎችን አበርክቷል።


የአለም አቀፍ የስኳር ህመም ፌደሬሽን (IDF) እና የአለም ጤና ድርጅት (WHO) በአለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን የስኳር ህመም ለመግታት በማሰብ እኤአ ከ1991 ጀምሮ በዶ/ር ባንቲንግ የልደት ቀን ህዳር 5 (November 14) በየአመቱ የአለም የስኳር ህመም ቀን ይከበራል። እኤአ በ2006 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአዋጅ 61/225 ውሳኔ በማፅደቅ ኦፊሻል ቀን ሆኗል። ዋና አላማዉም በስኳር ህመም ዙሪያ ዓለም አቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻ ማካሄድ ነው። ይህን ቀን ማክበር የስኳር ህመም የሁላችንንም ትኩረት የሚሻ አሳሳቢ አለም አቀፍ የማህበረሰብ ጤና ጉዳይ መሆኑን ግንዛቤ ለማሳደግ እና የበሽታውን መከላከል ፣ ምርመራ እና ህክምና ለማሻሻል የሚያስፈልጉትን የጋራ እርምጃዎችን ለማጉላት እድል ይሰጣል።


የዚህ አመት የአለም የስኳር ህመም ቀን ዋና መሪ ቃል ችላ የተባለው የህክምና ገጽታ ነው – የስኳር ህመም እና ደህና መሆን (Diabetes and Well-being)። ግለሰቡን ያማከለ የተሟላ ደህንነት የሚያመጣ የስኳር ህክምና (Holistic Diabetes Care) ማረጋገጥ ለስኳር ታካሚዎች የተሻለ ህይወት ለመምራት ወሳኝ እንደሆነ ለማጠየቅ ነው።


የአለም አቀፍ የስኳር ህመም ፌዴሬሽን (IDF) አጉልቶ እንዳስቀመጠው የስኳር ታካሚዎች የህክምናው ጫና በአእምሯዊም ሆነ በአካላዊ ጤንነታቸው ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ውስጥ ይወድቃሉ። የስኳር ህመም ላለባቸው ከግማሽ ቢሊዮን በላይ የሚቆጠሩ ሰዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ትግል ሊሆን ይችላል። በእያንዳንዱ ቀን ስለምትበሉት ነገር ሁሉ ማሰብ፣ እያንዳንዱ የእለት ከእለት እንቅስቃሴ ውስጥ በጣም ጥንቁቅ መሆን፣ ስኳር ለመለካት ደጋግሞ መርፌ መወጋት፣ መድሃኒት መውሰድ ወዘተ ከተለመደው የህይወት ዉጣ ውረድ ጋር ተደምሮ ቀላል ሃላፊነት አይደለም።


የስኳር ህመም ያለባቸው ሰዎች ህይወት አካላዊ እና አእምሮአዊ ጤናቸው ላይ የማይናቅ ተጽእኖ ቢኖረውም ቅሉ የስኳር ህክምና እንክብካቤ ትኩረቱ ብዙውን ጊዜ የደም ስኳር ማስተካከል ላይ ብቻ ነው። የተለመደው የስኳር ህመም እንክብካቤ በስኳር ግቦች ላይ አፅንዖት ይሰጣል። ለበርካቶች የስኳር ህክምና እንክብካቤ ሲባል ስኳርን መለካትና ቁጥር ማስተካከል ብቻ ይመስላቸዋል።


የዛሬው የአለም የስኳር ህመም ቀን ዘመቻም ይህን ምሉእ ያልሆነ የህክምና አሰጣጥ ልማድ ለማስተካከል ዛሬዉኑ ለውጥ እንጀምር የሚል ነው። በስኳር ህክምና ስንሰጥ ከስኳር ቁጥር ባሻገር የተሟላ ደህንነትን ቅድሚያ እንስጥ የሚል ተራማጅ የለውጥ ንቅናቄ ይዟል።


አጠቃላይ ደህንነት ማረጋገጥ ከስኳር ቁጥሮች በላይ ነው። እውነተኛ የጤና ስኬት የሚመጣው ሁሉን አቀፍ የደህንነትና ጤንነት ጉዳዮች ቅድሚያ ሲሰጣቸው ነው። ማለቂያ የሌለው የደም ስኳር ምርመራ ቁጥሮች በላይ ደህንነት ላይ ማተኮር ይገባል። የስኳር ቁጥርን ለመቆጣጠር ከሚደረግ ግብግብ ይልቅ ደህንነትን ያማከለ የህክምና አካሄድ የስኳር ህመም ያለበትን ግለሰብ ህይወት የበለጠ ደስተኛ ያደርገዋል።


ስለሆነም ዋናው የስኳር ህክምና ለታካሚው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ መስጠት፣ ጫናን መቀነስ እና በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ደስተኛ መሆን ማስቻል ነው። የስኳር ህክምና የስኳር መጠን ከመከታተል ባሻገር አእምሯዊ፣ አካላዊ እና የስሜትን ደህናነት የሚያካትት የተሟላ ጤንነት ስለማግኘት ነው። የአእምሮ ጤናን፣ የአኗኗር ዘይቤዎችን እና የህብረተሰቡን ድጋፍ ከስኳር ህክምና ጋር በማቀናጀት ታካሚዎች ደስተኛ ህይወት እንዲኖሩ ማገዝ ዋና የህክምና ትኩረት መሆን አለበት።


ደህንነት (wellness) ሲባል አካላዊ፣ አእምሮአዊ እና ማህበራዊ ጤንነትን ያጠቃልላል። ይህን ማድረግ የስኳር ህክምና ውጤቶችን ያሻሽላል። ከስኳር ህመም ጋር የተሟላ ደስተኛ ህይወት ለመኖር አስፈላጊ ነው። የተሟላ ደህንነትን ለማምጣት የስኳር ህክምና የደም ስኳርን መጠን ከመቆጣጠር የበለጠ ዘርፈ ብዙ ስራ ይፈልጋል። ከግሉኮስ ቁጥጥር በላይ የሆነ የተሟላ ደህንነት የሚያረጋግጥ የስኳር ህክምና እንክብካቤን እውን ለማድረግ የሚከተሉትን ቁልፍ ነገሮችን ያካትታል።


ለተሟላ ደስተኛ ህይወት ወሳኝ ቁምነገር ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ ልማዶች ናቸው። ትናንሽ ለውጦች በደህንነት ላይ በጎ ተጽእኖ ያሳድራሉ። የአኗኗር ማስተካከያ ያድርጉ የሚል ምክር ሲሰጠን የተከለከልን፣ የተገዘትን፣ የተገደብን አይነት አሉታዊ ትርጉም ከምንሰጥ ይልቅ ለበለጠ ጤና አወንታዊ እርምጃዎችን አንደመውሰድ ማሰብ ይጠቅማል። ትናንሽ  የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች ትልቅ ትሩፋቶች ያስገኛሉ። የአመጋገብ ወይም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ በጣም ከባድና አሰልቺ መሆን አያስፈልገውም። ለመተግበር የሚቀል በቀላል ልማድ ይጀምሩ። የስኳር ህክምና የረዥም ጊዜ ጉዞ  እንጅ የአንድ ሳምንት ሩጫ ስላልሆነ በትንሹ ጀምሮ ቀስ በቀስ እያሻሻሉ የሚሄዱ የአኗኗር ለውጦችን በማድረግ ወደ ጤናማ፣ ደስተኛ እና አምራች ህይወት በጽናት መቀጠል ነው። ለስኳር ቁጥጥር ብቻ ሳይሆን ለመደበኛ ህይወታችን ደስታ የምንወደውን አመጋገብና እንቅስቃሴ ማድረግ የተሻለ አዋጭ ነው።


አይበገሬ የመቋቋም ችሎታ በማዳበር ከስኳር ህመም ጋር የተያያዙ በእለት ተዕለት የህክምና ጫናዎችን እና የስኳር ችግሮችን ፍራቻ ሊያመጣ የሚችለውን ጭንቀት ተቋቁሞ በጽናት ጤናንን መንከባከብና ማሻሻል ይገባል። አስፈላጊውን ድጋፍና ሙያዊ ምክሮች ከባለሙያ በማግኘት ከስኳር ህክምና ጋር የሚመጡ ተግዳሮቶችን እንዲጋፈጡ ያስችላል።


ፍፁምነትን ለማምጣት እስኪሰለች ከመታገል ትናንሽ መውደቆች ሲከሰቱ ለራስ ደግ በመሆን የበለጠ ለማሻሻል መስራት ይመከራል። በየግሉኮስ መለኪያ ግሉኮሜትር ላይ ባለው እያንዳንዱ የስኳር ቁጥር በጣም ከመጨነቅ እና  ከፍ ያሉ ቁጥሮችን እንደ ስህተት ከማየት ይልቅ የበለጠ የተሻለ አመጋገብና ስፖርት ለማስተካከል እንደ ጠቋሚ መረጃ ማየት መጀመር ይበጃል። ነገሮች ሳይስተካከሉ ሲቀሩ እንኳን እራስዎን በደግነት ለራስ ገር መሆን እና ርህራሄ ማድረግም ይገባል። “ዛሬ አልተሳካልኝም” ከማለት “ዛሬ የቻልኩትን ሁሉ አድርጌያለሁ” ብሎ ለቀጣይ ማቀድና የበለጠ መበርታት ይፈልጋል። ትንንሽ ድሎችን ማድነቅ፣ ከዚያ የበለጠ ማሻሻል ብሎም በዘላቂነት ማጽናት ወደ ትልቅ የጤና ለውጦች ያመራል።


ከመሰል ቡድኖች ወይም ከእኩዮች ጋር በመገናኘት የጋራ ልምዶችን መጋራትና ድጋፍ ማግኘት በደንብ ይረዳል። ሌሎች ሞክረው የሰራላቸውን ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ እና የችግር መቋቋሚያ ስልቶችን ለመማር አስተማማኝ የትምህርት ቦታ ይሰጣል። የቤተሰብ፣ ጓደኞች እና ወዳጆች ሁሉ ለጤናችን በጎ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። በዙሪያችን ያለ ሰው ሁሉ እንዲተባበር ማሳተፍ ይጠቅማል። ጭንቀትን ለመቆጣጠር፣ ተነሳሽነትን ለመጨመር እና የህክምና ግቦችን ለማሳካት ትልቅ አቅም ይፈጥራል።


የጤና ባለሙያ ድጋፍ ማግኘትም እንዲሁ ለተሻለ ጤና መሰረት ነው። ስለሚያጋጥሙዎት ተግዳሮቶችን ለጤና ባለሙያ ያሳውቁ። ብዙውን ጊዜ የዕለት ተዕለት ህክና ሸክም የሚያቃልሉ ምክረ ሃሳቦችን በቀላሉ ሊያገኙ ሊያቀርቡ ይችላሉ።


የአእምሮ ጤናን ችግሮችን መለየትና በተገቢው ማከም ሌላኛው ትኩረት የሚሻ የህክምና አካል ነው። የስኳር ህመምና የአእምሮ ጤና ችግሮች የማይነጣጠሉ ናቸው። የብቸኝነት ስሜትና አብዝቶ ጭንቀት በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ሊያባብሰው ይችላል። በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን መለዋወጥም እንዲሁ የስሜት ለውጦችን ያመጣል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት የስኳር ህመም ያለባቸው ሰዎች የአእምሮ ጤና ድጋፍ ሲያገኙ የስኳር ቁጥጥራቸው ደረጃ ይሻሻላል። ይህ ማለት የአእምሮ ጤናን በመደበኛ የስኳር ህክምና እንክብካቤ አካል አድርጎ ማካተት ያለውን ጠቀሜታ ያጎላል። ለዚህም ነው ለስኳር ታካሚዎች የአእምሮ ጤናን ትኩረት መስጠት አስፈላጊ የሚሆነው። የአእምሮ ጤና መሻሻል ለስኳር ህመም እንክብካቤ ወሳኝ አካል ነው።


የማጠቃለያ ምክረ ሃሳብ፤ የስኳር ህክምና እንክብካቤ ስንሰጥ የተሟላ ደህንነትን ያረጋገጠ ይሁን!


በስኳር ህክምና ውስጥ የተሟላ ደህንነትን ማምጣት ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው። በዘንድሮው የአለም የስኳር ህመም ቀንም ሁሉን አቀፍ ደህንነት በተጨባጭ የታካሚው ህይወት ላይ ለውጥ እንዲያመጣ የስኳር ህክምናን አሰጣጥን እንደገና እናድስ። የስኳር ቁጥርን ከማስተካከል ባሻገር ታካሚውን ያማከለ እና መላ ደህነት ላይ ያተኮረ ህክምና ተደራሽ በማድረግ የስኳር ታካሚዎች ደስተኛና አምራች ሆነው ለረጅም እድሜ ጤናማ ህይወት እንዲመሩ ማስቻል ይቻላል። የአለም ስኳር ፌደሬሽን አጽንዖት እንደሰጠው ‘ከስኳር ህመም ጋር በጤና ለመኖር አጠቃላይ ደህንነትና ማረጋገጥ የህክምናው የማዕዘን ድንጋይ ነው’።


በዚህ የአለም የስኳር ህመም ቀን ከስኳር ህመም ጋር ብቻ ሳይሆን በደስታ ህይወትን በመኖር ላይ እናተኩር።


ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና የጤና ባለሙያዎን ያማክሩ።


ተጨማሪ ምክር፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት በኢሜል፦ contact@melakutaye.com እና ስልክ፦ +251921720381 ማግኘት ይችላሉ። በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ገጾችና በዶ/ር መላኩ ብሎግ www.melakutaye.com ማንበብ ይችላሉ። ለግል ህክምና ዶ/ር መላኩ ወይም የስራ ባልደረቦቹ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top