የአይነት አንድ ስኳር ህክምና አሁናዊ መመሪያዎችና ተስፋ ሰጪ ምርምር ዉጤቶች

የአይነት 1 ስኳር ህመም (type 1 diabetes) ያለበት ልጅ ያላቸው ወላጆች ለልጃቸው ህክምና ተስፋ የሚሰጥ ዜና መፈለግ ያለ ነው። ወላጆች የልጃቸው ህይወት ከኢንሱሊን መርፌ ነፃ እንዲሆን መመኘታቸው ተፈጥሯዊ ነው። ግን በሚያሳዝን ሁኔታ እነዚህ መሬት ያልያዙ ተስፋዎች አሳሳች ሊሆኑ ይችላሉ። አንዳንዴም አደገኛ የሆኑ አሳች ዜናዎች የልጅን ህይወት ሊቀጥፉ ይችላሉ።


በዚህ ሳምንት በቲክቶክና ሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች በጣም ሲታይ የነበረ አንድ መረጃ ነበር። ዜናው ‘የአይነት አንድ የስኳር ህመም ስርየት ተገኘለት፣ ከእንግዲህ ኢንሱሊን መርፌ መወጋት እስከወዲያኛው አከተመ እልልልልል አንኳን ደስ አላችሁ’ የሚል ይዘት ያለው የሚያጓጓ ብስራት የያዘ አሳሳች መረጃ ነው። ይህን መረጃ የሰሙ ወላጆች የስኳር ህመም ያለባቸው ልጆቻቸውን ይዘው እኔ ወደምሰራበት የግል ሆስፒታል ጨምሮ ሌሎችም ተቋማት ለልጄ ይሄን ፈዋሽ ህክምና አዝዙልን አሊያም ወደውጭ ሪፈር አርጉን እያሉ ሲጨነቁ ነበር። 


ከጥቂት አመታት በፊትም አንድ እናት ልጇን ለቆሽት ንቅለ ተከላ ወደ ዉጭ ሪፈር ለማስደረግ ሃኪሞች አዝነው ቦርድ ይጽፉልኛል፣ ይተባበሩኛል ብላ በማሰብ የልጇን ኢንሱሊን እንዳይወጋ እየከለከለች የልጇን ህይወት በተደጋጋሚ አደጋ ላይ ስትጥል እንደነበር ትዝ ይለኛል። አሁንም ቅድምም በሚናፈሱ ለታይታ የሚሰራጩ አሉባልታዎች በመታለል ኢንሱሊን ህክምናቸውን በማቋረጥ የሚሞቱትን ወገኖቻችንማ ቤት ይቁጠረው።


ይህ ጽሑፍ ሕይወት አድን የሆነውን የኢንሱሊን ሕክምናን አስፈላጊነት በማጉላት አሁን ያሉ የአይነት 1 ስኳር ህክምና እውነታ፣ ወቅታዊ ተስፋ ሰጭ ግኝቶችና ቀጣይ የምርምር አቅጣጫዎችን ግልጽ ለማድረግ ያለመ ነው።


የዓይነት 1 የስኳር ህመም ምንድን ነው?

አይነት 1 የስኳር ህመም በአብዛኛው በልጆችና በጎልማሶች ላይ የሚከሰት ሲሆን ሆድ ውስጥ የሚገኘው ቆሽት (pancreas) መሉ በሙሉ ኢንሱሊንን ማምረት ሲያቆም የሚመጣ ነው። መንስኤውም የራሳችን ሰውነት በሽታ አምጭ ተዋህሲያንን እና ባእድ ነገሮችን ለመከላከል የሚያመነጫቸው ጸረ-ባእድ ንጥረ ነገሮች (antibodies) በቆሽት ውስጥ ኢንሱሊን የሚያመነጩ ቤታ ሴሎችን (beta cells) በስህተት ሲያጠቃ (autoimmune disease) ነው። ይህ የስኳር ህመም አይነት በዘላቂነት በኢንሱሊን መድሃኒት መታከም ይኖርበታል።


የዓይነት 1 የስኳር ህመም ሶስት ደረጃዎች አሉት። እነዚህን ደረጃዎች ማወቅ ስለበሽታው በተሻለ ሁኔታ እንድንረዳ፣ ተጋላጭ ግለሰቦችን እንዲለዩ እና በሽታን ለማዘግየት ወይም ለመከላከል ሊሆኑ የሚችሉ ህክምናዎችን ለመዘየድ ይረዳል።


ደረጃ 1፡ ምንም አይነት የስኳር ህመም ምልክቶች የሉትም።  ይህ ደረጃ ዋና መገለጫው ከስኳር ህመም ጋር የተገናኙ ጸረ-ባእድ ኬሚካሎች (Autoantibodies) በደማቸው ውስጥ ይታያሉ። የእነዚህ አንቲቦዲዎች መታዬት ስለወደፊቱ የስኳር ህመም ሊከሰት እንደሚችል ጠንካራ ትንበያ ይሰጣሉ። በዚህ ደረጃ በደም ውስጥ ያለው የግሉኮስ መጠን በተለመደው ክልል ውስጥ ነው። ምክንያቱም ቆሽቱ ላይ መቆጣት ቢኖርም በቂ ቤታ ሴሎች አሁንም አስፈላጊ ኢንሱሊን ማምረት ይችላሉ። ምንም አይነት የስኳር ህመም ምልክቶች ስለማይታይ ይህ ደረጃ ሊገኝ የሚችለው ጸረ-ባእድ ኬሚካሎች (Autoantibodies) በደም ምርመራ በማጣራት ብቻ ነው። እንዲህ አይነት ምርመራ የሚታዘዘው በቤተሰብ የአይነት አንድ ስኳር ህመም ታሪክ ላላቸው ከፍተኛ ተጋላጭነት ያላቸው ግለሰቦች ላይ ብቻ ነው።


ደረጃ 2፡ በዚህ ደረጃ ከላይ የጠቀስናቸው በርካታ የስኳር ህመም የሚያመጡ ጸረ-ባእድ ኬሚካሎች (Autoantibodies) በደም ውስጥ መመረት ይቀጥላሉ። እነዚህ አንቲቦዲዎች መኖር በቤታ ህዋሶች ላይ ቀጣይነት ያለው ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ያሳያል። አሁን የደም ግሉኮስ መጠን መለዋወጥ እና ያልተለመደ የደም ስኳር መጠን ማሳየት ይጀምራል። ቅድመ-ስኳር ደረጃ ሊባል ይችላል። ይህም ቆሽት መደበኛውን የግሉኮስ ቁጥጥር ለማስጠበቅ እየታገለ ቢሆንም የቤታ ህዋሳት ሥራ እየተዳከመ መምጣቱን ይጠቁማል። ሆኖም ግለሰቡ ምንም ምልክት አይታይበትም። በዚህ ደረጃ ላይ ያሉ ግለሰቦችን ወደ ለየለት ስኳር እንዳይባባስ የሚረዱ የመከላከል ወይም ማዘግየት ህክምናዎች እንዳሉ በጥናቶች ተረጋግጠዋል።


ደረጃ 3፡ ይህ ደረጃ የስኳር ህመም ምልክቶች የሚያሳይና በስኳር ምርመራ የሚገኝ ነው። ከፍተኛ ቁጥር ያለው የቤታ ህዋስ ወድሟል ማለት ነው።  ቆሽት ከዚህ በኋላ በቂ ኢንሱሊን ማምረት ስለማይችል መደበኛውን የደም ግሉኮስ መጠን ለመጠበቅ አይችልም። በዚህ ደረጃ የተለመዱ የዓይነት አንድ የስኳር ህመም ምልክቶች መታየት ይጀምራሉ። ለአብነትም የሽንት መብዛት፣ የማይረካ ከፍተኛ የውሃ ጥማትና ረሃብ ስሜት እንዲሁም ክብደት መቀነስ ያካትታል። ሲብስም አሲድ ደም ውስጥ በመጠራቀም (diabetic ketoacidosis) ለህይወት አስጊ ደረጃ ይደርሳል። በዚህ ደረጃ በኢንሱሊን መታከም ግድ ነው።


እነዚህን ደረጃዎች ማወቅ በተለይም በደረጃ 1 እና 2 ያሉ ግለሰቦችን መለየት የቅድመ መከላከል ስራ ለመስራት አስፈላጊ ነው። ሙሉ በሙሉ መከላከል ባይቻል እንኳ ወደ ደረጃ 3 የሚደርሱበትን ሂደት ሊያዘገዩ የሚችሉ ህክምናዎች እድል ይሰጣል። ለምሳሌ ቴፕሊዙማብ (teplizumab) የተባለ መድሃኒት በአሁኑ ጊዜ የስኳር ህመም የሚያዘገይ ሆኖ እየተሰጠ ነው።


የኢንሱሊን ሕክምና ወሳኝ ሚና

ኢንሱሊን ለአይነት 1 የስኳር ሕክምና የማዕዘን ድንጋይ ነው። ኢንሱሊን እንደዉሃና ኦክስጅን ሁሉ ለሜታቦሊዝም መሳለጥ፣ ለጤናማ እድገትና ሰውነት ግንባታ አስፈልጊ የሆነ ለህልውና ወሳኝ ሆርሞን ነው። ስለሆነም ይህ ችግር ያለባቸው ግለሰቦች ኢንሱሊንን በተፈጥሮ ማመንጨት ስለማይችሉ መደበኛ የኢንሱሊን መርፌ ወይም የኢንሱሊን ፓምፕ መጠቀም ያስፈልጋቸዋል። የኢንሱሊን ሕክምናን ማቆም በጥቂት ቀናት ለሕይወት አስጊ ይሆናል።


የዓይነት 1 የስኳር ሕክምና አሁናዊ መመሪያዎች ምን ይላሉ?

የቅርብ ጊዜ የተሻሻሉ የአይነት አንድ ስኳር ህክምና አለም አቀፍ መመሪያዎች እንደሚደነግጉት ኢንሱሊን ውጤታማና አይተኬ አማራጭ ነው። የተሻለ የግሉኮስ ቁጥጥር ለማምጣት እና የስኳር ህመም ተያያዥ የጤና ችግሮችን ለመከላከል አይነተኛ መፍትሄ ኢንሱሊን ነው።


ኢንሱሊን በየቀኑ በሚወጋ መርፌ ወይም የኢንሱሊን ፓምፖች ሊሰጥ ይችላል። በተለይ አሁን አሁን የተራቀቁ ስማርት የኢንሱሊን ፓምፖች ኢንሱሊንን ከምግብና የስኳር መጠን ጋር አመጣጥነው ስለሚሰጡ የስኳር ህክምናን በሃይለኛው አሻሻለዋል። አውቶሜትድ የሆኑ የኢንሱሊን ፓምፕ ቴክኖሎጂ የስኳር መጠንን በእያንዳንዷ ቅጽበት ያለማቋረጥ እየለካ የሚያስለገውን ኢንሱሊን መጠን የሚያስተካክልና የሚወስን ስልተ-ቀመር አልጎሪዝም አለው። የደም ውስጥ ያለውን አሁናዊ የስኳር መጠን ላይ ተመስርቶ የተመጣጠነ ኢንሱሊን ይሰጣል።


ከኢንሱሊን ህክምና ጎን ለጎን በየለቱ የግሉኮስ ክትትል ማድረግ ይመከራል። በየቀኑ በተደጋጋሚ በመደበኛነት ግሉኮስ ከምግብ በፊትና በኋላ መለካት ያስፈልጋል። ከተለመደው አልፎ አልፎ ጣትን በመውጋት ከሚደረገው ስኳር ክትትል ባለፈ ዘመናዊ የሆነ ክንድ ላይ የሚለጠፍ የደም ግሉኮስን ያለማቋረጥ በየደቂቃው ለመከታተል የሚያገለግል መሳሪያ አለ። ይህ የማያቋርጥ የግሉኮስ ክትትል (continuous glucose monitors, CGMs) በመባል ይታወቃል። ይህ አዲስ የግሉኮስ ክትትል ዘዴ ተወዳጅነት እያገኘ መጥቷል። አንድም የደም ውስጥ የግሉኮስ መጠንን በየሴኮንዱና ደቂቃው ያለማቋረጥ ማወቅ ያስችላል፤ እንዲሁም የግሉኮስ መጠን ወደላይ ከፍ እያለ ወይም ወደታች ዝቅ እያለ እንደሆነ አካሄዱን ያሳያል፤ በተጨማሪም ጣትን ደጋግሞ ከመውጋትን ይልቅ የበለጠ ምቹ ነው። የስኳሩን አሁናዊ ልኬት በየደቂቃው (real time glucose levels) ያሳያል።


ከኢንሱሊን በተጨማሪ የሚታዘዙ አንዳንድ በመርፌ ወይም በሚዋጥ የሚሰጡ አጋዥ መድሃኒቶች አልፎ አልፎ በተለይም ለክብደት ህክምና ወይም ለሌላ ምክንያት ጥቅም ላይ ሊዉሉ ቢችሉም ኢንሱሊንን አይተኩም።


በአይነት 1 የስኳር ህክምና ላይ የሚታዩ ያልተሟሉ ጉድለቶች (unmet needs) ምንድን ናቸው?

ዘመኑ የደረሰበት የተሻሻለው የኢንሱሊን ሕክምና እና ክትትል ጥበብ የህመሙ ተጠቂዎችን ጤናና ህይወት በእጅጉ ያሻሻለና ረጅም፣ አምራችና ደስተኛ ህይወት መምራትን ያስቻለ ቢሆንም አሁን ያለው ሕክምና ተግዳሮቶች አለው። ብዙ መስተካካልና የበለጠ መሻሻል ያለባቸው ያልተሟሉ ፍላጎቶች አሉ። ለአብነትም ከ20-25% ታካሚዎች የስኳር ቁጥጥራቸው በሚፈለገው መጠን ግብ አይመታም፤ በርካታ ታካሚዎች ተደጋጋሚና አደገኛ የስኳር ማነስ (hypoglycemia) ያጋጥማቸዋል፤ እንዲሁም ከኢንሱሊን መድሃኒት ጋር የተያያዘ መጠነኛ ክብደት መጨመር አሁን አለም የደረሰብት ህክምና ገደቦች ናቸው።


ምንም እንኳን የኢንሱሊን ሕክምና እና የግሉኮስ ክትትል ከፍተኛ መሻሻል ቢኖርም የደም ግሉኮስ ቁጥጥርን ለማስተካከል የሚደረገው ትግል ቀላል አይደለም። የሚመከሩ የግሉኮስ ቁጥጥር ግቦችን ማሳካት የስኳር ተጓዳኝ ችግሮችን ለመከላከል ወሳኝ ቢሆኑም ለብዙ ታካሚዎች የኢንሱሊን መጠንን ከምግብ፣ እንቅስቃሴ፣ ከስራ ጫናና ውጥረት ጋር በማመጣጠን ትክክለኛውን የግሉኮስ መጠን ማምጣት በጣም ፈታኝ ነው። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሩብ በላይ ታካሚዎች የታለመላቸውን የደም ግሉኮስ መጠን በተገቢው ሁኔታ ባለማሳካታቸው በልብ፣ በኩላሊት፣ በአይን እና በነርቭ ላይ ለሚደርሰው የረዥም ጊዜ ውስብስብ የጤና ችግሮች ይጋለጣሉ።


ስኳሩን ልክ ለማስገባት ህክምናው ጠበቅ ሲል ደግሞ በተቃራኒው ሌላ ጉዳት ሊያመጣ ይችላል። ይህም የስኳር ማነስ ነው። የደም ስኳር መጠን ማነስ የሚከሰተው ኢንሱሊን በደም ውስጥ ያለውን የግሉኮስ መጠን በጣም በሚቀንስበት ጊዜ ነው። ስኳር ማነስ በራሱ ጎጂና አደገኛ ነው። የስኳር ህክምናውን በተፈለገው መጠን እንዳናስተካክል ሌላ ተግዳሮት ይሆናል። ስኳር በደንብ ወደመደበኛ መጠን እንዳናወርደው ይገድባል። ይህም የወቅቱን የሕክምና አማራጮች ውስንነት ፍንትው አድርጎ ማሳያ ነው።


በተጨማሪም ኢንሱሊን የሰውነት ክብደትን በመጨመር የማወፈር ያልተፈለገ የጎንዮሽ ጉዳት አለው። ይህ የክብደት መጨመር ሌላ የጤና አደጋዎችን ሊፈጥር ይችላል፤ የደም ውስጥ የግሉኮስ ቁጥጥርን የበለጠ አስቸጋሪ ያደርገዋል። በተለይ ለታዳጊዎች ስለሰውነት ቅርጻቸው አብዝተው እንዲጨነቁ ስለሚያደርግ የስነ-ልቦና ጫናን እና ጭንቀትን ያመጣል።


እነዚህ የአይነት አንድ ስኳርን የመቆጣጠር ተግዳሮቶች መኖርና አሁን ባለው ሕክምና ላይ ክፍተቶች መኖራቸው የተሻሻሉ ሕክምናዎች ፍለጋ አስፈላጊነት ያሳያል። አሁን ከደረስንበት ህክምና የበለጠ የተሻሻሉ የሕክምና ዘዴዎችን አስፈላጊነት ያስረግጣሉ።


እነዚህ ያልተሟሉ ፍላጎቶችን ለመሙላት ነው ተመራማሪዎች የተለያዩ የሙከራ መድሃኒቶችን እና ፈውስ ሊሆኑ የሚችሉ መፍትሄዎችን ማሰስ የቀጠሉት። የአዳዲስ ሕክምና አማራጮች ፍለጋ ከተቻለም ፈጽሞ ለማዳንና አስቀድሞ ለመከላከል የሚረዱ መፍትሄዎችን ለመፈልሰፍ የተራቀቁ ምርምሮችን ማድረግ እንደቀጠለ ነው። እስካሁንም አስደናቂ እመርታዎች ተመዝግበዋል።


አዳዲስ የአይነት አንድ ስኳር ሳይከሰት አስቀድሞ መከላከያ ሕክምናዎች

ዓይነት 1 የስኳር ህመምን በከፊል አስቀድሞ መከላከል የሚቻልበት ስኬታማ ህክምና በቅርቡ ይፋ ሆኗል። እንደ ቴፕሊዙማብ እና ቬራፓሚል ባሉ መድሃኒቶች የአይነት አንድ ስኳር ህመም ሂደት በመቀየር ስኳር የሚከሰትበትን ጊዜ ለጥቂት አመታትም ቢሆን ማዘግየት ተችሏል።


ቴፕሊዙማብ (Teplizumab) ዓይነት 1 የስኳር በሽታን ባይፈውስም ከፍተኛ የመያዝ እድል ባላቸው ልጆች ላይ ተሞክሮ የበሽታው መከሰትን በጥቂት አመታት የማዘግየት አቅም እንዳለው ተረጋግጧል። ይህ ማለት እናት ወይም አባት የአይነት አንድ ስኳር ያለባቸው ከሆኑ ልጆቻቸው የመያዝ እድላቸው ከሌላው ማህበረሰብ ጋር ሲነጻጸር ከፍ ያለ የጄኔቲክ ቅድመ-ዝንባሌ ስላላቸው ይህ በመርፌ የሚሰጥ መድሃኒት በመውሰድ ስኳር የመያዝ አጋጣሚውን ያዘገያል። ቴፕሊዙማብ የሚሰራው የራሳችን ሰውነት በሽታ የመከላከል ስርአት የገዛ ቆሽታችንን የሚያጠቃበትን ሂደት በማርገብና በመቀነስ ነው። ሲዲ3 ከተባለ ትንሽዬ ሞለኪዩል (monoclonal antibody targeting CD3) ጋር በመቆራኘት የተዛባውን የሰውነትን በሽታ የመከላከል ስርአት ያስተካክላል። ይህም የቆሽት ህዋሳትን ጉዳት ይቀንሳል፣ የህመሙን ሂደት ያዘገያል።


ቴፕሊዙማብ በዓይነት 1 ስኳር ህክምና ውስጥ የመጀመሪያው ዉጤታማ የበሽታ መከላከያ ግኝት ሆኖ እ.ኤ.አ. በኖቬምበር 2022 በአሜሪካው የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ፈቃድ በማግኘት ታሪክ ሰርቷል። የዚህን መድሃኒት ዉጤታማነት ያረጋገጠው አስደናቂ  ጥናት Teplizumab Prevention Study (TN-10 study) ይባላል። በዚህ ጥናት ቴፕሊዙማብ ከፍተኛ ተጋላጭነት ባላቸው ከ8 አመት እድሜ በላይ ላሉ ልጆችና ጎልማሶች ላይ የዓይነት 1 የስኳር ህመምን በሁለት ዓመት ጊዜ ሊያዘገየው እንደሚችል አሳይቷል።


ቬራፓሚል (Verapamil) የሚባል መድሃኒትም እንዲሁ አዎንታዊ ግኝት አሳይቷል። ቬራፓሚል በአሁኑ ጊዜ ለደም ግፊት እና ሌሎች የልብ ህመሞች ለማከም ጥቅም ላይ ይውላል። በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በቅርብ የተከሰተ ዓይነት 1 የስኳር ህመም ያለባቸውን ግለሰቦች ሊጠቅም እንደሚችል ነው። CLVer የተሰኘው ጥናት ውጤቶች እንደሚያመለክቱት ቬራፓሚል በቆሽት መቆጣት ምክንያት ቤታ-ሴል ላይ ያለውን ጫና በመቀነስ የህዋሳቱን ኢንሱሊን የማምረት ተግባር ተጠብቆ እንዲቆይ በማድረግ የታካሚዎችን የኢንሱሊን ፍላጎትን ለመቀነስ እንደረዳ ነው።


እነዚህ የአይነት አንድ ስኳር ህመም መከላከያ ዘዴዎች ስኳሩ የሚከሰትበትን እድሜ በማዘግየት ህፃናት ለጥቂት አመታትም ቢሆን ከኢንሱሊን ጥገኛነት ነጻ ሆነው እንዲያድጉ ይረዳሉ። ጨርሶ ፈውስ ባይሆኑም ህመሙን ካዘገዩ ከስኳር ጋር ለተያያዙ ችግሮች የመጋለጥ እድላቸው ዝቅ እንዲል ሊያደርጉ ይችላሉ።


አዳዲስ የአይነት አንድ ስኳር ለማዳን የሚሞከሩ ህክምናዎችና ምርምሮች

የቆሽት ወይም ቤታ ሴል ንቅለ ተከላ (Beta Cell Replacement Therapy: whole pancreas transplantation or Islet Cell Transplantation)

ኢንሱሊን የሚያመነጩ ቤታ ህዋሶችን (Beta cells) በሌላ ጤነኛ ህዋስ በመተካት የኢንሱሊን ምርት በተፈጥሯዊ መንገድ እንዲስተካከል የማድረግ የህክምና ዘዴ ነው።


በአለማችን ብዙ የቆሽት ንቅለ ተከላ በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል። አዲስ የተተከለው የለጋሽ ቆሽት ህዋሳት ኢንሱሊን በማምረት ታካሚውን ከኢንሱሊን መርፌ ውጤታማ በሆነ መንገድ ነፃ ያደርጋል። ይህ ህክምና የሚወጋውን የኢንሱሊን መጠን ከመቀነስ እስከ ኢንሱሊን ማቆም ድረስ ሊሰራ ይችላል።


ነገር ግን የለጋሹ የቆሽት ህዋሳት ከተቀባዩ ጋር በቀላሉ ስለማይላመድ ብሎም የተቀባዩ ሲስተም ፈጽሞ ላይቀበለው ስለሚችል እንደሌሎች ንቅለ ተከላ ህክምናዎች ሁሉ የዕድሜ ልክ በሽታ የመከላከል አቅምን የሚያዳክሙ የኬሞ መድሃኒቶችን መውሰድ ይፈልጋል። እነዚህ የኬሞ መድሃኒቶች የጎኞሽ ጉዳታቸው ከኢንሱሊን ጋር ሲወዳደር እጅግ ከፍተኛ ነው። በህይወት ካለ ሰው ቆሽት መለገስ ስለማይቻልም በሰፊው ተደራሽ ማድረግ አልተቻለም።


ከላይ ከጠቀስነው ውስንነቶች በተጨማሪ ይህ የንቅለ ተከላ ህክምና ሙሉ በሙሉ ፈውስ አይደለም። የህመሙን መነሻ ምክንያት አያክምም። አንዳንዴም መጀመሪያ ላይ ቆሽቱን የጎዳው የራሳችን በሽታ የመከላከያ ሲስተም ይሄንን አዲሱንን ቆሽትም ሊያጠቃውና እንዳይሰራ ሊያደርገው ይችላል።


በእነዚህ ተግዳሮቶች የተነሳ ይህ ህክምና በጣም ውስን ለሆኑ ታካሚዎች ብቻ ነው የሚሰራው። ብዙ ጊዜ የቆሽት ንቅለ ተከላ የሚደረገው የኩላሊት ንቅለ ተከላ ለሚፈልጉ ሰዎች ብቻ ነው።


የቆሽት ሕዋስ ማደስ ሕክምና (Beta Cell Regeneration therapy)

ይህ የህክምና ዘዴ ደግሞ የራስን ቅድመ-ህዋስ (stem cell-based treatments) በማበልጸግ ኢንሱሊን የሚያመነጩ አዲስ የቆሽት ህዋሶችን መፍጠር የሚያስችል ህክምና ነው። የሰውነታችን ሁሉም ህዋሳት ምንጭ የሆኑትን ቅድመ-ህዋሳት በላቦራቶሪ በማሳደግ ኢንሱሊን ወደሚያመነጩ የቆሽት ቤታ ሴሎች እንዲቀየሩ ይደረጋል።


ይህ ህክምና በሙከራ ደረጃ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን አሳይቷል። ነገር ግን ገና ለክሊኒካል አገልግሎት ዝግጁ አይደሉም።


የዘረመል አርትዖት (Gene Editing)

ይህ የዘረመል እርማት ማድረግ ህክምና ደግሞ በጣም የተራቀቀ ሲሆን ለበሽታ የሚያጋልጠውን ዘረመል ነጥሎ የሚሰረዝበት፣ የሚሻሻልበት ወይም የሚተካበት የጄኔቲክ ሳይንስ ነው። ችግር ያለበትን ዘረመል ለይቶ በማረም ማስተካከልን ያካትታል። የተበላሸን ዘረመል በመቀስ ቆርጦ እንደመጠገን አስቡት።


ይህን የህክምና ዘዴ የሚሰራበት ቴክኖሎጂ ክሪስፐር ጂን አርትዖት (CRISPR Gene Editing) ይባላል። ይህ ህክምና ገና ገና በጅምር ምርምር ደርጃ ላይ ያለ ነው። ነገር ግን አስካሁን ያሉት ዉጤቶች የአይነት አንድ ስኳር ህመም ዋና መነሻ መንስኤዎችን ለመፍታት የሚያስችል እድል የሚሰጥ ተስፋ ሰጭ ዜናዎች እየተሰሙ ነው። የእድሜ ልክ የሆነውን የስኳር ሕክምና ሊፈውስ እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል።


ከላይ የጠቀስናቸው በሙከራ ደረጃ ያሉ ህክምናዎች የረጅም ጊዜ ጤና የማሻሻል ትልቅ ተስፋ የሰጡ ሆነዋል። ነገር ግን እስካሁን ኢንሱሊንን ለመተካትና ከምርመር ሙከራ ደረጃ አልፈው እንደዋና ህክምና ለመጠቀም ገና ዝግጁ አይደሉም።


ሃይ ባይ ያጡ የማህበራዊ ሚዲያ አሳች መረጃዎች

ብዙዎቻችን የጤና ምክር ለማግኘት ወደ ማህበራዊ ሚዲያ ብቅ እንላለን። እነዚህ መድረኮች ሰዎች ልምድ ለመለዋወጥ ቢያስችሏቸውም የተሳሳተ መረጃንም ያሰራጫሉ። ገና በሙከራ ደረጃ ያለን ዜና ተአምር እንደተፈጠረ አድርገው ሲያወሩት ታካሚዎችንና ወላጆችን ያሳሳቸዋል። ኢንሱሊን ለማቆም ይገፋፋሉ። ቁንጽል ግንዛቤ ይዘን ያለጊዜው እነዚህን ሕክምናዎች ማስተዋወቅ ታካሚዎችን ሊያሳስትና ሊጎዳ ይችላል።


ስለሆነም ተፅዕኖ ፈጣሪዎች እና ሚዲያዎች ተመልካች ለመሳብና ለታይታ ብቻ ተብሎ ያልተረጋገጡ ሕክምናዎችን ሲወያዩ ከፍተኛ ጥንቃቄ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። የጤና ሚኒስቴርና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት አሳሳች የጤና መረጃ የሚለቁ ሃላፊነት የማይሰማቸው አሳቾችን ሃይ የሚል የሚቆጣጠር፣ ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ ህገ ደንብ ማውጣትና ማስፈጸም ይገባቸዋል።


ታካሚዎችና ወላጆችም ፈውስ ለማግኘት በተስፋ እየጠበቅን እስከዚያ ግን የተረጋገጠ ህክምና ብቻ ያለማቋረጥ ይቀጥሉ። ስለሆነም የጤና ባለሙያዎች ህይወት አድን የሆነውን ኢንሱሊንን መጠቀምና ማዘዝ መቀጠል አለባቸው።


በተስፋ ወደፊት መገስገስ

ለአይነት 1 የስኳር ህመም ዘላቂ ስርየት እስካሁን ባይገኝም የሕክምና ሳይንስ አዳዲስ ተስፋዎችን እየፈነጠቀ ነው። የህክምና ሳይንስ ከላይ የጠቀስናቸውን ተስፋ ሰጭ ህክምናዎች በንቃት እየመረመረ ነው። ሳይንቲስቶች ከኢንሱሊን ባለፈ ለስኳር ህመም መፍትሔ ለማግኘት ሌት ተቀን እንደቀበሮ በላቦራቶሪ ክፍል መሽገው እየሠሩ መሆናቸውን ማወቃችን ለወደፊቱ የተሻለ ተስፋ ይሰጣል።


እነዚህ ተስፋ ሰጪ የሙከራ ደረጃ ሕክምናዎች ገና ጥቅም ላይ ለመዋል ዝግጁ አይደሉም። አበረታች ውጤቶችን ቢያሳዩም ገና በሙከራ ደረጃ ላይ ናቸው። ለሁሉም ታካሚ በሰፊው ከመሰጠታቸው በፊት ብዙ ተጨማሪ ጥብቅ ምርመራ እና ማሻሻያ ያስፈልጋቸዋል።


የጠቀስናቸው እና ሌሎችም የሚያጓጉ ሕክምናዎች እስኪገኙ ድረስ ዓይነት 1 የስኳር ህመምን በኢንሱሊን ማከም ና ስኳርን መቆጣጠር ወሳኝ ነው። እነዚህን ለዉጦች በተስፋ እየተጠባበቅን አሁን ላይ የተረጋገጡ ተጨባጭ ህክምናዎችን በቁርጠኝነት መቀጠል ይገባል። ስለሆነም አሁን ላይ ያሉትን የሚመከሩ የተረጋገጡ ህክምናዎች መቀጠል አስፈላጊ ነው። የኢንሱሊን ህክምና ፍጹም እንከን የለበትም ባይባልም ሕይወት አድን ነው።


ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል ወይም የግል ሆስፒታሎች መመካከር ይችላሉ።


ተጨማሪ ምክር፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት በኢሜል፦ contact@melakutaye.com እና ስልክ፦ +251921720381 ማግኘት ይችላሉ። በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ ብሎግ www.melakutaye.com ፣ ቴለግራምና ቲክቶክ ይከታተሉ። እነዚህን የተረጋገጡ መረጃዎች ለሌሎችም እንዲያጋሩ በትህትና እጋብዛለሁ።

1 thought on “የአይነት አንድ ስኳር ህክምና አሁናዊ መመሪያዎችና ተስፋ ሰጪ ምርምር ዉጤቶች”

  1. Dr Assalif Demissew

    Dear Dr Melaku, I get your blog as so important and timely. I made a video of your article on my YouTube channel for further reachability of this important information and to create awareness among the community. I hope it will reach and help to some audiences. Thank you for this informative article.
    Link: https://youtu.be/SLcooyth3kw

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top