ውፍረት ማለት የሰውነት ስብ ከመጠን በላይ መብዛት ጋር የተያያዘ ስር የሰደደና የሚያገረሽ ውስብስብ በሽታ (Adiposity Based Chronic Disease) ነው። በተለምዶ የመጠነ ክብደት (body mass index) ከ30 በላይ ሲሆን ከመጠን በላይ ውፍረት ይባላል። ለከባድ የጤና ችግሮች የሚያጋልጥ ሲሆን ህክናምናዎቹ አመጋገብ ማስተካከል፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን መጨመር፣ በመድሃኒትና የውፍረት ኦፕሬሽን የመሳሰሉ የህክምና አማራጮችን ያካትታሉ።
የውፍረት አሳሳቢነት በአለም አቀፍና በሃገራችን ምን ይመስላል?
በአለም አቀፍ ደረጃ እየተስፋፉ የሚገኙትን የስኳር ህመምና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በፍጥነት መጨመር ዋነኛ ተቀዳሚ ምክንያት ከመጠን ያለፈ ውፍረት ነው። እንደወረርሽኝ ስርጭታቸው እየጨመረ የመጡት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሁሉ ከጀርባ ያለው ግንባር ቀደም ድብቅ ምክንያት ውፍረት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ውፍረት የበሽታዎች ሁሉ እናት ነው ብለው የሚጠሩትም አሉ።
ከመጠን ያለፈ ውፍረት በአጠቃላይ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሰዎችን ይጎዳል። በሰሜን አሜሪካ ሃገራት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ውፍረት ከሲሶ በላይ የሚሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ያጠቃል። የበለጠ የሚያሳስበው ደግሞ በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ውስጥ ወደ 2 ቢሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን እንደሚጎዳ ይገመታል።
ውፍረትን የሃብታም ሃገሮች ብቻ ችግር እንደሆነ ተደርጎ ይታሰባል። ነገር ግን ውፍረት ሃገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ የመካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሃገሮችም ጭምር ወረርሽኝ በሚባል መልኩ በከፍተኛ ፍጥነት እያሻቀበ ይገኛል። በኢትዮጵያ ያለው ውፍረት ከፍተኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ያነሰ ቢሆንም በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ነው።
የውፍረት ህመም ስርጭት የተቀናጀ አለም አቀፋዊና ሁለንተናዊ ምላሽ መስጠት የሚፈልግበት አስጊ ደረጃ ላይ የደረሰ ቢሆንም አሁንም ለጉዳዩ ቅድሚያ መስጠት አልቻልንም። ቅድሚያ ከሚሰጣቸው የጤና ጉዳዮች ሁሉ የላቀ ትኩረት የሚሻ ቢሆንም ችላ ማለቱን ቀጥለናል። ይህ ውፍረትን ችላ ማለት ውሎ አድሮ ከፍተኛ ዋጋ እንዳያስከፍለን ያስፈራል።
የተቀናጀ አለምአቀፋዊ ትኩረት የሚሻ አሳሳቢ የማህበረሰብ ጤና ስጋት ቢሆንም አብዛኛው ሰው ውፍረትን የውፍረት ተጠቂው ግለሰብ ጉዳይ ብቻ አድርገው ስለሚያስቡ ሁሉን አቀፍ የህክምና እና መከላከያ ስልቶች በበቂ ሁኔታ ለመቅረጽ አዳጋች አድርጎታል። አፋጣኝ እርምጃ እንደሚያስፈልግ የሚያሳዩ መረጃዎች እየጨመሩ ቢሄዱም ውፍረትን በተለመደው ባለሙያና የህክምና ግብአት ብቻ እንደሚታከም ማሰብ ቀጥሏል።
ሌላኛው የቸልተኝነት ምንጭ ደግሞ ስለ ውፍረት መንስኤዎች እና ተፅእኖዎች የተሳሳተ መረጃ ነው። ውፍረትን እንደ አንድ ራሱን የቻለ በሽታ አድርጎ ያለመቁጠር ግዴለሽነት የህክምና ባለሙያዎች ውጤታማ እርምጃ መውሰድ አንዳይችሉ እንቅፋት ይሆናል።
ውፍረት ከአሁን በኋላ ችላ ሊባል አይችልም። የአለም ውፍረት ፌዴሬሽን በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ውፍረት ላይ የተቀናጀ እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርቧል። ውፍረት የዘመናችን ትልቅ የጤና ፈተና እንደሆነ ገልጾ የአለም ጤና ማህበረሰብ ሙሉ ትኩረት ሊነፍገው የማይገባ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥቷል። ውፍረት በአለም አቀፍ የጤና አጀንዳዎች ግንባር ቀደም መሆን አለበት ሲል አበክሮ አሳስቧል።
የውፍረት መንስኤዎች ምንድን ናቸው?
ውፍረት በጣም በርካታ ምክንያቶች ያሉት በሽታ ነው። ዋነኛው የውፍረት መንስኤ ያልተስተካከለ አመጋገብ ልማድ ነው። ከሰውነት የእለታዊ የሃይል ፍላጎት በላይ የሆነ ብዙ ትርፍ ምግብ/ካሎሪ ስንበላ ክብደት ይጨምራል። ኦርጋኒክ ከሆኑት ምግቦች ይልቅ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ከፍተኛ ካሎሪ የበዛባቸው ምግቦችን መመገብ፣ ስኳር የበዛባቸው ምግቦች እና መጠጦች እንዲሁም ከፍተኛ መጠን ያለው ጮማ የያዙ ምግቦችን መመገብ ከመጠን በላይ ውፍረት ያስከትላል።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አዘውትሮና በበቂ አለመስራትም እንዲሁ ለውፍረት ይዳርጋል። በተለይ በቢሮ እና ቤት ውስጥ አብዝቶ መቀመጥ፤ ለረጅም ሰአት ቲቪ መመልከት፣ የቪዲዮ ወይም በሞባይል ላይ ጊዜ ማሳለፍ ለእንቅስቃሴ ያለን ጊዜ ይቀንሳል።
ሁላችንም ማስተዋል ያለብን ነገር ቢኖር ውፍረት በአኗኗር ዘይቤ አለመስተካከል ብቻ የሚመጣ የስንፍና ህመም አይደለም። ክብደትን መቆጣጠር የምናስገባው እና የምናስወጣው ካሎሪ ምጥጥን ጉዳይ ብቻ አይደለም። ለብዙ አመታት ሲታመንበት የነበረው የክብደት አስተሳሰብ የሚገባና የሚወጣ ካሎሪ መጠን (Calories-In, Calories-Out) ማመጣጠን የሚል ነበር። ‘ትንሽ ከበሉ እና ብዙ ከተንቀሳቀሱ ክብደት ይቀንሳል’ ይባል ነበር – የሚመገቡትን ምግብ ከመጠኑ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ከጨመሩ ክብደት መቀነስ ጥርጥር የለውም የሚል ንድፈ-ሃሳብ!
ይህ የክብደት እሳቤ በከፊል ትክክል እንዳልሆነ አሁን አሁን አዳዲስ ጥናቶች ተስማምተውበታል። በርካታ ሆርሞኖች ሜታቦሊዝም እና በሰውነት ክብደት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። እነዚህ ሆርሞኖች በተለያዩ የሜታብሊክ ሂደቶች ላይ የቁጥጥር ስራ ይሰራሉ። ለምሳሌ የምግብ ፍላጎት፣ የረሃብ ስሜት፣ የስብ ክምችትና የደም ስኳር መጠን ወዘተ ይዘውራሉ።
በሜታቦሊዝም እና በሰውነት ክብደት ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ቁልፍ ሆርሞኖች ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉትን ያካትታሉ፡-
- ኢንሱሊን (insulin)፡ ከቆሽት የሚመረት ሲሆን በደም ውስጥ ያለውን የግሉኮስ መጠን ይቆጣጠራል። ግሉኮስ ወደ ህዋሳት ሰርጎ እንዲገባ በማድረግ ወደሃይል ሰጪነት እንዲቃጠል ወይም ትርፍ ከሆነ በስብ መልክ እንዲከማች ያደርጋል። የኢንሱሊን ስራ ከተስተጓጎለ የስብ ክምችት እንዲጨምር እና ሰውነት እንዲፋፋ ሊያደርግ ይችላል። ከቆሽት የሚመነጨው ግሉካጎን የተባለው ሆርሞን ደግሞ ከኢንሱሊን በተቃራኒው የተከማቸ ስኳርና ጮማ/ስብ እንዲቃጠል ያደርጋል።
- ሌፕቲን (leptin)፡ በስብ ህዋሶች (adipocytes) የሚመረት ሲሆን የጥጋብ ስሜት እንዲሰማን የሚያደርግ ዋነኛ ሆርሞን ነው። የረሃብን ስሜት ያስታግሳል። የምግብ አወሳሰድን መጠን ይገድባል። ስለሆነም ክብደትን ይቀንሳል። ህዋሶቻችን ለሌፕቲን ተገቢውን ምላሽ በማይሰጡበት ጊዜ የሌፕቲን ስራ ይስተጓጎላል። ይህ ሲከሰት ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያመጣል።
- አዲፖኔክቲን (adiponectin)፡- ሌላው በስብ ሴሎች የሚለቀቀው ሆርሞን ሲሆን የሜታቦሊዝምን መጠን ይጨምራል፣ የተከማቸ ስብ እንዲቃጠል ያግዛል፣ የምግብ ፍላጎትን ይገድባል። የዚህ ሆርሞን መቀነስ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ጋር የተያያዘ ነው።
- ግሬሊን (ghrelin)፡ የሚመረተው በዋነኛነት ከጨጓራችን ሲሆን ብዙ ጊዜ ‘የረሃብ ሆርሞን’ ተብሎ ይጠራል። የረሃብ ስሜት በማምጣት የምግብ ፍላጎትን ያነቃቃል፣ ምግብ አምጣ አምጣ ይወተውታል፣ የምግብ አወሳሰድን ይጨምራል። በተጨማሪም ከአንጀት የሚመነጩ ፔፕታይድ ዋይ (PYY)፣ ኮሌሲስቶካይኒን (Cholecystokinin, CCK) እና ሌሎችም በርካታ ሆርሞኖች የምግብ ፍላጎትን፣ የረሃብ ስሜትን፣ የምግብ መፈጨት ሂደትን ወዘተ በመቆጣጠር የሰውነት ክብደት ላይ አወንታዊ ወይም አሉታዊ ተጽእኖ ያመጣሉ።
- ኮርቲሶል፡- በአድሬናል እጢዎች (adrenal glands) የሚመረተው ኮርቲሶል ‘የጭንቀት ሆርሞን’ (stress hormone) በመባል ይታወቃል። የኮርቲሶል ሆርሞን መጠን ለረጅም ጊዜ ከፍ ብሎ ሲቆይ የምግብ ፍላጎት እንዲጨምር፣ ምግብ አምጣ አምጣ የሚል ስሜት እንዲበዛ፣ በተለይ ሱስ እስኪመስለን ጣፋጭ አብዝተን መሻት እንዲኖር፣ የስብ ክምችት እንዲጨምር ወዘተ በማድረግ ክብደት ይጨምራል። ድባቴ ሲኖር፣ ጭንቀት ሲበዛ፣ እንቅልፍ ሲያንሰን እንዲሁም ሌሎች ማህበራዊ ጫናዎች ሲኖሩ ኮርቲሶልን ስለሚጨምር ለውፍረት ያጋልጣል።
- የታይሮይድ ሆርሞኖች፡- እነዚህ ሆርሞኖች ሜታቦሊዝምን ለመቆጣጠር ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። በተለይ የታይሮይድ ወይም እንቅርት ሆርሞን ማነስ ሲኖር ክብደትን ይጨምራሉ።
ከላይ የዘረዘርናቸው ሆርሞኖች መዛባት ሲኖር ወደ ሜታቦሊዝም መዛባት፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ የስኳር ህመም እና ሌሎች ተያያዥ ሁኔታዎችን ሊያመጣ ይችላል።
ከላይ ከጠቀስናቸው የአኗኗር ዘይቤ ጋር የተያያዙና ከሆርሞኖች መዛባት በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ውፍረት የሚያመጡ መንስኤዎች አሉ። አንዳንድ በህክምና የሚታዘዙ መድሃኒቶች ሊያወፍሩን ይችላሉ። ሌሎች ህመሞችን ለማከም የሚወስዷቸው መድሃኒቶች ለክብደት መጨመር አስተዋፅዖ ያደርጋሉ። ለምሳሌ በርካታ የጭንቀት መድሃኒቶች፣ ስቴሮይድ፣ የስኳር መድሃንቶች፣ የልብ መድሃኒቶች ወዘተ ክብደት አምጭ ናቸው።
በዘር የሚወረሱ የውፍረት መንስኤዎችም አሉ። የጀነቲክስ / ዘረመል ችግር ሲኖር ለውፍረት ተጋላጭነት ይኖራል።
የመኖሪያ እና መስሪያ ከባቢም ለውፍረት የሚያጋልጥ ሊሆን ይችላል። ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ማህበረሰቦች የተሻሉ ምግቦችን ማግኘት አዳጋች ስለሚሆንባቸው ለውፍረት ይጋለጣሉ። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ አስቻይ መዋቅራዊ ሁኔታዎች ከሌሉ ለውፍረት ያመቻቸናል። የጤና ስርአቱም ቢሆን ውፍረትን ለመለየትና ተገቢውን ዉጤታማ ህክምና ለመስጠት ዝግጁነት ይጎድለዋል። ይህ ሁሉ ውፍረትን እያባባሰው ነው።
የውፍረት ምልክቶች ምንድን ናቸው?
ውፍረት አሳሳቢ በሽታ ሆኖ ሳለ የተለየ የህመም ምልክቶችን አያሳይም። ይባስ ብሎ ውፍረት በጥናቶች፣ በማኅበራዊ ግንዛቤ እና በህክምናው ዘርፍ አሁንም ግልጽ የሆነ ‘መለኪያ (diagnostic tool)’ የለውም።
በጣም የተለመደው መለኪያ መንገድ መጠነ ክብደት (Body Mass Index, BMI) ነው። ክብደት በኪሎግራም ሲካፈል ቁመት በሜትር ካሬ ሆኖ የሚሰላ ቀላል ልኬት ነው። የBMI ስሌት ከ18.5 እና ከዛ በታች ከሆነ ከመደበኛ ክብደት በታች ሲሆን የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ሊያመለክት ይችላል። የBMI ውጤቶ ከ 18.5 እስከ 24.9 ሲሆን ደግሞ ጤናማ ክብደት ነው። የBMI ውጤቶ ከ25 – 29.9 ከሆነ ከመጠን በላይ ክብደት ያለዎት ሲሆን እንደ የደም ግፊት፣ የስኳር በሽታ፣ እና የልብ ሕመም በሽታዎች ተጋላጭነትዎ ይጨምራል። ከመጠን ያለፈ ውፍረት የሚባለው ደግሞ BMI 30 እና ከዚያ በላይ ከፍ ሲል ነው።
BMI ለማስላት ይቅለል እንጅ ጉልህ ጉድለቶች አሉት። BMI በጡንቻ ፈርጣማ ለሆኑት እና ጠንካራ አጥንት ላላቸው ሰዎች አይሆንም። በስብ ስርጭት (fat distribution) ላይ ያለውን ልዩነትም አያመለክትም። ለምሳሌ፣ ጡንቻ የገነባና ዝቅተኛ የሰውነት ስብ መጠን ያለው አትሌትና ብዙ ጡንቻ የሌለው ቦርጫም ሰው ተመሳሳይ እኩል BMI ሊኖራቸው ይችላል። ነገር ግን እነኚህ ሁለቱ ሰዎች እኩል ጤናማ አይደሉም። ቦርጫሙ ሰው BMIዩ መደበኛ ክልል ውስጥ ቢሆንም ቅሉ አደገኛ የሆነ የስብ ክምችት ሊይዝ ይችላል።
BMI ስለ ስብ ስርጭት ምንም መረጃ አይሰጥም። አብዛኛው ስብ የሚያከማችበት ቦታ የት ነው የሚለው ለጤና ወሳኝ ነው። በሆድ አካባቢ የተከማቸ ከመጠን በላይ ስብ (“apple-shaped” bodies) በተለይም ጉበትና ሌሎች የውስጥ ሰውነት ክፍሎቻችን (visceral fat) ላይ ሲጠራቀም እንደ ስኳር እና የልብ በሽታ ለመሳሰሉት የሜታቦሊክ በሽታዎች አደጋ ነው። በአንጻሩ ደግሞ በዳሌና ጭን አካባቢ ላይ ያለ ስብ የሚበዛባቸው ሰዎች (“pear-shaped” body) ለሜታቦሊክ በሽታዎች የመጋለጥ እድላቸው አነስተኛ ነው።
ከእነዚህ የBMI ጉድለቶች አንጻር ውፍረት እና ተዛማጅ የጤና ችግሮችን ለመገምገም አዳዲስ መለኪያዎች እየመጡ ነው። ስለአጠቃላይ ጤንነታችን ሻል ያለ መረጃ የሚሰጡ አዳዲስ መለኪያዎች የሚከተሉትን ያካትታል።
የወገብ ዙሪያ ከዳሌ ስፋት ጥምርታ (Waist-to-Hip Ratio): በእምብርት ልክ ያለው የወገብ ስፋትን ከዳሌ ስፋት ጋር የሚያነጻጽር መለኪያ ነው። የወገብ ከዳሌ ጥምርታ ከፍ ካለ በሆድ አካባቢ የተከማቸ ብዙ ስብን (belly fat) ይጠቁማል። ይህም ከBMI የበለጠ የልብ እና የስኳር ህመም ተጋላጭነትን ይተነብያል። ይህ ልኬት ከBMIና ከሌሎችም በጣም የተሻለ የሜታቦሊክ ጤና አመላካች እንደሆነ በርካታ ጥናቶች አረጋግጠዋል። BMI ምንም ይሁን ምን የወገብ ከዳሌ ስፋት ጥምርታ ከ1 በላይ ከሆነ ጤናማ ያልሆነና መፍትሄ የሚሻ አደገኛ የስብ ክምችት አለ ማለት ነው።
ሌላኛው ልኬት ደግሞ የወገብ ስፋት (Waist Circumference) ሲሆን አደገኛ የሆድ ውስጥ ስብን ለመገመት ሁነኛ መሳሪያ ነው። የወገብ ዙሪያ ስፋት ከ80 ሳንቲ ሜትር በላይ ከለካ ጤናማ ያልሆነና መፍትሄ የሚሻ አደገኛ የስብ ክምችት አለ ማለት ነው።
ሶስተኛው መለኪያ የሰውነት ስብ መጠን መቶኛ (Body Fat Percentage) ሲሆን ይህ ሜትሪክ ከሰውነታችን ክብደት ውስጥ ስብ ስንት ፐርሰንቱን ይይዛል የሚለውን ይገምታል። የሰውነታችንን የስብ መጠን በፐርሰንት ከሚለካባቸው መንገዶች መካከል የቆዳ እጥፋት መጠን (skinfold measurements)፣ ባዮኤሌክትሪካል ኢምፔዳንስ (bioelectrical impedance) እና ልዩ ኤክስሬይ (DEXA scan) የመሳሰሉ ዘዴዎች ይገኙበታል። የሰውነት ስብ መቶኛ ለወንድ ከ25% እና ከዚያ በላይ እንዲሁም ለሴት 30% እና ከዚያ በላይ ከሆነ ከልክ ያለፈ ውፍረት እንደሆነ ይቆጠራል፣ ምንም እንኳን የBMI ቁጥር ከተለመደው ኖርማል ክልል ባይበልጥም።
እነዚህ ከላይ የዘረዘርናቸው መለኪያ መንገዶች አደገኛ የጤና ጠንቅ የሆነውን በሰውነት ውስጥ የተከማቸ ስብ (Visceral fat) መጠን ይጠቁማሉ፤ ስለሆነም እንደ ስኳር፣ የልብ ሕመም እና አንዳንድ የካንሰር በሽታዎች ካሉ ሥር የሰደዱ ገዳይ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድልን ያሳያሉ።
ውፍረት የሚያስከትላቸው ችግሮች ምንድን ናቸው?
ውፍረት ጤናን በብዙ መልኩ ይጎዳል። በአጠቃላይ ጤናን በቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆነ ተጽእኖ የሚያስከትል ሲሆን ከበርካታ ከበባድ የጤና ችግሮች ጋር የተቆራኘ ነው።
ለበርካታ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና ካንሰር ህመም የመጋለጥ እድልን የሚጨምር የሜታቦሊዝም መታዎክ ሊያስከትል ይችላል። በተለይም ስር የሰደዱ የካርዲዮቫስኩላር በሽታዎች (የልብና የደም ቧንቧ በሽታዎች) ተጋላጭነትን ይጨምራል።
የስኳርና ህመማና የደም ግፊት መብዛት ያስከትላል። የኮሌስትሮል መጠን ከፍ ያደርጋል።
የኩላሊት መድከም ሊያመጣ ይችላል።
ጉበት ላይ ከመጠን በላይ ስብ መብዛት እስከ ሥር የሰደደ የጉበት መጎዳትና መድከም (cirrhosis) ያስከትላል።
የሐሞት ጠጠር የመያዝ እድልን ይጨምራል።
በተጨማሪም በርካታ ገዳይ የካንሰር ህመሞች ለአብነትም የጡት፣ የአንጀት፣ የጉበት ካንሰር ወዘተ ያሉ አንዳንድ ካንሰር ህመሞች ያጋልጣል።
ከአካላዊ ጤና መዛባት ባለፈ በርካታ የአእምሮ ጤና ችግሮች ያስከትላል። ስነልቦናዊ ጫና ያሳድራል። ለምሳሌ የጭንቀት፣ ድብርት የመሳሰሉ ስነ-ልቦናዊ ተፅእኖዎች አሉት።
ውፍረት በግለሰቡ ላይ ከሚያስከትላቸው የጤና አክሎች ባለፈም የማህበራዊና በአጠቃላይ የሃገር የህክምና ወጭን በመጨመርና የሰራተኛውን ምርታማነት በመቀነስ ኢኮኖሚን ይጎዳል። እነዚህ ውስብስብ የውረት ችግሮች በቤተሰብ እና በጤና አጠባበቅ ስርዓት ላይ ከባድ ሸክም ይሆናሉ።
ውፍረትን ለመቀነስ ምን እናድርግ?
ውፍረት የሚያመጣውን መዘዝ በመገንዘብ እና ተግባራዊ ለውጦችን በማድርግ ከልክ ያለፈ ውፍረትን ማከም እና ማስተካከል ይቻላል። ውፍረትን መቆጣጠር ሁሉን አቀፍ ለውጥ ማድረግን ይጠይቃል።
ጤናማ የህይወት ዘይቤን ማዘውተር ውፍረትን ለመቀነስ የሚያስችለን መሰረታዊው መፍትሄ ነው። ጤናማ የህይወት ዘይቤን ማዘውተር ሲባል የተመጣጠነ ጤናማ አመጋገብ፣ በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድርግ፣ የሰውነት ክብደት ማስተካከልና ከሱስ የጸዳ አኗኗር መከተልን ያካትታል። ሆኖም ግን ለሁሉም ሰው የሚሰራ አንድ ፍቱን ቀመር የለውም። ስለዚህ ከጤና ባለሙያ ጋር በመወያየት ለእያንዳንዱ ግለሰብ የሚስማማ የውፍረት ማስተካከያ ዘዴ ማበጀት እንመክራለን።
ጤናማና የተመጣጠነ አመጋገብ ዋነኛ መሳሪያ ነው። በመጀመሪያ ማቀድና ግብ ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ለምሳሌ በሳምንት ግማሽ ኪሎ ልቀንስ ብሎ ከታቀደ ወደዚያ የሚያደርሱ ስራዎችን መጀመር። ሌላ ሰው ስኳሬን ማስተካከል፣ ግፌቴን ማሻሻል፣ ኮሌስትሮል መቀነስ፣ ቦርጭ ማጥፋት ወዘተ እያለ እንደየብሶቱ ሊያቅድ ይችላል።
መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ሌላኛው የውፍረት ህክምና የማዕዘን ድንጋይ ነው። የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በየጊዜው እየጨመሩና እያሻሻሉ በመስራት (በተለይ የጥንካሬ ስፖርት በማካተት የጡንቻን ጥንካሬ መጠበቅ) ክብደትን ማስተካከልና ጤናን የበለጠ ማበልጸግ ይቻላል።
እንዳስፈላጊነቱ በተለይም በአመጋገብና ስፖርት ክብደት ማስተካከል እምቢ ያለቸው ግለሰቦች በሃኪም የታዘዙ ፀረ-ውፍረት መድሃኒቶችን (Anti-obesity medication) በመውሰድ ሊታከሙ ይችላሉ። እነዚህ መድሃኒቶች መታዘዝ ያለባቸው በውፍረት ህክምና ስፔሻላይዝ ያደረገ ይህ ካልሆነ በውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሃኪም ቢሆን ይመከራል። መርሳት የሌለብን ነገር ቢኖር የፀረ-ውፍረት መድሃኒት በሚጠቀሙበት ጊዜ ጤናማ አመጋገብን፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን እና ሌሎችንም የአኗኗር ለውጦች ማስቀጠል ያስፈልግዎታል። መድሃኒቱ ተጨማሪ አጋዥ እንጅ የሻተንን አብዝተን ለመብላትና ስፖርት ላለመትጋት ሰበብ ይሁን ማለት አይደለም።
ከመድሃኒቶች ባሻገር የሜታቦሊክ ቀዶ ጥገና (metabolic/bariatric surgery, weight loss surgery) በተለይ መጠነ ክብደታቸው በጣም ከፍተኛ ለሆነ ሰዎች ሊሰራ ይችላል።
ውፍረትን አስቀድሞ መከላከል
ውፍረትን ሳይከሰት አስቀድሞ መከላከል ይቻላል። የመከላከያ እርምጃወች መውሰድ አንዴ ውፍረት ከመጣ በኋላ ለመቀነስ ከመታገል ይቀላል።
ቁልፍ የመከላከያ እርምጃዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ፡-
- ሁሌም ቢሆን ጤናማና የተመጣጠነ አመጋገብን ማዘውተር ተገቢ ነው። በፍራፍሬ፣ አትክልት እና አሰርነት ያላቸው ምግቦች በቫይታሚንና ማእድናት የበለፀጉ ምግቦችን ቀለብ ማድረግ። በተቃራኒው በፋብሪካ የተቀነባበሩ፣ ስኳር የበዛባቸው ምግቦችን እና ጣፋጭ መጠጦችን መገደብ።
- የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ጨምሩ። ለእርስዎ ተስማሚ የሆነ እንቅስቃሴን በማዘውተር አብዝቶ መቀመጥን መቀነስ። ከትምህርት ቤቶች እና ከስራ ቦታዎች ጀምሮ መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማበረታታት። ስልክና ቴሌቪዥን ላይ የሚጠፋ ጊዜዎን ይቀንሱ።
- ትናንሽ ለውጦችን እንጀምር። በጊዜ ሂደት እያሻሻልን ማስቀጠል።
እንደሃገር ምን እናድርግ?
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሃገሮች ረሃብና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ገና ባልተቀረፈበት ውፍረት አሳሳቢ የማህበረሰብ ጤና ፈተና ደቅኗል። ይህ የጤና ችግር ሳይቃጠል በቅጠል ሃይ ካልተባለ ከባድ የጤና፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ መዘዞችን ያስከትላል።
ውፍረት ለሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞች ተቀዳሚ አጋላጭ ምክንያት እንደመሆኑ ውፍረትን እንደ አንድ ህመም/በሽታ በመቁጠር ለችግሩ እውቅና መስጠት የመጀመሪያው እርምጃ ነው።
የጤና አገልግሎት ሰጪዎች ውፍረትን በብቃት እንዲመረምሩና እንዲያክሙ እንዲቆጣጠሩ ይሰልጥኑ።
በውፍረት ዙሪያ የሚሰረ የማህበረሰብ ጤና አንቂዎችን በመደገፍና በማበረታታት ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ያሳተፈ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ መፍጠር ወሳኝ ነው።
ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞችን ለመቆጣጠር በሚደረገው ስራና በሚወጡ የህክምና መመሪያዎች ሁሉ ውፍረትን ትኩረት መስጠት ይገባል። ለውፍረት ህክምና እና መከላከል እርምጃዎች ከችግሩ ስፋት ጋር የሚመጣጥን የራሱን ሃብት በመመደብ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት የያዘ የተቀናጀ እርምጃ መውሰድ ለነገ የሚባል አይደለም።
ውፍረትን ለመግታት አጠቃላይ የፖሊሲ ማዕቀፍን ይፈልጋል። ምግብ ምርቶችን እና ስኳር የበዛባቸው መጠጦችን በአመጋገብ ፖሊሲዎች መቆጣጠር ይገባል። የእግር ማድረኝ የሚያበረታቱ መኖሪያ ከባቢን መፍጠር እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ለማበረታታት በሕዝብ መናፈሻ ቦታዎች ላይ የበለጠ ኢንቨስት ይደረግ።
ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ይዘቶች ወይም ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና የጤና ባለሙያዎን ያማክሩ።
ተጨማሪ ምክር፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት በኢሜል፦ contact@melakutaye.com እና ስልክ፦ +251921720381 ማግኘት ይችላሉ። ለግል ህክምና ዶ/ር መላኩ ወይም የስራ ባልደረቦቹ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ።