መደበኛ ክብደት ያለው ውፍረት (Normal Weight Obesity)፡ በቀጭንነት የተደበቀ ውፍረት

ክብደትህ ኖርማልና ጤናማ ክልል ውስጥ እንደሆነ ሁልጊዜም ይነገረሃል እንበል። ስለዚህ ጤንነትህ አሪፍ እንደሆነ እና ከክብደት ጋር በተያያዘ ምንም የጤና ስጋት እንደሌለብህ እርግጠኛ ትሆናለህ። እስኪ ለማንኛውም አጠቃላይ የጤና ምርመራ ላሰራ ብለህ ናሙና ስትሰጥ ግን ‘ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠን ያሳያል፤ ስኳርም ትንሽ ከፍ ብሏል፤  ልብህ ላይም ጫና እንዳመጣ ያሳያል’ ዱብዳ ተነግሮህ የኮሌስትሮል መድሃኒትና ደም ማቅጠኛ አስፕሪን ጀምር ልትባል ትችላልህ።  ‘ዘላለም እንዲህ ቀጭን ሆኜ  ሳለሁ ይህ ወፍራሞችን የሚይይዝ ህመም እኔ ጋር ከየት መጣ’ ትገረማለህ።


ይህ ታሪክ በቀጭንነት የተደበቀ መደበኛ ክብደት ያለው ውፍረት (Normal Weight Obesity, Metabolically obese normal weight) አንድ ማሳያ ነው። የክብደት ቁጥሩ እና መጠነ ክብደት ብቻውን የሙሉ ጤንነት አስተማማኝ መለኪያ አይደለም። ቁጥሩ ብቻ ሳይሆን ‘ክብደቱ ስርጭቱ የቱ ጋር ነው ያለው?’ የሚለውም ወሳኝ ነው። ክብደት ቁጥሩ ብቻውን የጤናን ሙሉ ታሪክ እንደማይናገር አስረጅ ነው።


መደበኛ ክብደት ያለው ውፍረት (የቀጭን ወፍራም) ምንድን ነው?


መደበኛ ክብደት ያለው ውፍረት (የቀጭን ወፍራም) ሲባል አንድ ግለሰብ መደበኛ የሰውነት ክብደት እና መጠነ ክብደት (Body mass index, BMI) እያለው ነገር ግን የሰውነት ስብ መጠን በመቶኛ (Body Fat Percentage) በጣም ከፍተኛ ሲሆን ነው። ማለትም ከሰውነታችን ክብደት ውስጥ ስብ የሚይይዘው ፐርሰንት ለወንድ ከ25% እና ከዚያ በላይ እንዲሁም ለሴት 30% እና ከዚያ በላይ ከሆነ ከልክ ያለፈ ውፍረት እንደሆነ ይቆጠራል፣ ምንም እንኳን የክብደትና የBMI ቁጥር ከተለመደው ኖርማል ክልል ባይበልጥም። ከውጭ እንደሚታየው ውፍረት ሳይሆን እነዚህ ሰዎች መደበኛና ትክክለኛ ክብደት መጠን እያላቸው ሲታዩም ቀጭን ሆነው ሳለ ከመጠን በላይ የሰውነት ስብ የያዙ ናቸው። በተለይም ጉበትና መሰል የውስጥ ሰውነት ክፍሎቻችን ላይ ከፍተኛ የስብ ክምችት ይኖራቸዋል።


ይህ ሁኔታ በተለምዶ ከመጠን በላይ ውፍረት ባላቸው ሰዎች ላይ የሚከሰቱ እንደ የልብ ሕመም፣ የስኳር ህመም፣ የኮሌስትሮል ህመም እና የሜታቦሊክ መዛባት የመሳሰሉ የጤና እክሎችን ሊያመጣ ይችላል።


ለምሳሌ መግቢያችን ላይ ያነሳነው ታሪክ ክብደቱ ኖርማል ስለሆነ ብቻ እራሱን ለጤና ችግር እንደሚያጋልጥ አይቆጥርም ነበር።  ነገር ግን ምርመራዎቹ ሌላ ታሪክ ያሳያሉ። ምንም እንኳን ጤናማ የሚባል BMI ቢኖረውም መደበኛ ክብደት ሁሌም እንዴት ጤናማ ማለት እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው።


መደበኛ ክብደት ያለው ውፍረት (የቀጭን ወፍራም) ከሌሎቹ የውፍረት አይነቶች በምን ይለያል?


በተለምዶ ውፍረት የሚባለው አንድ ሰው ከመጠን በላይ ክብደት በተለይም BMI 30 እና ከዚያ በላይ ሲሆን ነው። መጠነ ክብደት (Body mass index, BMI) የሚሰላው ክብደት በኪሎግራም ሲካፈል ቁመት በሜትር ካሬ ሲሆን በስብ ስርጭት (fat distribution) ላይ ምንም መረጃ አይሰጥም። በስብ እና በጡንቻዎች መካከል ያለውን ልዩነት አይለይም። ለምሳሌ፣ ፈርጣማ ጡንቻ ያለው አትሌት ከመጠን ያለፈ የሰውነት ስብ ሳይኖረው ከፍተኛ BMI ሊኖረው ይችላል፣ መደበኛ BMI ያለው ሌላ ሰው ግን ጤናማ ያልሆነ ከፍ ያለ የሰውነት ስብ ክምችት ሊኖረው ይችላል።

ልክ እንደተለመደው በግልጽ የሚታየው ውፍረት ስለማይታይ  መደበኛ ክብደት ያለው ውፍረት (የቀጭን ወፍራም) ለመለየት አስቸጋሪ ነው።  ምክንያቱም ለተመልካች በቀላሉ የሚታዩ የአካል ለውጦችን አያሳይም። ስለሆነም ትኩረት ሳይሰጠው ችላ ሊባል ይችላል።


መደበኛ ክብደት ያለው ውፍረት (የቀጭን ወፍራም) ብዙ ሰዎች ከሚያስቡት በላይ በጣም የተለመደ ነው። ከ2010 አካባቢ ጀምሮ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ይህ አይነት በቀጭንነት የተደበቀ ውፍረት አይነት ከ20 እስከ 30% የሚደርሱ ኖርማል BMI ያላቸው ሰዎች ከፍተኛ የሰውነት ስብ ያላቸው የዚህ ስውር ውፍረት ተጠቂዎች እንደሆኑ ነው። ነገር ግን ይህ የውፍረት አይነት ገና ብዙም ያልታወቀ ጉዳይ እንደመሆኑ የችግሩ ስፋት ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። ስለዚህ ከውጭ ሲታዩ ሸንቃጣ ቢመስሉም አንዳንድ ሰዎች መጥፎ የሆነ ድብቅ የስብ ክምችት ሊኖራቸው ይችላል።


መደበኛ ክብደት ያለው ውፍረት የጤና ጉዳቶች


ይህ የውፍረት አይነት በተለምዶ ከምናውቀው ውፍረት የሚያመጣቸው የጤና እክሎች በሙሉ ሊያመጣ ይችላል። እነዚህም የሚከተሉትን ያካትታሉ፡

  • ሜታቦሊክ መዛባት፤ ኢንሱሊን ረዚስታንስ፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ ስኳር ህመም፣ የኮሌስትሮል ህመም
  • የልብና ደም ስር ህመም (Cardiovascular Disease)፡ ለልብ ህመም እና ለስትሮክ አጋላጭ ነው።
  • ዓይነት 2 የስኳር ህመም
  • የጉበት ስብ ክምችት በሂደትም ለጉበት በሽታ እና የጉበት ካንሰር ሊያመራ ይችላል

እነዚህንና ሌሎችን ከባድ የጤና መዘዝ የሚያመጡ በሽታዎች አስቀድሞ ለመከላከል መደበኛ ክብደት ያለው ውፍረት ማወቅና መለየት  አስፈላጊ ነው።


መደበኛ ክብደት ያለው ውፍረት እንዴት ማወቅ ይቻላል?


ይህንን ሁኔታ በትክክል ለመለየት የሚከተሉትን ከBMI የተሻሉ አዳዲስ መለኪያዎች መጠቀም ይቻላል።


የወገብ ዙሪያ ከዳሌ ስፋት ጥምርታ (Waist-to-Hip Ratio): በእምብርት ልክ ያለው የወገብ ስፋትን ከዳሌ ስፋት ጋር የሚያነጻጽር መለኪያ ነው። የወገብ ከዳሌ ጥምርታ ከፍ ካለ በሆድ አካባቢ የተከማቸ ብዙ ስብን (belly fat) ይጠቁማል። ይህም ከBMI የበለጠ የልብ እና የስኳር ህመም ተጋላጭነትን ይተነብያል። ይህ ልኬት ከBMIና ከሌሎችም በጣም የተሻለ የሜታቦሊክ ጤና አመላካች እንደሆነ በርካታ ጥናቶች አረጋግጠዋል።


ሌላኛው ልኬት ደግሞ የወገብ ስፋት (Waist Circumference) ሲሆን አደገኛ የሆድ ውስጥ ስብን ለመገመት ሁነኛ መሳሪያ ነው።


ሶስተኛው መለኪያ የሰውነት ስብ መጠን መቶኛ (Body Fat Percentage) ሲሆን ይህ ሜትሪክ ከሰውነታችን ክብደት ውስጥ ስብ ስንት ፐርሰንቱን ይይዛል የሚለውን ይገምታል። የሰውነታችንን የስብ መጠን በፐርሰንት የሚለዩ የሰውነት ስብጥር ትንተና ከሚሰራባቸው መንገዶች መካከል የቆዳ እጥፋት መጠን (skinfold measurements)፣ ባዮኤሌክትሪካል ኢምፔዳንስ (bioelectrical impedance) እና ልዩ ኤክስሬይ (DEXA scan) የመሳሰሉ ዘዴዎች  ይገኙበታል።


በግርድፉ ሲታይ BMI ምንም ይሁን ምን የወገብ ከዳሌ ስፋት ጥምርታ ከ1 በላይ ከሆነ ወይም የወገብ ዙሪያ ስፋት ከ80 ሳንቲ ሜትር በላይ ከለካ ጤናማ ያልሆነና መፍትሄ የሚሻ አደገኛ የስብ ክምችት አለ ማለት ነው። የሰውነት ስብ መቶኛ ለወንድ ከ25% እና ከዚያ በላይ እንዲሁም ለሴት 30% እና ከዚያ በላይ ከሆነ ከልክ ያለፈ ውፍረት እንደሆነ ይቆጠራል፣ ምንም እንኳን የBMI ቁጥር ከተለመደው ኖርማል ክልል ባይበልጥም። ሰዎች ኖርማል ክብደትና መደበኛ BMI ሊኖራቸው ይችላል ነገር ግን አደገኛ የጤና ጠንቅ የሆነውን በሰውነት ውስጥ የተከማቸ ስብ (Visceral fat) ምክንያት ለጤና ችግሮች የተጋለጡ ናቸው።


በተጨማሪም የደም ምርመራዎች ለምሳሌ የስኳር፣ ኢንሱሊን፣ የኮሌስትሮል መጠን እና የሰውነት መቆጣት ምልክቶች (ለምሳሌ C-reactive protein) ያሉ ጠቋሚዎች የሜታቦሊክ ችግሮችን ሊያሳዩ ይችላሉ።


BMI ብቻውን ውፍረት ይኖርብን አይኖርብን መለየት ስለማይችል እንዲህ አይነት ምርመራዎች ሰዎች የሰውነታቸውን ስብጥርና ውቅር በተሻለ ሁኔታ እንዲረዱ እና ከባድ የጤና ችግሮችን ለማስወገድ የመከላከያ ህክምና ስልቶችን በጊዜ እንዲተገብሩ ያስችላል። ውፍረትን ለመመርመር ወይም የጤና ተጋላጭነትን ለመገምገም BMI ብቻውን በቂ አይደለም። መደበኛ BMI ያለው ሰው ከፍተኛ የጤና አደጋዎችን የሚያስከትሉ ጎጂ የሰውነት ስብ ክምችቶችን ሊይዝ ይችላል።  የክብደታችን ቁጥር ባሻገር የሰውነት አካላዊ ስብጥርን መረዳት አስፈላጊ የሚሆነው ለዚህ ነው። ውፍረት ሲባል ከክብደትና ከBMI ቁጥር በላይ ውስብስብነት ያለው መልከ ብዙ ህመም ነው።


መደበኛ ክብደት ያለው ውፍረት ህክምና ምን ይመስላል?


ይህ የውፍረት አይነት በዋናነት የአኗኗር ዘይቤን በማስተካከል መታከም የሚችል ነው። ውጤታማ ከሆኑት መንገዶች ጥቂቶችን እንደሚከተለው ናቸው።


የተመጣጠነ አመጋገብ ማዘውተር ወሳኝ ነው። በጤናማ ንጥረ-ምግብ የበለፀጉ ምግቦችን አዘውትሮ መመገብ የሰውነት ስብን ለመቆጣጠር ይረዳል። ይህ ከውጭ ወፍረው ለሚታዩ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ሰው የሚገባ አመጋገብ ነው።


መደበኛ የሰውነት እንቅስቃሴን ማካተት። በተለይም የጥንካሬ ስፖርት መስራት። ጡንቻን የሚያፈረጥሙና የሚያጎለብቱ የጥንካሬ ስፖርቶች መስራት የስብ መጠንን ለመቀነስ ይረዳል፣ ጡንቻው ሲሰራ ሜታቦሊዝምን ስለሚጨምር።


መደበኛ ምርመራና ክትትል ማድረግ መደበኛ የሰውነት ክብደት ላላቸው ሰዎችም ቢሆን የተደበቀ ከውጭ የማይታይ ውፍረትን አስቀድሞ ለመለየት ይረዳል።


ማጠቃለያ


መደበኛ ክብደት ያለው ውፍረት ለብዙዎች የማይታይ የተደበቀ አደጋ ነው። በተለይም ቀጭን መስለው ነገር ግን ከፍተኛ የሰውነት ስብ ያላቸው ሊኖሩ ይችላሉ። ይህንን ሁኔታ መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው።  ምክንያቱስ ቢሉ እንደተለመደው የሚታየው ውፍረት ሁሉ የጤና ችግሮችን ስለሚያመጣ አስቀድመን የጤና ማሻሻያ ተግባራዊ እርምጃወችን በመውሰድ ብዙ ሰዎች ጤናማ ህይወት እንዲመሩ መርዳት እንችላለን።


ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ይዘቶች ወይም ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና የጤና ባለሙያዎን ያማክሩ።


ተጨማሪ ምክር፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት በኢሜል፦ contact@melakutaye.com እና ስልክ፦ +251921720381 ማግኘት ይችላሉ። ለግል ህክምና ዶ/ር መላኩ ወይም የስራ ባልደረቦቹ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ። ይህን መረጃ ጠቃሚ ሆኖ ካገኙት ለሌሎች ያጋሩ።

1 thought on “መደበኛ ክብደት ያለው ውፍረት (Normal Weight Obesity)፡ በቀጭንነት የተደበቀ ውፍረት”

  1. Dr Melkamu Bezabih Yitbarek

    The information is very vital. It gives a good knowledge.Anybody should read and take his/ her awareness.
    Keep up this good work.

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top