በዶ/ር መላኩ ታዬ (በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳርና ውፍረት ህክምና ስፔሻሊስት)
እስቲ አስቡት አመጋገብ አስተካከለው፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ወጥረው ሰርተው ከወራት እልህ አስጨራሽ ልፋት በኋላ ቦርጭን ልክ አስገባችሁት እንበል። በዚህ ስኬት ደስታና ፈንጠዝያ ይሆናል። በሰራችሁት አስደናቂ ተግባር ኩራት ይሰማችኋል። ግን ሰብሰብ ያለውን ወገብ ‘እኔ እኮ እችላለሁ፤ 8 ቁጥር ሽንቅጥ አልኩ እኮ!’ አድንቀው ሳይጨርሱ አንድ የሚያበሳጭ ነገር ይከሰታል – ያ የአራገፉት ክብደት ቀስ በቀስ መመለስ ይጀምራል፤ ጮማ ድጋሜ ከሸሚዝ ማሸትለክ ነገር ያመጣል። የተቻለውን ምንም ያህል ጥረት ብታደርግ የቀነስከውን ክብደትህን ማስጠበቅ (sustaining weight loss) ወይም የበለጠ መቀነስ (losing weight further) ትልቅ ፈተና ይሆናል።
እንዲህ አጋጥሞህ የሚያውቅ ከሆነ ብቻህን አይደለህም። ያንተ/ያንች ጥፋት አይደለም። በጣም የተለመደ ሁኔታ ነው። ክብደት መጨመር በጣም ቀላል ሂደት ሲሆን አንድ ኪሎ ለመቀነስ እና የተቀነሰውን ማስጠበቅ ግን ራስ ዳሽን እንደመውጣት ዳገት ነው።
ክብደትን መቆጣጠር የምናስገባው እና የምናስወጣው ካሎሪ ምጥጥን ጉዳይ ብቻ አይደለም። ለብዙ አመታት ሲታመንበት የነበረው የክብደት አስተሳሰብ የሚገባና የሚወጣ ካሎሪ መጠን (Calories-In, Calories-Out) ማመጣጠን የሚል ነበር። ‘ትንሽ ከበሉ እና ብዙ ከተንቀሳቀሱ ክብደት ይቀንሳል’ ይባል ነበር – የሚመገቡትን ምግብ ከመጠኑ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ከጨመሩ ክብደት መቀነስ ጥርጥር የለውም የሚል ንድፈ-ሃሳብ! ይህ የክብደት እሳቤ በከፊል ትክክል እንዳልሆነ አሁን አሁን አዳዲስ ጥናቶች ተስማምተውበታል። ለዚህም ነው የሃይል ሜታቦሊዝም (energy metabolism) ከካሎሪ ገቢና ወጪ ቁጥር በላይ ውስብስብ ተለዋዋጭ ሂደት ነው የሚባለው።
ይልቁንም የሰውነታችን ሃይል አጠቃቀም በጣም ዳይናሚክ ሂደት ነው። ክብደትን መቀነስ ከባድ ሆኖ ሳለ መልሶ መወፈር ግን በጣም ቀላል የሆነው ለምንድነው የሚለው ሳይንስ ሙሉ በሙሉ ያልተፈታ እንቆቅልሽም ጭምር ነው። የራሳችን ሆርሞኖች፣ ሜታቦሊዝም እና በአኗኗር ሁኔታዎች መካከል የሚደረግ ተለዋዋጭ መስተጋብርን የሚያካትት በጣም የተወሳሰበ ፊዚዮሎጂ አለው።
ሰውነታችን ክብደት ከተወሰነ ቁጥር በላይ እንዳይቀንስ ጥርሱን ነክሶ መዋጋት ዋና ሰዋዊ ባህሪው ነው። ክብደት በሚቀንስበት ጊዜ ሰውነታችን ያጋጠመውን የካሎሪ እጥረት ለመቋቋም በተለያዩ መንገዶች አዳዲስ የሜታቦሊክ አሰራር ይላመዳል (Metabolic adaptation)። ምግብ ስንቀንስ ሰውነታችን መአት እንደመጣበት በማሰብ ማካካሻ መንገድ ይዘይዳል። የሜታቦሊዝም ፍጥነት ዝግ እንዲል በማድረግ ከበፊቱ ያነሰ ካሎሪ ያቃጥላል። ሰውነት የሃይል ቁጠባ ያበዛል፤ ለክፉ ቀን እያለ ማከማቸት ይጀምራል።
የረሃብ ሆርሞኖች እየጨመሩ ይሄዳሉ። በተለይም ግሬሊን (ghrelin) የተባለው ሆርሞን ከአንጀት እጥፍ ድርብ እየመነጨ የረሃብ ስሜት እንዲሰማን በማድረግ የምግብ ፍላጎትን ይጨምራል። አምጣ አምጣ ይወተውታል።
ይህ የሜታቦሊዝም መላመድ ሂደት በምግብ እጥረት ጊዜ በሃይል ቁጠባ የረሃብ ዘመንን እንድንሻገር ታስቦ የተፈጠረ ሰዋዊ ባህሪ ቢሆንም ምግብ በቀላሉ ማግኘት በሚቻልበት የተትረፈረፈ አለም ውስጥ ግን ውፍረትን ለማከም ትልቅ እንቅፋት ይሆናል። አሁን ላለንበት ዘመን ኢ-ጠቃሚ (mal-adaptive) የፊዚዮሎጂ ለውጥ ነው። ክብደት እንዳይቀንስ ይሞግታል። የራሳችን ሰውነት የሚያመነጫቸው ሆርሞኖች በድብቅ ይታገሉናል።
ክብደት የመቀነስ ሂደት የሚረጋበት (Weight Loss Plateaus) ተፈጥሯዊ የሰውነት አሰራር
ሰዎች የክብደት መቀነስ እቅድ አውጥተው ተፍ ተፍ ሲጀምሩ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታት/ወራት ውስጥ ፈጣን ስኬት ያስመዘግባሉ። ነገርግን ብዙም ሳይቆይ ይህ ሂደት የመጨረሻው አምባ (Plateau) ላይ ይቆማል። መጀመሪያ ላይ ሲሰራልን የነበረ እያንዳንዱ አመጋገብ፣ እያንዳንዱ ስፖርት፣ እያንዳንዱ መድሃኒት ውሎ አድሮ ይለግማል። ክብደታችን ከዚህ በኋላ አልወርድም ፈቀቅ አልልም ብሎ ይገግማል።
ይህ የሚከሰተው ሰውነት የክብደት መቀነሱን እንደ ስጋት ስለሚገነዘብ እና በምላሹም ሜታቦሊዝም ቀስስስ እንዲል በማድረግ ካሎሪ ማቃጠል ይቀንሳል፤ ይባስ ብሎ የረሃብ ስሜት ይለቅብናል። ሰውነታችን በቻለው አጋጣሚ ሁሉ ኃይልን ለመቆጠብ ይሞክራል። በተለይ ክብደት ስንቀንስ የጡንቻን መሳሳትና መድከም የሚያስከትል ከሆነ ጭራሽ የበላናት አንድ እፍኝ ምግብ እንኳ አልቃጠል ትላለች። ያልተቃጠለ ትርፍ ምግብ ሁሉ ይከማቻል፣ ክብደት ይሆናል።
ይህ ሁሉ ፕሮሰስ ክብደት የበለጠ እንዳይቀንስ ጥብቅና ይቆማል። መክሳትን አጥብቆ ይከላከላል።
ክብደትን ለመቀነስ የሰውነታችን እምቢ ማለት (Weight Loss Resistance)
ክብደትን ለመቀነስ የሰውነታችን እምቢ ማለት ሲባል ምግባ ስፖርት እያስተካከልን ሳለ ክብደት መቀነስ አለመቻል ነው።
ከአንጎላችን ወሳኝ ክፍሎች ውስጥ አንዱ የሆነው ሃይፖታላመስ (hypothalamus) የክብደት ቁጥጥር ማእከል ሆኖ ያገለግላል። ይህ ትንሽ ነገር ግን ኃይለኛ የአንጎል ክፍል የረሃብ ስሜትን፣ የምግብ ፍላጎትን እና የካሎሪ መቃጠል ሂደትን የሚቆጣጠር ማእከላዊ አዛዥ ነው። ይህን የሚያደርገው የተወሰነ የሰውነት ክብደትን ለመጠበቅ በሚሰሩ የሆርሞኖች እና የነርቭ መረብ መስተጋብር ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ከሚሳተፉት ቁልፍ ሆርሞኖች አንዱ ሌፕቲን (leptin) ነው።
ሌፕቲን ‘የጥጋብ ሆርሞን (satiety hormone)’ ተብሎ ይጠራል። የሚመነጨው ከስብ ህዋሳት (adipocytes) ሲሆን በደም ውስጥ ወደሃይፖታላመስ በመዝለቅ ጥጋብ እንዲሰማን ያደርጋል፤ የረሃብ ስሜትን ይቆጣጠራል።
ከመጠን ያለፈ ውፍረት (obesity) ባለባቸው ሰዎች ላይ ግን ሌፕቲን ስራውን በአግባቡ አይሰራም (leptin resistance)። አንጎላችን ለሌፕቲን መልእክቶች ምላሽ መስጠት ያቆማል። ይህ ማለት ሰውነት ስንበላ እንደ ሚገባው መጥገብን እና መርካትን አይሰማውም። በተቃራኒው የተራበ እንዲመስለው ስለሚሆን ካሎሪ ማቃጠል ይቀንሳል።
ይህ አስከፊ ዑደት በሂደት ክብደት መቀነስን በጣም ከባድ ያደርገዋል እና እንደገና መልሶ መወፈር ለብዙዎች የማይቀር ይሆናል።
ክብደትን የመቀነስ ሂደትን ከባድ የሚያደርጉ ማህበራዊ ጉዳዮች
ከላይ የጠቀስናቸው ባዮሎጂካል ምክንያቶች በተጨማሪ ክብደትን መቀነስ በጣም ከባድ የሚያደርጉ በርካታ ጤናን የሚነኩ የአኗኗር ዘይቤዎች እና የአእምሮ ጤና ጉዳዮችም ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳድራሉ። ብዙ ማህበራዊ ተጽእኖዎች የእያንዳንዱን ግለሰብ ክብደት የመቀነስ ጥረቶች የሚያደናቅፉ ናቸው። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እንድንበላ፣ እንድንጠጣ እና እንዳንቀሳቀስ የሚገፋፋ ማህበራዊ ጫና ሁላችንም የተከበብን ነን።
ጤናማ የአመጋገብ ዕቅድና ለውጥን በጥብቅ መከተል በተለይም በቀጣይነት መተግበር በጣም ከባድ ነው። ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ልማድ በቀላሉ አይፋታም፣ አይቀየርም። ወዳጅ ሁሉ ‘ኧረ ይህቺ ምን አላት፣ አፈር ስሆን ብላልኝ እንጂ’ እያለ ያጎርስሃል፣ እንድትወፍር ይተባበርሃል። ውፍረት ሲታከም ቤተሰብ፣ ወዳጅና ጎረቤት ሁሉ ማስተማር ይፈልጋል የሚባለው ለዚህ ነው – ማህበራዊ ከባቢያችን የጀመርነውን የአመጋገብ ለውጥ ሊቀለብስብን ስለሚችል።
ዘመናዊ ህይወትም ለረጅም ሰአት መቀመጥ የሚያስገድድ ስለሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ይገድባል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኑሯችን የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በሚገድቡ ብቻ ሳይሆን ረዘም ላለ ጊዜ መቀመጥ በሚጠይቁ ሁኔታዎች ውስጥ መኖር አስገዳጅ እየሆነ መጥቷል።
ጭንቀትና ድብርት የተመጣጠነ ምግብ ምርጫን ሊያዛቡ ይችላሉ። በተለይም በዘላቂነት ቋሚ የአመጋገብ ማሻሻያ ለማድረግ ይገዳደራሉ። እንቅልፍ ማጣትም ከሆርሞን መዛባት ጋር የተቆራኘ ሲሆን ረሃብን በማባባስ ከፍተኛ የካሎሪ ይዘት ያላቸውን ምግቦች የመመገብ ፍላጎት ይጨምራል።
የክብደት መቀነስ ተቃዋሚ ፈተናዎች እንዴት ማሸነፍ ይቻላል?
የቀነሱትን ክብደት ማስጠበቅ ወይም የበለጠ መቀነስ አልቻል ካለ ተስፋ አይቁረጡ። አትችልም አይሳካልህም ቢሉህ እንዳትሰማ። የአንተ/ች ድክመት ብቻ ሳይሆን በርካታ የረጅም አመታት ክትትል ያደርጉ ጥናቶች ላይ እንደታየው ብዙ ሰዎች መጀመሪያ ላይ በምግብና ስፖርት ብቻ ከፍተኛ መጠን ያለው ክብደት መቀነስ ቢችሉም አብዛኞቹ በጊዜ ሂደት መልሰው እንደሚወፍሩ አመላክተዋል።
ክብደትን ወደነበረበት የመመለስ ትግል የሰውነት ተፈጥሯዊ ምላሽ ነው። ክብደትን መቀነስ እና የቀነስነውን ክብደት ማስጠበቅ በጣም አስቸጋሪ የሚያደርገው የሆርሞን ለውጥ ነው። እነዚህን ሆርሞኖች መዋጋት በጣም ከባድ ነው። የቀነስነውን ክብደት ለረዥም ጊዜ አስጠብቆ ለማቆየት የሚከለክለንን ይህን ውስጣዊ ተቃዋሚ ሃይል አስካላሳመነውና እስካልሸወድነው ድረስ አንዳች የማይተኛ ተፈጥሯዊ ሂደት ነው።
ይህን ጊዜ ብቻን ታግለን ለማሸነፍ ሊከብድ ይችላል። ስለሆነም ይህን የክብደት መቀነስ አምባ ለማለፍ የውፍረት ህክምና የጤና ባለሙያ የታገዘ የክብደት ህክምናና ምክር ያስፈልጋል።
ወደሚፈልጉት ክብደት ልክ ለመድረስ እና ለረጅም ጊዜ ክብደት ሳይመለስ ለማቆየት ቀጣይነት ያለው ተነሳሽነት፣ ትዕግስት እና ጽናት የሚጠይቅ የዕድሜ ልክ ጥረት ግድ ነው። የበለጠ አመጋገብ በማስተካከል የሙጥኝ መጽናት ይገባል። የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ከበፊቱ ጨመር አድርጎ በመስራት (በተለይ የጥንካሬ ስፖርት በማካተት የጡንቻን ጥንካሬ መጠበቅ) ክብደትን ማስተካከልና ጤናን የበለጠ ማበልጸግ ይቻላል። እንቅልፍ ማስተካከል፣ ጭንቀት መቀነስ፣ ድባቴን መታከምም እንዲሁ ጠቃሚ ነው።
እንዳስፈላጊነቱ በሃኪም የታዘዙ ፀረ-ውፍረት መድሃኒቶችን (Anti-obesity medication) በመውሰድ ፈታኝ የሆነውን የረሃብ ስሜት ያስታግሳሉ፤ የምግብ ፍላጎትን በመቀነስ ምግብ ሳናውቀው እንዳናበዛ ይረዳሉ። እነዚህ መድሃኒቶች መታዘዝ ያለባቸው በውፍረት ህክምና ስፔሻላይዝ ያደረገ ይህ ካልሆነ በውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሃኪም ቢሆን ይመከራል። መርሳት የሌለብን ነገር ቢኖር የፀረ-ውፍረት መድሃኒት በሚጠቀሙበት ጊዜ ጤናማ አመጋገብን፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን እና ሌሎችንም የአኗኗር ለውጦች ማስቀጠል ያስፈልግዎታል። መድሃኒቱ ተጨማሪ አጋዥ እንጅ የሻተንን አብዝተን ለመብላትና ስፖርት ላለመትጋት ሰበብ ይሁን ማለት አይደለም።
ከመድሃኒቶች ባሻገር የሜታቦሊክ ቀዶ ጥገና (metabolic/bariatric surgery, weight loss surgery) በተለይ መጠነ ክብደታቸው በጣም ከፍተኛ ለሆነ ሰዎች ሊሰራ ይችላል።
ማጠቃለያ
ክብደት መቀነስ ፈታኝ ነው። የቀነስነውን ክብደት ማስጠበቅም እንዲሁ ከባድ ነው። ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ሰውነታችን ራሱን ከረሃብ ስጋት ለመከላከል ክብደትን በጥብቅ የሚጠብቅ ተደርጎ ከጥንተ ፍጥረቱ የተነደፈ ስለሆነ ነው። ይህንን ፈተና ለመሻገር ከበስተጀርባ በድብቅ የሚታገሉንን ሆርሞኖችና ሜታቦሊክ ለውጥ መረዳት የበለጠ የስትራቴጂካዊ ተግባራትን እንድንወስድ ይረዳል።
ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ይዘቶች ወይም ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና የጤና ባለሙያዎን ያማክሩ።
ተጨማሪ ምክር፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት በኢሜል፦ contact@melakutaye.com እና ስልክ፦ +251921720381 ማግኘት ይችላሉ። ለግል ህክምና ዶ/ር መላኩ ወይም የስራ ባልደረቦቹ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ።
This is very informative and a very concerning issue for most peoples including me. Thank you for bringing this to our attention and briefing this secret which we all struggle.
Thank you again Dr. Melaku.
Thanks Doc, do u work anywhere? If u do, can we get the clinic name please
Dr. Melaku’s clinic schedule (October to November 30, 2024)
Private clinic
1. Heal Venture medical center
🕐 Monday, & Wednesday afternoon.
Book at +251926454647
Address: Megenagna 24 area infront of Sidra Hotel.
ከለም ሆቴል ወደ 24 የሚወስደዉን ድልድይ እንደጨረሱ በመጀመሪያው መታጠፊያ ወደ ቀኝ 50ሜ ገባ ብሎ።
📍Location- https://maps.app.goo.gl/1j52DhHCnxQ2bwgm6?g_st=i
2. Gesund Medical & Cardiac center
🕑 Wednesday & Saturday morning.
Book at +251994000095
0955927583
Location: near CMC Michael
https://maps.app.goo.gl/e8XngmFG3EP5U2DDA
Public hospital
1. Tikur Anbessa Specialised Hospital, Addis Ababa University
💚💛❤️
Melaku Taye, M.D.
Let us connect at Blog (https://melakutaye.com/) | TikTok (https://www.tiktok.com/@hakimmelaku) | Telegram (https://t.me/hakimmelaku) | Google Profile (https://g.page/r/CaCoYXX0TnQrEBE/review)