የኮሌስትሮል ህመም የሁሉም ሰው ጉዳይ እንጂ ጮማ ለሚበሉ ሀብታሞች ወይም ቦርጭ ላላቸው ብቻ አይደለም! ማንኛውንም ሰው ሊያጠቃ ይችላል — አንተ/ችንም ጭምር!
በየእለቱ የህክምና ስራዬን አዳጋች ከሚያደርጉብኝ ተግዳሮቶች መካከል አንደኛው በተለምዶ የኮሌስትሮል ህመም እና ተያያዥ የልብና የደም ቧንቧ በሽታዎች በሀብታሞች፣ ቦርጭ ባላቸው ግለሰቦች ወይም ጮማ ስጋ የሚያዘወትሩ ሰዎችን ብቻ የሚያጠቃ በሽታ ነው የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ነው። የኮሌስትሮል ህመም ‘የብልጽግና’ በሽታ (disease of affluence) ብቻ እንደሆነ ነው የሚታሰበው። ማለትም ቅባት የበዛባቸው ምግቦችን የሚመገቡ፣ ጮማ የሚቆርጡ፣ ያማራቸውን መብላት የሚችሉ ወይም ወፍራም የሆኑ ሰዎች ብቻ የሚያጠቃ እንደሆነ ይታሰባል። በዚህ የተሳሳተ ግንዛቤ ምክንያት ብዙ ሰዎች ወፍራም ስላልሆኑ፣ ጮማ ስላማያዘወትሩ ወይም ሃብታም ስላልሆኑ ብቻ ከኮሌስትሮል ችግሮች ነፃ እንደሆኑ እንዲያምኑ ያደርጋቸዋል። እንደ አለመታደል ሆኖ ይህ አስተሳሰብ አሳሳች ብቻ ሳይሆን አደገኛም ነው።
የኮሌስትሮል ህመም ክብደት፣ የአመጋገብ ዘይቤ፣ ማህበራዊ ሁኔታ፣ የሃብት መጠን፣ ሃይማኖት፣ ዘር፣ እድሜና ጾታ ሳይለይ በማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት ይችላል።
የኮሌስትሮል ህመም የሃብታሞች በሽታ ብቻ አይደለም። ይልቁንም የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኑሮ ጫና ያለባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ የበለጠ ይበረታል።
ቀጭን ሰዎችም ከኮሌስትሮል ህመም ነፃ አይደሉም። መደበኛ ወይም ዝቅተኛ ክብደት ያላቸው ያላቸው ሰዎች በዘረመል ወይም በሌላ ሜታቦሊዝም በሚያዛቡ ህመሞች ምክንያት የኮሌስትሮል መጠናቸው አስደንጋጭ ደረጃ የሚሆንበት ብዙ አጋጣሚዎች አሉ። የኮሌስትሮል መጠን ሁልጊዜ ከውጭ አይታይም። በደም ምርመራ ብቻ ነው ማወቅ የሚቻለው።
አመጋገብ በኮሌስትሮል መጠን ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያለው ቢሆንም ኮሌስትሮል ከቅባታማ ምግብ ብቻ አይደለም የምናገኘው። ምንም ጮማ የማይቀምስ ወይም ምንም የእንሣት ተዋጽኦ የማይወስድ ሰውም የኮሌስትሮል ህመም ሊኖርበት ይችላል።
ኮሌስትሮል ማንንም ሊጎዳ እንደሚችል በርካታ አሳማኝ ሳይንሳዊ ማስረጃ ያለው እውነታ ነው። በርካታ ግዙፍ አለምአቀፍ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የኮሌስትሮል ህመም ዘር፣ ሃብት፣ ክብደት፣ ጾታ እና ሌሎችም ማህበራዊና የአመጋገብ ሁኔታ አይመርጥም። ከዋነኞቹ አስደናቂ ምርምሮች ለመጥቀስ ያክል የፍራሚንግሃም ጥናት (Framingham Heart Study) አንዳረጋገጠው የተለመዱ ኮሌስትሮል አምጭ መንስኤዎች የሌላቸው (እንደ ውፍረት ወይም ከፍተኛ ቅባት ያለው አመጋገብ የሚያዘወትሩ) ግለሰቦች እንኳን ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠን ሊጠቁ እንደሚችሉና ለልብ እና የደም ቧንቧ ችግሮች ተጋላጭ መሆናቸውን ነው።
ማንኛውም ሰው የኮሌስትሮል ህመም ተጋላጭ መሆኑን መረዳት በጣም አስፈላጊ ሆኖ ሳለ እርግጥ ነው አንዳንድ ሰዎች ከሌሎች የበለጠ ለከፍተኛ ኮሌስትሮል ስጋት ያላቸው አሉ። ለአብነትም በቤተሰብ ከፍተኛ የኮሌስትሮል ችግር ያላቸው ግለሰቦች፣ እድሜ ሲጨምር፣ የተዛባ የአኗኗር ዘይቤ ያላቸው፣ ቅባት ወይም ስብ የበዛባቸው ምግቦች የሚያዘወትሩ፣ ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው፣ አልኮል የሚጠጡ ወዘተ ከሌሎች ሰዎች የኮለስትሮል ህመም የመያዝ እድላቸው ከፍ ያለ ነው።
ከፍተኛ ኮሌስትሮል በአመዛኙ ምንም ምልክት ስለሌለው ብዙ ሰዎች በጣም እስኪዘገይ ድረስ ችግር እንዳለባቸው አይገነዘቡም። ስለሆነም የኮሌስትሮል ምርመራ እድሜያቸው ከ20 አመት በላይ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ አስፈላጊ ነው። ሁሉም አዋቂዎች ከ20 አመት ጀምሮ የኮሌስትሮል መጠናቸውን በየጊዜው መመርመር አለባቸው። ቀላል የኮሌስትሮል ምርመራ በማድረግ በልብ ሕመም ወይም በአንጎል ውስጥ ደም ከመፍሰሱ በፊት ለአደጋ የተጋለጡ ሰዎችን በመለየት ሕይወትን ማዳን ያስችላል።
የኮሌስትሮል ችግር ለሀብታሞች እና ለቦርጫሞች ብቻ አይደለም! የኮሌስትሮል ህመም ሁሉንም ሰው ይጎዳል – ዛሬውኑ ይመርምሩ። የኮሌስትሮል ስፔሻሊስት ሃኪም በማማከር ጤናዎትን ይጠብቁ።
ማስታወሻ፡ በዚህ ጽሁፍ የተካተቱት ይዘቶች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና የጤና ባለሙያዎን ያማክሩ።
ይህ መረጃ ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኙት ተስፋ አደርጋለሁ! ተጨማሪ ጥያቄዎች ካሉዎት የዚህን መረጃ ያሰናዳዉን ዶ/ር መላኩ ታዬ እና የስራ ባልደረቦቹን በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል ማግኘት ይችላሉ።
thank you, doctor. betam ameseginalehu, mestegidoh betam des yilal, endatiselechen, bezihu ketil. Egziabher yirdah