የኮሌስትሮል ምርመራ፡ ለማን፣ መቼ እና ትክክለኛ መጠን?

ኮሌስትሮል ለልብና የደም ስር የጤና ችግሮች አንዱና ዋነኛው መንስኤ ነው። የኮሌስትሮል ምርመራ ከደም ናሙና የሚሰራ ሲሆን የኮሌስትሮል መጠን በትክክለኛው መጠን ውስጥ መሆኑን ለማወቅ አይነተኛ መንገድ ነው። በዚህ ጽሑፍ ስለ ኮሌስትሮል ምርመራ ማወቅ ያለብዎትን መሰረታዊ ጉዳዮች እናብራራለን – ምርመራው አስፈላጊነቱ ምንድን ነው? መቼ መመርመር አለብዎት? ምን ይታዘዛል? የምርመራ ውጤቱ ምን መምሰል አለበት?!

 

መቼ ነው የኮሌሌስትሮል ምርመራ ማድረግ መጀመር ያለብን?

 

ለአብዛኛዎቹ ሰዎች የኮሌስትሮል ምርመራ በ20 አመት እድሜ መጀመር አለበት። የምርመራ ውጤቱ ትክክለኛ ከሆነና ለልብ ህመም የመጋለጥ እድሎት ዝቅተኛ ከሆነ በየ 5 ዓመቱ ብቻ ምርመራውን በመድገም ማየት ይበቃል። ነገር ግን አዲስ የልብ ህመም አጋላጭ ሁኔታ ከተከሰተ ለምሳሌ ስኳር ህመም፣ የደም ግፊት ከፍ ካለ፣ ክብደት መጨመር ወይም ሌላ የጤና ችግር ካጋጠመ ድጋሜ የኮሌስትሮል ምርመራ መታየት ሊያስፈልግ ይችላል።

 

የሚከተሉት ከፍተኛ የልብ ህመም ተጋላጭነት ያላቸው ለምሳሌ በቤተሰብ የኮሌስትሮል መመም ካለ ወይም በቤተሰብ እድሜ ብዙ ሳይገፋ የልብ ሕመም ካለ፣ ውፍረት፣ የደም ግፊት፣ የስኳር በሽታ፣ ማጨስ ወዘተ ካለ መደበኛ የኮሌስትሮል ምርመራዎችን ከ20 አመት በፊት ቀደም ብለው መጀመር ጥሩ ነው።

 

ከ40 ዓመት በላይ ለሆኑ ባጠቃላይ የጤና ሁኔታ ላይ በመመስረት ቶሎ ቶሎ ቢያንስ በአመት አንዴ ምርመራ ማድረግ ሊመከር ይችላል።

 

የኮሌስትሮል ምርመራ ምን ምን ይይዛል?

 

መደበኛ የኮሌስትሮል ምርመራ (Lipid profile) አራት ቁልፍ ምርመራዎችን ያካትታል። እነዚህም አጠቃላይ ኮሌስትሮል፣ ጎጂ ኮሌስትሮል (LDL-C)፣ ጥሩ ኮሌስትሮል (HDL-C) እና ትራይግሊሲራይድ (triglyceride) ይይዛል። አንዳንድ የተራቀቁ ላቦራቶሪዎች ApoB መጠን ሊለኩ ይችላሉ። የ ApoB መጠን መለካት ከኮሌስትሮል መጠን የተሻለ የደም ስር ጤና ተጋላጭነትን ለማዎቅ ይረዳል። በተጨማሪም አድቫንስድ የሆኑ ላቦራቶሪዎች ካሉ በህይወት ዘመን አንዴ Lp(a) መጠን መለካት ወሳኝ እንደሆነ በርካታ ጥናቶች አረጋግጠዋል።

 

ትክክለኛ የኮሌስትሮል መጠን ስንት ነው?

 

ለጤነኛ ሰው (ውፍረት፣ ስኳር ህመም፣ የደም ግፊት ወይም መሰል የደም ስር ህመም የሌለበት እንዲሁም አልኮል የማይጠጣ እና ሲጋራ የማያጨስ) የኮሌስትሮል ምርመራዎች የሚከተለውን መምሰል አለባቸው።

 

 

    • ጠቅላላ ኮሌስትሮል (total cholesterol) ከ200 mg/dL በታች መሆን አለበት።

    • ጎጂ ኮሌስትሮል (LDL) ከ100 mg/dL በታች መሆን አለበት።

    • ጥሩ ኮሌስትሮል (HDL) ከ40 mg/dL በላይ መሆን አለበት።

    • ትራይግሊሲራይድ (Triglycerides) ከ150 mg/dL በታች መሆን አለበት።

ልብ ማለት ያለብን ትክክለኛ ወይም ኖርማል የኮሌስትሮል መጠን የሚባል በአብዛኛው የለም። ቁጥሩ የሚታየው ከአጠቃላይ የልብ ህመም ተጋላጭነት (cardiovascular risk) ጋር የሚሰላ መሆን ነው ያለበት። የስኳር ህመም፣ የልብ ሕመም ወይም ሌሎች የሚታዎቅ ህመም ካለብዎ ወይም የልብ ሕመም ተጋላጨነት ከፍተኛ ከሆነ፣ ለእርስዎት የሚሆን እንደ እድሜዎትና ጤና ሁኔታ የሚዎሰን  የኮሌስትሮል ግብ ሊያስፈልግዎት ይችላል።  በተለይም ጎጂ የኮሌስትሮል መጠንን በተቻለው ልክ በደንብ ማውረድ የተሻለ ጤናን ያመጣል (the lowest is the best)።

 

የኮሌስትሮል ምርመራ አስፈላጊነት

 

ከፍ ያለ የኮሌስትሮል መጠን በተለይም ‘ጎጂ’ ኮሌስትሮል (LDL-C) በደም ቧንቧዎችዎ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ሲጠራቀም የደም ስሩን ይደፍነዋል። የኮሌስትሮል ምርመራ ይህንን ለልብ ህመም፣ ስትሮክና ሌሎችም የደም ስር ህመሞች ያለንን ተጋላጭነት ለመለካት አንዱ መንገድ ነው።

 

ሌላው ምርመራውን አስፈላጊ የሚያደርገው ከኮሌስትሮል ጋር የተያያዙ የጤና ችግሮች ምልክት አልባ (asymptomatic) በመሆናቸው ነው። ምንም እንኳን ጥሩ የጤንነት ስሜት ቢሰማን ምንም ምልክት ሳይታይበት የኮሌስትሮል መጠን ከፍ ብሎ የጤና ችግሮችን ሊያመጣ ይችላል። የደም ስር ህመሞች ስር ሳይሰዱ ለማከምና ለመከላከል አስቀድሞ ለማወቅ የኮሌስትሮል ምርመራ ማድረግ ቀላል እና ውጤታማ ከሆኑ መንገዶች አንዱ ነው። በመደበኛነት በመመርመር የኮሌስትሮል መጠንዎን መቆጣጠር እና ስለ ጤናዎ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ማድረግ ይችላሉ።

 

ያስታውሱ፣ ኮሌስትሮል አንዱ የጤናማነት መለኪያ አንድ ክፍል ብቻ ነው። ጤናማ አመጋገብ፣ መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ አለማጨስ እና ጤናማ ክብደትን መጠበቅ ኮሌስትሮልን ለመቆጣጠር እና ለልብ ህመም ተጋላጭነትን ለመቀነስ ወሳኝ ናቸው።

 

ይህ ትምህርታዊ ጽሁፍ ኮሌስትሮል በጤናዎ ላይ ስላለው ተጽእኖ በደንብ እንዲረዱ ለማገዝ ያለመ ተከታታይ ትምህርት ሁለተኛው ክፍል ነው። በሚቀጥሉት ክፍሎች ኮሌስትሮል ልክ ለማስገባት ማድረግ ያሉብን የአኗኗር ለውጦችን፣ ህክምናዎችን እና ስለ ኮሌስትሮል የተሳሳቱ አመለካከቶችን በጥልቀት እንመረምራለን።

 

ማስታወሻ፡ በዚህ ጽሁፍ የተካተቱት ይዘቶች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና የጤና ባለሙያዎን ያማክሩ።

 

ይህ መረጃ ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኙት ተስፋ አደርጋለሁ! ተጨማሪ ጥያቄዎች ካሉዎት የዚህን መረጃ ያሰናዳዉን ዶ/ር መላኩ ታዬ እና የስራ ባልደረቦቹን በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል ማግኘት ይችላሉ። ውድ የሆነውን ጤናዎትን ለመጠበቅ ምን ማድረግ እንዳለብዎት ለማዎቅ ተጨማሪ ተግባራዊ ምክሮችን በድህረ ገጽና ማህበራዊ ሚዲያዎቻችን @hakimmelaku ይከታተሉ!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top