ለመሆኑ የልብና ተያያዥ የደም ስር ህመም ስጋትን በአስተማማኝነት ለመቀነስ የሚረዳው የኮሌስትሮል ህክምና ግብ ምን መሆን አለበት?
ኮሌስትሮልን በተገቢው ሁኔታ ማከም የልብን እና ተያያዥ የደም ስር ህመሞችን ተጋላጭነት ለመቀነስ ይረዳል። ከፍ ያለ የኮሌስትሮል መጠን በተለይም የጎጂ ኮሌስትሮል የሚፈለገውን ያክል ቁጥጥር ውስጥ አለመሆን ለልብ ድካም፣ ለስትሮክ እና ሌሎችም የደም ስር ህመሞች ተጋላጭነት በእጅጉ እንደሚጨምር ያለጥርጥር የተረጋገጠ ሳይንስ ነው።
ኮሌስትሮልን ለማከም በርካታ ውጤታማ እና ወጭ ቆጣቢ ህክምናዎች ያሉት ቢሆንም በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ተገቢውን ትኩረት ስላልተሰጠው ተላላፊ ያልሆኑ የልብና የደም ስር ህመሞች እንደወረርሽኝ እየተሳፋፉ መጥተዋል።
በዚህ ጽሁፍ በ2019 በታተመው የአውሮፓ የልብ ማህበር የኮሌስትሮል ህክምና መመሪያ ላይ በመመርኮዝ የእያንዳንዱን ሰው የልብ ህመም ተጋላጭነት መሰረት ያደረገ የኮሌስትሮል ሕክምና ግቦችን እናብራራለን። እነዚህን ግቦች በመረዳት የልብዎን ጤንነት ለመጠበቅ ተግባራዊ እርምጃወችን ይውሰዱ።
በዚህ የኮሌስትሮል ህክምና መመሪያ መሰረት ዋናው የኮሌስትሮል ሕክምና ግብ ጎጂ ኮሌስትሮልን (LDL-C) መቀነስ ነው። ምክንያቱም የደም ስር ቧንቧዎችን በመዝጋት ሂደት ዋናው ጠላት ይህ ጎጂ ኮሌስትሮል ስለሆነ ነው። የዚህ ጎጂ ኮሌስትሮል መጠን ምን ያህል መውረድ አለበት የሚለው የሚወሰነው አጠቃላይ የልብ ህመም ተጋላጭነትን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው። ስለሆነም ለሁሉም ሰው የሚሆን ተመሳሳይ ግብ ሳይሆን እንደየ ግል ተጋላጭነት የኮሌስትሮል የቁጥጥር መጠን ይለያያል።
የልብ ህመም ተጋላጭነትህ/ሽ በጣም ከፍተኛ (very high risk) ከሆነ (ለምሳሌ፡ ቀደም ሲል የልብ ድካም ወይም ስትሮክ አጋጥሞ ከነበር፣ ከስኳር ህመም ጋር የተያያዙ የደም ስር ህመሞች ካሉ) አላማው ጎጂ ኮሌስትሮልን ከ55 mg/dL በታች ማውረድ ነው።
የልብ ህመም ተጋላጭነትህ/ሽ ከፍተኛ (high risk) ከሆነ (ለምሳሌ የደም ግፊት ካለብህ፣ የስኳር ህመም፣ ወይም ሌሎች የልብ ህመም አጋላጭ መንስኤዎች ካሉ) የጎጂ ኮሌስትሮል ኢላማው ከ70 mg/dL በታች ማድረግ ነው።
የልብ ህመም ተጋላጭነትህ/ሽ መጠነኛ (moderate risk) ከሆነ የጎጂ ኮሌስትሮል ግቡ ከ100 mg/dL በታች ማድረግ ነው።
ለተቀሩት የልብ ህመም ተጋላጭነታቸው ዝቅተኛ (low risk) ለሆኑ ግለሰቦች በአጠቃላይ ግቡ ጎጂ ኮሌስትሮልን ከ 116 mg / dL ያነሰ እንዲሆን ማድረግ ነው።
| የልብ ህመም ተጋላጭነት ደረጃ | የጤና ሁኔታ ገላጮች | የጎጂ ኮሌስትሮል ግብ |
| በጣም ከፍተኛ (very high risk) | የልብ ድካም ወይም ስትሮክ ያለበት ሰውከስኳር ህመም ጋር የተያያዙ የደም ስር ህመሞች ካሉውስብስብ የሆነ በዘር የሚወረስ የኮሌስትሮል መብዛት ችግር ካለደረጃ 4 የኩላሊት ህመም ካለ | <55 mg/dl |
| ከፍተኛ (high risk) | የደም ግፊት፣ የስኳር ህመም፣ ደረጃ 3 የኩላሊት ህመም፣ሌሎች የልብ ህመም አጋላጭ መንስኤዎች ካሉ | <70 mg/dl |
| መጠነኛ (moderate risk) | እድሜያቸው ያልገፋ (እድሜ <40 አመት) እና ተጓዳኝ ህመም የሌላቸው የስኳር ህመም ታካሚዎች | <100 mg/dl |
| ዝቅተኛ (low risk) | ከላይ የተጠቀሱት የልብ ህመም አጋላጭ ምክንያቶች የሌላቸው | <116 mg/dl |
በህክምና ውስንነት ከላይ የጠቀስናቸውን ግቦች ማሳካት ባይቻል እንኳ የኮሌስትሮል መጠንን የተቻለውን ያክል መቀነስ በተለይም ኮሌስትሮልን ከመጀመርያው መጠን ቢያንስ በ50% መቀነስ የልብ ሕመምን አደጋ ለመቀነስ ትልቅ ለውጥ ያመጣል።
መደበኛ የጤና ምርመራዎች፣ የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች (እንደ ጤናማ አመጋገብ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ) እና እንዳስፈላጊነቱ የኮሌስትሮል መድሃኒት መውሰድ እነዚህን ግቦች ለማሳካት የየራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ።
በተለይም የስኳር ህመም ያላቸው፣ የልብና ተያያዥ የደም ስር ህመም ያላቸው፣ የኮሌስትሮል መጠን በከፍትኛ ሁኒታ የጨመረባቸው እንዲሁም ተደራራቢ አጋላጭ ህመም (multiple risk factors) ያላቸው የኮሌስትሮል መቀነሻ መድሃኒት ያለማቋረጥ መውሰድ ተገቢ ነው። ዋናዎቹ የኮሌስትሮል መቀነሻ መድሃኒቶች ስታቲን (statin) በመባል ይታወቃሉ። በርካታ የስታቲን መድሃኒት አይነቶች ቢኖሩም ኮሌስትሮልን በከፍተኛ ሁኔታ በማስተካከል ውጤታማነታቸው የተረጋገጠው ሮሱቫስታቲን (Rosuvastatin) እና አቶርቫስታቲን (Atorvastatin) የተባሉት የስታቲን መድሃኒቶች ናቸው።
እነዚህን የሕክምና ግቦች መረዳት በጤናዎ ላይ የተሻሉ ውሳኔዎችን እንዲወስኑ እና ለጤናማ ህይወት አስፈላጊ እርምጃዎችን እንዲወስዱ እንደአንድ ግብኣት ይረዳዎታል ብዬ አስባለሁ።
የኮሌስትሮል መጠንዎን እና የህምክና ግብዎን በመረዳት እና ተጨባጭ ስራ በመስራት ለልብ ህመም ተጋላጭነትዎን በእጅጉ ይቀንሱ።
ማስታወሻ፡ በዚህ ጽሁፍ የተካተቱት ይዘቶች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና የጤና ባለሙያዎን ያማክሩ።
ይህ መረጃ ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኙት ተስፋ አደርጋለሁ! ተጨማሪ ጥያቄዎች ካሉዎት የዚህን መረጃ ያሰናዳዉን ዶ/ር መላኩ ታዬ እና የስራ ባልደረቦቹን በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል ማግኘት ይችላሉ።