የደም ቅባት መጠን መዛባት (Dyslipidemia) የሚባለው ህመም የደም ውስጥ የኮሌስትሮል ወይም ስብ መጠን ከተለመደው ውጭ ሲዛባ እና ይህም የልብና የደም ሥር በሽታዎች ታጋላጭነትን ሲጨምር የሚከሰት ተላላፊ ያልሆነ በሽታ ነው። በአኗኗር ዘይቤዎች መዛባት ወይም በዘር ተጋላጭነት የሚከሰት ሆኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለልብ ሕመም ከሚዳርጉ ምክንያቶች አንዱ ነው። የደም ስር ቧንቧዎች ውስጥ በመከማቸት እንዲዝጉና እንዲደፈኑ በማድረግ ወደልብ፣ አንጎል እንዲሁም ወደሁሉም የሰውነት ብልቶቻችን የሚሄድ የደም ፍሰት ይገድባል።
የደም ቅባት መጠን መዛባት በሶስት ዋና ዋና የህመም አይነቶች ይከፈላል። እነዚህም የኮሌስትሮል (የጎጂ ኮሌስትሮል) መብዛት (high cholesterol)፣ የደም የስብ መጠን መብዛት (High Triglycerides) እና የኮሌስትሮል ማነስ (የጥሩ ኮሌስትሮል መጠን ማነስ) (low HDL) ናቸው።
የኮሌስትሮል ችግሮች በአለም አቀፍ ደረጃ ስርጭቱ እየጨመረ ነው። በኢትዮጵያም ያሉ የዳሰሳ ጥናቶች እንዲሁ የኮሌስትሮል ህመም ከ20 በመቶ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን እያጠቃ እንደሆነ የጤና ሚኒስቴር እኤአ በ2015 ባደረገው አገር አቀፍ ጥናት አረጋግጧል (Gebreyes et al. PLoS ONE. 2015;13(5): e0194819 )። አንዱ ምክንያት የአኗኗራችንና የአመጋገባችን ለውጥ ነው። በከፍተኛ ደረጃ በፋብሪካ የተቀነባበሩ፣ የተጠባበሱ፣ ቅባት እና ስኳር የበዛባቸው ምግቦችን ዋና ቀለባችን ሆነዋል። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማዘተርም ሌላኛው ለኮሌስትሮል መጠን መጨመር ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያደርግ አጋላጭ ምክንያት ነው። የዘመናዊ ህይወት አካል የሆነው የየለት የኑሮ ጫና ጭንቀትም እንዲሁ የኮሌስትሮል መጠንን ያውካል። ይህ የሚያመላክተው የኮሌስትሮል ጤናን ለማሻሻል አብዛኛው የመፍትሄ ቁልፍ የሚቻልና በእጃችን ያለ መሆኑን ነው።
የኮሌስትሮል ህመም ለደም ስር በሽታዎች የሚያጋልጠው ለምንድን ነው?
ኮሌስትሮል ከልብና ሌሎችም የደም ስር በሽታዎች ጋር ጥብቅ ትስስር አላቸው። የደም ኮሌስትሮል መጠን መጨመር የደም ስር ህመም የመያዝ እድልን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምር በጥናቶች የተረጋገጠ ነው። በተለይም ኤል ዲ ኤል ኮሌስትሮል (LDL-cholesterol) የደም ስር ላይ የሚያስከትለው ጠንቅ አደገኛ ነው።
ኮሌስትሮል ደማችን ውስጥ ሲጠራቀም የደም ስር ግድግዳ ላይ እንደሙጫ ይጣበቃል። በጊዜ ሂደት እየደደረ የኮሌስትሮል ንጣፍ ይሰራል። ቀስ በቀስ የደም ቧንቧዎችን ያጠባል። ይህ ሂደት አተሮስክሌሮሲስ (atherosclerosis) ይባላል። ውሎ አድሮ የደም ስር እያጠበበ የደም ዝውውርን ይገታል፤ የደም ፍሰትን ይቀንሳል። በኦክስጅን የበለጸገው ደም ወደልብ ወይም አንጎልዎ ሊደርስ ካልቻለ ድንገተኛ የልብ ድካም ወይም የአንጎል መታዎክ ያስከትላል።
በምሳሌ ለማስረዳት ያክል የደም ስሮችን የውሃ ቱቦዎች እንደሆኑ አድርገን እናስብ። እነዚህ ቧንቧዎች ውሃ ያለችግር እንዲፈስ ንጹህ እና ክፍት መሆን አለባቸው። ነገር ግን ቅባትና መሰል ቧንቧ የሚያዝጉ ቆሻሻዎች ከተጠራቀመበት ቧንቧው ይደፈንና ውሃ ማሳላፍ አይችልም። ደም ውስጥ ከመጠን በላይ ቅባት (መጥፎ ኮሌስትሮል) ሲበዛ ልክ እንደ የውሃ ቧንቧ ውስጠኛው ክፍል ጋር እንደሚጣበቅ ቅባት ያለ ቆሻሻ ነው። በመጀመሪያ ከደም ስሮች ግድግዳ ላይ መጣበቅ ይጀምራል። ከጊዜ በኋላ እየደደረ ይከማቻል፣ ቀስ ብሎ እያደረ እየደረበ ሲሄድ ጥንክር ያለ ንብርብር ሽፋን (ፕላክ – atherosclerotic plaque) ይፈጥራል። ሲያድግ የደም ስር ክፍተት እየጠበበ ይሄዳል። ሲብስ የደም ስር በከፊል ይዘጋልና የደም ፍሰት ያስተጓጉላል። በተለይም የፕላኩ ንጣፍ ከተሰነጠቀ በድንገት ደም እንዲረጋ ያደርግና የደም ፍሰቱን ሙሉ በሙሉ ሊገድበው ይችላል። ይህ ነው ድንገተኛ የልብ ድካም፣ የአንጎል መታዎክ፣ የእግር ጋንግሪን ወይም ስንፈተ ወሲብ የሚፈጥረው። ለዚህ ነው የደም ስሮች ንፁህ እና ክፍት እንዲሆኑ እና ደም ያለችግር እንዲፈስ የኮሌስትሮል መጠንን መቆጣጠር አስፈላጊ የሚሆነው።
የኮሌስትሮል ህመም መንስኤዎች ምንድን ናቸው?
የኮሌስትሮል ህመም በማንኛውም እድሜ ክልል ያለን ሰው፣ ጾታ፣ ዘር፣ ሃብታም ድሃ፣ ወፍራም ቀጭን ሳይል ሊያጠቃ ይችላል። አንዱ ክፋቱ ደግሞ ብዙ ሰዎች ላይ ከፍ ያለ የኮሌስትሮል ምልክቶችን አያሳይም። ዝምተኛ ገዳይ ከሚባሉት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች አንዱ ነው።
የኮሌስትሮል ህመም መንስኤው ዘርፈ ብዙ ሲሆን በዘረ መል፣ በአካባቢያዊ እና በአኗኗር ሁኔታዎች ተፅእኖ ምክንያት ይከሰታል። ውጤታማ ህክምና እና የመከላከያ ስልቶችን ለመቀየስ እነዚህን አምጭ ምክንያቶች መረዳት ወሳኝ ነው። አምጭ ምክንያቶቹ በዋናነት በ 2 ዓይነቶች ይከፈላሉ። እነዚህም በዘረመል (ጄነቲክ) የሚመጣ የኮሌስትሮል ህመም (Primary dyslipidemia) እና በሌሎች ምክንያቶች የሚመጣ የኮሌስትሮል ህመም (secondary dyslipidemia) ናቸው።
በዘረመል (ጄነቲክ) የሚመጣ የኮሌስትሮል ህመም (Primary dyslipidemia) የሚከሰተው የደም ቅባት ሜታቦሊዝምን በሚጎዳ በዘረመል ለውጥ ምክንያት ነው። በዘር ሊወረስ ይችላል። የኮሌስትሮል መጠኑ እጅግ ከፍተኛ ሲሆን ብዙውን ጊዜ ገና በለጋ እድሜ ይከሰታል። ስርጭቱ ያልተለመደ ሲሆን ከ300 ሰዎች በአንዱ እንደሚገኝ ጥናቶች ያሳያሉ።
በሌሎች ምክንያቶች የሚመጣ የኮሌስትሮል ህመም (secondary dyslipidemia) ደግሞ የሚከሰተው በአኗኗር ሁኔታዎች መዛባት ወይም ሌሎች የጤና እክሎች ምክንያት ነው። ዋና ዋና ምክንያቶቹን ለመጥቀስ ያክል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማዘውተር፣ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ ውፍረት፣ የስኳር በሽታ፣ የእንቅርት ሆርሞን መዛባት፣ የኩላሊት ህመም፣ የጉበት ህመም፣ አልኮል መጠጣት፣ ሲጋራ ማጨስ እና አንዳንድ መድሃኒቶችን መጠቀም ያካትታሉ።
የኮሌስቶርል መብዛት ምልክቶች ምንድር ናቸው?
ከፍተኛ ኮሌስትሮል ለብዙ ሰዎች ምንም ዓይነት ምልክቶች አያሳይም። ከፍተኛ ኮሌስትሮል በሰውነትዎ ውስጥ ሌሎች ችግሮችን እስኪያመጣ ድረስ ምንም ዓይነት ምልክቶች አያሳይም። ምልክት አልባ ነው። ከፍተኛ ኮሌስትሮል እንዳለ ለማወቅ ብቸኛው መንገድ የደም ምርመራ በማድረግ ነው።
ማስታወሻ፡ በዚህ ጽሁፍ የተካተቱት ይዘቶች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና የጤና ባለሙያዎን ያማክሩ።
ይህ መረጃ ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኙት ተስፋ አደርጋለሁ! ተጨማሪ ጥያቄዎች ካሉዎት የዚህን መረጃ ያሰናዳዉን ዶ/ር መላኩ ታዬ እና የስራ ባልደረቦቹን በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል ማግኘት ይችላሉ። ውድ የሆነውን ጤናዎትን ለመጠበቅ ምን ማድረግ እንዳለብዎት ለማዎቅ ተጨማሪ ተግባራዊ ምክሮችን በዶ/ር መላኩ ድህረ ገጽ www.melakutaye.com እና ማህበራዊ ሚዲያዎች @hakimmelaku ይከታተሉ!