የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ (Lifestyle) ለኮሌስትሮል ህክምና ያለው ሚና

ኮሌስትሮልን ለመቆጣጠር መድሃኒት መውሰድ ብቻ በቂ አይደለም። ይልቁንም ጤናማ የአኗኗር ዘይቤዎችን ማዘውተር ኮሌስትሮልና ከኮሌስትሮል ጋር የተያያዙ የልብና የደም ስር ህመሞችን ለማከም የማይተካ ሚና ይጫወታል። ጥሩነቱ አባዛኛዎቹ ለኮሌስትሮል ህክምና የሚመከሩ የአኗኗር ለውጥ መፍትሄዎች በቀላሉ ተግባራዊ ሊደረጉ የሚችሉ ናቸው።


ጤናማ የአኗኗር ዘዬ መከተል፣ በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እንዲሁም አልኮል መጠጥ መቀነስ ለኮሌስትሮል ህክምና መሰረታዊ ናቸው።  በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ኮሌስትሮልን ለመቀነስ የሚያግዝዎት የአኗኗር ዘይቤዎች እንመረምራለን።


ለኮሌስትሮል ህክምና የሚመከሩ አመጋገብ ለውጦች


ኮሌስትሮልን ለመቆጣጠር ከሚረዱን ወሳኝ የህክምና አማራጮች ውስጥ አንዱ አመጋገብዎን ጤናማ ማድረግ ነው። አንዳንድ ምግቦች የኮሌስትሮል መጠንን ለመቀነስ ይረዳሉ፤ ሌሎች ደግሞ ከፍ ሊያደርጉ ይችላሉ።


ኮሌስትሮልን ለማስተካከል የሚረዱ ምግቦች መካከል የሚከተሉትን ያካትታል።

  • አትክልትና ፍራፍሬ፡ በፋይበር፣ በቪታሚኖች እና በፀረ-ኦክሲዳንት የበለጸጉ ፍራፍሬዎች እና አትክልቶች መጥፎ ኮሌስትሮልን ለመቀነስ ይረዳሉ። ሁሌም ግማሹን የምግብ ሳህንዎትን ክፍል እንደ ኢትዮጵያ ባንዲራ በተ፤ለያዩ ቀለማት የአሸበረቁ ቅጠላ ቅጠሎች እና ፍራ ፍሬዎች ለመሙላት ይሞክሩ። ሲመገቡም እነዚህን በመጀመሪያ መብላት ጥሩ ነው።
  • አሰርነት ያላቸው የእህል ዘሮች፡- አሰርነታቸው ያልጠፋ ያልተፈተጉ ጥራጥሬና እህል ምግቦችም እንዲሁ የተሻሉ ናቸው።
  • ጤናማ ቅባት ያላቸው እንደየቅባት እህሎች ለምሳሌ ለውዝ፣ አልሞንድና መሰል ዘሮች የጎጂ ኮሌስትሮል መጠንን ለማሻሻል ሊረዱ ይችላሉ። ከተጠባበሱ መቆያ ስናክ ምግቦች ይልቅ አንድ እፍኝ ለውዝ መመገብ በኮሌስትሮል ጤና ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል።
  • አሳ፡ የተለያዩ የአሳ ምግቦች ጠቃሚ የሆኑ ኦሜጋ -3 የቅባት አይነቶች የበለጸጉ ናቸው። እነዚህ የአሳ ቅባት ምግቦች ኮሌስትሮልን ለመቀነስና የደም ስር ህመምን ተጋላጨነት ይቀንሳሉ።
  • ጤናማ የዝይት አይነቶችን መጠቀም፤ ቅቤን ወይም ማርጋሪን ከመጠቀም ይልቅ በወይራ ዘይት በመተካት ጎጂ ኮሌስትሮልን መቀነስና ጥሩ ኮሌስትሮልን ከፍ እንዲል ይረዳል።

ኮሌስትሮልን የሚያባብሱ ምግቦችስ የትኞቹ ናቸው?

  • ትራንስ ፋት (trans fat): እነዚህ በተጠበሱና የተቃጠሉ ምግቦች ውስጥ የሚገኙ መርዛማ የቅባት አይነቶች ሲሆኑ ጎጂ ኮሌስትሮን ይጨምራሉ። በአንጻሩ ጥሩ ኮሌስትሮልን ዝቅ ያደርጋሉ። በዘይት ማሸጊያዎች ላይ “partially hydrogenated oils” የሚል የተለጠፈባቸው የምግብ ዘይቶች በዛ ያለ ትራንስ ፋት ስላላቸው አይጠቀሙባቸው።
  • ሳቹሬትድ ፋት (saturated fat): መጥፎ ቅባት የበዛባቸው ምግቦችን በብዛት መመገብ የኮሌስትሮል መጠንን ይጨምራል። የሳቹሬትድ ስብ በዋነኛነት በቀይና ጮማ ስጋ፣ ሙሉ ቅባት ያላቸው የወተት ተዋጽኦዎች እና ቅቤ ከፍተኛ  ሳቹሬትድ ፋት መጠን ያላቸው ሲሆን መወገድ ያልባቸው ቅባት አይነቶች ናቸው። እነዚህን ምግቦች መገደብ የኮሌስትሮል ውጤትን ለማሻሻል ይረዳል።
  • ስኳር የበዛባቸው ምግቦች እና መጠጦች፡- ከፍተኛ ያለቀለት የስኳር መጠን የበዛባቸው ምግቦች የደም ቅባት መጠን መጠን ከፍ እንዲል ከማድረግ በተጨማሪ ለውፍረትና ቦርጭ መጨመር አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።

በርካታ የስነ ምግብ ባለሙያዎች የተለያዩና አንዳዴም እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ የአመጋገብ አይነቶችን ሲመክሩ እንሰማለን። ለመሆኑ የትኞቹ ናቸው የሚሰሩት እና በሳይንስ የተደገፉት?

  • የሜዲትራኒያን አመጋገብ (Mediterranean Diet)፡ ይህ የአመጋገብ ስርአት ስላለው የጤና ጥቅሞች ከሌሎች የአመጋገብ አይነቶች ሻል ያለ ሳይንሳዊ ማስረጃዎች አሉት። ለአጠቃላይ ጤና በሚሰጠው ላቅ ጥቅም በሰፊው ይወደሳል። ይህ የአመጋገብ አይነት አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ጥራጥሬ፣ አሰርነት ያላቸው እህል ምግቦች፣ አሳ እና የወይራ ዘይትን መጠቀም ይመክራል። በአንጻሩ  በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችና ስጋን መገደብ ያዝዛል። በርካታ ጥናቶች ከሌሎችን የአመጋገብ አይነቶች የተሻለ ኮሌስትሮልን ለማስተካከል፣ የደም ግፊትን ለማስተካከልና የልብ ህመም ተጋላጭነትን ይቀንሳል ሲሉ ያስረዳሉ።
  • የደም ግፊት ለመቀነ የሚረዱ የአመጋገብ ዘዴዎች ( Dietary Approaches to Stop Hypertension, DASH Diet): በመጀመሪያ የደም ግፊትን ለመቀነስ የተነደፈ የአመጋገብ ስልት ቢሆንም ኮሌስትሮልንም ለመቀነስ ውጤታማ ነው። ይህ የአመጋገብ ስልት አትክልቶችን፣ ፍራፍሬዎችን፣ ያልተፈተጉ ሙሉ እህሎችን፣ አሳ እና ዶሮ ምግብን ማዘውተር የሚመክር ሲሆን ጨው፣ ቀይ ሥጋ እና ጣፋጮች መገደብ ይደግፋል። ይህ አመጋገብ የኮሌስትሮል መጠን እና አጠቃላይ የልብ ጤናን እንደሚያሻሽል በበርካታ ጥናቶች ተረጋግጧል።
  • ቬጀቴሪያን አመጋገብ (vegetarian diet): ይህ አመጋገብ የእጽዋት ተዋጽኦ ምግቦችን ብቻ መመገብ የሚመክር ሲሆን ምንም አይነት ስጋ እና የባህር ምግቦችን የማያካትት ነው። አንዳንድ ለዘብተኛ የቬጀቴሪያን አመጋገብን የሚከተሉ ሰዎች እንቁላል እና የወተት ምግቦችን ሊበሉ ይችላሉ። ከእንሣት ተዋጽኦ ብቻ የሚገኘውን የሳቹሬትድ ቅባት መጠን በእጅጉ ይቀንሳል። ስለሆነም የኮሌስትሮል መጠን ለማስተካከል ይረዳል።
  • ከፍተኛ ቅባት ያላቸውን የስጋ ምግቦች መገደብ ተገቢ ነው። በተለይም በሃይል የሰባ ስጋ እና ጉበት ይገድቡ። በተጨማሪም የተጠበሱ ስጋ ምግቦች ያስወግዱ። ስጋን ጠብሶ ከመመገብ ይልቅ ስጋን ቀቅለው መብላት የተሻለ ነው። ከአንሣት ስጋ ይልቅ የዶሮ ስጋ የተሻለ ነው – ዶሮን ሲያዘጋጁ የሚታዬውን ስጋ መልቀምና ቆዳውን ማውጣት ይመከራል።
  • በፋብሪካ የተቀነባበሩና ያለቀላቸው ምግቦችን ይገድቡ። እንደ ቺፕስ፣ ኩኪስ፣ የታሸጉ ጣፋጭ ለስላሳ መጠጦችና ጁሶች፣ ለረጅም ሰአት ፍሪጅ የቀዘቀዙ ተጠባሽ ምግቦች መመገብ ይገድቡ። በሳቹሬትድ ፋት እና ትራንስ ፋት የበለፀጉ ከመደብር የሚገዙ ያለቀላቸው ምርቶችን ይገድቡ።

እነዚህና ሌሎችም የመጋገብ ስልቶች በስፋት እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ሲሟገቱ ይሰማሉ። እውነታው ግን አንዱ ከሌላው ይበልጣል የሚል ጥርት ያለ ሳይንሳዊ ጥናት የለም። ለሁሉም ሰው የሚሰራ የአመጋገብ ቀመር ማስቀመጥ ያስቸግራል። ዋናው በዘላቂነት መተግበር የሚችል ስልት መንደፍና በየጊዜው እያሻሻሉ መሄድ መልካም እንደሆነ አብዛኛውን የስነ ምግብ ባለሙያዎች የሚያስማማ ጉዳይ ነው።


የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለኮሌስትሮል ህክምና ያለው ሚና


የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚጠቅመው ሸንቀጥ ለማለት ብቻ አይደለም። ይልቁንም የኮሌስትሮል መጠንን ለማሻሻል እና የልብ ጤናን ለመጠበቅ ከሚረዱት ምርጥ መንገዶች አንዱ ነው። መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ጥሩ ኮሌስትሮልን ይጨምራል፣ ጎጂ ኮሌስትሮልን ይቀንሳል፣ ትራይግሊሰርይድን ይቀንሳል። በተለይም ከጤናማ አመጋገብ ጋር ሲጣመር እጅግ ከፍተኛ የጤና ጥቅሞች አሉት።


ምን ያህል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስራት ያስፈልጋል?


የአካል ብቃት እንቅስቃሴን የጤና ጥቅሞች ለማጣጣም የግድ ማራቶን ሯጭ መሆን አያስፈልግዎትም። ማንኛውም አይነትና መጠን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጠቃሚ ነው። የቻሉትና ያክል መንቀሳቀስ እና አብዝቶ መቀመጥን መቀነስ ነው። በተለይም በሳምንት ቢያንስ ከ150 ደቂቃ ያላነሰ ኤሮቢክ እንቅስቃሴዎችን አዘውትሮ መስራት መልካም ነው። በሳምንት ሁለት ወይም ሶስቴ የጥንካሬ ስፖርቶች መስራት ተጨማሪ የጤና ቱሩፋቶች ያጎናጽፋል።


ጭንቀት መቀነስ


ከጤናማ አመጋገብና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከመስራት በተጨማሪ ሌሎች የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች ለኮሌስትሮል ጤና ይረዳሉ። ከእነዚህ አንዱ ጭንቀት መቀነስ ነው። አብዝቶ መጨነቅ የደም ግፊትን እና ስኳርን ከመጨመር  ባለፈ በአጠቃላይ የልብ ጤና እና ኮሌስትሮል መጠን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል። ጭንቀት ለመቀነስ የሚረዱ ዘና የሚያደርጉ ዘዴዎችን ማዘውተር ኮሌስትሮልዎን ዝቅ ለማድረግ ሊረዳ ይችላል።


በቂ እንቅልፍ ማግኘት  


ብዙ ሰዎች ከሚያስቡት በላይ በቂና የሚያረካ እንቅልፍ መተኛት ለጤና እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። የእንቅልፍ ችግር ከከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠን፣ የደም ግፊት መብዛትና ስኳር ህመም ጋር የተያያዘ ነው። ስለሆነም የኮሌስትሮል መጠን ለመቆጣጠር እና አጠቃላይ ጤንነትና ለማበልጸግ በእየለቱ ከ6-8 ሰአታት ጥራት ያለው እንቅልፍ ይኑርዎት።


ጎጂ ሱሶችን ማስወገድ


ሲጋራ የሚያጨሱ ከሆነ አሁኑኑ ማቆም ለልብዎ ጤና ሊያደርጉት ከሚችሉት ምርጥ ውሳኔዎች ውስጥ አንዱ ነው። ሲጋ ማጨስ የጥሩ ኮሌስትሮልዎን ይቀንሳል፣ የልብ ህመም የመያዝ እድልን በአያሌው ይጨምራል። ማጨስ በማቆም በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ኮለኢስትሮል መጠን ይሻሻላል፤ ልብም ማገገም ይጀምራል።

የአልኮል መጠጥን ይገድቡ። መጠነኛ አልኮል መጠጣት ለጤና ጥቅም አለው የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ አለ። ነገር ግን የተሻለው ምንም አለመጠጣት ነው። አልኮል መጠጣት ኮሌስትሮልን እና ትራይግሊሲራይድ ከማዛባት አልፎ ለቦርጭና በርካታ የካንሰር በሽታዎች አጋላጭ መርዝ ነው።


ክብደትን ማስተካከል


ከመጠን በላይ መወፈር በተለይም ቦርጭ የመጥፎ ኮሌስትሮል መጠን እንዲያሻቅብ ሲያደርግ ትሪግሊራይድም እንዲጨምር ያደርጋል። ትንሽም ብትሆን ክብደት መቀነስ የኮሌስትሮል ጤና ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያሳያል።


ከላይ እንደዘረዘርነው ሁሉን አቀፍ የአኗኗር ለውጥ ማድረግ ከፍ ያለ ትርፍ እንደሚያስገኝ አውርተናል። ለሁሉም ሰው የሚሆን አንድ የአኗኗር ዘይቤ መቀመር ባይቻልም ዋናው ነጥብ ትንንሽ ለውጦች ትላልቅ ውጤቶችን እንደሚያመጡ እሙን ነው። በተጨማሪም የኮሌስትሮል መጠንን መቆጣጠር በአንድ ጀምበር ከባድ ለውጦችን በማድረግም አይደለም። ይልቁንም በጊዜ ሂደት ሊወጥሏቸው የሚችሏቸው ጤናማ ልማዶችን ስለመጀመርና በጽናት ስለመቀጠል ነው። ወደ ትክክለኛው የጤና መንገድና አስተሳሰብ ይመለሱ። የትኞቹን ለውጦች ማድረግ እንዳለቦት፣ እንዴት እንደሚቀጥል እና አንደሚያጸኑት ያቅዱ፣ ይወስኑ፣ እርምጃ ይጀምሩ። በእራስዎ ፍጥነት ይሂዱ፤  ቀስ በቀስ ተጨማሪ ለውጦችን ያካትቱ። ጤናማ የአኗኗር ለውጥ ለማድረግ መቼም አይረፍድም። ትንሽ ለውጦች ዛሬ በመጀም በረጅም ጊዜ ጤናዎ ላይ ከፍተኛ መሻሻሎችን ሊያመጡ ይችላሉ።


እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የአኗኗር ለውጥ ማድረግ ቀላል አይደለም። ለውጡን ለመተግበር ጠንካራ ፍላጎት እና ዝግጁነት ይፈልጋል።  ግልጽና ቆራጥ ምክንያቶች ሊኖሩዎት ይገባል። አንዳንድ ለውጦችን ለማድረግ ዝግጁ መሆንዎን ለመፈተሽ  የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ይሞክሩ። የኮሌስትሮል መጠንዎን ለምን ዝቅ ማድረግ ይፈልጋሉ? ጤናን መመለስ ለእርስዎ ምን ፋይዳ አለው? ከዚህ በፊት በአመጋገብና ስፖርት ላይ ለውጦችን እንዳያደርጉ የከለከለዎት እንቅፋት ምንድን ነው?  እነዚህን መሰናክሎች ለማሸነፍ አሁን ምን ማድረግ እንደሚችሉ ይሰማዎታል?


በተጨማሪም ከጤና ባለሙያዎ ጋር በመማከር የኮሌስትሮል መቀነሻ መድሃኒት ሊታዘዝ ይችላል። በተለይም የስኳር ህመም ያላቸው፣ የልብና ተያያዥ የደም ስር ህመም ያላቸው፣ የኮሌስትሮል መጠን በከፍትኛ ሁኒታ የጨመረባቸው እንዲሁም ተደራራቢ አጋላጭ ህመም (multiple risk factors) ያላቸው የኮሌስትሮል መቀነሻ መድሃኒት ያለማቋረጥ መውሰድ ተገቢ ነው።  ዋናዎቹ የኮሌስትሮል መቀነሻ መድሃኒቶች ስታቲን (statin)  በመባል ይታወቃሉ። በርካታ የስታቲን መድሃኒት አይነቶች ቢኖሩም ኮሌስትሮልን በከፍተኛ ሁኔታ በማስተካከል ውጤታማነታቸው የተረጋገጠው ሮሱቫስታቲን (Rosuvastatin) እና አቶርቫስታቲን (Atorvastatin) የተባሉት የስታቲን መድሃኒቶች ናቸው።


ማስታወሻ፡ በዚህ ጽሁፍ የተካተቱት ይዘቶች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና የጤና ባለሙያዎን ያማክሩ።


ይህ መረጃ ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኙት ተስፋ አደርጋለሁ! ተጨማሪ ጥያቄዎች ካሉዎት የዚህን መረጃ ያሰናዳዉን ዶ/ር መላኩ ታዬ እና የስራ ባልደረቦቹን በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል ማግኘት ይችላሉ። ውድ የሆነውን ጤናዎትን ለመጠበቅ ምን ማድረግ እንዳለብዎት ለማዎቅ ተጨማሪ ተግባራዊ ምክሮችን በዶ/ር መላኩ ድህረ ገጽ www.melakutaye.com እና ማህበራዊ ሚዲያዎች @hakimmelaku ይከታተሉ!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top