ብዙዎቻችን የደም ቅባት (lipids)፣ ስብ (fat) ወይም ኮሌስትሮል (cholesterol) የሚል ነገር በተደጋጋሚ እንሰማለን። ለመሆኑ በትክክል ምንድን ናቸው? አንድነትና ልዩነታቸው ምንድን ነው? እነኚህ ቃላት ስንጠቀም አንዱ ሌላውን ሊተካ ይችላል ወይ? ከቃላት ትርጓሜ ባሻገር ስለደም ቅባት ማወቅ ለምን አስፈለገ? በዚህ መጣጥፍ ከደም ቅባት ጋር በተያያዘ ለጤናዎ እንክብካቤ የሚሆኑ ተግባራዊ ምክሮችን የመጀመርያ ክፍል እናቀርባለን።
የደም ቅባቶች ስብነት ያላቸው በሰውነታችን እያንዳንዱ ህዋሳት ውስጥና ደም ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች ናቸው። በሰውነት ውስጥ በርካታ ቁልፍ ሚናዎችን ይጫወታሉ። ጠቀሜታቸውም ለህዋሳት ሞተር የሚያንቀሳቅሱ ሃይል ምንጭ፣ የህዋሳትን ሽፋንና ግድግዳ (membranes) ለመገንባት፣ ምግብ ለመፍጨት የሚረዳው የሃሞት ፈሳሽ ይሰራሉ፣ ለአንዳንድ ሆርሞኖችና ቫይታሚን ዲ ለማምረት ይረዳሉ። ይሁን እንጂ ከመጠን በላይ ሲሆኑ የተበላሸ የመኪና ዘይትና ነዳጅ በተሽከርካሪው ላይ ችግር እንደሚፈጥር ሁሉ በደም ውስጥ ብዙና የተበላሹ ቅባቶች መኖራቸው በተለይ በልብ እና በደም ስሮች ላይ ከፍተኛ የጤና ችግርን ያስከትላል።
የደም ቅባት (Lipids) ሲባል የተለያዩ ስብ እና ኮሌስትሮል አይነት ንጥረ ነገሮችን የሚያጠቃልል ሰፊ ምድብ ነው። የደም ስብ (fat) እና ኮሌስትሮል (cholesterol ) የሚያካትት የወል ስም ነው።
ኮሌስትሮል (cholesterol)
ኮሌስትሮል አንደኛው የሰውነት ቅባት አይነት ነው። ሰውነታች የሚያስፈልገውን ኮሌስትሮል በራሱ ማምረት ይችላል። ስለሆነም ኮሌስትሮል ለማግኘት የግድ ከምግብ መሆን አያስፈልገውም ማለት ነው። ኮሌስትሮልን ከእንስሳት ተዋጽኦዎች ለምሳሌ ስጋ፣ ወተትና የወተት ውጤቶች፣ የእንቁላል አስኳልና ሌሎችም ምግቦች ውስጥ ይገኛል። ኮሌስትሮል ከእጽዋት ምግቦች ውስጥ የለም (እጽዋት phytosterol የሚባል ኮሌስትሮል-መሰል ቅባት አላቸው። ከበዛ ከኮሌስትሮል እኩል ለጤና ጎጂ ነው)።
በርካታ የኮሌስትሮል አይነቶች ያሉ ሲሆን ዋነኞቹ LDL ኮሌስትሮል (መጥፎ ኮሌስትሮል) እና HDL ኮሌስትሮል (ጥሩ ኮሌስትሮል) ናቸው። ኮሌስትሮል በርካታ ጠቃሚ ተግባራት ያሉት ሲሆን መጥፎ ኮሌስትሮል ሲበዛ የደም ስር ግድግዳ ላይ እንደማስቲካ በመጣበቅ ስር የሰደዱና ገዳይ የሆኑ የልብ ህመምና ሌሎችም የደም ስር በሽታዎች ያመጣል።
ስብ (fats)
ሌላኛው የሊፒድ አይነት። ከፍተኛ ሃይል (ጉልበት) ሰጪ ሲሆን ሃይል ለማከማቸት ይረዳል።
ከምግብ የምናገኛቸው ሁለት ዋና ዋና የስብ አይነቶች አሉ። እነዚህም አንሳቹሬትድ ፋት – unsaturated fat (እንደ የወይራ ዘይት፣ ለውዝ እና አሳ ባሉ ምግቦች ውስጥ ይገኛሉ) እና የሳቹሬትድ ፋት – saturated fat ( ከእንስሳት ተዋጽኦዎች እንደ ቅቤ እና ስጋ ባሉ ምግቦች ውስጥ የሚገኝ ሲሆን መርዛማ ነው) ናቸው።
በርካታ የሰውነት ስብ አይነቶች ያሉ ሲሆኑ እነዚህም ትራይግሊሰራይድ (Triglyceride)፣ ፎስፎሊፒድ (Phospholipids)፣ ግላይኮሊፒድ (Glycolipids)፣ ነጻ ፋቲ አሲድ (Free Fatty Acids) ወዘተ የመሳሰሉ የየራሳቸው ተግባር ያላቸው የስብ አይነቶችን ያካትታል።
ከሁሉም የስብ አይነቶች በጣም የተጠናውና የሚታወቀው ትራይግሊሰራይድ ነው። ከተመገብን በኋላ ትርፍ የሆነ ሰውነታችን ወዲያውኑ የማይፈልገውን ሃይል (ካሎሪ) ወደ ትራይግሊሰርይድ ይለውጣል፣ ከዚያም በስብ መልክ ሴሎችና ጮማ ውስጥ ይከማቻል። ከዚያም ምግብ በማንበላበት ጊዜ ወይም ሰውነታችን ተጨማሪ ሃይል ሲፈልግ ትራይግሊሪየይድ እየተቃጠለ ሃይል ይሰጣል።
ፎስፖሊፒድ (Phospholipids) ደግሞ ሌላኛው የስብ አይነት ሲሆን የእያንዳንዱን ሴል ሽፋን ለመስራት ይረዳል። እንደቤት ግድግዳ ከለላ በመስጠት ሴሎችን ለመጠበቅ እና ንጥረ ነገሮች ወደ ውስጥ እና ወደ ውጭ የሚገባ የሚወጣውን ሂደት ይቆጣጠራል። በተጨማሪም ህዋስ ከህዋስ ያለውን ግንኙነትና መስተጋብር ያሳልጣል።
ግላይኮሊፒድ (Glycolipids) ካርቦሃይድሬት (ስኳር) የያዙ የስብ አይነቶች ናቸው። በሴል ሽፋኖች ውስጥ በተለይም በነርቭ ሴሎች ውስጥ ይገኛሉ። ሴሎች እርስ በርሳቸው እንዲነጋገሩ ይረዳሉ።
ነፃ ፋቲ አሲድ (Free fatty acids) ሌሎች የስብ አይነቶች ማለትም የትሪግሊሲራይድ፣ ፎስፎሊፒድና ሌሎችም ስቦች ለመስራት የሚረዱ ሲሆን በሰውነት ውስጥ በቀጥታ ለኃይል አገልግሎት የሚውሉ የስብ አይነቶች ናቸው። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ሁል ጊዜ ለኃይልነት ለማቃጠል ዝግጁ ስለሆኑ ፈጣን ጉልበት ይሰጣሉ።
የደም ቅባት እንዴት እንደሚዋሃዱ እና እንደሚጓጓዙ?
ቅባት የያዙ ምግቦችን ስንበላ አንጀት ውስጥ በተለያዩ ምግብ የሚያልሙ ኤንዛይሞች (lipase) አማካኝነት ተፈጭተው ወደ ትናንሽ ቅንጣቶች ይቀየራሉ። እነዚህ ቅንጣቶች በደም በኩል ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች መሄድ አለባቸው። ነገር ግን ቅባታማ ስለሆኑ ከውሃ ወይም ደም ጋር አይዋሃዱም (ዘይት ከውሃ ጋር እንደማይቀላቀል ሁሉ)። ስለዚህ በደም ውስጥ በራሳቸው መንቀሳቀስ አይችሉም።
ስለዚህ ሰውነታችን እነዚህን ቅባቶች በደም ውስጥ ለማጓጓዝ ሊፖፕሮቲን (lipoprotein) የሚባሉ ልዩ ‘የጭነት ማጓጓዣ ካርጎ’ መሳይ ማጓጓዣ መንገዶች ነው። ሊፖፕሮቲን የደም ቅባትን የሚያጓጉዙ እንደ ትናንሽ መጓጓዣ መኪናዎች እንደሆኑ ማሰብ ይቻላል።
በዋናነት አራት አይነት ሊፖፕሮቲኖች አሉ። እነዚህም ካይሎማይክሮን (Chylomicrons – ቅባትን ከአንጀት ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች የሚወስዱ ትላልቅ የጭነት መኪና መሳይ ንጥረ ነገሮች ናቸው)፣ Very Low-Density Lipoprotein (VLDL – በጉበት ተመርተው ቅባትን ከጉበት ወደ ተለያዩ ሰውነት ክፍሎች የሚያደርሱ)፣ Low-Density Lipoprotein (LDL –ብዙ ጊዜ ‘መጥፎ ኮሌስትሮል’ ተብሎ የሚጠራው ሲሆን የኮሌስትሮል ሜታቦሊዝም ተረፈ ምርት ናቸው) እና High-Density Lipoprotein (HDL – ‘ጥሩ ኮሌስትሮል’ በመባል የሚታወቀው ሲሆን ኮሌስትሮልን ከደም ውስጥ እየለቀመ ያጸዳና ወደ ጉበት እንዲወገድ ይመለሳል)።
ሊፖፕሮቲኖች አንዴ ኮሌስትሮልን እና ትራይግሊሰርይድን ወደ ጉበት ካደረሱ በኋላ ጉበት ሁሉንም ነገር በማቀነባበር እርምጃ ይወስዳል። ጉበት ሰውነታችን ምን ያህል ኮሌስትሮል እንደሚያስፈልገው ይወስናል፣ የማያስፈልግ ኮሌስትሮልን በመሰባበር ከሰውነት በሃሞት ፈሳሽ መልክ ያስወግዳል።
በጣም ብዙ ኮሌስትሮል ካለ ምን ይከሰታል? እነዚህ ማጓጓዣ የጭነት መኪና መሳይ ሊፖፕሮቲኖች ከመጠን በላይ ኮሌስትሮል እና ትራይግሊሲራይድ ሲኖር ሁሉንም ወደሚፈለግበት የሰውነት ክፍል ለማጓጓዝ ይከብዳቸዋል። ስለሆነም ደም ውስጥ የሚከማች ቅባት ይበዛል። በሂደት በደም ቧንቧ ግድግዳ ላይ እንደማስቲካ ተጣብቆ ይከማችና ይደድራል። እነዚህ የስብ ክምችቶት (atherosclerotic plaques) በጊዜ ሂደት የደም ስርን ወደማጥበብና መድፈን ያመራል። ይህም ለደም ዝውውር አስቸጋሪ ያደርጋል። ሲብስ አስፈላጊ የአካል ክፍሎች የደም ዝውውርን ያውካል ብሎም ድንገተኛ የልብ ድካም (heart attack)፣ የአንጎል መታዎክ (stroke)፣ የስንፈተ ወሲብ (የብልት ደም ስር መዘጋት) እና ሌሎች መሰል የደም ስር ችግሮችን ያስከትላል።
ትክክለኛ የኮሌስትሮል መጠን ስንት ነው?
ለጤነኛ ሰው (ውፍረት፣ ስኳር ህመም፣ የደም ግፊት ወይም መሰል የደም ስር ህመም የሌለበት እንዲሁም አልኮል የማይጠጣ እና ሲጋራ የማያጨስ) የኮሌስትሮል ምርመራዎች የሚከተለውን መምሰል አለባቸው።
- ጠቅላላ ኮሌስትሮል (total cholesterol) ከ200 mg/dL በታች መሆን አለበት።
- ጎጂ ኮሌስትሮል (LDL) ከ100 mg/dL በታች መሆን አለበት።
- ጥሩ ኮሌስትሮል (HDL) ከ40 mg/dL በላይ መሆን አለበት።
- ትራይግሊሲራይድ (Triglycerides) ከ150 mg/dL በታች መሆን አለበት።
ይህ መጣጥፍ ወደ ቀጣይ በኮሌስትሮል ዙርያ ጠለቅ ያለ ማብራሪያ ለመስጠት የሚረዱ ተከታታይ ትምህርታዊ ጽሁፎች መግቢያ ነው። ኮሌስትሮልን መቆጣጠር ለጤና ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ እና የኮሌስትሮል ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት ለመከላከል ሊወስዷቸው ስለሚችሏቸው ተግባራዊ እርምጃዎች የበለጠ እንነጋገራለን። የተለመዱ የተሳሳቱ አመለካከቶችን እንመረምራለን።
ማስታወሻ፡ በዚህ ጽሁፍ የተካተቱት ይዘቶች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና የጤና ባለሙያዎን ያማክሩ።
ይህ መረጃ ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኙት ተስፋ አደርጋለሁ! ተጨማሪ ጥያቄዎች ካሉዎት የዚህን መረጃ ያሰናዳዉን ዶ/ር መላኩ ታዬ እና የስራ ባልደረቦቹን በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል ማግኘት ይችላሉ። በተጨማሪም በድህረ ገጽና ቴሌግራም ይከታተሉን፣ በኢሜል contact@melakutaye.com ወይም ስልክ +251921720381 ማግኘትም ይችላሉ።