Diabetes remission – የስኳር ህመምን ማዳፈን ወይስ ማዳን?

የዛሬዉን ሃተታ በአንድ የታካሚዬ ታሪክ ልጀምር። ጋሽ ተስፋዬ የ50 አመት ጎልማሳ ናቸው። የዓይነት 2 የስኳር ህመም ህክምና ከጀመሩ ከአሥር ዓመት በላይ ሆኗቸዋል። በየቀኑ ኢንሱሊን ይወጋሉ፤ የስኳር ኪኒንም ይወስዳሉ። ታዲያ አንድ ቀን የሚወዱት ወዳጃቸው  ቴሌግራም ላይ አንድ ቪዲዮ ላከላቸው። ቪዲዮው እንዲህ ይላል፦ «ሐኪሞች የማይነግሯችሁ ምሥጢር! ስኳር በ90 ቀን ውስጥ ሙሉ በሙሉ ይድናል። መድሃኒትህን ተውና ይህችን ምስጢራዊ ፈውስ ተጠቀም።»


ጋሽ ተስፋዬ በጣም ጎበዝና ስኳራቸውን በደንብ ተቆጣጥረው ጤናቸውን ጠብቀው የሚኖሩ ናቸው። ነገር ግን እንዲህ አይነት አጓጊ የፈውስ ዜና የማያሰቀልለው ሰው የለምና በአቋራጭ ከመርፌ መገላገል ፈለጉ — ማን የማይፈልግ አለ?


አብዛኛዎቻችን የሚፈትነን ሃሰተኛ የጤና መረጃ እንዲህ ከቅርብ ሰው የሚላኩ፣ የሚያጓጉ፣ ተስፋን የሚያስጨብጡ የሚመስሉ አጭቤ መረጃዎች ናቸው።


የዛሬው ጽሁፍ ፍሬ ነገር ይህ ነው፦ ስኳር ህመም ይድናል ወይስ ይዳፈናል?


በ2021 (እ.ኤ.አ.) የወጣው የህክምና መመሪያ ሰነድ እንደሚያስረዳው አንድ የስኳር ህመም የነበረበት ግለሰብ ዉጤታማ እና ዘላቂ የአመጋገብ (እና ሌሎችም አኗኗር ዘይቤ) ማስተካከያዎች በማድረግ አመርቂ የክብደት መሻሻል ሲመጣ የደም ስኳር መጠን በእጅጉ ተስተካክሎ የስኳር መድሃኒት ማቆም የሚቻልበት ደረጃ ሲደርስ Diabetes Remission ይባላል። የስኳር መድሃኒቶች ተቋርጠው ቢያንስ ለሶስት ወር እና ከዚያ በላይ የደም ስኳር መጠን ተመልሶ ሳይጨምር በአስተማማኝነት ጤናማ ከሆነ ነው ስኬታማ diabetes remission የሚባለው።


ይህ ሳይንሳዊ ግኝት ለታካሚዎችና የጤና ባለሙያዎች አስደሳች የምስራች ሆኖ ሳለ ስያሜውን እና ፍቺዉን በሃገራችን ቋንቋዎች በተገቢው ስላላሰረጽነው ከሳይንሳዊው አውድ ዉጭ ወጥቶ ለተለያዩ አሳች ትርጓሜዎች ተጋልጧል።


የተለያዩ ባለሙያዎች በርካታ አማራጭ የስያሜ ትርጉሞች ሲሰጡት ይሰማል። ለአብነትም ስኳርን ማዳን፣ መፈወስ፣ ስርየት፣ መቀልበስ፣ ማሻሻል፣ መቆጣጠር፣ ማስታገስ ወዘተ የሚሉ ትርጓሜዎችን ይጠቀማሉ። እኔ በበኩሌ እነዚህ ቃላት diabetes remission ከሚለው ሳይንሳዊ አገላልጽ ሙሉ በሙሉ አይገጥሙም። diabetes remission ስኳርን ማዳፈን እንጅ ማዳን አይደለም።


እናቶቻችን ማታ እሳት እንዴት እንደሚያዳፍኑ ታውቃላችሁ? ፍሙን በአመድ ያለብሱታል። እሳቱ ይሸፈናል፣ ነበልባል ጸጥ ይላል፣ ጭሱ ይጠፋል፣የቤቱ ሙቀት ጋብ ይላል። ነገር ግን እሳቱ ሙሉ በሙሉ አልጠፋም፤ ተዳፍኖ ነበር እንጂ።። ሁኔታው ሲመቸው መልሶ ይነዳል። ነፋስ አመዱን ካቦነነው፣ እፍ ካልንበት፣ ምድጃውን ከገላለጥነው ወይም ጭራሮ ከቆሰቆስክበት እሳት ተመልሶ ይንቦገቦጋል።


diabetes remission እንዲሁ የተዳፈነ የስኳር ህመም ነው። በዘር የወረስነውም ይሁን በሌላ ምክንያት ያለን ተጋላጭነት አብሮን ይቀጣላል። ክብደቱ ሲመለስ፣ በአመጋገብ እንደቀደመው ስንዘናጋ የስኳር ህመሙም ይመለሳል። ከስኳር ህመሙ ማገርሸት በተጨማሪ ስኳሩ ቢዳፈንም ቀደም ብሎ ስኳር ከፍ ብሎ የቆየባቸው ዓመታት የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻችን ላይ ለምሳሌ በዓይን፣ በኩላሊትና በነርቭ ላይ ጠባሳ  ትቶ ሊሆን ይችላል። እሳት ከመዳፈኑ በፊት የነበረው ጭስ ግድግዳ ወይም ጣሪያ ላይ ጥላሸት ጥሎ እንደሚያልፈው ሁሉ ይህ የስኳር ጠባሳም አይጠፋም (metabolic memory)። ስለሆነም ስኳር ቢዳፈንም የስኳር ህክምና ክትትል እና አንዳንድ መድሃኒቶች በቀጣይነት ሊታዘዙ ይችላሉ።


እሳት በአመድ ቢዳፈን ተመልሶ ይቀጣጠላል። የስኳር ህመምም ይዳፈን እንጂ ተመልሶ ሊያገረሽ ይችላል። ይህን መሰረት በማድረግ ከዚህ በኋል የስኳር ህመም መዳፈን፣ ማዳፈን የሚለው አገላለጽ diabetes remission የሚለውን ተክቼ የምጠቀምበት ይሆናል። ስኳርን ማዳፈን የሚለው ትርጓሜ ከሳይንሳዊ ፍቺዉ ሳይርቅ፣ የታካሚውን ከመድሃኒት ነጻ የመሆን ተስፋ ሳያጠፋ ጥረታቸውን የሚያበረታ አገላለጽም ነው።


ስኳር ህመም እንዴት ይዳፈናል?

የእንግሊዙ ፕሮፌሰር ሮይ ቴይለር ያቀረቡት ቲዮሪ ለዚህ መልስ ይሰጣል። እያንዳንዳችን ሰውነታችን ሊሸከመው የሚችል ጤናማ የክብደት መጠን አለው። ይሄ የክብደት መጠን ከገደቡ ሲያልፍ ትርፍ ስብ መከማቸት ይጀምራል። ይህ ትርፍ ስብ ጉበት ላይ ይጠራቀማል። ስብ የሞላው ጉበት የኢንሱሊንን ትእዛዝ አይሰማም ስለዚህ ስኳር ከመጠን በላይ ማምረት ይጀምራል። ስብ አሁንም አየበዛ ሲሄድ ከጉበት አልፎ ተርፎ ወደማይገባው ቦታ ይፈስሳል ለምሳሌ ወደ ቆሽት።  ስብ በቆሽት ህዋሳት ላይ እንደማስቲካ እየደደረ ኢንሱሊን የሚያመርቱት «ቤታ ሴሎች» ላይ ጉዳት ያደርሳል። በጊዜ ሂደት የደም ስኳር እየጨመረ ይሄድና የስኳር ህመም ይከሰታል።


በተቃራኒው አመጋገባችንን በማስተካከል በህክምና የታገዘ የካሎሪ ቅነሳ በማደረግ፣ ውፍረት በማስተካከል ጉበት ያገግማል፣ ቆሽት ተመልሶ ይለመልማል። በሂደት የጉበትና ቆሽት መደበኛ ተግባራቸውን በተገቢው መስራት ሲችሉ የደም ስኳር መጠን ይስተካከላል። በሃኪም ክትትል መድሃኒት እየተቀነሰ ይሄድና ሙሉ በሙሉ የስኳር መድሃኒቶች ሊቆሙ ይችላሉ።


ሳይንሳዊ ማስረጃው ምን ይላል?

ጥናት ተሳታፊዎች ውጤት
ዳይሬክት (DiRECT)፣ እንግሊዝ ስኳር ከታወቀባቸው ከ6 ዓመት ያልበለጠ፣ ትርፍ ክብደት ያላቸው፣ ኢንሱሊን የማይወስዱ ከ1 ዓመት በኋላ 46% ተዳፍኗል፤ ከ2 ዓመት 36%፤ ከ5 ዓመት 13%።
ዳያደም (DIADEM-I)፣ ኳታር ዕድሜያቸው 18–50፣ ስኳር ከታወቀ ≤3 ዓመት ከ1 ዓመት በኋላ 61%


እነዚህ ጥናቶች ላይ ሶስት መልእክቶች ጎልተው ይወጣሉ።


አንደኛ፣ ስኳርን የማዳፈን እድላችን የሚወሰነው መቀነስ የቻልነውን ክብደት  መጠን ነው። ለምሳሌ በዳይሬክት ጥናት 15 ኪሎና ከዚያ በላይ ከቀነሱት ከመቶው 86ቱ ስኳራቸው ተዳፍኗል፤ ከ5 ኪሎ በታች ከቀነሱት ግን 7ቱ ብቻ።


ሁለተኛ፣ ጊዜ ወሳኝ ነው። ስኳሩ ብዙ ስር ሳይሰድ የታወቀላቸው ስኳር የማዳፈን ዕድሉ ይሰፋል። «ሳይቃጠል በቅጠል» የሚባለው ለዚህ ነው። የዘንድሮው የዓለም የስኳር ህመም ቀን መሪ ቃል «በስኳር ህመም ላይ ቀድመን እርምጃ እንውሰድ» የሚለውም ይህንኑ ነው። ስለዚህ ስኳር ህመም ላይ ቀድመን እንንቃ!


ሶስተኛ፤ ብዙዎች ስኳርን ለጊዜው ማዳፈን ቢችሉም ከአመታት በኋላ አገርሽቶባቸዋል።


ስኳርን ለማዳፈን የተሻለ እድል ያላቸው ታካሚዎች እነማን ናቸው?

የስኳር ህመሙ ስንት ዓመት እንደቆየ፣ ኢንሱሊን አምራች ህዋሳት ምን ያህል ማገገም ይችላሉ፣ ክብደት ለመቀንስና ውፍረት እንዳይመለስ ምን ያህል ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት አለን? ወዘተ የሚሉት ሁኔታዎች አስቻይነት ስኳርን ለማዳፈን ወሳኝ ናቸው። መርሳት የሌለብን የተለያዩ ሰዎች አንድ ዓይነት ጥረትና ማስተካከያዎች አድርገው የተለያየ ውጤት ሊያገኙ ይችላሉ።


ስኳር ህመም ብዙ ስር ሳይሰድ የታወቀላቸው እና በጊዜ የታከመ ከሆነ፣ የስኳር ህመም ከታወቀ አጭር ጊዜ ከሆነ፣ የስኳር ህመሙ በውፍረት / ቦርጭ ምክንያት የመጣ ከሆነ፣ ከስኳር ህመም የሆኑ የደም ስር ህመሞች አለመኖር፣ የአኗኗር ዘይቤ ማስተካከያ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታዎች መኖር ስኳርን ለማዳፈን የሚረዱ ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው። ቀድመን ከነቃን ዕድሉ ይሰፋል።


እዚህ ላይ ማስታወስ ያለብን ስኳርህን ባያዳፍንም ክብደት ማስተካከል እና ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ ለውጦችን ማድረግ ሌሎች በርካታ የጤና በረከቶችን ይሰጣል። ስለዚህ ስኳር አልተዳፈነም ብለን ጥረቶቻችንን እንዳናቋርጥ።


ቀድመን ከነቃን ስኳርን የማዳፈን ዕድሉ ይሰፋል

    • አስቀድመን እንከላከል፤ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን መተግበር ለሁሉም ሰው ይመከራል።

    • ቀድመን እንመርመር፤ ዓይነት 2 የስኳር ህመም ለዓመታት ምልክት ሳያሳይ ይቆያል።  እድሜው ከ35 አመት በላይ የሆነ ማንኛውም ግለሰብ መደበኛ የስኳር ምርመራ ያድረግ። ስኳርን ማዳፈን የሚቻለው ቀድመው ላወቁት ነው።

    • በጊዜ እንታከም፤ ስኳር ከተገኘብን በቶሎ ከወደጤና ተቋም ሄዶ ከባለሙያ ጋር በመመካከር የህክምና እቅድና ክትትል በማድረግ በጊዜ እና በተገቢው ሁናቴ መታከም የቆሽት ህዋሳት ጉዳት የማያገግምበት ደረጃ እንዳያልፍ ይረዳል። 

ማጠቃለያ

«ዶክተር፣ ስኳር ይድናል እንዴ?» ለሚለኝ ታካሚ የምሰጠው ወቅታዊ መልስ ይህ ነው፦ ማዳን ባይቻል፣ ማዳፈን ይቻላል!


ከዚህ የተሻለ ለdiabetes remission ሃገርኛ (በተለያዩ ቋንቋዎች) ስያሜ እና ትርጓሜ አለኝ የምትሉ ኮመንት ጻፉልኝ።

 

ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ። ይህ ጽሁፍ የሚመለከተው ዓይነት 2 የስኳር ህመምን ነው።


በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ  Blog, Telegram, & Tiktok ይከታተሉ።

ጥያቄ፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ካለዎት በዚህ አድራሻ ሊንክ ይጻፉልኝ።

ይህን መረጃ ጠቃሚ ሆኖ ካገኙት ለሌሎች ያጋሩ።

1 thought on “Diabetes remission – የስኳር ህመምን ማዳፈን ወይስ ማዳን?”

  1. This is one of the best and true information I’ve ever came across about diabetes. It has always been not clear about the cure and traditional approaches to it but this blog has equipped me with all the necessary information to the fullest.
    Thanks a lot Dr. Melaku. Please keep on updating us with these precise information and keep up the good work 👏

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top