የኢትዮጵያ ፍልስፍናዊ እሴቶች

ከኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በስተቀር ሌላው አለም አዲስ አመት የሚቆጥረው ከጃንዋሪ ወር ጀምሮ ነው። የአሮጌው አመት መጨረሻ ሰባት ቀናት በአፍሪካዊ አሜሪካዊያን ዘንድ ክዋንዛ (Kwanzaa) ተብሎ ይከበራል። ይህም የፓን አፍሪካ ሰባት ፍልስፍናዊ እሴቶች ለማዘከር ታስቦ የሚውል ነው። በመከባበር፣ በመተሳሰብ እና በመትጋት ለጋራ ዓላማ እንዴት አብሮና ተዳምሮ መኖር እንደሚቻል የሚያስትምሩ ሰባት ማህበረሰባዊ የአፍሪካ እሴቶች ናቸው።


ኢትዮጵያም ምድረ ቀደምት እንደመሆኗ እንደሃገር፣ እንደማህበረሰብ ለሺህ አመታት በአብሮነት ለመኖር ያስቻሉን የስነህግ፣ የስነምግባር፣ የስነጥበብ የብዝሃ-ብሄር ማህበራዊ ፈጠራዎች / ቴክኖሎጂዎች (እሴቶች፣ ፍልስፍናዎች፣ መርሆች) እንዳሏት አያጠራጥርም።


በዚህ ጽሁፍ ከክዋንዛ የሚስተካከሉ ሰባት እንደእኔ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ የሆኑ ማህበረሰባዊ እሴቶች ላካፍል።


ምድረ ቀደምትነት (land of origins)

ስለሰው ልጅ አመጣጥ ጥሩ ማስረጃ ያለው እኛ ጋር ነው። ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛነቷ ባሻገር የቡና መገኛ፣ የራሷ የዘመን አቆጣጠር ያላት፣ የራሷ ፊደላት የቀረጸች ቀደምት ሃገር ነች። ኢትዮጵያ የበርካታ የሰብል ብዝሃ-ህይወት እና እጽዋት (agro-biodiversity “gene center”) ዋና ማእከል ነች ለአብነትም ጤፍ፣ እንሰት፣ ኑግ፣ ቡናን መጥቀስ ይቻላል። የኢትዮጵያ ስልጣኔያዊ ወጎችም (ቅኔ፣ የአምልኮ ስርአቶች) ልዩ እና ድንቅ ናቸው።


አርበኝነት (patriotism)

የሃገር ፍቅር ጉዳይ ኢትዮጵያዊያን አንድ የሚያደርግ እሴት ነው። በተለይ የውጭ ጠላት ላይ አንድ ላይ ሆ ብለው በመዝመት የሚችለን የለም።


በጦርነት ጊዜ ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ ተጋዳይ ጀብደኝነት ጂናችን ነው። ይህን ጀግንነት አድዋ እና ሌሎችም የጦር ሜዳዎች ላይ አስመስከረን ኩሩ እና ነጻ ህዝብ ልንሆን በቅተናል። እንኳን ለኢትዮጵያ ለኮሪያም ሲዘምቱ ጀግንነታችን አለምን ጉድ ያስባለ ነበር።


አርበኝነታችን ከጦር ሜዳም ባሻገር በሃገር ግንባታም አሌ የማይባል እንዳልሆነ ጥንታዊ ስልጣኔዎቻችን እና ቅርሶቻችን ህያው ምስክሮች ናቸው።


ሰላም ወዳድነት (peace building)

መጣላት፣ መኳረፍ፣ መጋጨት የሰው ልጅ ማህበረሰባዊነት (ከሌላ ሰው ጋር አብሮ የመኖር) የማናስቀራቸው የጎንዮሽ ጉዳት ናቸው። ኢትዮጵያዊያንም ከጥንት ጀምሮ በአብሮነታቸው ውስጥ ሰላማዊ የግጭት አፈታት ባህል ያለን ህዝቦች ነበርን። በእድሜም ይሁን በቅቡልነት የተከበሩ የሀገር ሽማግሌዎች የሚመራ ልማዳዊ የእርቀ ሰላም ባህል አለን። የሀይማኖት አባቶች፣ የማህበረሰብ ተወካዮች የሰላም አምባሳደሮች ሆነው ሰላምን ያወርዳሉ። ሰላምታችን ሳይቀር ‘ሰላም አደርክ‘ አይደል?!


አንተ ተው አንቺም ተይ ተባብሎ ማህበራዊ ግንኙነትን በእርቅና ስምምነት ወደነበረበት ሰላም መመለስ ላይ ያተኮረ የሽምግልና እሴት አለን። የገዳ አባቶችና ሃደ ስንቄ ስርአትም እንዲሁ በግንኙነት፣ በመሬት፣ በማንነት ወዘተ ላይ የሚነሱ ግጭቶችን በውይይት አስታርቀው ግጭትን ያርቃሉ። በሶማሊም የኢሳ ሥርዓት (Xeer Ciise / Xeer ) በኡጋዝ የሚመራ ማህበረሰባዊ ባህላዊ የፍትህና የሰላም ጉባኤ ነው። ከነዚህ ባሻገር በሁሉም የኢትዮጵያ አጽናፍ በርካታ የሰላም ማስከበር ባህሎች አሉ ለአብነትም በአፋር ማዳ (Mada’a)፣ በጉራጌ የጆካ (Yejoka Qicha)፣ በትግራይ ገረብ (Gereb)፣ በሲዳማ አራራ (Arara) ወዘተ መጥቀስ ይቻላል።


አሁን ላይ በሃገራችን የምናየው ጠብ አጫሪነት እና ጽንፈኛ ብሄርተኝነት ምንጩ ከእኛው ከራሳችን ክፋት ይሁን አይሁን ሶሲዮሎጂያዊ መረጃው የለኝም። ከድህነት የተነሳ የሃብት ንጥቂያ መብዛት ነው የሚሉ አሉ፣ የስልጣን አያያዛችን አሳታፊ ስላልሆነ የስልጣን ሽኩቻም ሊሆን ይችላል፣ የማህበረሰቡ አስታራቂ ሞራል ጠባቂዎች መመናመን ነው የሚሉም አሉ፣ አይ ከባህር ማዶ ከቅኝ ገዥዎች የተቀዳው የትምህርት ስርአት ክሽፈትም ሊሆን ይችላል (አባዛኛው ችግር ፈጣሪዎቹ አስኳላ ትምህርት በተገቢው ሳይቀስሙ የአእምሮ መካንነት ያጋጠማቸው ብላሽ ምሁሮች ናቸው)። በስደት ምክንያት አስተማሪ፣ መካሪና መሪ የሚሆን የቁርጥ ቀን ምሁር ማጣትም ሊሆን ይችላል።


ስርአተ ህግ (Indigenous governance)

የሺህ አመታት ታሪክ ያለን ሃገር እንደመሆናችን መንግስታዊ አስተዳደር ልምምድ አለን። በርካታ አገር በቀል የአስተዳደር፣ የስነ ምግባር እና ህግ ስርአቶች አሉ። በጦርነት እና በአቅም ውስንነት መንግስታዊ መዋቅር አሁንም የማይደርሳቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ኑሯቸውን የሚቀጥሉት እንዱህ ባለው የቆዬ ልምምድ ነው።


የገዳ ስርአትን ብንወስድ የስልጣን ሽግግር፣ ማህበራዊ ትስስር፣ የግጭት አፈታት እና ካሳ ደንቦችን ያቀፈ የተዋቀረ ባህላዊ አስተዳደር ነው። ጨፌው ለአመራሩ የስልጣን ገደብ እና ተጠያቂነት ያሰፍናል።


የሸንጎ አመራር ስርአትም ሌላ ኢትዮጵያዊ የአስተዳደር እና አመራር ሥርዓት ሲሆን ቅቡልነት ባላቸው ደንብ እና መመሪያዎች እየሸመገለ የሚያስተዳድር ስርአተ ህግ ነው። የጎበዝ አለቃው ብዙውን ጊዜ በማህበረሰቡ ቅቡልነት ያለው መሆን ያሻዋል።


የጉራጌ  የጆካ ቂቻ (Yejoka Qicha System) አንዲሁ አገር በቀል የአስተዳደር ስርዓቶች አንዱ ነው።


በአብሮነት መልማት (shared care and capital)

ኢትዮጵያዊያን እንደእድር እና እቁብ ያሉ የዳበሩ የማህበረሰብ ተቋማት አሉት። እነዚህ የጋራ መረዳጃ እና ካፒታል መፍጠሪያ መደራጀቶች በአብሮነት መረዳዳት እና የማህበረሰብ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ አሰራር ናቸው።


እድር በችግር ጊዜ ቀውስን በጋራ ለመጋፈጥ ያለሙ የሴፍቲኔት ሞዴል ነው። ከገንዘብ እርዳታ ባሻገር የስነ-ልቦና ድጋፍ የጋራ እንክብካቤም ይሰጣል።


እቁብም የቁጠባ እና የብድር ማህበራት ናቸው። የሚገርመው እንደአሁን ባንኮች በማስያዣ ሳይሆን በቤተሰባዊ መተማመን ላይ የተመሰረተ ተቋም ነው።


ደቦ (ወንፈል) ሌላኛው የጋራ ትብብር ነው።


ምክክር (Community Dialogue)

የቡና ወግ ብቻ ብንወስድ ኢትዮጵያዊያን እንዴት የዳበረ ማህበረሰባዊ ውይይትና ምክክር እንደሚችሉበት ማረጋገጫ ነው። በአብሮነት በመሰብሰብ መመካከር እና አውጥቶ አውርዶ በጋራ መወሰን የተለመደ ኢትዮጵያዊ ልምምድ ነው። በቡና ፕሮግራም ላይ የማይነሳ ማህበራዊ ጉዳይ የለም፤ ስለጤና፣ የጎረቤት ደህንነት እና የአካባቢው ጸጥታ፣ ስለገበያው ሁኔታ፣ ስለማሳው አዝመራ ይመካከራሉ። ይነጋገራሉ። ቡና ከመጠጥነት ባለፈ ዲፕሎማሲም ይፈላል፣ ይጠጣል። መረጃ መለዋወጫ ነው።


የማህበር ጽዋ / ሰንበቴም ሌላኛው የመወያያ መድረክ ነው።


ይህን መሰል የምክክር ልምምዶች አሁን ላይ ልናደርግ ካሰብነው ሃገራዊ ምክክር ጥሩ ልምድ ሊሆኑ ይችላሉ። 


አይበገሬ ጽናት (Resilient Mindset)

ኢትዮጵያዊያን እንደችግሮቻችን መብዛትና ተከታታይነት አልተሰበርንም። እንደጠላት ወሬ ቢሆን ፈራርሰን በተበታተንን። ነገር ግን የኢትዮጵያዊያን የልቦና ውቅር እያደር በችግር የሚጠነክር ስነልቦና ነው ያለን።


ስነልቦናችን እንደእንሰት ነው። እንሰት አደገኛ ድርቅ እና ችጋር የሚቋቋም ችግኝ እና በንጥረምግብ የበለጸገ መብላችን ነው። ኢትዮጵያዊያንም ለአለም አጥኝዎች ተቃርኖ የፈጠረ የማህበረሰብ ጽናት አለን። ብንራብ፣ ብንቆራቆስ፣ ብንቀነጭር ኢትዮጵያዊ ቀለማችን አልጠፋም። በአለም ዙሪያ ብንሰደድ ተቋቁመን እና ተላምደን አለን። ብንቀጥንም ጠጅ ነን!


ነገር ግን ይህን አይበገሬ ጽናት ወደልማት እና ሁለንተናዊ ብልጽግና የማሳደግ ቁልፍ እንደተቆለፈብን ነው። ከአለም ቀድመን እንዳልፈጠርን እና እንዳልሰለጠንን አሁን ማጣፊያው አጥሮብን ያለንበት ሁናቴ ላይ ነው። አይናችንን እንዲገልጥልን የዘወትር ጸሎቴ እና ትጋቴ ነው።


ማጠቃለያ

እነዚህ የመላ ኢትዮጵያን ሰባት እሴቶች የመተሳሰብ፣ የመከባበር እና የጋራ ልማት ፍልስፍና ናቸው ብዬ አስባለሁ። ቢቻለን ከኢትዮጵያም ተሻግረው የየመላው አፍሪካ የጋራ የወደፊት እጣ ፈንታ መሰረቶች ቢሆኑ በጎ ምኞቴ ነው።


እናንተስ ከነዚህ ሰባት እሴቶች ውስጥ አይ ኢትዮያዊ አይደለም የምትሉት እሴት አለ? ሌላስ ምን ሀገር በቀል እሴት አለን?


እነዚህ እሴቶችን እንደመድሃኒት በመጠቀም የስርአት ስብራቶቻችንን እንዴት ማከም እንችላለን?


ሃሳባችሁን ኮሜንት ላይ ..

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top