የማረጥ (menopause) ምልክቶች

ማረጥ ኖርማል የሴትነት ህይወት ተፈጥሯዊ ምእራፍ ነው። እንቁላል አመንጭ የሆኑት የሴት አካል (እንቁልጢ / ኦቫሪ) ስራ መጨረስን ያሳያል። ማረጥ በራሱ በሽታ አይደለም። ነገር ግን አንዳንድ ሴቶች ምቾት የሚነሱ ምልክቶቹ ሊያስተናግዱ ይችላሉ። በተለይም አንዳንዶቹ በእንቅልፍ፣ ስሜት፣ ጾታዊ ግንኙነት፣ ማህበራዊ ግንኙነቶች እና በስራ ላይ ተጽእኖ ማሳደር የሚደርሱ ምልክቶች ሊያዩ ይችላሉ። እንዲህ ሲሆኑ ተገቢ የህክምና እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል።


ማረጥ ለምን ይከሰታል?

እንቁላል አመንጭ የሆኑት የሴት አካል (እንቁልጢ / ኦቫሪ) በተፈጥሮ ያላቸው “የእንቁላል ክምችት” መጠን ውስን ስለሆነ ከእድሜ ጋር እየቀነሰ ይሄዳል። ሴት ልጅ ያላት “የእንቁላል ክምችት መጠን” ከተወለደች በኋላ አይጨምርም። ሴት ጽንስ ገና በእናቷ ማህጸን ውስጥ እያለች ወደስድስት ሚሊዮን የሚጠጋ ታዳጊ እንቁላል ይኖራታል። ስትወለድ ይህ ቁጥር ወደሁለት ሚሊዮን አካባቢ ይቀንሳል።


ለአቅመ ሄዋን ደርሳ የወር አበባ ማዬት ስትጀምር ወደግማሽ ሚሊዮን ገደማ እንቁላሎች ይቀራሉ። የወር አበባ ማየት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ በየወሩ በሺዎች የሚቆጠሩ እንቁላሎች ይረግፋሉ። በየወሩ ጽንስ መሆን የሚችለው የዳበረ እንቁላል (ovulated egg) አንድ ብቻ ቢሆንም ሌሎች በርካታ አጃቢ እንቁላሎች አብረው በየወሩ ይወርዳሉ (atresia)።


እንዲህ እያለ ቀስ በቀስ የእንቁላል ክምችት መጠን በሂደት እየቀነሰ ይሄዳል። ወደአርባ አመት አካባቢ ቀሪ የእንቁላል ክምችት መጠን ከሶስት በመቶ በታች ይቀራል። አርባዎቹ ማገባደጃ እድሜ ላይ የሚቀሩት የእንቁላል ክምችት ከአንድ ሺህ ያነሰ ይሆናል። በዚህ ጊዜ በቂ የኢስትሮጅን ምርትን ለማመንጨት አይሆንም። ማረጥ የሚመጣው እንዲህ ነው።


የማረጥ ሂደት ደረጃዎች

ማረጥ የአንድ ጀምበር ክስተት ሳይሆን በሶስት ደረጃዎች የሚገለጽ በእድሜ ጸጋ የተባረከች ሴት የህይወት ጉዞ ነው። ሶስቱ የማረጥ ደረጃዎች የሚከተሉት ናቸው፤


1. ቅድመ ማረጥ (perimenopause)

•         የሴት ሆርሞን መጠን የሚዋዥቅበት የሽግግር ወቅት ነው፣

•         ኦቫሪዎች ቀስ በቀስ እንቁላል እና የሴት ሆርሞኖች (ኢስትሮጅን እና ፕሮጀስትሮን) ማምረት ይቀንሳሉ፣

•         የወር አበባ መደበኛ ኡደት ይዛባል፣

•         የማረጥ ምልክቶች መታዬት ይጀምራሉ (ለምሳሌ ብልጭ የሚል ትኩሳት፣ ማላብ፣ የእንቅልፍ ችግር፣ የስሜት መለዋወጥ እና ድካም ሊጀምሩ ወይም ሊበዙ ይችላሉ) ፣

•         በአርባዎቹ አጋማሽ እድሜ ይጀምራል።

•         በዚህ ጊዜ እርግዝና ሊከሰት ይቻላል።


2. ማረጥ (menopause)

•         አንዲት ሴት የወር አበባ ሳታይ ለ12 ተከታታይ ወራት ሲያልፉ

•         የኦቫሪ እንቁላልን የማምረት ተግባር ሲያከትም ማለት ነው። እንቁልጢዎች ሙሉ በሙሉ እንቁላል ማምረት ስላቆሙ ከዚህ በኋላ እርግዝና የለም።


3. ድህረ ማረጥ (postmenopause)

•         የወር አበባ ከነአካቴው ካቆመ በኋላ ያለው ቀሪው የሴትነት ህይወት ይገልጻል።

•         እንደትኩሳት ያሉ የማረጥ ምልክቶች በጊዜ ሂደት መጥፋት ይጀምራሉ። በተቃራኒው እንደ የብልት መድረቅ፣ የሽንት ፊኛ ችግሮች፣ የአጥንት መሳሳት ያሉ ሌሎች ምልክቶች ሊቀጥሉ ወይም ሊባባሱ ይችላሉ።

•         ከዚህ በኋላ የሚመጣ የማህጸን መድማት ካንሰር ሊሆን ስለሚችል በቶሎ መመርመር ይፈልጋል።


የማረጥ ምልክቶች

በማረጥ ወቅት በርካታ ሴቶች የተለያዩ ምልክቶቹ ያሳያሉ። በተለይም አንዳንዶቹ በእንቅልፍ፣ ስሜት፣ ጾታዊ ግንኙነት፣ ማህበራዊ ግንኙነቶች እና በስራ ላይ ተጽእኖ ማሳደር የሚደርሱ ምልክቶች ሊያዩ ይችላሉ። የማረጥ ምልክቶች ከዚህ እንደሚከተለው አናብራራቸው።


የእርጣት ማተኮስ (hot flashes)

ሰውነት ሙቀት ሙቀት ማለት በተለይም ደረት አካባቢ የሚነሳ የሚዘፍቅ ማተኮስ፣ ሌሊት ላይ ማላብ እና የሚያስጨንቅ ውስጣዊ ማተኮስ የተለመደው የእርጣት ምልክት ነው። ይህ ማተኮስ ድንገት ብልጭ ብሎ የሚመጣ ከደረት / ፊት ላይ የሚሰማ ኃይለኛ የሙቀት ማዕበል ነው። ሙቀቱ ሲያልህ ቀዝቃዛ ላብ እና ብርድ ብርድ ማለት ይኖራል።


ወደማረጥ እድሜ ክልል ሲገባ የሚታየው የመጀመሪያ ምልክት ነው። ምልክቱ መታዬት ከጀመረ በአማካይ ከ7-10 ዓመታት ሊቆዩ ይችላሉ።


ይህ ስሜት የሚረብሽ ከሆነ፣ በእንቅልፍ/ሥራ ላይ ተጽዕኖ ካሳደሩ የሕክምና አማራጮችን ያማክሩ። በቀላሉ ሊያከም የሚችል ስለሆነ ብቻን በዝምታ መሰቃየት አያስፈልግም። ስለአማራጭ ህክምናዎቹ በዝርዝር በዚህ ሊንክ ታገኙታላችሁ።


እንቅልፍ መዛባት

የእንቅልፍ ችግሮች በማረጥ ወቅት የተለመዱ ናቸው። ማታ ላይ የሚመጣ ሙቀት እና ማላብ አንዱ እንቅልፍ የሚነሳ ችግር ነው። ከረጅም እንቅልፍ በኋላ የማረካ መሆን እና ድክም ብሎ መነሳት ሊያጋጥም ይችላል።


ጥሩ ጭልጥ ያለ የሚያረካ እንቅልፍ ለመተኛት ከሚረዱ ምክሮች የሚከተሉትን ያጠቃልልላሉ፤ የመሞቅ ስሜትን እና ማላብን ማከም፣ ወጥ የሆነ የመተኛ ሰአት ማበጀት፣ እንቅልፍ ከልካይ ነገሮችን ማስወገድ (ከመሸ ቡና መጠጣት፣ አልኮል፣ ሲጋራ፣ ስልክ/ቴሌቪዥን)።


የስሜት ለውጦች

ያለምንም ምክንያት ድንገት ሳይታሰብ በሐዘን ስሜት ተዋጥኩ፣ እምባ እምባ አለኝ፣ ላብድ ነው እንዴ ብዬም አሰብኩ ወዘተ የሚሉ ያልተለመደ የስሜት መለዋወጥ የእርጣት ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ።


ታይቶ በማይታዎቅ ሁናቴ በባነነ በተነነው ብስጭት ብስጭት ማለት ስለሚኖር ከባል፣ ከዘመድ፣ ከስራ ባልደረባ ጋር መጋጨት ሊያመጣ ይችላል።  ምክንያቱ የማይታዎቅ ጭንቀት እና የስሜት መዋዥቅ እንደሚሰማቸው ብዙዎች ይገልጻሉ። በትንሹ መከፋት እና ወዲያዉኑ የጥፋተኝነት ስሜት መሰማትም ይታያል። በጥቅሉ “ምን ነካኝ?” የሚያስብል ለውጦች ናቸው። ከየት መጣ የሚያስብል አጥንት ድረስ የሚሰማ ብቸኝነት ስሜት ሊኖር ይችላል።


እንደዚህ ባስ ያለ ምልክት ሲኖር ከእርጣት ሆርሞን ህክምና ባሻገር የስነ-ልቦና ህክምና እና ድጋፍ ማግኘት ያስፈልጋል።


የአእምሮ መጨገግ (“brain fog”)

የአንጎል መጨገግ ሲባል አየእምሮ ጭጋግ መልበስ፣ የማስታዎስ ችግር፣ ትኩረት ማጣት እና መሰል ተዛማጅ ለውጦችን የሚይዝ አገላለጽ ነው።


ሁሉንም ነገር ታስታውስ የነበረች ሴት አሁን ማስታዎስ ፈተና ይሆንባታል። ማን ምን እንዳለ እና መቼ፣ የልደት ቀን፣ የተደባበረችበት ቀን ሁላ ልቅም አድርጋ የምታስታውስ የነበርች ሴት አሁን ስልኳን የት እንዳለ ትረሳዋለች። ስራ ለመከወን ወደማድ ቤት ገብታ ምን ለመስራት አስባ እንደነበር ሦስት ጊዜ ደጋግማ ታስባለች። ትኩረት መሰብሰብ ቀላል አይሆንም። ራስ ምታትም ሊኖር ይችላል።


እነዚህ ሁሉ ለውጦች በሆርሞን ህክምና ይታገሳሉ። ከሆርሞን ህክምና በተጨማሪ የስራ ጫና በመቀነስ፣ ማስታዎሻ መዝገብ በመያዝ፣ እንቅልፍ በማስተካከል ይሻሻላሉ።


የወሲብ ስሜት መቀነስ

ከማረጥ ጋር የተያያዙ በርካታ የማህጸን እና ብልት ለውጦች ያሉ ሲሆን በዋነኛነት የብልት መድረቅ እና የወሲብ ስሜት መቀነስ ይገኙበታል። በወሲብ ጊዜ ህመም እና ብልት ማሳከክ / ማቃጠል ያጋጥማቸዋል።


የሽንት ማጣደፍ እና ተደጋጋሚ የሽንት ኢንፌክሽንም ያስቸግራል። ሽንት መቋጠርም ያለመቻል ምልክቶች ይከሰታሉ። አንዲት ሴት ስታስነጥስ ወይም ስትስቅ ሽንት ማምለጥ ሲከሰት የሚያሳፍር ነገር ሊሆን ይችላል።


እነዚህ ለውጦች በቀላሉ መታከም የሚችሉ ሲሆኑ የኢስትሮጅን ቅባቶች / ክሬሞች በመቀባት ይስተካከላሉ።


የክብደት እና ሜታቦሊክ ለውጦች

ሌላው ብዙ ሴቶችን የሚያበሳጨው የማረጥ ምልክት ጂም እየቀጠቀጡ፣ ምግብ እየተጠነቀቁ ክብደት መጨመር ነው። በተለይም ዳሌ እና ጭን / እግር ላይ የነበረ ጮማ ወደቦርጭ ይዛወራል። የሞት ሽረት ብትታገል ተስፋ በሚያስቆርጥ ሁናቴ ቦርጭ እየጨመረ ይሄዳል። እነዚህ የሚደረጉ አካላዊ ለውጦች በሴቶች በራስ የመተማመን ስሜት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራሉ።


ይህ የአንቺ ስንፍና አይደለም። የሆርሞን ለውጡ ያመጣው ነው። የሴት ሆርሞን ሲቀንስ የምግብ ስርአተ እንሽርሽሪት ላይ ለቅጥ ይኖራል፣ ሜታቦሊዝም ዝግ ይላል፣ የበላሽው አንድ እፍኝ አይቃጠልም። አጥንት እና ጡንቻ እየሳሳ፣ ቦርጭ እየፋፋ ይሄዳል። አንዳንዴ ክብደት ስትለኪው ሳይጨምር ቦርጭ ግን እየገፋ ይሄዳል።


መፍትሄው የጀመርሽውን አመጋገብ ስልት የበለጠ ማጠንከር ነው። እንቅስቃሴሽን መቀጠል ያስፈልጋል። በተለይም ጢንቻ የሚያጠነክሩ ስፖርቶች መጨመር ጡንቻን ይጠብቃል፣ ቦርጭን ያቃጥላል።


ሌሎች የእርጣት ምልክቶች

ብዙ ያልተለመዱት ሲኖሩ ግን የሚያሳስቡት ሌሎች የማረጥ ምልክቶች የሚከተሉትን ያካትታል፤

  • የአጥንት እና መገጣጠሚያ ህመም፣
  • የቆዳ መድረቅ፣
  • የጸጉር መሳሳት፣
  • ማይግሬይን መሰል የራስ ህመም፣
  • ከልክ ያለፈ የድካም ስሜት፣
  • የልብ ምት መፍጠን።

የህክምና አማራጮች

ከላይ የዘረዘርናቸው ሁሉም የማረጥ ምልክቶች በግልጽ ስለማይታዩ ለሰው ለማስረዳት ይከብዳሉ። ባል ብትነግሪው ላይረዳቸው ይችላል። አስጠልቼሽ ቢሆን እንጂ እንዲህ በአንዴ እንዴት ተለወጥሽ ብሎ ሊያኮርፍ ይችላል።  ጓደኛሽን ብታማክሪያት ድራማ ሊመስላት ይችላል። አለቃ እና የስራ ባልደረባ እያለመጥሽ ሊመስለው ይችላል። በዚህ የተነሳ ብዙ ሴቶች ህመማቸውን አምቀው መደበቅ ይመርጣሉ። ነገር ግን በቀላሉ መታከም የሚችል ስለሆነ የባለሙያ ድጋፍ መፈለግ ይመከራል። ብቻሽን ችለሽ መሰቃየት አይገባም። ተገቢ ድጋፍ እና ህክምናዎች ካገኙ ሴቶች የማረጥ ሽግግሩን ቀላል ማድረግ ይችላሉ፤ ከማረጥ በኋላ ጤናማ እና ጣፋጭ ህይወት መኖር ይችላሉ።


የእርጣት ምልክቶችን ለማስታገስ የሚረዱ በርካታ የህክምና አማራጮች አሉ። ለእያንዳንዷ ሴት የሚስማማው ህክምና የሚወሰነው በምልክቶቹ ክብደት/ብሶት፣ እድሜ፣ የወር አበባ ከቆመ ስንት አመት ሆነው? የራስ ወይም የቤተሰብ የህክምና ታሪክ (የጡት/ማህጸን ካንሰር፣ የልብ ህመም፣ የደም መርጋት ታሪክ መኖር አለመኖር)፣ የሴቷ የግል ምርጫ ወዘተ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው።


የአኗኗር ዘይቤ መፍትሄዎች እና ራስን የመንከባከብ ስልቶች

ፍቱን የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ በማምጣት ከቀላል እስከ መካከለኛ የእርጣት ምልክቶችን ማከም ይቻላል። ለብዙ ሴቶች ስሜቶችን ይቀንሳል። ከሙቀት ሙቀት ማለት ስሜት ማስታገስነት ባሻገር ከእርጣት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ተጓዳኝ በሽታዎችን ለመከላከል (ለምሳሌ አጥንት መሳሳት፣ ስኳር፣ ቦርጭ፣ ልብ ህመም ወዘተ) ይጠቅማል።


አመጋገብ ማስተካከል ወሳኝ ነው። አትክልት እና ፍራፍሬ ማዘውተር፣ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን መቀነስ ይገባል።  እንደ አኩሪ አተር፣ ለውዝ እና ተልባ ያሉ ፋይቶኢስትሮጅንን ማካተት ይጠቅማል። ካልሲየም እና ቫይታሚን ዲ የበለጸጉ ምግቦችም ለአጥንት ጤና ይረዳሉ። በላብ የሚወጣውን ፈሳሽ ለመተካት ውሃ በደንብ ጠጪ። በአንጻሩ ሙቀት ስሜትን የሚቀሰቅሱ ትኩስ መጠጦች፣ አልኮል እና ቅመም የበዛባቸው ምግቦችን ይቀንሱ።


አካላዊ እንቅስቃሴ ማዘውተርም ይጠቅማል። ከመደበኛ የኤሮቢክ እንቅስቃሴ (የእግር ጉዞ ማድረግ፣ ብስክሌት መንዳት፣ ዋና፣ ሩጫ፣ ዳንስ ወዘተ) በተጨማሪ ጡንቻ የሚያጠነክሩ የጥንካሬ ስፖርቶችን (ትናንሽ ክብደትቶች ማንሳት፣ የሚወጠሩ ባንዶች መስራት፣ ሲት አፕ፣ ፑሽ አፕ፣ ቁጭ ብድግ ስኳት ማድረግ፣ ግድግዳ መግፋት ወዘተ) መስራት ክብደትን ለመቆጣጠር፣ አጥንትን ለማጠንከር ይረዳሉ። መንፈስን ዘና የሚያደርጉ የዮጋ እንቅስቃሴዎችም ይረዳሉ። የብልት ጡንቻ ስፖርቶች (kegel exercises) የማህጸን እና ሽንት ፊኛ አቃፊ እንዳይላላ ይረዳል።


እንቅልፍ ለማስተካከል መስራትም ይፈልጋል። መደበኛ የእንቅልፍ መርሃ ግብር ማውጣት እና መተግበር፣ አእምሮን የሚያረጋጉ ልማዶችን ማድረግ (ለምሳሌ ዮጋ፣ ሜዲቴሽን፣ ጸሎት ማድረግ፣ በረጅሙ መተንፈስ ልምምዶች ወዘተ)። ከመተኛቱ በፊት እንቅልፍ የሚከለክሉ ካፌይን / አልኮልን ያስወግዱ።


ታዲያ በዚህ ወቅት ባል እና ሚስት በግልጽ ስለእርጣት መነጋገር አለባቸው። በተለይ ባል የባለቤቱን ስሜት ለውጦች በደንብ መረዳት ይገባዋል::


በጾታዊ ግንኙነት ጊዜ በሚከሰት ህመም ሴቷ ደስተኛ ካልሆነች ትዳር ላይ ችግር እንዳይፈጠር በግልፅ በመነጋገር ህክምና መሻት ይገባል። ከኢስትሮጂን ቅባቶችን /ክሬም/ በተጨማሪ ብልት ማለስለሻ ቅባቶችን መጠቀም ያስፈልጋል::


የእርጣት ሆርሞን መድሃኒቶች (Menopausal Hormone Therapy, MHT)

የእርጣት ሆርሞን መድሃኒት / ቴራፒ በጣም ዉጤታማ እና ደህንነታቸው የተረጋገጠ መድሃኒቶች ናቸው። የሴት ሆርሞንን በመድሃኒት በመጨመር የማረጥ ምልክቶችን ለማስታገስ ይረዳሉ። በተጨማሪም የአጥንት መሳሳትን ለመከላከል ጥቅም ይሰጣሉ። የብልት መድረቅንም ያክማሉ።


በተለያዩ መልክ ሊሰጥ ይችላል (የሚዋጥ እንክብል / ክኒን፣ የሚቀባ ክሬም / ጄል፣ ቆዳ ላይ የሚለጠፍ/የሚነፋ ወዘተ ሊሆን ይችላል)። ይህ የሆርሞን መድሃኒት የሴት ሆርሞን የሆኑት ኢስትሮጅን እና ፕሮጀስትሮን ድብልቅ ነው። ማህጸናቸው በተለያዬ ምክንያት በኦፕሬሽን የወጣላቸው ሴቶች ኢስትሮጂን ብቻ ያለው መድሃኒት ይታዘዝላቸዋል።


እነዚህ የሆርሞን መድሃኒቶች የሚታዘዙት ለሚከተሉት ሴቶች ነው፤

•         እድሜያቸው ከ 60 ዓመት በታች፣

•         የወር አበባቸው ከቆመ ከ10 ዓመታት ያልበለጠ፣ እና

•         የሆርሞን መድሃኒት የሚከለክል የጤና ችግር የሌለባቸው (ካንሰር፣ የደም መርጋት)


የሆርሞን መድሃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት ሊኖራቸው ይችላል። በተለይም የጡት/ማህጸን ካንሰር አለመኖሩ ካለተረጋገጠ እና የካንሰር ተጋልጭነታቸው ከፍተኛ ለሆኑ ሴቶች አይሰጡም። በተለይ ክኒኖቹ የደም መርጋት አደጋን ሊጨምሩ ይችላል።


ነገር ግን እነዚህ ስጋቶች ትንሽ ናቸው። ጥቅሙ ስለሚያመዝን አብዛኛዎቹ የህክምና መመሪያዎች ለአብዛኛዎቹ ሴቶች እንዲሰጥ ይመክራሉ።


ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ።


በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ  Blog, Telegram, YouTube & Tiktok ይከታተሉ።

ጥያቄ፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ካለዎት በዚህ አድራሻ ሊንክ ይጻፉልኝ።

ይህን መረጃ ጠቃሚ ሆኖ ካገኙት ለሌሎች ያጋሩ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top