እርጣት (menopause)

ማረጥ የሴቶች ሆርሞን ኡደት አንዱ ምዕራፍ ነው። እርጣት የሚባለው የሴት የወር አበባ በቋሚነት የሚቆምበት ጊዜ ነው። ይህ የሚሆነው ኦቫሪ እንቁላልን ማምረት ማቆም ተከትሎ የሴት ሆርሞኖች (ኢስትሮጅን፣ ፕሮጀስትሮን) ስለሚቀንሱ ነው። የወር አበባ ሙሉ በሙሉ ከመቆሙ በፊት የሚቆራረጥበት የሽግግር ወራት/አመታት ሊኖሩት ይችላሉ። በአብዛኛው ከ45 እስከ 55 አመት እድሜ ላይ ይመጣል።


የወር አበባ በእርግዝና፣ በህመም፣ በእርግዝና መከላከያ መድሃኒት ምክንያት ቢቋረጥ እርጣት አይባልም።


የማረጥ ምልክቶች

ማረጥ ኖርማል የሴትነት ህይወት ተፈጥሯዊ ምእራፍ እንጅ በሽታ አይደለም። ብዙ ሴቶች ሄድ መጣ የሚሉ ቀለል ያሉ የማረጥ ምልክቶች ብቻ ይታይባቸዋል።


ነገር ግን አንዳንድ ሴቶች ምቾት የሚነሱ ምልክቶቹ ሊያስተናግዱ ይችላሉ። በተለይም አንዳንዶቹ በእንቅልፍ፣ ስሜት፣ ማህበራዊ ግንኙነቶች እና በስራ ላይ ተጽእኖ ማሳደር የሚደርሱ ምልክቶች ሊያዩ ይችላሉ። እንዲህ ሲሆኑ ተገቢ የህክምና እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል።


የማረጥ ምልክቶች መካከል፤

  • ሰውነት ሙቀት ሙቀት ማለት 🔥 በተለይም ደረት አካባቢ የሚነሳ የሚዘፍቅ ማተኮስ፣ ሌሊት ላይ ማላብ (hot flushes)፣
  • የእንቅልፍ ማጣት፣
  • የስሜት ለውጦች፤ ብስጭት ብስጭት ማለት፣ ጭንቀት፣ የስሜት መዋዥቅ
  • ራስ ህመም፣ አእምሮ ጭጋግ መልበስ፣ የማስታዎስ ችግር፣ ትኩረት ማጣት፣
  • የልብ ምት መፍጠን፣
  • የብልት መድረቅ፣ የወሲብ ስሜት ማጣት፣ የሽንት ማጣደፍ፣ ተደጋጋሚ የሽንት ኢንፌክሽን ወዘተ ይገኙበታል።

የእርጣት ህክምና

እርጣት ህክምና አለው። በሆርሞን መድሃኒት፣ ካለሆርሞን መድሃኒት ወይም ካለመድሃኒት ቀላል የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች በማድረግ ሊታከም ይችላል።


የሆርሞን ህክምናዎች (hormone replacement therapy – HRT / menopausal hormone therapy – MHT) የሴት ሆርሞኖችን የኢስትሮጅን እና ፕሮጀስትሮን በመድሃኒት ይተካል። ይህ ህክምና በጣም ውጤታማ ነው። በተለይም ማተኮስን፣ ላብን እና የብልት ድርቀትን ያሻሽላሉ። በተጨማሪም የአጥንት መሳሳትን ይከላከላሉ፣ የአጥንት ስብራትን ይቀንሳሉ። እነዚህ መድሃኒቶች የሚታዘዙት የወር አበባ ከቆመ ጀምሮ ከአምስት እስከ አስር አመት ሊሰጡ ይችላሉ። በታብሌት መልክ፣ በጄል መልኩ፣ በሚነፋ፣ በሚቀባ፣ በሚለጠፍ አይነት በተለያዩ አይነቶች ሊሰጥ ይችላል።


የሆርሞን ህክምናዎች የሚከለከሉበት ሁኔታዎች አሉ። ለምሳሌ ካንሰር ካለ፣ የደም መርጋት ካለ እነዚህ የሆርሞን መድሃኒቶች አይሰጡም። ሆርሞን ለሚከለከሉ ሴቶች ሆርሞን የሌላቸው መድሃኒቶች አሉ።


ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ።


በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ  Blog, Telegram, YouTube & Tiktok ይከታተሉ።

ጥያቄ፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ካለዎት በዚህ አድራሻ ሊንክ ይጻፉልኝ።


ይህን መረጃ ጠቃሚ ሆኖ ካገኙት ለሌሎች ያጋሩ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top