ኢትዮጵያዊያን ሲናደዱ፣ ሲጨነቁ፣ በንዴት ድብን ሲሉ ‘ቆሽቴ አረረ’ ይላሉ። በእርግጥ ይህ አገላለጽ ምን ትርጉም አለው?
ይህ ንግግር ስለ ስኳር ህመም መነሻ ምክንያት ያመላክታል። ምንም እንኳን ሰዎች ስለሕክምና የአስኳላ ትምህርት ባይኖራቸው ስለበሽታ አመጣጥ ያላቸውን ጥንታዊ ፍልስፍናዊ አረዳድ ይዳስሳል። ስንቆጣ ‘ኧረ ቆሽቴ አረረ፣ አቃጥለህ ልትገድለኝ እኮ ነው‘ ስንል፤ በሃይል ስንበሳጭ ቆሽት ላይ ምን ጉዳት እንደሚፈጠር እና ከስኳር በሽታ ጋር እንዴት እንደሚገናኙ እንይ።
ቆሽት (pancreas) እና የስኳር ህመም
ቆሽት በሆድ ውስጥ የሚገኝ ኤንዛይም እና ሆርሞን የሚያመነጭ የሰውነት ክፍላችን ነው። ቆሽት ኢንሱሊን የሚባል ወሳኝ ሆርሞን ያመነጫል። የኢንሱሊን ሆርሞን ዋና ተግባሩ ለሰውነታችን ተቀዳሚ ነዳጅ የሆነውን ግሉኮስ ወደህዋሶቻችን እንዲገቡ በማገዝ ለሃይል ሰጪነት / እንደነዳጅ እንዲቃጠል ያደርጋል። ስኳሩን ከደም ውስጥ አውጥቶ ወደ ሴሎች / ህዋሳት ሰርጎ በመግባት ሰውነት ለሃይል ምንጭነት እንዲጠቀምበት ያደርጋል።
እንደሚታወቀው ግሉኮስ የሰውነታችን ዋና ነዳጅ ስለሆነ ሁሉም ህዋሶቻችን ይፈልጉታል። በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን የሚቆጣጠረው ሆርሞን ኢንሱሊን ነው። የኢንሱሊን ምርት ወይም ተግባር መስተጓጎል በሚፈጠርበት ጊዜ ስኳር ጥቅም ላይ መዋል ስለማይችል ደም ውስጥ እየተከማቸና እየበዛ መሄድ ይጀምራል። ስኳር በደም ውስጥ እየተከማቸ በጊዜ ሂደት ወደ አደገኛ ደረጃ ከፍ በማለት ለተለያዩ የጤና ችግሮች ይዳርጋል።
ይህ የቆሽት ሆርሞን የማምረት ስራ መስተጓጎል ሰዎች ሲናደዱ ‘ቆሽቴ አረረ’ ከሚሉት ጋር የሚቀራረብ ጽንሰ ሃሳብ ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያዊያን “ቆሽቴ አረረ” አገላለጽ ከስኳር ህመም መነሻ ምክንያትን ያንፀባርቃል።
በቆሽት ላይ የተራዘመ ጫና ሲኖር የኢንሱሊን ምርት ይቀንሳል። ነገር ግን መናደድ እና መበሳጨት ብቻ በድንገት ቆሽትን አቃጥሎ አያሳርረውም። የቆሽት ስራ መስተጓጎል ሂደት ረዥም ዓመታትን የሚፈጅ የሜታቦሊክ ጫና እንጅ በንዴት ብቻ አይደለም።
ጭንቀት በደም ስኳር ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?
ስትናደድ፣ ስትጨነቅ፣ ስትፈራ ወይም ስትደነግጥ ሰውነት ራስን ከጥቃት የመከላከል ምላሽ ይሰጣል። ከአደጋ ለማምለጥ የሚረዱ የነርቭ ሥርዓት ይቀሰቀሳል (sympathetic nervous system)፣ የጭንቅ ወቅት ሆርሞኖች ከአድሬናሊን እጢ ይለቀቃሉ። እነዚህ ለውጦች የደም ስኳር ይጨምራሉ። የኢንሱሊንን ምርት ሂደት እና ተግባር ያውካሉ። ይህ በድንጋጤ ወቅት ጉልበት/ነዳጅ ሰብስበን ከጥቃት ለማምለጥ ወይም ለመጋፈጥ እንዲረዳ ሆኖ የተዘጋጀ ተፈጥሯዊ ምላሽ ነው።
ነገር ግን የስኳር ህመም ወይም ቅድመ የስኳር ህመም ላለባቸው ሰዎች በጭንቀት ጊዜ ድንገተኛ የደም ስኳር ከፍ እንዲል የሚያደርግ እና ቁጥጥርን አስቸጋሪ የሚያደርግ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ “ተናድጄ ስለነበር የስኳር ህመሜ ተባብሷል” ሲል ትክክል እያለ ነው።
የተራዘመ ጭንቀት እና ከፍተኛ ጫና ሲኖርብን ቆሽት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያመጣል። ከልክ ያለፈ ጭንቀት፣ ብስጭት፣ ንዴት ወዘተ ቀስ በቀስ ለቆሽት መዳከም የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል። ጭንቀት ብቻዉን በራሱ የስኳር በሽታን ባያመጣም በተለይም ቦርጭ ላላቸው፣ ለማይንቀሳቀሱ፣ ጤናማ አመጋገብ ለማያዘወትሩ፣ የዘር ተጋላጭነት ላለባቸው እንደአንድ ተጨማሪ አጋላጭ ምክንያት ይሆናል።
‘ቆሽቴ አረረ’ የሚለው ንግግር ከቆሽት እና ስኳር ህመም ባሻገርም ከፍተኛ ጭንቀትና የአእምሮ ጤና ችግሮች አካላዊ ጤና ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተጽእኖዎች ያንጸባርቃል። ስሜታችን እርር ሲል ሙሉ ሰውነታችን እንደሚቃጠል በተለይም ሜታቦሊዝም እንደሚያዛባ ያጠይቃል።
ቆሽታችን እንዳያር ምን እናድርግ?
የኑሮ ውድነቱ፣ የአናዳጁ መብዛት ሕይወትን ከባድ አድርጎብናል። ቢሆንም ከጤና የሚበልጥ ሃብት የለምና በተቻለን ጭንቀት ለመቀነስ ማሰብ፣ ማቀድና ተግባራዊ እርምጃዎች መውሰድ ይገባል።
ጭንቀትን መቆጣጠር ያስፈልጋል። እኛ ላልፈጠርነው፣ የማይመለከተን ወይም ከእኛ ቁጥጥር ውጭ ላለ ችግር አብዝቶ መጨነቅ መጠበብ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ይልቁንም በእኛ አቅም ማድረግ የምንችለው መፍትሄ ላይ ብቻ ማተኮር ይገባል። ባስ ካለ ከባለሙያ ጋር መመካከር።
ማስታዎስ ያለብን ቆሽትን የሚያሳርረው የአእምሮ ጭንቀት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም በርካታ ጫናዎች አሉ። ጤናማ አመጋገብ ከሌለን ቆሽትን ያስጨንቃል፤ በሂደት ቆሽትን ይጠብሳል። በተቃራኒው ጤናማ አመጋገብ ስንከተል ቅሽት ያገግማል፣ ይለመልማል።
በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግም ቆሽትን ይጎዳል። ስለዚህ እየተንቀሳቀስን ቆሽታችንን እናስደስት።
ከመጠን ያለፈ ውፍረት በተለይም ቦርጭ ለቆሽት አደገኛ ነው። ሸንቀጥ ስንል ደግሞ ቆሽታችን ትቦርቃለች፣ ፋታ ታገኛለች።
አልኮል እና ሲጋራ ማጨስ ለቆሽት መርዝ ናቸው። አልኮል ስንጠጣ እና ሲጋራ ስናጨስ ቆሽትን ምድጃ ላይ ጥዶ እርርርርር አድርጎ እንደማቃጠል አስቡት። ጣፋጭ ነገሮችንም ማዘውተር እንደዚያው ለቆሽት ጎጂ ነው። አልኮል፣ ሲጋራ፣ ጣፋጭ ምግቦችን ስናቆም ደግሞ ቆሽት እፎይ ትላለች።
ማጠቃለያ
“ቆሸቴ አረረ” አገላለጻችን ቅኔያዊ ነው። ጭንቀት፣ ውጥረት፣ ብስጭት ስናበዛ ቆሽታችንም በመብሰክሰክ እንደምትጎዳ የሚያረዳ የአበው ስልታዊ አነጋገር ነው። በተለይም ቀድሞውኑ ለስኳር ህመም ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ጭንቀት ሲጨመርባቸው ለስኳር ህመም አብልጠው የተጋለጡ ይሆናሉ።
ሁሉንም ጭንቀት ከህይወት ውጣውረድ ማስወገድ ባንችልም በልክ በመቆጣጠር ቆሽት “ከመቃጠሉ በፊት” ማከም እንችላለን።
ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ።
በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ Blog, Telegram, YouTube & Tiktok ይከታተሉ።
ጥያቄ፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ካለዎት በዚህ አድራሻ ሊንክ ይጻፉልኝ።
ይህን መረጃ ጠቃሚ ሆኖ ካገኙት ለሌሎች ያጋሩ።