ስግጥና ወይስ ፕሮፌሽናሊዝም – ማን ይፈምሳል?

የሰው ልጅን ቀልብ መግዛት አዲሱ ገበያ እየሆነ ነው። የማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪዎች የሚጠቀሙት ዋናው ማጥመጃ ስሜታችንን ነው። የሰው ልጅ ሳይኮሎጂ የገባቸው ናቸው ማህበራዊ ሚዲያ ላይ አሸናፊዎች። የሚያወዛግብ፣ የሚያስፈራ፣ የሚያስቆጣ፣ የሚያነሳሳ፣ የሚያስቅ አሊያም የሚያስደንቅ ድንቃድንቅ ዜና በመርጨት ተከታታዮቻቸውን ያጠምዳሉ። ከባድ ሳይኮሎጂ ነው የሚጫወቱት።


የማህበራዊ ሚዲያ ቫይራል አልጎሪዝም

ቫይራል የመውጣት አልጎሪዝም አስማት አይደለም። በጥበብ የሚመጣ ነው። በፈጠራ የሚሆን ነው። ጮማ የሆነን ሃሜትና ቧልት በኢንተርኔት ያለገደብ ማሰራጨት በሉት። አንድ ሰው የለጠፈውን ቧልት/ኮንቴንት አምስት ሰዎች አይተው ለጓደኞቻቸው ይልካሉ። ተቀባዮቹ እያንዳንዳቸው ወደ ሌሎች አምስት ተጨማሪ ያስተላልፋሉ። እንዲህ እያለ የጀመረ ሃሜት በፍጥነት ሃገር የሰማው ወሬ ይሆናል። ይህ ነው ቫይራል ወጣ የሚባለው።


በማህበራዊ ሚዲያ የመፈመስ ጥበብ የራሱ ሳይንስ አለው። ዋና ዋና ምስጢሮቹ አራት ናቸው፤


የመጀመሪያው የኮንቴንቱ የመጋራት ምጣኔ (share rate) ነው። ከአጠቃላይ እይታዎች ውስጥ ስንቱ አጋራልን የሚለው ዋናው ቫይራል የመውጣት ቁልፍ ነው። የአንድ ፖስት የመጋራት ምጣኔ ከ3% በላይ ከሆነ ቫይራል ይወጣል። ይህ የመጋራት መጠን ላይ ሲደርስ አልጎሪዝሙ እንደተወደደ ይቆጥረውና እንደሰደድ እሳት ለሌሎችም ያዛምተዋል። አንድ ኮንቴንት ቫይራል የሚሆነው በይዘቱ ሳይሆን አንድ አድማጭ/ተመልካች ለሌላ በሚያጋሩት ልክ ነው። ስለዚህ ቫይራል ለመሆን ዋናው ሰዎች እንዴት ያጋሩልኛል የሚለውን ኮድ ማወቅ ነው። አንድ ፖስት በደንብ እንዲጋራ የሚያስፈልጉት ሶስት መሰረታዊ አለባውያን አሉት። እነዚህም የሃሳቡ ሳቢነት/ትኩስነት፣ ሃሳቡ የሚመለከታቸው ተደራሲያን ብዛት (Large applicable audience / total addressable market) እና ልዩ እይታ (unique perspective) መኖር ናቸው። ሰዎች ያዩትን መረጃ የሚያጋሩት ስሜት የሚነካ ከሆነ፣ ግርምት የሚፈጥር  ከሆነ፣ ከእነሱ ጋር የሚዛመድ ከሆነ ነው። ሰው የሚያጋራው የተሰማውን እንጂ የተረዳውን አይደለም። ለምሳሌ ‘ዋው ይሄንን አላውቅም/አልጠበኩም ነበር’ የሚል ስሜት ከፈጠረ አሊያም ‘ይህ በጣም ያስቃል፣ ያምራል፣ ያስገርማል፣ ይደንቃል’ ወዘተ እያሉ ነው የሚያጋሩት። ሌላኛው ደግሞ መልካም እና አዋቂ የሚያስመስለን ከሆነ ነው የምናጋራው (social currency)። ከስሜት ጋር ካልተቆራኘ ቫይራል አይሰራጭም።


ሁለተኛው ቀልብ የሚገዛ አገባብ (የመክፈቻ hook) ነው። አሳ አጥማጅ አሳውን በመንጠቆ እንደሚያጠምደው ሁሉ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ ዜናዎች/መረጃዎች ያበደ እንዲታይ እና እንዲጋራ የተመልካቾችን ትኩረት በመሳብ እንዳያልፉት ቀልብ እንዲይዝ ተደርጎ ይዘጋጃሉ። ገና ከጅምሩ እንደሚታደነው አሳ አፋችንን በማስከፈት እስከመጨረሻው እንድንከታተል ማስገደድ ግድ ነው። አንድ ኮንቴንት ለማዘጋጀት 80% ፈጠራን እና ጊዜን እዚህ መግቢያ ላይ አዉል ይባላል። ‘ስለኮሌስትሮል ዶክተሮቹ የማያውቁት’ ብሎ ሲጀምር ጉጉት ለመፍጠር ነው እንጅ ዶክተሩ የማያውቀዉን መድሃኒት በድፍረት ሊጽፍልህ አይችልም። ‘ስለክትባት የተነገርን ውሸቶች’ ብሎ ሲያምባርቅ ለአልጎሪዝም እንጅ አንድም እውነት አታገኝበትም።  ይህ መግቢያ አጭር እና ቅመም መሆን አለበት። አንዳንድ ፖስቶች ርእስ አይተህ ገብተህ የማይገናኝ ወሬ ይዘው ልታገኝ ትችላለህ። አልጎሪዝሙ ግን መክፈትህን አይቶ እንደተወደደ ይቆጥረዋል። 


ሶስተኛው ቁልፍ የሚስብ ታሪክ ማውራት ነው። አንዴ በመንጠቆ ቀልባቸውን ከያዝክ በኋላ እስከመጨረሻው እንዲከታተሉህ ወሳኙ ማቆያ ታሪክ ነው። የሰዎች ታሪክ ከደረቅ ሳይንስ የበለጠ ቫይራል ይሆናል። ‘የስኳር ህመም ካልታከመ የጤና ችግር ያመጣል‘ የሚል ደረቅ ሳይንስ ከማውራት ‘አጎቴ እኮ ስኳሩን ችላ ብሎ እግሩ ተቆረጠ’ ብዬ ብጀምር አድማጭ ይስባል። ታሪኩ ለመረጃው የሰውነት ገጽ እና ስሜት ያላብሰዋል። ታሪክን ስናካፍል የመረጃውን ጭብጥ ይዞ እንደልቦለድ ልብ አንጠልጣይ፣ እየጦዘ የሚሄድ ሆኖ መጨረሻ ላይ  ፍጻሜ የሚያገኝ መሆን አለበት።


 አራተኛው ተባባሪዎች መፈለግ ነው። በተለይ ከ100 ሺህ በላይ ተከታይ ያላቸው ቀድመው የፈመሱ ሰዎች በተባባሪነት ካጋሩልን በእሳት ላይ ጋዝ እንደማርከፍከፍ ነው። በአንዴ ብድግ ነው የሚለው ፖስታችን። አካውንትህን በአንዴ ነው ሞቅ የሚያደርጉት። በተለይ በተቀራራቢ ዘርፍ ላይ የሚሰሩ ከሆነ ወሳኝ ነው።


የህክምና ጋዎን ለመፈመስ ይሰግጥ ወይስ አይሰግጥ?

ከላይ የጠቀስናቸው የፍምስና ምስጢር ለጤና ትምህርታዊ መረጃ ለሚያስተላልፉ ባለሙያዎችም ይሰራል። ሆኖም የጤና ባለሙያዎች የሚሰሯቸው ኮንቴንቶች ከሌላው ዘርፍ በተለየ የሚያጋጥማቸው ተግዳሮት አሉ። አንደኛው ችግር ትምህርታዊ መረጃዎች በተፈጥሮ ተደራሽነታቸው ውስን ነው። ትምህርቱ አዲስ አይደለም (የሚታዎቅ ነገርን ነው የሚያስተምሩት)፣ ብዙ ተደራሲያን የለውም (የታመመን ሰው ወይ የዚያ ርእስ ተማሪን ነው የሚመለከተው)፣ ከእውነታዉ እንዳይርቅ ለመጠንቀቅ የተለዬ ድራማ ማስመሰልም የለበትም። በእነዚህ ሶስት ምክንያቶች ትምህርታዊ ኮንቴንቶች ብዙ አይታዩም።


በተጨማሪም የጤና ባለሙያዎች እንደውሪ ቲክቶከሮች እንዳሻቸው መሆን አይችሉም። የህክምና ስነ ምግባር ደንብ ገደብ ይጥልባቸዋል። አንድ አላጋጭ ቲክቶከር ቢባልግ ስሙ ቢጠፋ ነው፤ ሌላ ችግር የለውም። አብዛኛው ቲክቶከር ለመፈመስ ይሉኝታ ቢስ መሆን በቂው ነው። እንዲያው የሚያውቁት ሰዎችን ወይ ጎረቤት ካልፈራ ካለይሉኝታ የሚፈልገውን መረጃ ሊያጋራ ይችላል። የሚያጋራው መረጃ፣ የሚያስተላልፈው መልእክት ምን ያመጣል? ማንን ሊጎዳ ይችላል? ለሃገር ይጠቅማል ወይ? ትውልድ ይቀርጻል ወይስ ያበላሻል? ብሎ ማሰብ የለም፤ ሃላፊነት መውሰድ የለም። በህግ የሚያስጠይቅ እንኳን ቢሆን ማንነቱን ደብቆ ሊያደርገው ይችላል።


ባለሙያ ለሆነ ሰው ግን ይህ አይሰራም። የሚታዎቅ፣ ላይሰንስ ያለው ሰው ነው። የጤና ባለሙያ ከግል ስሙ ባሻገር የሙያው ስነ ምግባር ደንብ አለ፣ የሙያ ፈቃድ የሰጠው ባለስልጣን አለ፣ ተገልጋዩ ማህበረሰብ አለ፣ የስራ ባልደረቦቹ አሉ። ይህ ሁሉ ባለድርሻ አካል ነው አብሮ ስሙ የሚጠፋው።  የሙያ ክብር ነው የሚዋረደው። ይህ ሁሉ መርህ እንዳይለቅ ቀፍድደው ይይዙታል። ስለሆነም ቫይራል ለመውጣት ብሎ መረጃን አጋኖ፣ አኮስሦ ወይም አጣሞ የተመልካችን ቀልብ መግዛት አይችልም። ወደእውነታ የቀረበ መረጃ ብቻ ነው ማስተላለፍ የሚችለው።  


በጣም የገባቸው ባለሙያዎች ግን ይህን አጥር አልፈውት ከህክምና ስራ በላይ በማህበራዊ ሚዲያ የተዋጣላቸው ‘ዶክቶከር / ቲክዶክ’ ሆነዋል። ከላይ የጠቀስናቸውን የታይታ ሳንካዎች ለመሻገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተለመደ የመጣው የጤና ባለሙያዎች  ቫይራል የመሆን አንዱ መንገድ ‘ታካሚዎቹ ለመቀረጽ ፈቅደዋል’ በማለት የፈውስ ምስክርነቶችን ማሳየት ነው።


አንዱ ‘አንድስ የሚያክል አተር ፍሬ ከአፍንጫ ጎልጉዬ አወጣሁለት’ እልል በሉ ይለናል። ሌላኛው ‘ይኀውላችሁ ሰላሳ አመት ሽንቱ ሲደማ የነበረን ምእመን የኩላሊት ጠጠር አድቅቄ በተንኩት’ ተአምር ያስመስለዋል። በሌላ ሚዲያ ደግሞ ‘ካንሰሩን መንግዬ አውጥቼ የአልጋ ቁራኛ የሆነውን ወጣት ፈወስኩት’። እናት ዘጠኝ ወር ጽንስን ወደሰውነት አሳድጋ አምጣ ለወለደችው ‘አገላገልኳት፣ በልጅ ባረኳት’ ይሰግጣሉ። ‘ቦርጭን አቅልጬ አጠፋለሁ’ ያለውማ እስካሁን እንዳሳቀኝ አለ።


ሙሉ ኦፕሬሽን ክፍል እንደቲያትር ቤት እየቀረጹ ላይቭ የሚያስተላልፉም ብቅ ብቅ ብለዋል። አባቴ ኦፕሬሽን በተለዬ ትኩረትና ጥንቃቄ የሚሰራ እንጅ ቀረጻው አማረልኝ አላማረልኝ አያልክ የምትኳኳልበት የመድረክ ስራ አይደለም። የሰው ህይወት ላይ አንተውንም! ስም ያለው፣ ታሪክ ያለው፣ ጎረቤቶቹ የሚያውቁት ሰው ነው ኦፕሬሽን እያደረክ ያለኀው! ኦፕሬሽን የሚሰራውስ ከተሻለው በኋላ እንዲያ ቲክቶክ ላይ እራሱን ሲያይ ምን ይሰማዋል? እንዲያው ፈጣሪ የሰጠንን ሙያዊ ችሎታ እዩኝ አድንቁኝስ ልክ ነው የሰው ስቃይ እና ገመና እያሳዩ?!


ታካሚዎችን እንደኮንቴንት ማቅረብ ተገቢ ነው?

የጤና ባለሙያዎች ይዘውት የመጡት አንዱ የ”ይዘት ለውጥ” ታካሚዎችን እንደኮንቴንት መጠቀም ነው። ስለአንድ በሽታ መረጃ አጥንቶ፣ ጽፎ፣ ቀርጾ ከመስራት ይልቅ የታካሚዎችን ህመም፣ ስቃይ፣ የህክምና ሂደት፣ የማገገም ሂደት ወዘተ በማሳዬት ቫይራል ለመሆን የመሞከር ዘዴ ነው። የታካሚዎቹ ህይወት እንደህክምና ሳይንስ ውስብስብ ስላልሆነ ለሁሉም ሰው ለመረዳት ይቀላል፣ ስሜት ይነካል።


ይህ አካሄድ ግን ከማስተማሪያነት አልፎ ወደታካሚ ብዝበዛ ሊሸጋገር የሚችልበት አጋጣሚ አለ። የሙያዊ ስነ ምግባርም ሊጥስ ይችላል።  በመጀመሪያ ደረጃ ‘ታካሚውን አስፈቅደናል’ የሚለው በህግ ፊት ሚዛን የሚያነሳ አይደለም። ታካሚው ለመቀረጽ ፈቃዱን የሰጠው ‘እምቢ ለማለት አስቻይ ሁኔታ’ ሳይኖር ነው። ኦፕሬሽን ሊሰራ ልብሱን አወላልቆ አልቀረጽም ቢል ምን ሊያጋጥመው እንደሚችል ያስባል። አልቀረጽም ያለው ሃኪም እንደድሮው በሙሉ ልቡ ያክመኛል ወይ? ብሎ ይሰጋል። ይሉኝታ ይዞት ነው ግዴለም ቅረጸኝ የሚለው። ፈቃጅ እና አስፈቃጅ እኩል የሃይል አሰላለፍ በሌላቸው ሁናቴ ‘ታካሚውን አስፈቅደናል’ ማለት አይሰራም። የተጻፈም ስላልሆነ አንዱ ተነስቶ ካለፈቃዴ ቀርጾ ተጠቅሞብኛል፣ ሸቅሎብኛል ቢል መከላከያ ማስረጃ የለም። በተለይ የህክምና ዘርፍ የህግ ባለሙያዎች (medical lawyers) እያየሉ ሲመጡ ይህንን ክፍተት ለእንጀራቸው ሲሉ ሊገቡበት ይችላሉ። ሚዲያ ላይ የወጣው ማስረጃ ግን አይፋቅምና ማስተባብያ እንዳያጥረን። ቲክቶክ ላይ የሰበሰብከውን ላይክ አካፍለኝ የሚል ቢመጣስ ምን ልንል ነው? ፌስቡክ ላይ በእኔ ፎቶ ማስታዎቂያነት የሸቀልከውን ኮሚሽን ክፈል ቢልስ ማን ገላጋይ አለ?


ሌላው የሚስፈራኝ ነገር ቢኖር እነዚህ ህመማቸው ጋኃድ የወጣ ሰዎች ከሆስፒታል ወጥተው ወደማህበረሰብ ሲቀላቀሉ ምን ያጋጥማቸው ይሆን? የሚለው ነው። ማህበረሰቡ አዲስ ማንነት ሊሰጣቸው ይችል ይሆን? ስማቸው ተረስቶ ‘ያ በሽተኛ መጣ’ ሊባሉ ይችላሉ እኮ። ‘በሽታህን እንዳታስተላልፍብን’ ተብለውም ሊገለሉ ይችላሉ። በተለይ ልጆች፣ ታዳጊዎች ሲሆኑ በሰፈር በትምህርት ቤት ትልቅ ፈተና ሊያጋጥማቸው፤ ጓደኞቻቸው እንደቀልድ የለጠፉባቸው የፉገራ መጠሪያ የሚያድገውን ማንነት ሊበርዘው ይችላል። ይህ የማያልፍ ጠባሳ ቢጥባቸውስ?


አዎ ለተመልካች ጥሩ ነው፣ አስተማሪ ሊሆን ይችላል። ቅድመ ምርመራ እንዲያደርጉ ሊያግዝ ይችላል፣ ተመሳሳይ ህመም ያለበት ሰው ሌላው ላይ አይቶ በጊዜ እንዲታከም ሊያነቃቃ ይችላል። ግን ወደታካሚ ብዝበዛ እንዳይሄድ ልክ ያስፈልገዋል። የሙያ ስነ ምግባር ጥሶ ወደሙያ ዝቅጠት እንዳያመራ ሃይ ባይ ያሻዋል። ለስግጥና መድረኮች እና ለአልጎሪዝም ምርጥ ቢሆንም ለሙያው አደገኛ የሚሆንበት አካሄድ አለ።


ቫይራልነት ወይስ ፕሮፌሽናልነት – ሙያዊ ስነምግባር ያልጣሰ ፍምስና

ቫይራልነት በራሱ ሃጢያት አይደለም። ችግሩ ቫይራል የመሆን መቋመጥ ከፕሮፌሽናችን ቃለ መሃላ ሲጋጭ ነው። ያልሰገጠ (ሙያዊ ስነ ምግባር ያልሳተ) ፍምስና ማግኘት የማይቻል ባይሆንም በቀላሉ የሚሳካ አይደለም። አሁናዊ መድረኮች ስግጥና ይፈልጋሉ። ለመፈመስ መሰገጥ ዋና እርሿቸው ነው። ማህበራዊ ሚዲያ ጆሮ የሚሰጠው ለሁከት እንጅ ለእውነት አይደለም። ለሰብር ዜና እንጅ ለመልካም ዜና ጊዜ የለንም። ከቁም ነገር ይልቅ ወሬ ነው ሰደድ የሚሰራጨው።


ይዘትን ቫይራል የማውጣት ስትራቴጂ ከህክምና ስነ ምግባር ጋር አብዝቶ ይጋጫል። አንዳንዴ ሊታለፍ የማይገባው ቀይ መስመር ማኖ ያስነካሃል። አልጎሪዝሙ መረጃህን በቀላሉ እና በአጭሩ አስቀምጥ ይልሃል። የህምክና ትምህርቶች እንዲህ እንቆንጽል ስንል ትርጉሙን ሊስት ስለሚችል መጠንቀቅ ይፈልጋል። ቃላት አጠቃቀም ላይም በጥንቃቄ መምረጥ ይፈልጋል። አልጎሪዝሙ የሚሸልመው የሚያስፈራ ወይ የሚያስቅ ነገር ነው። ላስፈራራ ብለህ ‘ስኳር ህመም ጉበትህን ያበላሻል’ ብትል አውዱን ስቶ ሌላ የአእምሮ ጤና ችግር ያመጣል። አልጎሪዝሙ ታሪክ ይመርጣል ብለህ የታካሚህን ታሪክ ብታካፍል ወይ ብትቀርጽ ዋናውን የህክምና ምስጢራዊነት አፈረስክ ማለት ነው።


እንደእኔ እንደእኔ በስግጥና ከመፈመስ የሙያ ስነ ምግባር ይበልጣል። ስለነገ ግድ የሚላቸው፣ ስለሙያ የሚከነክናቸው፣ ስለሃገራቸው መጻኢ ተስፋ የሚያስቡ ባለሙያዎች ከስግጥና ፕሮፌሽናሊዝምን ገንዘብ ያደርጉ ዘንድ እመክራለሁ። የታካሚዎቻችን መረጃ ገሃድ በማውጣት ከሚገኝ ፍምስና የላቤ ደሞዝ ይሻለኛል፣ ባይሆን አገልግሎቴን አሰፋለሁ ማለት ይሻላል። ገና እንስሣት ላይ እየተሞከረ ያለን የህክምና ጥናት ‘በአንድ መርፌ ስኳር ህመምን ጨርሶ የሚፈውስ መድሃኒት ተገኘ’ እያሉ ህዝብን ከማወናበድ እራስን መቆጠብ ይገባል።


ቫይራል የመውጣት የዲጂታል ዘመን እየኖርን እንደመሆኑ ማህበራዊ ሚዲያን ለማስታወቂያ፣ ለማንቂያ፣ ለመንቂያ መጠቀም ያለ ነው። ግን ቫይራል ለመሆን ተብሎ ሙያ አይተውም። በተለይ ጤና ላይ ቀልድ የለም። የጤና ባለሙያ ‘ኮንቴንት ፈጣሪ’ ብቻ ሳይሆን ከፈጣሪ በታች የማህበረሰቡን ጤና ለመጠበቅ መኃላ አለብን። ከቻልክ የጻፍከው ወይ የቀረጽከው ቫይራል ይውጣልህ ነገር ግን ከቃለ መሐላህ እንዳያረክስህ!


የጤና ባለሙያዎች ህክምናውን ከሚዲያ እውቀት አጣምረን ብንይዝ ምንኛ ባማረብን! ከሙያችን ሥነ-ምግባር ሳናፈነግጥ ቫይራል መውጣት ከቻልን እሰየው ነው። እንዲህ ቢሆን የበለጠ ጤናን ተደራሽ አደረኝ ማለት ነው። ሙያና ቁም ነገር እንደማንኛውም ወሬ በፍጥነት የሚሰራጭበት ዲጂታል ቦታ ፈጠርን ማለት ነው። ይህ ካልሆነ ግን ቢቀር ይጠንቀር እንጅ እንዳንወርድ! ባለሙያዉም፣ ቲክቶከሩም፣ ፖለቲከኛውም አብሮ ከወረደ እንደሃገር መቀመቅ መግባታችን ነው።


የስኬት መለኪያ የማህበራዊ ሚዲያ ታይታዎች እና ማጋራቶች ብቻ አይሁን።


በሉ ይህ ኮንቴንት ቫይራል እንዲወጣ ለሌሎችም አጋሩ ፡)


ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ።


በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ  Blog, Telegram, YouTube & Tiktok ይከታተሉ።

ጥያቄ፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ካለዎት በዚህ አድራሻ ሊንክ ይጻፉልኝ።

1 thought on “ስግጥና ወይስ ፕሮፌሽናሊዝም – ማን ይፈምሳል?”

  1. ሸጋ ነው በርታልን! ሳትሰግጥ እንድትፈምስ፣ ከቻልክ ሳትፈምስ እንድትረካ እርሱ እግዚአብሔር ይርዳህ!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top