ኢትዮጵያ ሚሊኒየሙን ከተቀበለች ከጥቂት አመታት በኋላ የሞቀ ቤቴን ትቼ እውቀት ለመገብዬት ዩኒቨርሲቲ ስገባ ከቤተሰብ ጫንቃ ወርጄ ወደ ‘ራስን የመቻል’ ጉዞ የጀመርኩ መስሎኝ ነበር። የሆነው ግን ቦታ ከመቀየር ውጭ እንደእናት ባይሆንም ሌላ ኮምፎርት ዞን ነበር። የትምህርት ክፍያ የለ፣ የቤት ኪራይ አላውቅ፣ የመብራት አይሉኝ! ምግብ አላበስል፣ አስቤዛ አላስብ! ከእንቅልፍ የሚያነቃ ሃሳብ አልነበረብኝም። አንዲት ስራዬ እንደምንም ክላስ መግባትና ፈተናዬን ማለፍ ብቻ!
የምእራባዊያን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ብናይ ግን ከዚህ ይለያል – ገና ሃይስኩል እያሉ ለኮሌጅ ብለው ቀላል ስራ ይጀምራሉ። ቆጥበው ዩኒቨርሲቲ ይገባሉ። እዚያም ካፌም ይሁን ሞል አስተናጋጅነት ተፍ ተፍ እያሉ ነው ትምህርታቸውን የሚያስኬዱት። ነጻ ትምህርት የሚባል የለም። ቤተሰብም ከአስራ ስምንት አመት በኋላ አሽሩሩ አይልም።
የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ኑሮው ብቻ ሳይሆን ትምህርታችንም ቢሆን የነባራዊውን የስራ አለም አይመስልም ነበር። የኔ የህክምና ትምህርት ለምሳሌ መላ ሰባት አመቱን ከህክምና ተማሪዎች ጋር ብቻ በሃኪም አስተማሪዎች ብቻ የሚሰጥ ነበር። የስራ አለም ግን ከሃኪም ጋር ብቻ አይደለም፣ እንዲያውም ሌላ ሃኪም ጋር የምገናኘው አልፎ አልፎ ነው። አብዛኛዉን ስራዬን የምሰራው ከነርሶች ጋር፣ ከፋርማሲዎች ጋር፣ ከላብራቶሪ ባለሙያዎች ጋር፣ ከሪሰርቸሮች ጋር፣ ከጤና አመራሮች ጋር ወይም ሌሎች ባለሙያዎች ጋር በመሆን ነው። የህክምና ስራ የበርካታ ከተለያዩ ዘርፎች የተውጣጡ ብዝሃ-ፕሮፌሽናል ባለሙያዎች የቡድን ስራ የሚፈልግ ሆኖ እያለ ትምህርቱ ግን በተናጥል ለየብቻ ነው። በትምህርት አለም ተገናኝተው የማያውቁ ስራ ላይ አብራችሁ ስሩ ሲባል የሚናቆሩት ለዚያ ነው። የሆነ ጉድለት ሲከሰት ‘ነርሷ ነች፤ ሃኪሙ ነው እንጂ፤ ኧረ ላብራቶሪ ስላልገባ ነው፤ አይ መድሃኒት ዘግተው ነው?’ እያልን የምንደናቆረው እኮ አብረን ተምረን ተገናኝተን ስላላደግን ነው። አንዴ ተመርቆ ማእረግ ከጫነ በኋላማ ሁሉም በየራሱ አትንኩኝ ባይ ሆኖ ይተብታል፤ ተስማምተህ በቡድን ስራ ብትለው ከየት የተማረውን!
ከምረቃ በኋላ አለም ሌላ ነች። ወደእውነተኛ አለም ሽግግሩ በጥፊ እንደመመታት አስደንጋጭ ነው። ‘እሱኮ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነው’ እያሉ የሚያነግሱህ ዘመድ ጎረቤቱ በአንዴ ራስህን ቻል ይሉሃል። ህይወትን እንደአዲስ ሀ ብለህ ለመጀመር ትከሻህ መጫን ይጀምራል። እኔ ከዩኒቨርሲቲ ስወጣ አለም ገሃነም ነበር የሆነብኝ። የቤት ኪራይ፣ የራስን ልብስ ማጠብ፣ ምግብ ማብሰል መማር፣ የማህበራዊ ግዴታዎች ወዘተ በመማሪያ መጽሐፍት ብቻ በገበየሁት እውቀት የሚቻል አልነበረም። የዩኒቨርሲቲ ህይወት ከገሃዱ ውስብስብ ህይወት በእጅጉ የተፋታ ነው። በዪኒቨርሲቲ እና ዩኒቨርስ መካከል አንዳችም ግንኙነት እንደሌለ ነው የተሰማኝ! የስፔሻሊቲ እና ሰብስፔሻሊቲ ስልጠና ቶሎ አከታትዬ የመማሬ ምስጢር ይህ ኑሮን ከመፍራት የመነጨ ይመስለኛል ፡) ትምህርት ላይ ከሆንክማ እያሉ የትራንስፖርት፣ የአስቤዛ የሚልኩልኝ ዘመዶች አላሳጣኝም – የድህረ ምረቃ ዩኒቨርሲቲ ህይወት!
ከዚህ የግል ታሪክ መነጽር ተነስቼ በኢትዮጵያ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ብሄራዊ አገልግሎት ሊጀምር መሆኑን አስመልክቶ ምልከታዬን ላካፍላችሁ ወደድኩ።
ይህ አዲስ የብሄራዊ አገልግሎት የሶስተኛ አመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በየትምህርት ዘርፋቸው ለአንድ አመት ማህበራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ያዝዛል። ሁሉም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በመሰማራት “ነፃ ትምህርት የሰጣቸውን ማህበረሰብ እንዲያገለግሉ” የውዴታ ግዴታ ተጥሎባቸዋል። ይህም በሚቀጥለው አመት ተግባራዊ እንደሚሆን ይታሰባል።
አለም አቀፋዊ የጎልማሶች ብሄራዊ አገልግሎት ልምዶች ምን ይመስላሉ?
በርካታ ሃገሮች አንዲህ አይነት የብሄራዊ አገልግሎት (አንዳንዶች በግዴታ፣ ሌሎች በውዴታ) ህግ አላቸው። አንዳንድ ሃገሮች የሲቪል ሌሎች የሚሊታሪ ብሄራዊ ስልጠናና አገልግሎት ደንቦች አላቸው። እንዲህ አይነት ብሄራዊ አገልግሎቶችን የተወጡ ጎልማሶችም በስራ አለምም ይሁን በማህበራዊ አገልግሎቶች ቅድሚያ ይሰጣቸዋል። ለአብነትም በካናዳ በብሄራዊ የውትድርና ስልጠናና አገልግሎት የሰጠ ወጣት/ጎልማሳ የህክምና ትምህርት በነጻ እና ከእዳ ነጻ መማር ይችላል፤ ሌሎች በርካታ ጥቅማጥቅሞችንም ያፍሳል።
ጉዳዩ አከራካሪ ነው። አንዳንዶች ሽንጣቸውን ገትረው ጠቃሚ ነው ይስፋፋ የሚሉ አሉ፤ ገሚሶች መቅረት ያለበት ነው የሚሉም አሉ።
ታዳጊ ጎልማሶችን በብሄራዊ አገልግሎቶች ማሳተፍ የሃገር ፍቅር ለማስረጽ እና ብሄራዊ አንድነትን ለማስጠበቅ ወሳኝ ነው የሚሉ አሉ። ተማሪዎች አይተውት በማያውቁት አካባቢ ተሰባጥረው ሲሰማሩ አዳዲስ ባህል፣ ቋንቋ፣ አኗኗር ዘይቤ ይማራሉ። ይህ ብሄራዊ መግባባትን ያጎለብታል። ሃገራዊ ህብረብሄራዊ ስሜትን ያንጻል።
ነባራዊ አለሙን የሚመስል ክህሎት ለመቅሰምም ይጠቅማል። ህይወት ከዩኒቨርሲቲ ምርቃት በኋላ ምን እንደሚመስል አስቀድሞ ለመቅመስ ይረዳል።
በተለይ የሰው ሃይል እጥረት ላለባቸው ሙያዎች ትልቅ ቀዳዳ ይከድናል። እንደበጎ ፈቃድ አገልግሎት አይነት ስለሆነ ሰራተኛ ለመቅጠር የሚፈጀውን ወጪ በእጅጉ ይቀንሳል። ለምሳሌ እንደየዘርፋቸው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቶችን ሊያስተምሩ ይችላሉ፣ ባልተነካ ጉልበታቸው የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን አሳምረው ሊሰሩት ይችላሉ። በተለይ የጤና ተማሪዎች የብዝሃ-ሙያ ስራን ሳይተብቱ በለጋነታቸው በቡድን መስራት እንዲለማመዱ እድል ሊፈጥር ይችላል፤ የጤና ኬላ የህክምና ስራ ሊሸፍኑ ይችላሉ፣ ክትባት መስጠት አያቅታቸውም፣ የማህበረስብ ጤና ግንዛቤን የሚፈጥሩ ትምህርቶችን ተደራሽ ያደርጋሉ። በዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ሪፈር የሚባሉ ኬዞችን ብቻ ከማየት ባሻገር የተለመዱ የማህበረሰብ ጤና ችግሮች እንዲማሩ ይረዳል።
በተቃራኒው ደግሞ የአስገዳጅ ብሄራዊ አገልግሎትን የሚቃወሙ ተቺዎች የሚያነሷቸው መከራከሪያዎችም አሉ። የታዳጊዎችን ነጻነት ይጋፋል ሲሉ ያነሳሉ። በተለይ ብሄራዊ አገልግሎት አልሰጥም ለሚሉት ህጋዊ ወይም ትምህርታዊ ቅጣት የሚጥል ከሆነ የግለሰብ ነጻነትን መጣስ ነው ይላሉ። የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን ከግል ነጻነት ማስበለጥ እንደሆነ ስለሚቆጥሩ ኮሚኒዝም-ዘመምነት ነው ይላሉ። ከግዳጅ የጉልበት ብዝበዛ በምን ይለያል የሚሉም አሉ።
አተገባበሩ ላይም የክትትል ጉድለት ካለው እና ሰርቶ የሚያሰራ የሚያሳይ ሞዴል አስተማሪ ከሌላቸው በዋል ፈሰስ አንድ አመት ሊባክንባቸው ይችላል። ስለዚህ ይህ ብሄራዊ አገልግሎት በደንብ ዲዛይን ካልተደረገ የሚፈለገውን ሃገራዊ ጥቅም ከማምጣት ይልቅ የልጆችን እድሜ ማባከን እና ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ሌላ የገንዘብ እና ሎጂስቲክ ወጪ ነው የሚሆነው። ተማሪዎችም ከእቁብ ቆጥረው የተግባር መማሪያ አመት ከማድረግ ይልቅ ዲታችመንት አድረገው ሊያዩት ይችላሉ (በህክምና ትምህርት ቤት ቋንቋ ዲታችመንት ማለት ጫና የሌለው የመስክ ምልከታ ወይም ግሬድ የሌለው ኮርስ ሲሆን ተማሪዎች በግዴለሽነት ናቅ አድርገው የሚያልፉት ትምህርት ማለት ነው)።
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ብሄራዊ አገልግሎት በኢትዮጵያ
መግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት እና ገሃዱ አለም ኑሮ አልተገናኝቶም። ዩኒቨርሲቲ ሰባት አመት ካቃጠልኩት ይልቅ የመርካቶ ጮሌ ያጮለኝ የበለጠ አስተምሮኛል። መከራ የመከረኝ ይልቃል።
ይህን የብሄራዊ አገልግሎት ዜና የመደገፍም ሆነ የመቃዎም አላማ የለኝም – ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ተማሪዎች እና የሚያስተምሯቸው ዩኒቨርሲቲዎች ተወያይተው ይወስኑበት። የኔ ሃሳብ ይሁን ካልንም በስርአት መክረን፣ ደግሰን፣ አሰራር ዘርግተን በተገቢው እናድርገው ነው። አይሆንም ይቅርብን ካልንም በስምም እናድርገው፤ ወደሌላ ትርምስ እንዳያመራ። ለጥንተ ጠላታችን መግቢያ በር እንዳንከፍትለት!
የተማሪዎች ስምሪት ሲዋቀር ከተለያዩ ሙያዎች የተውጣጡ ድብልቅ እንዲሆኑ አድርጎ በጋራ ስራ መስራት እንዲለማመዱ ቢሆን መልካም ነው። ሜዳውም ፈረሱም ይኀው ብሎ መልቀቅ ሳይሆን ለደህንነታቸው አስተማማኝ ከለላ መስጠትም ይፈልጋል።
ይህ አገልግሎት እስኪለመድ ለተወሰኑ አመታት በፈቃደኝነት ላይ ብቻ የተመሰረተ እንዲሆን ቢሆን መልካም ነው፤ አገልግሎቱን የሰጡትን ተማሪዎች ማበረታቻ ጥቅማጥቅም ቢሰጥ (ለምሳሌ የስራ እድል ማመቻቸት፣ የትምህርት ወጪ መጋራት እዳ መቀነስ፣ ለድሀረ ምረቃ ትምህርት ቅድሚያ መስጠት፣ የማህበራዊ አገልግሎቶች ነጻ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ወዘተ ሊሆን ይችላል) ብዙዎችን ይስባል።
ደሞ አቅም በፈቀደ አበል ቢጨመረበት ማንም አይጠላም – ጨላ ካለው እኔ እራሴ የዘለልኩት ኮርስ አለ ብዬ ዩኒቨርሲቲ ልመለስ ሁላ እችላለሁ።
ተማሪው ብቻ ሳይሆን ከፊት እየቀደመ ሰርቶ የሚያሰራ መሪ (አስተማሪ) አብሮ ይሰማራል ወይ የሚለውም ለእኔ እስካሁን ግልጽ አልሆነልኝም?! ካለእውነተኛ ጠባቂ እረኛ ይሆናል ብዬ አላስብም! ከአካዳሚክ አለም የራቁ የቦታው ባለሙያዎች በሚፈለገው ልክ እና ጥራት ተማሪዎችን ላይቀርጿቸው ይችላሉ። እንዲያውም አንዳንዶቹ ዋልጌ ሰራተኞች ‘ስትመረቅ እኮ ቀላል ነው፣ ከትምህርቱ ጋር አይገናኝም’ እያሉ ሊያሳንፏቸው ይችላሉ።
ስለዚህ ኢትዮጵያ ይህንን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የብሄራዊ አገልግሎት ተግባራዊ ከማድረጓ በፊት ከወላጅ፣ ከተማሪዎች፣ ከአስተማሪዎች እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር ጊዜ ወስዶ መማከር መልካም ነው። መክረው ያደረጉት ይሰምራል። ቅቡልነት እንዲኖረው በተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች እና የሙያ ዘርፎች ብቻ የሙከራ ጊዜም ያስፈልገዋል። የትግበራ ሂደቱ ፓይለት መደረግ አለበት። ከአስገዳጅነት ይልቅ የዉዴታ ግዴታ አይነት ይዘት ቢኖረው ደግሞ የበለጠ የተሻለ ይሆናል።
ቸር ያሰማን!