ማረጥ ተፈጥሯዊ የሴትነት ህይወት ምእራፍ እንጅ በሽታ አይደለም። ነገር ግን ብዙ ሴቶች ምቾት የሚነሱ የማረጥ ምልክቶች ሊያስተናግዱ ይችላሉ። የተለምደው እና በጣም የሚረብሸው የማረጥ ምልክት የሰውነት ሙቀት ሙቀት ማለት ነው። በተለይም ደረት አካባቢ የሚነሳ የሚዘፍቅ ማተኮስ እና ሌሊት ላይ ማላብ ይገኝበታል። በሳይንሳዊ አጠራሩ vasomotor symptoms (VMS) ይባላል።
እነዚህ የማተኮስ እና የማላብ ስሜቶች ድንገት ብልጭ የሚሉ ክስተቶች ሲሆን ብዙውን ጊዜ ከደረት ፣ ከፊት ወይም ከአንገት የሚጀምሩ ናቸው። ወደመላ ሰውነት ላይ ሊሰራጭ ይችላል።
አንዳንድ ሴቶች የሚሰማቸው ኃይለኛ ሙቀት ስሜት ከውጭ የማይታይ “ውስጣዊ ማቃጠል” ብለው ይገለጹታል። አንዳንዴ እንደተናደደ ሰው የደም ስር ፈልቶ ፊት ቅልት ማለት ሊያሳይ ይችላል።
ይህ የማተኮስ / መሞቅ ስሜት ሲመጣ የልብ ምት ይፈጥናል። የጭንቀት ስሜትም ሊሰማት ይችላል።
ሙቀቱ ሲያልፍ ላብ ዝፍቅ ያደርጋል። በኋላም ብርድ ብርድ ማለት ይመጣል። በሂደት ወደቀድሞ ደህና ስሜታቸው ይመለሳሉ። ይህ ሙሉ ኡደት “ሙቀት → ላብ → ቅዝቃዜ → ማገገም” በአጠቃላይ ከ20-30 ደቂቃዎች የሚደርስ አማካይ ቆይታ ይኖረዋል።
እነዚህ ክስተቶች በሌሊት ሲከሰቱ እንቅልፍ ይረብሻል፣ የመኝታ ልብስ ያረጥባል፣ እንቅልፍ ሲቆራረጥ ቀን ላይ ድካም እንዲጫጫነን ያደርጋል።
አብዛኛዎቹ የማተኮስ ስሜቶች ለጥቂት ደቂቃዎች ብልጭ ብለው የሚጠፉ ናቸው፤ ከ3-5 ደቂቃዎች ይቆያሉ። አንዳንድ ሴቶች ከ10-20 ደቂቃ ወይም ከዚያ በላይ ይቆይብኛል ይላሉ።
በየትኛው እድሜ ይመጣል?
ይህ ምልክት የሚጀምረው በቅድመ ማረጥ ሽግግር ወቅት ላይ ነው። በአርባዎቹ እድሜ መጀመሪያ ላይ ወይም አንዳንዴ ሰላሳዎቹ መጨረሻ ላይ ይጀምራል።
ይህ ምልክት ከሴት ሴት ቢለያይም ከአምስት እስከ አስር አመት ሊቆይ ይችላል። በአማካኝ ሰባት አመት ገደማ ይቆያል። ከአስር አመት በላይ መቆዬት የተለመደ አይደለም።
የእርጣት ማተኮስ ለምን ይከሰታል?
ይህ የትኩሳትና የላብ መፈራረቅ የሚከሰተው የሴት ሆርሞኖች የሰውነትን የሙቀት መጠን በሚቆጣጠረው የአንጎል ክፍል ላይ በሚያመጡት ተጽእኖ ምክንያት እንደሆነ ይታሰባል።
ሁላችንም በአንጎል ውስጥ ሃይፖታላመስ (hypothalamus) የሚባል የሙቀት መቆጣጠሪያ ማእከል አለን። ይህ የሙቀት ቁጥጥር ማእከል (ቴርሞስታት) የሰውነት ሙቀት መጠን ይወስናል። ይህን የቁጥጥር ስራ ሆርሞኖች ይዘውሩታል። ኢስትሮጅን አንዱ ተዋናይ ነው።
በማረጥ ጊዜ የኢስትሮጅን መጠን ይቀንሳል። ኢስትሮጅን ሲቀንስ የአንጎላችንን ቴርሞስታት ቁጥጥር በመቀየር በትንሽ ከባቢያዊ የሙቀት ለውጥ የሴቷ ሰውነት የተጋነነ ምላሾችን እንዲሰጥ በማድረግ ሙቀት ሙቀት ማለት ያመጣል።
ከሆርሞን በተጨማሪ የሙቀት ስሜቱን የሚያጋግሉ ሌሎች አባባሽ ምክንያቶች አሉ። ለምሳሌ ሲጋራ ማጨስ ችግሩን ያባብሰዋል። ከመጠን ያለፈ ውፍረት እና ቦርጭም እንዲሁ የማረጥ ምልክቶችን እንዲበረቱ ያጋልጣል። የስራ ወይም የኑሮ ጫና እና ጭንቀት ያለባቸው ሴቶችም የበለጠ ተጠቂ ይሆናሉ። ሞቃት አካባቢ የሚኖሩ፣ ሙቅ ሻወር፣ ቅመም የበዛባቸው ምግቦች፣ ትኩስ መጠጦች እና አልኮል ሌሎች ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው።
የእርጣት ማተኮስ በራሱ እንደበሽታ የሚያመጣው የጤና ጠንቅ ባይኖርም መላ ስራን፣ ማህበራዊ/ቤተሰባዊ ግንኙነት፣ ጾታዊ ግንኙነት፣ እንቅልፍ በመረበሽ ሊያቃውሱን ይችላሉ። በተጨማሪም የማረጥ ምልክት መምጣት የእድሜ ወደመጋመስ እያመራን መሆኑን አመላካች ስለሆነ መደበኛ የስኳር፣ ኮሌስትሮል፣ ግፊት፣ ልብ፣ ካንሰር ወዘተ ቅድመ ምርመራ መጀመር ይገባል።
የእርጣት ማተኮስ ይታከማል?
የማረጥን የሙቀት ስሜት የሚያስታግሱ በርካታ የሕክምና አማራጮች አሉ። ለእያንዳንዷ ሴት የሚስማማው ህክምና የሚወሰነው በምልክቶቹ ክብደት/ብሶት፣ እድሜ፣ የወር አበባ ከቆመ ስንት አመት ሆነው? የራስ ወይም የቤተሰብ የህክምና ታሪክ (የጡት/ማህጸን ካንሰር፣ የልብ ህመም፣ የደም መርጋት ታሪክ መኖር አለመኖር)፣ የሴቷ የግል ምርጫ ወዘተ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው።
የአኗኗር ዘይቤ መፍትሄዎች እና ራስን የመንከባከብ ስልቶች
ፍቱን የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ በማምጣት ከቀላል እስከ መካከለኛ የሙቀት ስሜቶችን ማከም ይቻላል። ለብዙ ሴቶች ምልክቶችን ትርጉም ባለው መልኩ ሊቀንስ ይችላል። ከሙቀት ስሜት ማስታገስነት ባሻገር ከእርጣት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ተጓዳኝ በሽታዎችን ለመከላከል (ለምሳሌ አጥንት መሳሳት፣ ስኳር፣ ቦርጭ፣ ልብ ህመም ወዘተ) ይጠቅማል።
አለባብስ ማስተካከል ይረዳል። የመሞቅ ስሜቱ ድንገት ሲመጣ ልብሶችን በፍጥነት መቀነስ እንድትችይ በጣም ደራርቦ አለመልበስ። ቀላል የሚያናፍሱ ጨርቆችን መጠቀም። እርጥበት የሚይዙ ልብሶች ምረጪ። መኝታ ቤትንም ቀዝቃዛ ማድረግ። ሙቀት ሲመጣ በማራገብ ስሜቱ እንዲረግብ ይረዳል። በጨርቅ ወይም በረዶ አንገት ወይ ደረት ላይ ማቀዝቀዣ ማድረግ። ሙቅ ሻዎር፣ ሳዉና ማስወገድ።
አመጋገብ ማስተካከል ወሳኝ ነው። አትክልት እና ፍራፍሬ ማዘውተር፣ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን መቀነስ ይገባል። እንደ አኩሪ አተር እና ተልባ ያሉ ፋይቶኢስትሮጅንን ማካተት ይጠቅማል። ካልሲየም እና ቫይታሚን ዲ የበለጸጉ ምግቦችም ለአጥንት ጤና ይረዳሉ። በላብ የሚወጣውን ፈሳሽ ለመተካት ውሃ በደንብ ጠጪ። በአንጻሩ ሙቀት ስሜትን የሚቀሰቅሱ ትኩስ መጠጦች፣ አልኮል እና ቅመም የበዛባቸው ምግቦችን ይቀንሱ።
አካላዊ እንቅስቃሴ ማዘውተርም ይጠቅማል። ከመደበኛ የኤሮቢክ እንቅስቃሴ (የእግር ጉዞ ማድረግ፣ ብስክሌት መንዳት፣ ዋና፣ ሩጫ፣ ዳንስ ወዘተ) በተጨማሪ ጡንቻ የሚያጠነክሩ የጥንካሬ ስፖርቶችን (ትናንሽ ክብደትቶች ማንሳት፣ የሚወጠሩ ባንዶች መስራት፣ ሲት አፕ፣ ፑሽ አፕ፣ ቁጭ ብድግ ስኳት ማድረግ፣ ግድግዳ መግፋት ወዘተ) መስራት ክብደትን ለመቆጣጠር፣ አጥንትን ለማጠንከር ይረዳሉ። መንፈስን ዘና የሚያደርጉ የዮጋ እንቅስቃሴዎችም ይረዳሉ። የብልት ጡንቻ ስፖርቶች (kegel exercises) የማህጸን እና ሽንት ፊኛ አቃፊ እንዳይላላ ይረዳል።
እንቅልፍ ለማስተካከል መስራትም ይፈልጋል። መደበኛ የእንቅልፍ መርሃ ግብር ማውጣት እና መተግበር፣ አእምሮን የሚያረጋጉ ልማዶችን ማድረግ (ለምሳሌ ዮጋ፣ ሜዲቴሽን፣ ጸሎት ማድረግ ወዘተ)። ከመተኛቱ በፊት እንቅልፍ የሚከለክሉ ካፌይን / አልኮልን ያስወግዱ።
የእርጣት ሆርሞን መድሃኒቶች (Menopausal Hormone Therapy, MHT)
የእርጣት ሆርሞን መድሃኒት / ቴራፒ በጣም ዉጤታማ እና ደህንነታቸው የተረጋገጠ መድሃኒቶች ናቸው። የሴት ሆርሞንን በመድሃኒት በመጨመር የማረጥ ምልክቶችን ለማስታገስ ይረዳሉ። በተጨማሪም የአጥንት መሳሳትን ለመከላከል ጥቅም ይሰጣሉ።
በተለያዩ መልክ ሊሰጥ ይችላል (የሚዋጥ እንክብል / ክኒን፣ የሚቀባ ክሬም / ጄል፣ ቆዳ ላይ የሚለጠፍ/የሚነፋ ወዘተ ሊሆን ይችላል)። ይህ የሆርሞን መድሃኒት የሴት ሆርሞን የሆኑት ኢስትሮጅን እና ፕሮጀስትሮን ድብልቅ ነው። ማህጸናቸው በተለያዬ ምክንያት በኦፕሬሽን የወጣላቸው ሴቶች ኢስትሮጂን ብቻ ያለው መድሃኒት ይታዘዝላቸዋል።
እነዚህ የሆርሞን መድሃኒቶች የሚታዘዙት ለሚከተሉት ሴቶች ነው፤
• እድሜያቸው ከ 60 ዓመት በታች፣
• የወር አበባቸው ከቆመ ከ10 ዓመታት ያልበለጠ፣ እና
• የሆርሞን መድሃኒት የሚከለክል የጤና ችግር የሌለባቸው (ካንሰር፣ የደም መርጋት)
የሆርሞን መድሃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት ሊኖራቸው ይችላል። በተለይም የጡት/ማህጸን ካንሰር አለመኖሩ ካለተረጋገጠ እና የካንሰር ተጋልጭነታቸው ከፍተኛ ለሆኑ ሴቶች አይሰጡም። በተለይ ክኒኖቹ የደም መርጋት አደጋን ሊጨምሩ ይችላል።
ነገር ግን እነዚህ ስጋቶች ትንሽ ናቸው። ጥቅሙ ስለሚያመዝን አብዛኛዎቹ የህክምና መመሪያዎች ለአብዛኛዎቹ ሴቶች እንዲሰጥ ይመክራሉ።
ሆርሞን ያልሆኑ መድሃኒቶች
የሆርሞን መድሃኒቶችን መውሰድ የሚከለከሉ ሴቶች አማራጭ መድሃኒቶች ናቸው።
በአሜሪካ የመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የእርጣት ህክምና ፈቃድ ያላቸው ሁለት መድሃኒቶች አሉ። እነርሱም ፌዞሊኔታንት (fezolinetant) እና ኤሊንዛኔታንት (elinzanetant) ናቸው። ሁለቱም የአንጎላችንን የሙቀት መቆጣጠሪያ ክፍል ላይ ይሰራሉ። ውጤታማነታቸው የታዬ ሲሆን የጉበት ክትትል ማድረግ ይፈልጋሉ።
ሌሎች መድሃኒቶችም አልፎ አልፎ ለእርጣት ህክምና ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ። ለምሳሌ የጭንቀት መድሃኒቶች፣ የነርቭ መድሃኒቶች ወዘተ የእርጣት ምልክቶችን ያስታግሳሉ።
የእርጣት ትኩሳት ጋር የሚመሳሰሉ ህመሞች
ከ40-60 አመት የሆናቸው ሴቶች ላይ የሚከሰት ሙቀት ሙቀት ማለት በአብዛኛው የሚከሰተው በማረጥ ሽግግር ምክንያት ነው። ነገር ግን ይህ ምልክት ከማረጥ ጋር የተያያዘ ነው ብሎ ከመደምደም በፊት በሌላ የጤና ችግሮች ምክንያት የተከሰተ መሆን አለመሆኑን በደንብ ማጣራት አስፈላጊ ነው።
የእንቅርት (ታይሮይድ) ሆርሞን መዛባት ሲኖር ሙቀት ሙቀት ማለት፣ ማላብ እና ሙቀት መቋቋም መቸገር ሊያመጣ ይችላል። ስለዚህ የእንቅርት ሆርሞን ምርመራ ማሰራት ያስፈልጋል። ሌሎችም አንዳንድ ሆርሞን ችግሮች እንዲያ ሊያደርጉ ይችላሉ።
የቲቢ በሽታ እና ሌሎችም ተላላፊ የኢንፌክሽን በሽታዎች ትኩሳት ያመጣሉ። ነገር ግን የእርጣት ትኩሳትና ማላብ ድንገት ብልጭ ብለው የሚታዩ እና ሄድ መጣ የሚሉ እንጅ እንደኢንፌክሽን እያየለ የሚሄድ የመላ ሰውነት ንዳድ አይደሉም።
ያልታወቀ ካንሰርም አንዳንዴ ያልለየለት ሙቀት ስሜት እና ማላብ ሊያመጡ ይችላሉ።
ሌሎችም በርካታ የጤና ችግሮች ከማረጥ ምልክቶች ጋር ሊመሳሰሉ ስለሚችሉ ከባለሙያ ጋር ተመካክሮ መታዬት እና መመርመር ይፈልጋል።
ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ።
በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ Blog, Telegram, YouTube & Tiktok ይከታተሉ።
ጥያቄ፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ካለዎት በዚህ አድራሻ ሊንክ ይጻፉልኝ።
ይህን መረጃ ጠቃሚ ሆኖ ካገኙት ለሌሎች ያጋሩ።