ጤናዬን እጠብቃለሁ፣ በፈጣሪም አምናለሁ

አንዳንድ ሰዎች ዘመናዊ ህክምና መጠቀም (ለምሳሌ ክትባት) በእምነታቸው ላይ የሚሰነዘር ጥቃት አድርገው ሲያዩት ተመልክቻለሁ። ህክምና መፈለግ የእምነት መጓደል አድርገው የሚቆጥሩም አይጠፉም። ለመሆኑ የሚያድን መድሃኒት ወይም ክትባት መኖር የጸሎታችን መልስ ማግኘት አይደለምን?  ፈጣሪ የሰጠንን ጥበብ በመጠቀም የፈጣሪን ፈዋሽነት ማመን መገለጫ መንገድ አይደለምን?

 

በዚህ ጽሁፍ ሃይማኖተኛ ሰዎች እምነታቸው ሳይቀነስ ዘመናዊ ሕክምናን ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ለማሳየት እሞክራለሁ። ሃይማኖት እና ህክምና አብረው የሚቆሙ የፈጣሪ ፈውስ አጋርነት መገለጫዎች እንደሆኑ እናያለን። እምነት፣ ጸሎትና ክትባት አብረው የሚሄዱ የፈጣሪ ችሮታዎች እንደሆኑ እናወራለን። ለማሳያነትም የጸረ–ህክምና አቋም አራማጅ ጽንፈኞች የሚያተኩሩባቸውን የክትባት እና ኮሌስትሮል መድሃኒትን እንጠቀማለን።

 

‘ህክምና ሃጢያት’ ከሆነ ‘በሽታው ቅዱስ’ ነው???

አንድ አስተማሪዬ የኮሮና ወረርሽኝ ጊዜ ያጋጠመዉን ልንገራችሁ። ይህ አስተማሪዬ የሆነ ሳይንቲስት በኮቪድ-19 የታመመ ዘመድ ለመጠየቅ ይሄዳል። የታማሚው ቤተሰብ እግዚአብሔርን የሚወዱ ናቸው፤ በቸርች የሚያገለግሉም አሉ። ሆኖም ግን ‘የምናምነው እግዚአብሔርን ብቻ ነው። ክትባት መውሰድ ክርስቲያናዊ አይደለም‘ በማለት ስለክትባቱ ተጠራጠሩ። የሚያደርገንን ያድርገን እንጅ አንከተብም አሉ።


ይህ ሳይንቲስት ከመጨቃጨቅ ይልቅ የንስሃ አባታቸውን አስጠርቶ እንዲማከሩበት አደርገ። ካህኑም በጥሞና ካዳመጡ በኋላ አንድ መሰረታዊ ጥያቄ ጠየቁ፤ “ክትባቱ ኃጢአት ከሆነ… ቫይረሱን የፈጠረው ማን ነው?” አስከትለውም ‘’ቫይረሱ ከሰይጣን ከሆነስ…. መድሃኒቱን የፈጠረው ማን ነው?”


መጽሐፍ ቅዱሱን ከፍተው እንዲህ ሲሉ አስተማሩዋቸውም፤ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ (ዘፍጥረት 1:31 )’’. ‘በሽታ እና ሞት ከእግዚአብሔር ሳይሆኑ በሃጢያት የወደቀው ዓለም ውጤቶች ናቸው’ በማለት የመውደቅን ጅማሮ ከዘፍጥረት 3 እና የመውደቅን ዉጤቶች ከሮሜ 8 ጠቅሰው አስተማሩ። ‘ስለሆነም ኮቪድ-19 ከእግዚአብሔር የተላከ (ቅዱስ) ነገር አይደለም። በሽታዉን ያመጣው የአለም አመጻ ነው። ሕይወትን በክትባት መጠበቅ ግን አመጽ አይደለም። ሞትን ለመከላከል የሚያስችል መድሃኒት እያለ አልከተብም ማለት ግን ሌላ አመጻ ነው፣ የበለጠ የአምላክን የፈውስ ሃይል አለማመን ችግር ሊሆን ይችላል” ብለው ሰበኩ።


ቤተሰቡ ጊዜ ወስዶ ጸለየ፣ እግዚአብሔር ክትባቱን ፈውስ እንዲያደርግላቸው ጠየቁ እና ለመከተብ ወሰኑ።


ይህ ታሪክ ለሁላችንም ይሰራል። ሃይማኖት እና ደህንነቱ/ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ መድሃኒት የሚጣሉ አይደሉም። ይልቁንም በጥበብ የተስማሙ ናቸው። የተረጋገጠ መድሃኒትን/ክትባትን አልወስድም ማለት “በሽታን ቅዱስ እያሉ ፈውስን ኃጢአት ነው?’ እንደማለት ነው። በሽታውን እንዳለ አምኖ ፈውስን መጠራጠር የበለጠ እምነት መጓደል ሊሆን ይችላል።


የተለያዩ ሃይማኖቶች ስለ ክትባትና የህክምና መድኃኒቶች ምን ይላሉ?

በእኔ አረዳድ ያነበብኳቸው የቲዮሎጂካል ጥናታዊ ምርምር እና የሃይማኖታዊ ተቋማት ኦፊሻላዊ መግለጫዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ የትኛውም ሀይማኖት በክትባት እና የህክምና መድሃኒቶች ላይ ክልከላ የለውም። በአብዛኛው ክትባቱን በተቋም ደረጃ ይደግፋሉ። አንዳንድ ተቋማት ውሳኔውን ለግለሰብ የግል ውሳኔ በመተው ጤናን እና ማህበረሰብን መጠበቅ ላይ ግን አጋርነታቸውን ይገልጻሉ። ክትባን ጨምሮ የተረጋገጡ የህክምና አማራጮችን መጠቀም የሚያበረታቱ የሃይማኖት ተቋማት እና መሪዎች ናቸው ያሉት።


በኢትዮጵያም ቢሆን ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት እና ዋና መሪዎች የህክምና መድሃኒቶችን ይሁን ክትባት መጠቀም ኃጢአት እንደሆነ አያስተምሩም። ሁሉም ቤተ እምነቶች የማህበረሰብ ጤናን ከመከላከል እስከ ህክምና በአደባባይ ያበረታታሉ።


ስለዚህ አልከተብም፣ መድሃኒት አልዎስድም እያሉ ማመንታት ብዙ ጊዜ የሚመጣው ከተሳሳተ መረጃ እንጂ ከሃማኖታዊ ትምህርት አይደለም። ከግል ፍርሃት ወይም በአሉባልታ ላይ የተመሰረተ እንጂ በእምነታችን አስተምህሮ ላይ የመነጨ አይደለም። የእነዚህ የተሳሳቱ መረጃዎች ምንጭ ብዙውን ጊዜ የሚነሱት ከተወሰኑ ቡድኖች ኢ-ሳይንሳዊ እሳቤዎች ነው።


ጤናዬን እጠብቃለሁ፣ በፈጣሪም አምናለሁ

ህክምና ፈጣሪ የሰጠንን ጥበብ መጠቀም ነው! አንዳንድ ሰዎች ‘ሃላፊነት ወስጄ ጤናዬን ልንከባከብ / ልጠብቅ ወይስ ፈጣሪን ተማምኜ ልተወው’ የሚል ዳይለማ ውስጥ ይገባሉ። አጭሩ መልስ ‘’አላህንም እመን ግመልህን እሰር!’’ ተብሎ እንደተጻፈው ነው። የተረጋገጠ የሙያ ፈቃድ ባላቸው የጤና ባለሙያዎች የሚታዘዝልንን ህክምና እና ምክሮች አድርሰን ነው በፈጣሪ መመካት ያለብን።


ህክምና ማድረግ ከፈጣሪ ጋር እንደ መተባበር እንጂ ሃጢያት አይደለም። ህክምና እጅግም መልካም የፈውስ ተግባር ነው። በተቃራኒው በሽታ፣ ወረርሽኝ፣ ረሃብ እና በአለም የምናያቸው ክፉ ነገሮች የሰው ልጅ ሃጢያትና መውደቅ ምልክቶች እንጂ የቅድስና ምልክቶች አይደሉም።


በመጽሐፍ ቅዱስ በሽታ እንደመልካም ነገር፣ ህክምና እንደመጥፎ ግኝት ተደርጎ አላየሁም። ይልቁንም ደጉ ሳምራዊ ወይን፣ ዘይት፣ ፋሻ እና ሌሎችም የህክምና ግብአቶችን በመጠቀም በርኅራኄ ሲያክም አይተናል (ሉቃስ 10፡34)። “ሂድና እንዲሁ አድርግ” ነው ያለን በስቴቶስኮፕ መክሊት ሲባርከን።


የህክምና ፈጠራዎች የፈጣሪ ስጦታዎች ናቸው። የህክምና ሙያ ‘በሥራ ሁሉ ብልሃት በጥበብም በማስተዋልም በእውቀትም የእዚአብሔርን መንፈስ’ ተሞልተዋል (ዘጸአት 31፡3)። ህይወትን ለማዳን፣ ጤናን ለመጠበቅ ጥቅም ላይ የሚዉሉ የህክምና ግኝቶች ሁሉ በፈጣሪ ፈቃድ የሰው ልጅ ፈጠራዎች ናቸው። መድሃኒት አያስኮንንም። ይልቁንም የእምነታችን መገለጫ ነው።


ክትባት ስንወስድ ጥንተ ጠላታችን ያመጣብንን በሽታ ለመከላከል በእምነት ፈጣሪን ተማምነን ነው። ገዳይ ኢንፌክሽን ለማዳን አንቲባዮቲክ ስንወጋ ፈጣሪ የሰጠንን ጸጋ እንደመጠቀም ነው።


በአዲስ የህክምና ቴክኖሎጂ የዘረመል አርትዖት (gene editing) አድረገን ትክክል ያልሆነ ዘረመል ታርሞ ሲስተካከል አንድን በሽታ ከስር መሰረቱ ማከም እንጅ “የአምላክን ስህተት’’ እያረምን አይደለም። በስነ መለኮት ጣልቃ መግባት ሳይሆን በተለያዩ የበሽታ አጋላጭ ምክንያቶች የመጡ ችግሮን በማስተካከል ታካሚው ዳግም ፈጣሪውን እንዲያመሰግን እድል መስጠት ነው። ፈጣሪ የሰጠንን ጸጋና ችሎታ ተጠቅመን ህይወትን የሚነጥቀዉን በሽታ እንመክትበታለን።


እንዲያዉም ህክምና የሃይማኖት አገልግሎት አካል ነው። የፈውስ አገልግሎት ነው። የጽድቅ ስራ ነው። ሌላው ዋናው የሃይማኖት ተቋማት ሃላፊነት መሆን ያለበት ህክምናዎች ደህንነታቸው የተረጋገጠ እንዲሆን ማገዝ፣ ህክምና ለሁሉም የሰው ልጆች ሁሉ በአቅራቢያቸው ተደራሽ እንዲሆን መስራት፣ የሰው ልጅ ተጎሳቁሎ በበሽታ እንዳይጠቃ መንከባከብ ነው መሆን ያለበት።


ማጠቃለያ

 ሃይማኖት እና የህክምና ሳይንስ ጠላቶች አይደሉም። እንዲያዉም ህክምና የፈጣሪ እጅግ መልካም ስራ የሆነውን የሰው ልጅ ከነጣቂ በሽታ የምንከላከልበት የተቀደሰ የፈጣሪ ውድ ስጦታ ነው።

ከበርካታ ተላላፊ በሽታዎች የሚከላከሉ ክትባቶች፣ የልብ ድካምን የሚከላከሉ የኮሌስትሮል መድሃኒቶች እንዲሁም ወደፊት በአንድ ቀን ህክምና በሽታን የሚፈውሱ የጄኔቲክ ሕክምናዎችን ከተረጋገጠ የህክምና መስጫ ተቋም በባለሙያ ትዛዝ በእምነት ከተጠቀምንባቸው ፈጣሪን ለማመስገን ተጨማሪ እድሎች ናቸው።


ስለህክምና ውሳኔ ምክር ሲፈልጉም ቅዱሳት መጻሕፍትን ያገላብጡ። ታማኝ የሃይማኖት መሪዎችን እና የህክምና ባለሙያዎችን ያዳምጡ። ተአማኝ ሳይንሳዊ ማስረጃውን ተመልከቱ እንጅ የማህበራዊ ሚዲያ ጯሂዎችን እየሰሙ አይደናገሩ።


በፈጣሪም እያመንን ጤናችንን እንጠብቅ!


ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ።


በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ  Blog, Telegram, YouTube & Tiktok ይከታተሉ።

ጥያቄ፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ካለዎት በዚህ አድራሻ ሊንክ ይጻፉልኝ።

ይህን መረጃ ጠቃሚ ሆኖ ካገኙት ለሌሎች ያጋሩ።

2 thoughts on “ጤናዬን እጠብቃለሁ፣ በፈጣሪም አምናለሁ”

  1. ዶክተር ስለ ማርበርግ በሽታ በአማርኛ ስለቀረበልን ግልፅ እና ቀላል ማብራሪያ እጅግ በጣም የሚመሰገን ነው። ይህንኑ ትምህርት የቃል በቃል የእንግሊዘኛውን ቅጂንም ብታጋራን የአማርኛ ቋንቋን ለማይረዱ አለማቀፍ እና ሀገር አቀፍ ተጓዦች ለምናስተላልፈው ትምህርት እጅግ በጣም ይረዳናልና።
    ለሁሉም ድጋፍዎ በቅድሚያ እናመሠግናለን ዶክተር።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top