ጤናማ የተመጣጠነ ማእድ

ለስኳር፣ ውፍረት ወይም ኮሌስትሮል ህክምና የሚመጡ ታካሚዎች ስለአመጋገባቸው የሚያጋሩኝ ታሪኮች ከሞላ ጎደል ተመሳሳይነት አላቸው። ስለአመጋገብ ልማዳቸው ስጠይቃቸው ‘ኧረ እንዲያው ጥሎብኝ እንጅ ስኳር ከየት አግኝቼ አብዝቼ?’ በሚል ብስጭት የሚመልሱልኝም አሉ። እንደምንም ተረጋግተው ሲዘረዝሩት ግን ‘ለቁርስ ግማሽ ፍርፍር በግማሽ እንጀራና አንድ መለስተኛ የገብስ ዳቦ ብቻ ነው የምበላው‘  ይጀምሩና ‘ረፋድ ላይ ለቡና ቁርስ መዳፍ የምታክል ቂጣ ከቆሎ ጋር ቀምሻለሁ’ ይጨምሩባታል። ‘ምሳ ደግሞ አንድ እንጀራ በወጥ ብቻ ነው የበላሁት‘ ይላሉ። ‘እንዲያው ምግብ ፍላጎት እምቢ ሲለኝ ጊዜ መክሰስ ላይ እንደሁልጊዜው ጨጨብሳ ብቻ ነው ያንከላወስኩት‘ ይቀጥላሉ። ‘እራት ላይ መድሃኒቱ እንዳይከብደኝ ብዬ ጠብሰቅ አድርጌ በልቻለሁ’። በተጨማሪም ‘እንጀራ ሲሰለቸኝ ቅንጬ፣ አጃ ወይ ሩዝ አዘወትራለሁ’ ይታከልበታል። ‘ገንፎም እወዳለሁ … ደሞ ገንፎ ምናለው?’። ‘ስንዴ ነገር ትቻለሁ። ስኳር በጭራሽ አልጠቀምም። ጮማ አልበላም‘ ያስከትሉና ‘ታዲያ ይህች ቦርጭ ከየት መጣች? ስኳሩ እንዴት አይወርድም?‘ እንቆቅልሽ ያስመስሉታል።


አብዛኛው የማህበረባችን ክፍል በጣም ውድ ያልሆኑ ምግቦችን ስለበላ ብቻ ጤናማ አመጋገብ የተከተለ ሊመስለው ይችላል። እውነታው ግን እንዲያ አይደለም። ከላይ የዘረዘርናቸው የተለመዱ የምግብ አይነቶች ውስጥ ምናልባት ሽሮው ከተዘጋጀበት ፕሮቲን ያለው ግብአት ውጭ ሁሉም አንድ አይነት (ሃይል ሰጪ ካርቦሃይድሬት) ነው። በየመስሪያ ቤቱ የምሳ እቃ ናሙና ብትወስዱ እንጀራ በእንጀራ፣ ካርቦ ሃይድሬት በካርቦሃይድሬት የታጨቀ ነው።


ይህ ጽሁፍ ጤናማ እና የተመጣጠነ ማእድ ለመመገብ የሚረዳ መረጃ ለማጋራት ያለመ ነው።


የጤናማ አመጋገብ ዋና መለኪያው አራት መሰረታዊ ነገሮች ናቸው።

1.       የምግብ መጠን (Quantity; portion size)

የምንመገበው ምግብ መጠን ዋናው የምግብ ጤናማነት መለኪያ ነው።


የተቻለንን ያክል የምግባችንን መጠን/ብዛት መመጠን ይፈልጋል። የምግብ መጠናችንን እየገመገምን እንዳገኘን ሳናግበሰብስ በመጠን ማድረግ ይገባል። በተለይ ሁሉም ምግብ ቢፌ ላይ ፊታችን ካለ ሲያልቅ እየጨመርን ስለምንበላ መጠናችን ላይታወቅን ይችላል። ከቤተሰብ ጋርም ስንመገብ የልጆችን ትርፍ ስናብስ፣ ስንጎራረስ መጠናችንን ሳናስተውል ልናልፍ እንችላለን። የመመገቢያ ሳህናችንንም አነስተኛ እንዲሆኑ ማድረግ መጠናችን ለመገደብ ይረዳል።


በጣም ጥግብ እስክንል ከመብላት ትንሽ ሲቀረው ማቆም ይመከራል።


ካልራበን በቀር ሰኣት ስለደረሰ ብች ወይም ስላስለመድን ብቻ አብዝተን መብላት መቀነስ ያስፈልጋል።


2.       የምግባችን አይነት (Quality)

ሁለተኛው የምግብ መለኪያ ነው። የምግባችን መጠን ባይበዛም አይነቱና ጥራቱ ጥሩ ካልሆነ የምንፈገውን ያክል ጤናማ ላያደርገን ይችላል። ጥራት ያለው ምግብ ሲባል በሽታ ተከላካይ፣ ገንቢና ሃይል ሰጪ ምግቦችን አመጣጥኖ በያይነቱ መመገብ ማለት ነው።


በመጀመርያ አሰርነት ያላቸውን (high fiber) ምግቦች ይመገቡ (ለምሳሌ ሰላጣ)። በአትክልትና ፍራፍሬ እንደባንዲራ ያሸበረቁ ምግቦች ሳህናችንን እንሙላ። እነዚህ ምግቦች የምንመገበውን ምግብ ግማሽ ያክል ቢሸፍኑ መልካም ነው።


በቀጣይነት ገንቢ ምግቦችን መመገብ። እንደ አሳ፣ እንቁላል፣ ዶሮ፣ ስጋ፣ ባቄላ፣ ለውዝ እና ሌሎች ጥራጥሬ የፕሮቲን ምንጮችን በአመጋገብዎ ውስጥ ያካትቱ። እነዚህ ምግቦች የሳህናችንን ሩብ ያክል ቢሸፍኑ መልካም ነው።


ሃይል ሰጪ ምግቦችን መጨረሻ ላይ ይመገቡ፤ መጠናቸውም ከምግባችን ሩብ ክፍል በላይ ባይበልጥ ጥሩ ነው። መጠናቸው ብቻ ሳይሆን አይነታቸውም ወሳኝ ነው። በንጥረ ምግብ የበለጸጉ ሙሉ እህሎች ቢሆኑ ይመረጣል። እንደ ነጭ ዳቦ፣ ፓስታ ወዘተ ፋይበራቸው የወጣላቸው ሙሉ በሙሉ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን መቀነስ ላይ አፅንዖት መስጠት ይገባል።


እስኪ ዝምብለህ የማይሆን ነገር አትዘብዝብ የሚል ካለ አንድ ሜኑ ላካፍላችሁ። የምሳ እቃን ወይም ሳህንን

    • ግማሹን አትክልትና ፍራፍሬ (ሰላጣ፣ ጎመን፣ ቲማቲም፣ ካሮት፣ ዝኩኒ፣ አቮካዶ ወዘተ) ባደርግ፤

    • አንድ አራተኛውን ሳህኔን በፕሮቲን ገንቢ ምግብ (ለምሳሌ ምስር፣ ሽምብራ፣ ለውዝ፣ ስጋ፣ እንቁላል ወዘተ) ብጨምር እና

    • የቀረውን ሩብ ሳህን ክፍል እንጀራ ወይ ቂጣ ባደርገው

                                                                       ሳህኔ የተሟላ ጤናማ ሆነ ማለት ነው። 

 

3.       የምንመገብበት ጊዜ (meal timing)

ሌላኛው የአመጋገብ መለኪያ ጊዜ ነው። ይህ ሲባል በቀን ስንቴ እበላለሁ? ምን ሰአት ላይ እበላለሁ? ስንት ሰአት እጾማለሁ? የሚሉትን ጉዳዮች የሚያካትት ነው። አልፎ አልፎ መጾም (Intermittent Fasting) ከዚህ ጋር የሚገናኝ የጤናማ አመጋገብ ስልት ነው።


ይህ ሳይንስ ገና እያደገ ያለ የምርምር ዘርፍ እንደመሆኑ ሁሉንም የሚያስማማ ቀመር ባይኖርም የምንመገብበትን ጊዜ ከጠዋት (ከ3-4 ሰአት) እስከ ከከሰአት (ሳይመሽ ከ11-12 ሰአት) ድረስ ባለው የስምንት ሰአት ክፍለ ጊዜ ብቻ በመገደብ በቀረው ከምሽት እስከ ጠዋት ባለው አስራ ስድስት ሰአት መጾም ለጤና ጥሩ እንደሆነ አሌ የማይባል እየሆነ ነው።


4.       በማስተዋል፣ በእርጋታ እና በፍቅር መመገብ (Mindful eating)

ሌላኛው የአመጋገብ መመዘኛ እየሆነ ነው። ስንመገብ በእርጋታ ሳንጣደፍ የምግቡን መአዛ፣ ጣእም፣ ቀለም እያጣጣምን በዝግታ ማኘክ ይገባል። ትኩረትን ከሚሰርቁ ስልክ፣ ቴሌቪዥን፣ ኮምፒተር ወዘተ በመራቅ ሃሳብ ሳይከፋፈል መመገብ ይመከራል። ይህ አእምሯችን የጥጋብ ስሜት ለመለየት የሚያስፈልገውን በቂ ጊዜ ስለሚሰጠው በቀላሉ ‘ጠገብኩ፣ ይብቃኝ’ ለማለት ያስችለዋል። የምግብ መፈጨትና መዋሃድ ሂደትም እንዲስተካከል ሊረዳ ይችላል።


የተለያዩ የአመጋገብ ባህል/ልማዶች (diet patterns)

ከላይ የዘረዘርናቸውን አራቱን ዋና ዋና የምግብ መለኪያዎች መሰረት በማድረግ የአመጋገብ ባህል/ልማዶች (diet patterns) በብዙ አይነት ይከፈላሉ። ለመሆኑ የትኞቹ ናቸው የሚሰሩት? በሳይንስ የተደገፉት የትኞቹ ናቸው?


በርካታ የስነ ምግብ ባለሙያዎች የተለያዩና አንዳዴም እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ የአመጋገብ አይነቶችን/ልምዶችን (diet patterns) ሲመክሩ ልንሰማ እንችላለን። አንዱ ባለሙያ ጥሩ ነው ያለውን ሌላኛው ጭራሽ እንዳትቀምሱት ሲል ሊሰማ ይችላል። አንዱ አትክልት ይሻላል ሲል ሌላኛ ገለባ አትብላ ጮማ ቁረጥ ሊል ይችላል። አንዱን አመጋገብ ደግፎ ሌላውን አፈር ድሜ ሲያስበላው በማህበራዊ ሚዲያ መስማት የተለመደ እየሆነ መጥቷል። አንዳንዱ ጽንፈኛ ባለሙያም ‘ዶክተሮቹ የማያዉቁትን አስማት ምግብ እነግራችኋለሁ’ ብሎ ልብህን ሊያንጠለጥለው ይችላል።


ይህ ዝብርቅርቅ ያለ መረጃ ምንጩ ሶስት ነው።


አንደኛው የስነ ምግብ ጥናቶች ባህሪ ነው። የስነ ምግብ ምርምሮች እንደመድሃኒት ሪሰርቾች በቀላሉ ለመስራት አይመችም። ለምሳሌ ‘መድሃኒት ሀ’ን ከሌላ ‘መድሃኒት ለ’ ጋር አወዳድሮ ከዚህኛው መድሃኒት ያኛው ይሻላል ለማለት ከባድ አይደለም። የተለያዩ ምግቦችን እንዲህ አውዳድሮ ይሄኛው ምግብ ከዚያኛ ይሻላል ለማለት አይመችም። ምክንያቱም አንድ የምግብ አይነት ሁሉም አይነት ንጥረ ነገር ሊኖረው ስለሚችል ጥርት ያለ የምግብ ውድድር ማድረግ አይቀልም። የምግቡንም ጥራት የሚወስኑት በርካታ ተጽእኖዎች አሉት ለምሳሌ የበቀለበት አፈር ለምነት፣ የተጠቀምንው ማዳበሪያ/ጸረ አረም፣ የተከማቸበት መንገድ፣ የተጓጓዘበት ሁኔታ፣ የበሰለበት/የተዘጋጀበት መንገድ ሁሉ የምግብን ጤናማነት ይወስናሉ። አመጋገባችንም በዘፈቀደ አንዱን ከሌላኛው ደበላልቀን ስለሆነ የዚያኛው ምግብ ይሁን የሌላኛው የምግቡን ጤና ላይ ያመጣዉን ጉዳት ወይም ጥቅም በትክክል መለካት ይከብዳል።


ሌላኛው ምክንያት የስነ ምግብ ጥናቶች የሚለኩት/የሚያወዳድሩት መለኪያ የተለያዬ መሆኑ ነው። እንዱ ጥናት የምግብ አይነትን ከካንሰር መያዝ ጋር እያነጻጸረ ሊሆን ይችላል። ሌላኛ ጥናት ውፍረትን/ቦርጭን ለመቀነስ ያላቸውን ጥቅም/ጉዳት እያዬ ሊሆን ይችላል። የሌላኛው ተመራማሪ ትኩረት የደም ግፊት ለመቀነስ የትኛው ይሻላል ሊሆን ይችላል። የገሚሶቹ የጥናት አላማ ደግሞ የልብ ህመም ወይ ረጅም እድሜ ለመኖር የትኛው ይሻላል ሊሆን ይችላል። የተለያዬ አላማ እና መለኪያ የሚጠቀሙ ሪሰርቾችን አወዳድረን ይሄ ምግብ ከዚያኛው ይሻላል ልንል አንችልም።


ሶስተኛው ምክንያት የአመጋገብ ባህል በተለያዬ ክፍላተ አለማት የተለያዬ መሆኑ ነው። ኢትዮጵያ የሚበላ ስንዴ እና ጣልያን ያለ ስንዴ ዝግጅቱ፣ አበላሉ፣ አብሮት የሚበላው ምግብ አይነት ወዘተ በጣም የተለያዬ ነው። ስለዚህ አሜሪካ ጎጂ ነው የተባለ ምግብ ኤዥያ ምርጥ ምግብ ነው ሊባል ይችላል። አመጋገባችን ብቻ ሳይሆን የምግብ አቀባበላችንም (ለምሳሌ በዘረመል ልዩነት) እንዲሁ ለየቅል ነው።


የስነ ምግብ ምክሮች እንዲህ ለየቅል ሆነው ግራ የሚያጋቡ ቢመስሉም ዋና ዋናዎቹ የአመጋገብ ዘይቤዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ።


ሀ) የሜዲትራኒያን አመጋገብ (Mediterranean Diet)

ይህ የአመጋገብ ስርአት ስላለው የጤና ጥቅሞች ከሌሎች የአመጋገብ አይነቶች ሻል ያለ ሳይንሳዊ ማስረጃዎች አሉት። በ1950ዎቹ ጀምሮ ከተሰሩት እንደ The Seven Countries Study of Cardiovascular Diseases (SCS) ያሉ ጥናቶች እንዲሁም አለም አቀፍ የህክምና መመሪያዎች የሚደገፍ የአመጋገብ ዘይቤ ነው። ለአጠቃላይ ጤና በሚሰጠው ላቅ ጥቅም በሰፊው ይወደሳል።


ይህ የአመጋገብ ልምድ በሜዲትራኒያን አካባቢ ያሉ እንደጣልያን፣ ግሪክ ወዘተ አገሮች የተለምደ ባህላዊ የአመጋገብ ስርአት ነው። ይህ የአመጋገብ አይነት በአመዛኙ አትክልት ላይ የሚያተኩር ሆኖ የሚከተሉትን አመጋገብ ስልቶች አጽንኦት ሰጥቶ መጠቀም ይመክራል፤

    • አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ጥራጥሬ፣ አሰርነት ያላቸው እህል ምግቦችን እና የወይራ ዘይትን በዋነኛነት ምግብ ላይ ማካተት ይመክራል።

    • አሳ፣ ዶሮና የወተት ተዋጽኦዎችን በመጠኑ መመገብን ያካትታል።

    • በአንጻሩ ቀይ ስጋን ጨምሮ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦች መገደብ ያዝዛል።

በርካታ ጥናቶች ከሌሎችን የአመጋገብ አይነቶች የተሻለ ኮሌስትሮልን ለማስተካከል፣ የደም ግፊትን ለማስተካከልና የልብ ህመም ተጋላጭነትን ይቀንሳል ሲሉ ያስረዳሉ።


ለ) የደም ግፊት ለመቀነስ የሚረዱ የአመጋገብ ዘዴዎች (Dietary Approaches to Stop Hypertension, DASH Diet)

በመጀመሪያ የደም ግፊትን ለመቀነስ በ1990ዎቹ የተነደፈ የአመጋገብ ስልት ነው።

ይህ የአመጋገብ ስልት የሚመክረው፤

    • አትክልቶችን፣ ፍራፍሬዎችን፣ ያልተፈተጉ ሙሉ እህሎችን፣ አሳ እና ዶሮ ምግብን ማዘውተር የሚመክር ሲሆን

    • ጨው፣ ቀይ ሥጋ እና ጣፋጮች መገደብ ይደግፋል።

    • ከሜዲትራኒያን አመጋገብ የሚለየው ግልጽ የሆነ የጨው አጠቃቀም ገደብ ስለሚያስቀምጥ ነው።

ይህ አመጋገብ የኮሌስትሮል መጠን ለመቀነስ ውጤታማ ነው። በአጠቃላይ የልብ ጤናን እንደሚያሻሽል በበርካታ ጥናቶች ተረጋግጧል።

 

ሐ) MIND diet

ይህ የአመጋገብ ዘዬ ከላይ የተጠቀሱትን የሜዲትራንያን አመጋገብ እና DASH አመጋገብ በመቀላቀል በ2015 አካባቢ የተፈጠረ ነው።  ቅጠላ ቅጠሎች እና ፍራፍሬዎች ላይ አፅንዖት በመስጠት ያተኩራል። በተለይ በእድሜ ምክንያት የሚመጣ የመርሳት ችግር (አልዛይመር) ይቀንሳል በሚል ይመረጣል። የጥናቶቹ ዋና መለኪያ የአንጎል/አእምሮ ጤና ላይ ያተኩራል።


መ) ቬጅቴሪያን አመጋገብ (Vegetarian diet)

ይህም ከላይ ከጠቀስናቸው የሚቀራረብ ሆኖ ምንም አይነት የእንሣት ተዋጽኦ አያካትትም። ብዙ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ይህ አመጋገብ የሚከተሉ ሰዎች ረጅም እድሜ ይኖራሉ፣ የልብ ህመም ተጋላጭነታቸው ይቀንሳል፣ በካንሰር የመያዝ እድል ይቀንሳል፣ የኮሌስትሮል መብዛት አያስቸግራቸውም።


በአንጻሩ የአንዳንድ ቫይታሚኖችና ማእድኖች እጥረት ሊያጋጥም ስለሚችል ክትትልና ከምግብ ተጨማሪ ሰፕሊመንት (dietary supplements) መውሰድ ይፈልጋል።


ሠ) ኪቶ አመጋገብ (ketogeneic diet, keto, low carb diet)

 የኪቶ አመጋገብ ካርቦሃይድሬትን በደንብ በመቀነስ ከፍተኛ ስብ ያለው ምግብ ማዘውተር ያካትታል። የካርቦሃይድሬት መጠን ዝቅተኛ ስለሆነ ሰውነታችን ለነዳጅነት ከካርቦሃይድሬት የሚገኘውን ግሉኮስን ከማቃጠል ይልቅ ወደስብ ማቃጠል እንዲዞር የሚያስገድድ ዘዴ ነው። ስብ በጉበት ሲቃጠል ኬቶን (ketone) የሚባሉ የሃይል (ነዳጅ) ምንጭ ይሰራል።


ከሶስት አራተኛው በላይ የሚሆነው ምግባችን ስብ/ጮማ እና ቅባት እንዲበዛው ይሁን ይላል። በኪቶ አመጋገብ የሚካተቱ ምግብ አይነቶች ከፍተኛ ቅባት ያላቸው ሲሆኑ የሚከተሉትን ያካትታል፤

    • ስጋ፣ አሳ፣ እንቁላል፣ አይብ/ቅቤ

    • ለውዝ፣ አቮካዶ

በአንጻሩ ‘ገለባ ብቻ ናቸው’ እያለ የሚኮንናቸውን አትክልት፣ ጥራጥሬ እና እህሎች ገድቡ ይላል።


ይህ አመጋገብ ክብደት ለመቀነስ፣ ስኳር ለማስተካከል እና የሚጥል በሽታ ለማሻሻል ይረዳል የሚሉ ጥናቶች አሉ። ነገር ግን እነዚህ የጤና ጥቅሞች የአጭር ጊዜ ለውጦች እንጂ የረጅም ጊዜ ዘለቄታዊ ፈውስ እንደማይሆን የሚያሳዩ በርካታ ጥናቶች አሉ። እንዲህ አይነት የለየለት ጮማ እና ቅባት ማዘውተር ለልብ ጤናም ስጋት አለው።


በዚህ ምክንያት ከአንዳንድ አፈንጋጭ ባለሙያዎች እና የማህበራዊ ሚዲያ ኢንፍሉዌንሰሮች ባሻገር በመደበኛ የህክምና መመሪያዎች ዘንድ እምብዛም ተቀባይነት የለውም። ኪቶ መመገብ አስማታዊ ለውጥ አለው እያሉ የግል ተሞክሯቸውን የሚያወሩ አንዳንድ ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያ ቢንጫጩም ለውጦች ታይተው የሚጠፉ የአጭር ጊዜ ከመሆናቸው ባለፈ ከልብ ጤና መመሪያዎች ጋር አይጣጣሙም።


በብዙዎች ዘንድ የሚዋጥና የሚለመድ ጣእም ስለሌለው ይህ አመጋገብ ለብዙ ጊዜ በዋና ምግብነት ለመቀጠል አዳጋች ነው። ይሄን ከምበላስ ‘መድሃኒት ብውጥ ይሻለኛል’ የሚሉ በርካታ ታካሚዎች አጋጥመውኝ ያውቃሉ። ምን ያክል ለአፍ ከባድ እንደሆነ አስቡት።


ማጠቃለያ

ለሁሉም ሰው የሚሰራ ወጥ የአመጋገብ ቀመር ማስቀመጥ ባይቻልም አብዛኛዎቹ ጥናቶች እና የህክምና መመሪያዎች እንደ ሜዲትራኒያን እና DASH አመጋገብ ያሉ አትክልት ምግቦች ላይ የሚያተኩሩ ዘይቤዎችን ይደግፋሉ። በተለይ ለልብ ጤና፣ ለደም ግፊት መሻሻል እና ኮሌስትሮል ቁጥጥር የተሻሉ በመሆናቸው ከኪቶ አመጋገብ የትሻለ አለም አቀፋዊ ቅቡልነት አላቸው።


ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ።


በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ  Blog, Telegram, YouTube & Tiktok ይከታተሉ።

ስለስቴሮይድ መድሃኒቶች ጥያቄ፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ካለዎት በዚህ አድራሻ ሊንክ ይጻፉልኝ።

ይህን መረጃ ጠቃሚ ሆኖ ካገኙት ለሌሎች ያጋሩ።

4 thoughts on “ጤናማ የተመጣጠነ ማእድ”

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top