አዘውትሮ መራመድ ከተቻለ መሮጥ ለተሻለ ጤና ጉልህ ሚና ይጫወታል። እርምጃ ለአካላዊና አእምሯዊ ጤናን እንደሚፈውስ የተረጋገጠ ለሁላችን የተሰጠን ጸጋ ነው። በዚህ ጽሁፍ በእግር መጓዝ የሚሰጠንን የጤና በረከቶች እንዳስሳለን። እየተራመድን!
አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ልማድ እንዲሆንብን ማድረግ ይገባል። እኔ በበኩሌ ወክ ማድረግ አብሶ መሮጥ ሱስ ሆኖብኛል ብል ማጋነን አይሆንም። ሲደክመኝ መሮጥ ነው የማስበው፤ ስራ ጫና ሲበዛ ራመድ ራመድ ማለት ነው የሚያምረኝ፤ ሲዘንብም ሲነፍስም ሲበርድም መሮጥ ነው የምፈልገው። የማደርገውም ያው ወክ ማደረግ ወይ መሮጥ ነው። አሁን ደግሞ በተለይ አዲስ አበባ ‘የማሰራራት ዘመን’ ፓርክ እና ኮሪደር ልማት ተከትሎ ለወክና ሩጫ የሰጠ ሆኗል። ከቀያችን ቢያፈናቅለንም ለጤና የተመቸ መሆኑን እንደ አንድ ‘የጎንዮሽ ጉዳት/ጥቅም side effect’ አይተን ቢያንስ ጤናችንን ለመጠበቅ እንጠቀምበት እንጅ። ቤታችንንም ጤናችንንም አጥተንማ አይሆንም! እንዲያዉም መንግስትን ‘የታባህ! አለሁ አልሞትኩም! እንዲያዉም ጤናዬ በልጽጓል፤ ጡንቻዬ ፈርጥሟል’ ብለን ‘ለህዝብ ካልታዘዝክ ወዮልህ’ ብለን ጓ ማለት ነው ያለብን። እየተራመድን!
አሁን አሁን ‘የለውጡ ሃይሎች ሃሳብ አመንጭነት ያልተጎበኘው’ የጤናው ዘርፍ ‘ጤና የሚነሳ’ ነገር ሲደረግ ሳይ/ስሰማ በምውልበት አገር ውስጥ ተስፋዬን ከሚያለመልሙ ነገሮች መካከል አንዱ በተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍሎች በመስቀል አደባባይ፣ በወዳጅነት ፓርክ፣ በእንጦጦ፣ በየካ ተራራ፣ በወንዝ ዳርቻዎች እና በየሰፈሩ በተሰሩ የእግረኛ መንገዶች የሚንሸራሸሩ ሰዎችን ማየት ነው። እነዚህ ትራኮች በሰው ሙልት ብለው ማየት ለስኳርና ውፍረት ሃኪም አንጀትን ቅቤ የሚያጠጣ አስደሳች ኩነት ነው። ‘ግቢዬ ውስጥ በአስር ደቂቃ እርምጃ ጀምሬ ዛሬ ግማሽ ሰአት እየተንከበከብኩ ተራራ መውጣት ቻልኩ’ የሚሉ የታካሚዎቼን ታሪክ መስማት እንዴት ደስስ ይላል መሰላችሁ።
ልጅም ሁን ጎረምሳ፣ ወጣትም ሁን ጡረተኛ፣ እጅ አጠርም ሁን ባለሃብት፣ ቀጮ ብትሆን ወፍራም፣ ስራ ቢበዛም ፍሪ ብትሆን እየተራመድክ!
የእግር ጉዞ ማድረግ የጤና በረከቶች
የእግር ጉዞ መራመድ ጤናን ለመጠበቅ፣ የበለጠ ለማሻሻል እና አጠቃላይ ንቁ ለመሆን ቁልፍ መድሃኒት ነው። እርምጃ ከቀላል እስከ መጠነኛ ኤሮቢክስ ስፖርቶች (low to moderate-intensity aerobic activity) መካከል የሚመደብ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ነው።
አዘውትሮ መራመድ የልብን እና አጠቃላይ የደም ስር ጤንነት ይደግፋል። የደም ዝውውርን ፍሰት በማሻሻል የደም ግፊትን ያስተካክላል፣ የልብ ጡንቻን ያበረታል። በየቀኑ ከግማሽ ሰአት በላይ ወክ የሚያደርጉ ሰዎች በልብ በሽታ እና ስትሮክ የመያዝ እድላቸው ከ20 እስከ 30 በመቶ ይቀንሳል።
ሜታቦሊዝምን በማሳለጥ ስኳርን እና ኮሌስትሮል ያሻሽላል። ሰውነታችን ኢንሱሊን በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲዉል ስለሚያግዝ የስኳር ህመም እና ተያያዥ የጤና ችግሮችን ተጋላጭነት በእጅጉ ይቀንሳል።
እንቅቃሴ ማድረግ ድካምም ይቀንሳል። ይህ ሲባል አንዳንድ ሰው ‘ሲደክመኝ እንዴት ተራመድ ትለኛለህ?’ ሊል ይችላል። ተቃርኖ ይመስላል ግን አይደለም። እንቅስቃሴ ማድረግ በመላ ሰውነት ውስጥ የኦክስጂን አቅርቦትን በማሻሻል ካሎሪዎችን ያቃጥላል እና ሃይልን ይጨምራል። ጡንቻ እና አጥንት ያጠነክራል። ስለዚህ ስንቀሳቀስ ድካም ይጠፋል። ቁጭ ስልን ደግሞ በተቃራኒው ጡንቻ እየዛለ እየሰነፈ የባሰ ድካም እየተጫጫነን ነው የሚሄደው (de-conditioning)።
ሰውነት ቅልል እንዲለን ያግዛል። የበለጠ በርትቶ ለሰራ ክብደትም ለመቀነስ እና ሸንቀጥ ለማለት ይረዳል። እርምጃ እና ሌሎችም ስፖርቶች መስራት በተለይ በምግብ ያጠፋነው ክብደት ወይም ቦርጭ ተመልሶ እንዳይጨምር ለመከላከል ሁነኛ መፍትሄ ነው።
በተጨማሪም ሳንባን ያበረታል። አንጎልን ያነቃል። የሚያረካ እንቅልፍ እንድንተኛ ይረዳል። ስራ ላይ ያለን ትኩረት እንዲሻሻል ያግዛል።
ከአካላዊ ጤና ባሻገር አዘውትሮ መንቀሳቀስ ለአእምሯዊ ጤናም ወሳኝ ነው። የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ለአእምሮ ጤና መሻሻል እንደ እንድ አጋዥ የሕክምና ዘዴ መጠቀም (exercise therapy or physical activity therapy) ይቻላል። ከሌሎች የአእምሮ ጤና ህክምና ጋር አብሮ ጥቅም ላይ ሊዉል ይችላል። ስንራመድ ጭንቀትን የሚያስታግሱ፣ ስሜትን የሚያሻሽሉ እንዲሁም ዘና እንድንል እና ስለራሳችን ያለን ግምት እንዲሻሻል የሚረዱ እንደ ኢንዶርፊን አይነት አእምሮን የሚያጸዱ ተፈጥሯዊ የነርቭ ኬሚካሎች እንዲመነጩ ያግዛል። የእነዚህ አነቃቂ ኬሚካሎች መለቀቅ የጭንቀት፣ ድብርት እና ሌሎችም ስሜቶች ያስተካክላል። የአእምሮ ጤና ባለሙያ እና የሰለጠነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ቴራፒስት የታካሚውን ግለሰብ ፍላጎት ባማከለ መልኩ የስፖርት ፕሮግራም በመንደፍ ሊተገበር ይችላል።
አዘውትሮ መራመድ የበሽታ መከላከል አቅማችንን ያጎለብታል የሚሉ ጥናቶችም አሉ። በደንብ የእግር ጉዞ የሚያዘወትሩ ሰዎች ጉንፋን ይሁን ሌላ ኢንፌክሽን ቶሎ ቶሎ አይዛቸውም፤ ሲይዛቸውም አይጸናባቸውም። እኔ እራሴ ‘ብርድ መታኝ፣ ነፋስ ነካኝ’ የሚል ስፖርተኛ አጋጥሞኝ አያውቅም።
ከጤና ባሻገር የልብ ወዳጅ ማፍሪያ መንገድም ነው። በጫካ ጽድት ያለ አየር እየማጉ ማዉጋት እና እየተሳሳቁ እርምጃ ማድረግ ጠንካራ የማህበራዊ ቦንድ ይፈጥራል። ተራራ ላይ ላብ በላብ ሆነው ለጤናቸው ሲኳትኑ የሚገናኙ ሰዎች አንደማይተዋወቁ ሰዎች ሳይተያዩ ነው አይዞህ አይዞሽ ተባብለው ጓደኛ የሚሆኑት። ከቤተሰብ እና ዘመድ ጋርም ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ ሁነኛ አማራጭ ነው። ማህበራዊነቱም ሃያል ነው!
ምን ያህል እርምጃ ነው ለጤና በቂ የሚባለው?
ለዚህ ጥያቄ አጭር መልስ ለሚሻ ከስፖርት የምናገኘው የጤና ጥቅም በሰራነው ልክ ነው። ቁጭ ከማለት ትንሽም ቢሆን መንቀሳቀስ ይሻላል። ‘ከተኛ የተቀመጠ፤ ከተቀመጠ የቆመ፣ ከቆመ የተንቀሳቀሰ ይሻላል’ ይል የለ የአበው ተረት!
የበለጠ በሰራን ቁጥር የላቀ እንጠቀማለን። አስበልጠን እና አዘውትረን ረጅም የእግር ጉዞ የቻለ በሶምሶማ ደሞ የተቻለው በሩጫ ስንሰራ የበለጠ የጤና ምርት እናጭዳለን። ከሆነ የተወሰነ ቁጥር በላይ እርምጃ ካልተጓዝኩማ ቢቀርስ የሚያስብል አስማታዊ ጣሪያ የለውም። ይልቁንም እያንዳንዷ ተጨማሪ እርምጃ የላቀ የጤና ጥቅም ያስገኛል (it’s dose-dependent – More movement brings more benefit)።
በዚህ ረገድ የተሰሩ ትላልቅ ጥናታዊ ትንታኔዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ከሶስት ሺህ እስከ አምስት ሺህ እርምጃዎችን በየቀኑ ማድረግ ጤናን በእጅጉ ያሻሽላል። የልብ ህመም እና ተያያዥ የደም ስር ችግሮችን ይቀንሳል። ከዚህ በበለጠ ከአምስት ሺህ እስከ አስር ሺህ እርምጃ በየእለቱ መንቀሳቀስ ደግሞ ካለእድሜ መሞትን ይከላከላል። ከዚህ የበለጠ መስራት የበለጠ ጥቅም ያስገኛል።
ስለዚህ ለእያንዳንዱ ሰው ምን ያህል እርምጃ (ወይም ከዚያ በላይ ስፖርት ቢሰራ) ነው ለጤና በቂ ነው የሚባለው ለሚለው ጥያቄ መልሱ ከላይ እንዳልነው በቁጥር ቅልብጭ ብሎ የሚቀመጥ ሳይሆን እንደ እያንዳንዱ ሰው ፍላጎት፣ አቅም፣ እድሜ እና የጤና ሁኔታ የሚወሰን ነው ማለት ነው።
ምንም እንቅስቃሴ አድርጎ የማያውቅ ሰው ትንሽ ተንከላውሶ ሊበቃው ይችላል። ከዚያ በቀጣይነት ወደአንድ ሺህ እርምጃ ወይም እስከቻለው ድረስ ገፋ አድርጎ ለመስራት ያቅድ። አቅም እና ጉልበት እንደፈቀደ ቀስ በቀስ እያሳደጉ መቀጠል። በየሳምንቱ ወይም በየወሩ አንድ አንድ ሺህ እርምጃ እንኳን እየጨመርን ደረጃ በደረጃ እያሻሻልን በጽናት ብንታገል በአመት ውስጥ የአካል ብቃታችን ሙሉ በሙሉ ሊስተካከል ይቻላል።
እያንዳንዱ ተጨማሪ እርምጃ ጠቃሚ ናቸው። የበለጠ ተጨማሪ ደቂቃ ባስረዘምነው ልክ የላቀ ይጠቅመናል። በጊዜ ሂደት ፍጥነቱንም እያፈጠንን ብንሄድ ደግሞ የበለጠ ይረዳናል። ሰውነትዎ እስከተቋቋመው ድረስ የእርምጃውን ቁጥር፣ የምንጓዘውን ርቀት እና የምንራመድበትን ፍጥነት እየጨመሩ መቀጠል ነው።
ዋናው ከትናንትናው የተሻለ ጥቂትም ቢሆን ተጨማሪ እርምጃዎች ለማድረግ ማቀድና መተግበር ነው። ይህ ጭማሪ በእርምጃ ብዛት ሊሆን ይችላል፤ በደቂቃ እርዝማኔው አሊያም ፍጥነት በመጨመር ሊሆን ይችላል።
የእግር ጉዞ ማድረግን እንዴት ልምድ እናድርግ?
መራመድም ይሁን ሌላ የአካል እንቅስቃሴ የአንድ ሳምንት ሆይ ሆይታ አይደለም። በዘላቂነት ልምድ አድርጎ መስራት ይፈልጋል።
አኗኗራችንን፣ ቀጠሯችንን፣ ዉሏችንን ሁሉ እንቅስቃሴ የበዛው ማድረግ ይገባል። ወደሱቅ፣ ወደቸርች ወይም መስጊድ ስንሄድ ወክ እናድርግ። ህንጻዎች ላይ ሊፍት ከመጠቀም በደረጃ እንውጣ። ቢሮ ስልክ ሲኖርብን እየተራመድን ማውራት መልመድ ቢዚ ስራ ላለው ሊጠቅም ይችላል። ትራንስፖርት መጠቀም ለሚያዘወትር አንድ ሁለት ፌርማታ ቀደም ብሎ ወርዶ ወደጉዳይ ቦታ መራመድ። መኪና የሚነዳም ራቅ ያለ ቦታ ፓርክ አድርጎ ወደቢሮ በእግር መሄድ። ዘመድ ወይ ጓደኛ ለማግኘት ቀጠሮ ሲያስይዝ ፓርክ ተቀጣጥሮ ሽርሽር ማለት ማስለመድ።
ጓደኛም ስንወዳጅ ዉረድ እንውረድ ተባብሎ ድራፍት ቤት ወይ ከተማ ካፌ ከመጎለት ተራራ እንውጣ፣ ጃንሜዳ ወክ እናድረግ፣ እንዋኝ፣ ጂም እንሂድ የሚል ባለንጀራ ማፍራት ይገባል።
የእግር ጉዞ ከመጀመር በፊት የሚያስፈልጉ ጥንቃቄዎች
አብዛኛው ሰው የእግር ጉዞ ለማድረግ የተለዬ ዝግጅት አያስፈልገውም። ሁሌም ቢሆን እንቅስቃሴ ከመጀመራችን በፊት በበቂ ሁኔታ ማሟሟቅ ያስፈልጋል። የሚመች ጫማ እና ልብስ መልበስ ይመከራል። ፈሳሽም በበቂ አስቀድሞ መጠጣት እንዲሁም ጉዞ ላይም ከጠማን ለመጠጣት ውሃ መያዝ ይገባል። በጣም በቀትር ቃጠሎ እንቅስቃሴ ማብዛትም እምብዛም አይመከረም። በጨለማም እንዲሁ በቂ ብርሃን በሌለበት በተለይ ያልተስተካከሉ የእግረኛ መንገዶች ባሉበት ለመንቀሳቀስ መሞከር ያልታሰበ ወድቆ መሰበር ሊያመጣ ይችላል።
የስኳር ታካሚ ከሆኑ (በተለይ ኢንሱሊን መርፌ የሚወስዱ ከሆነ ወይም የስኳር ቁስል ካለ – foot ulcer)፣ የልብ ህመም ካለብዎት ወይም ሲንቀሳቀሱ የደረት ህመም የሚሰማዎት ከሆነ፣ ሲንቀሳቀሱ ትንፋሽ ማጠር ወይም ማዞር ካለ፣ ከባድ የመገጣጠሚያ ህመም ካለ፣ በቅርብ አደጋ አጋጥሞዎት ከነበረ የእግር ጉዞ ወይም ሌላ እንቅስቃሴ ከመጀመር በፊት ከሃኪምዎት ጋር ይመካከሩ።
ክብደታቸው በጣም ተለቅ ያለም ከሆነ ጉልበት እና ሌሎች መገጣጠሚያዎች ላይ ጉዳት እንዳያስከትል በጥንቃቄ የእርምጃ መጠንን መገደብ እና የምንራመድበትን ቦታ ምቹነት ማረጋገጥ ይፈልጋል።
ማጠቃለያ
ከሃብት ሁሉ የላቀውን ጤናችንን የምንጠብቀው በትንንሽ ልምምዶች ነው። ጤናን ማበልጸግ የሚጀምረው እንደ እርምጃ ማዘውተር በመሳሰሉ ቀላል ድግግሞሾች ነው። ስለሆነም ዛሬዉኑ የእግር ጉዞ ለማዘውተር ይወስኑ። በጥቂት እርምጃዎች ይጀምሩ። ዛሬ ከትላንትናው የተሻለ ጥቂት ተጨማሪ እርምጃዎችን ያድረጉ። ነገ ከዛሬው የበለጠ ተጨማሪ እርምጃ በፍጥነት ይራመዱ።
የዛሬ ቀላል እርምጃዎች ነገ ከከፋ የጤና ችግር ይታደጉናልና። ትንንሽ እርምጃዎች ሲደጋገሙ ትልልቅ የጤና ቱሩፋቶች ያስገኛሉ።
እየተራመድን! እንጦጦ ተራራ ላይ እንገናኝ!
ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ።
በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ Blog, Telegram, YouTube & Tiktok ይከታተሉ።
ስለስቴሮይድ መድሃኒቶች ጥያቄ፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ካለዎት በዚህ አድራሻ ሊንክ ይጻፉልኝ።
ይህን መረጃ ጠቃሚ ሆኖ ካገኙት ለሌሎች ያጋሩ።