ኤች ዲ ኤል (high-density lipoprotein, HDL)

በአንድ ወቅት ለአንድ ታካሚ የኮሌስትሮል መድሃኒት እንዲዎስድ ከብዙ ሰአት ውይይት (‘ኧረ እባክህ ለልጆችህ ስትል’ ልመና) በኋላ ተስማምተን የኮሌስትሮል መቀነሻ መድሃኒት ማዘዣ ጽፌ በቀጠሮ ለመገናኘት ተለያዬን። ከሁለት ወር በኋላ ሲመለስ ስለ ‘የኮሌስትሮል የጤና ጥቅሞች’ የሚወሸክቱ የማህበራዊ ሚዲያ ቪዲዮዎችን አሰባስቦ ይዞ መጣ። መረጃ መሰብሰብ ያለ ነው። ነገር ግን የኮሌስትሮል መቀነሻ መድሃኒት በማዘዝ ‘እነዚህን የኮሌስትሮል ጥቅሞች’ ላስቀርበት እንደነበር በማሰብ የህክምና ሂደቱ ላይ ቂም ይዞ ነበር። በጣም ያበሳጨው ‘ኮሌስትሮል እንደቴስቶስቴሮን ያሉ የወንድ ሆርሞን ለማምረት ይረዳል። ስለዚህ የኮሌስትሮል መቀነሻ መድሃኒት መውሰድ ቴስቶስቴሮን እንዲያንስ ስለሚያደርግ ስንፈተ ወሲብ ያመጣል፣ መሃንነት ያስከትላል’ የሚል አሳች መረጃ ይገኝበታል።


በነገራችን ላይ እንደ ስታቲን (statin) ያሉ የኮሌስትሮል መቀነሻ  መድሃኒቶች ዋና ተግባራቸው ጎጂ ኮሌስትሮል የሚባሉትን የኮሌስትሮል አይነቶች ነው የሚቀንሱት። ‘የኮሌስትሮል የጤና ጥቅሞች’ እየተባሉ የሚዎሩትን የኮሌስትሮል መደበኛ ተግባራት የሚያከናውነው በተለምዶ ጥሩ ኮሌስትሮል በመባል የሚጠራው ኤች ዲ ኤል (HDL) ነው። በዚህ ጽሁፍ ኤች ዲ ኤል ኮሌስትሮል መጠነኛ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ ነው።


የኤች ዲ ኤል ኮሌስትሮል ተግባራት

ኤች ዲ ኤል በተለምዶ ጥሩ ኮሌስትሮል (the good cholesterol) በመባል ይጠራል። ኮሌስትሮልን ከደም ቧንቧዎች እያጸዳ ወደ ጉበት በመመለስ እንዲዎገድ አስተዋጽኦ ያደርጋል። እንዲሁ ስለተለመደ ‘HDL cholesterol’ እንበለው እንጅ ኤች ዲ ኤል ‘ኮሌስትሮል’ ሳይሆን ‘ኮሌስትሮል የሚያጓጉዝ’ ከፕሮቲን የተሰራ ውህድ (lipoprotein) ነው።


ኤች ዲ ኤል እንደከተማ የጽዳት ሰራተኛ በየደም ስሩ እየሄደ ትርፍ የኮሌስትሮል ቆሻሻ ይሰበስባል። የደም ስር ግድግዳ ላይ የተከማቸ ኮሌስትሮልን በመልቀም (pick up loose cholesterol from foam cells in the artery wall) የኤች ዲ ኤል ቅንጣት ሆድ ውስጥ ኮሌስትሮሉን ለማጓጓዝ እንዲመች በፓኬጅ በፓኬጅ ጠቅለል ጠቅለል ያደርገዋል (enzymatic packaging)።  ከዚያማ ኮሌስትሮሉን አዝሎ ወደጉበት ይመልስና ያራግፋል። ጉበት ሆዬ የተራገፈለትን ኮሌስትሮል የቻለውን ያክል አደባይቶ በሃሞት መልክ እንዲዎገድ ያደርጋል። ይህ ኮሌስትሮል የመልሶ ማጓጓዝ ሂደት Reverse Cholesterol Transport ይባላል።


ኤች ዲ ኤል ትጉህ የጽዳት ሰራተኛን ይመስላል የሚባለው ለዚህ ነው። ደም ስር ላይ የተከማቸን ኮሌስትሮል ለቅሞ በማሸግ ወደጉበት ይመልሳል። በዚህ ተግባሩም በደም ግድግዳ ላይ የሚፈጠር የኮሌስትሮል ክምችት ይቀንሳል፣ ስለሆነም የልብ ህመም ተጋላጭነት ያሻሽላል። ሻል ያለ የኤች ዲ ኤል መጠን/ተግባር ያላቸው ሰዎች ለልብ እና ሌሎች የደም ስር ህመሞች የመጋለጥ እድላቸው ይቀንሳል። በአንጻሩ በጣም አነስተኛ የኤች ዲ ኤል መጠን/ተግባር ያላቸው ሰዎች ለልብ እና ሌሎች የደም ስር ህመሞች የመጋለጥ እድላቸው ይጨምራል።


ኤች ዲ ኤል ደሊቨሪም (delivery) ይሰራል። ስቴሮይድ ሆርሞን ለሚያመርቱ (steroid hormones) አድሬናል ግላንድ (adrenal gland) እና የወንድ/የሴት ዘር ፍሬዎች (testes, ovary) ሆርሞን ለማመንጨት የሚያስፈልጋቸውን ግብአት የሚያደርስላቸው (ደሊቨር የሚያደርግላቸው) ኤች ዲ ኤል ነው። ከኤች ዲ ኤል በተጨማሪም እነዚህ ስቴሮይድ ሆርሞን የሚያመነጩ እጢዎች (glands) ሆርሞን ለማምረት የሚያስፈልጋቸውን የኮሌስትሮል ግብአት በራሳቸው ህዋሳት ውስጥ በበቂ መጠን ሊያመርቱት ይችላሉ። የኤች ዲ ኤል የዴሊቨሪ ስራ የግድ አያስፈልጋቸውም ማለት ነው።


‘ኮሌስትሮል ለቴስቶስቴሮን ሆርሞን ይጠቅማል’ የምትለዋ ጥራዝ ነጠቅ መረጃ ከዚህ የተወሰደ መሆኑ ነው። ጎጂ ኮሌስትሮልን ለመቀነስ የሚታዘዙ የኮሌስትሮል መቀነሻ መድሃኒቶች በፍጹም ይህን የኤች ዲ ኤል ተግባርና ሂደት አያስተጓጉሉም። ስታቲን የስቴሮይድ ሆርሞኖችን እንዲቀንስ አያደርጉም። ይልቁንም ከውፍረትና ኮሌስትሮል ምክንያት ወደመራቢያ አካሎቻችን የሚሄደው ደም ስለሚቀንስ ስንፈተ ወሲብ ሊያስከትል ይችላል። እዚህ ላይ አጥፊው የጎጂ ኮሌስትሮል መብዛት እንጅ የኮሌስትሮል መቀነሻ መድሃኒቱ አይደለም።


ኤች ዲ ኤል ለማስተካከል የሚረዱ መፍትሄዎች

የኤች ዲ ኤል መጠን ለወንድ ከ40 mg/dL በላይ፤ ለሴት ደግሞ ከ50 mg/dL በላይ እንዲሆን ይመከራል።


በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ዋነኛው መፍትሄ ነው።


ጤናማ አመጋገብ ማዘውተርም ጥሩው ኮሌስትሮል ከፍ እንዲል ይረዳል።


ሲጋራ ፈጽሞ አለማጨስ ይመከራል።


ቦርጭ ማጥፋትም እንዲሁ ጠቃሚ ነው።


ኤች ዲ ኤልን ለመጨመር የሚረዱ አንዳንድ መድሃኒቶች ያሉ ቢሆንም ከልብ ህመም የመጠበቅ ሃይላቸው እምብዛም ነው። አሁን ላይ ያለው የኮሌስትሮል ህክምና ትኩረት ጠቃሚውን ለመጨመር ከመታገል ይልቅ ጎጂ ኮሌስትሮልን መቀነስ ላይ ነው።


ማጠቃለያ

ኤች ዲ ኤል ጎጂ ኮሌስትሮልን ከደም ቧንቧዎች ግድግዳ ላይ ለማፅዳት ይረዳል በተጨማሪም ኮሌስትሮልን በሚፈልግበት ቦታ ያቀርባል። የኮሌስትሮል መቀነሻ መድሃኒቶች ዋና ስራቸው ጎጂ ኮሌስትሮልል (LDL) መቀነስ ስለሆነ ኤች ዲ ኤል ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የላቸውም።


‘የኮሌስትሮል ጥቅማጥቅሞችን’ እያወሱ የኮሌስትሮል መቀነሻ መድሃኒቶችን የሚወቅሱ የማህበራዊ ሚዲያ መረጃዎች ስህተት ኤች ዲ ኤልን (HDL) ከጎጂ ኮሌስትሮል ለመለየት ስለሚከብዳቸው ነው።

ኤች ዲ ኤል እንደጽዳት ሰራተኛ እና ደሊቨሪ/ተላላኪ ሆኖ የሚያገለገለግል ሲሆን ብቻውን ግን የጎጂ ኮሌስትሮልን ጉዳቶች ሙሉ በሙሉ ሊያስቀር አይቻለውም። ፈጣሪ ከቸረን የኤች ዲ ኤል ጠቃሚ ተግባራት በተጨማሪ ስለሆነም ጎጂ ኮሌስትሮልን በተረጋገጡ የሕክምና ዘዴዎች መቆጣጠር  ልብን ያለመልማል፣ ካለእድሜ መሞትን ይከላከላል።


ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ።


በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ  Blog, Telegram, YouTube & Tiktok ይከታተሉ።

ስለስቴሮይድ መድሃኒቶች ጥያቄ፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ካለዎት በዚህ አድራሻ ሊንክ ይጻፉልኝ።

ይህን መረጃ ጠቃሚ ሆኖ ካገኙት ለሌሎች ያጋሩ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top