በማህበራዊ ሚዲያ ከሚሰራጩ ጤና ነክ ‘አሉሽ አሉሽ ወሬዎች’ መካከል ‘ኮሌስትሮል የጤና ጉዳት አያመጣም እንዲያዉም ሊጠቅም ይችላል’ የሚል አሳች መረጃ ይገኝበታል። ‘ደግሞስ እንደኢትዮጵያ ያለ ገና በቀን ሶስቴ መብላት እውን ላልሆነበት ሃገር፣ ጮማ ሳንቆርጥ? ቅቤ ሳንጠጣ? የምን ኮሌስትሮል ነው?!’ የሚሉም አይጠፉም።
ይህ አስተሳሰብ የኮሌስትሮል ችግርን ጮማ የሚያዘወትሩ፣ ውፍረት የሚያጠቃቸው የአደጉ ሃገሮች በሽታ ብቻ አድርጎ የመቁጠር የተሳሳተ ግንዛቤ ነው። የኮሌስትሮል ችግር ዘር፣ ሃይማኖት፣ ጾታ፣ የኑሮ ደረጃ ሳይለይ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል የሚያጠቃ ህመም ነው።
ከላይ በርእሱ ያነሳነውን ጥያቄ ቀላሉ መልስ ‘አዎ፤ ኮሌስትሮል ለጤና ጎጂ ነው’ ሲሆን እንደሚከተለው እናብራራው።
ከፍተኛ ኮሌስትሮል ለጤና ጠንቅ የሚሆነው እንዴት ነው?
ኮሌስትሮል ደማችን ውስጥ ሲበዛ የደም ስር ውስጥ ዘልቆ በመስረግ ግድግዳው ላይ እንደሙጫ ይጣበቃል። በጊዜ ሂደት እየደደረ የኮሌስትሮል ንጣፍ ይሰራል። ቀስ በቀስ የደም ስር ግድግዳ ላይ እየተከማቸ የደም ቧንቧዎችን ያጠባል። ይህ ሂደት አቴሮስክሌሮሲስ (atherosclerosis) ይባላል።
ውሎ አድሮ የደም ስር እያጠበበ የደም ዝውውርን ይገታል፤ የደም ፍሰትን ይቀንሳል።
በሂደት የደም ቧንቧዎች መደፈን ያስከትላል። ይህ ማለት ልብ፣ አንጎል እና ሌሎችም ወሳኝ የሰውነታችን ክፍሎች በቂ ደም (ምግብ እና ኦክስጂን) አይደርሳቸውም ማለት ነው። በተለይ የደም ግድግዳው ላይ የተከማቸው የስብ ግግር በድንገት ተሰንጥቆ የረጋ ደም ከፈጠረ (plaque rupture) በቅጽበት የደም ስር ሙሉ በሙሉ ስለሚዘጋ ድንገተኛ ሞት ሊያስከትል ይችላል።
ይህ የደም ስር መጥበብ ልብ ላይ ሲከሰት ድንገተኛ የልብ ድካም (Heart attack) የሚባል ገዳይ የሆነ ከባድ ድንገተኛ አደጋ ይደርሳል። ወደ አንጎላችን የሚሄደው የደም ስር ሲጎዳ ደግሞ ድንገተኛ የአንጎል መታዎክ (ስትሮክ) ይባላል። ወደእግር የሚሄደው የደም ፍሰት ሲቋረጥ (peripheral arterial disease) ደግሞ ጋንግሪን (gangrene) ያመጣል። እነዚህ የደም ስር ህመሞች ሁሉም መንስኤቸውና ህክምናቸው ተመሳሳይነት ያለው ሲሆን በአንድ ላይ ስር የሰደደ የደም ስር ህመም (atherosclerotic cardiovascular diseases, ASCVD) ተብለው ይጠራሉ።
ስለኮሌስትሮል የሚወሩ የተሳሳቱ መረጃዎች
1. ምንም የህመም ስሜት ከሌለብኝ ስለኮሌስትሮል ማሰብ አይገባምን?
አንዱ የኮሌስትሮል ህመም ክፋት ከፍተኛ ኮሌስትሮል መኖሩ ምንም ዓይነት ምልክቶች አያሳይም። ከፍተኛ ኮሌስትሮል በሰውነት ውስጥ ስር የሰደዱ ችግሮችን እስኪያመጣ ድረስ ምንም ዓይነት ምልክቶች አያሳይም። ምልክት አልባ ነው። ኮሌስትሮል ድንገተኛ የልብ ድካም (heart attack) ወይም የአንጎል መታዎክ (stroke) እስኪያስከትል ድረስ ምንም የህመም ምልክት ላያሳይ ይችላል።
ከፍተኛ ኮሌስትሮል እንዳለ ለማወቅ ብቸኛው መንገድ የደም ምርመራ በማድረግ ነው።
2. ወፍራም ስላልሆንኩ ስለኮሌስትሮል አያሳስበኝምን?
የኮሌስትሮል ህመም የሁሉም ሰው ጉዳይ እንጂ ቦርጭ ላላቸው ብቻ አይደለም! ማንኛውንም ሰው ሊያጠቃ ይችላል — አንተ/ችንም ጭምር!
የኮሌስትሮል ህመም ክብደት፣ የአመጋገብ ዘይቤ፣ ማህበራዊ ሁኔታ፣ የሃብት መጠን፣ ሃይማኖት፣ ዘር፣ እድሜና ጾታ ሳይለይ በማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት ይችላል።
ቀጭን ሰዎችም ከኮሌስትሮል ህመም ነፃ አይደሉም። መደበኛ ወይም ዝቅተኛ ክብደት ያላቸው ያላቸው ሰዎች በዘረመል ወይም በሌላ ሜታቦሊዝም በሚያዛቡ ህመሞች ምክንያት የኮሌስትሮል መጠናቸው አስደንጋጭ ደረጃ የሚሆንበት ብዙ አጋጣሚዎች አሉ። የኮሌስትሮል መጠን ሁልጊዜ ከውጭ አይታይም። በደም ምርመራ ብቻ ነው ማወቅ የሚቻለው።
3. አመጋገቤ ጥሩ ስለሆነ የኮሌስትሮል ጉዳይ አይመለከተኝም?
ጤናማ አመጋገብ በኮሌስትሮል መጠን ላይ ከፍተኛ በጎ ተጽእኖ ያለው ቢሆንም ኮሌስትሮል ከቅባታማ/ጮማ ምግብ ብቻ አይደለም የምናገኘው። ምንም ጮማ የማይቀምስ ወይም ምንም የእንሣት ተዋጽኦ የማይወስድ ሰውም የኮሌስትሮል ህመም ሊኖርበት ይችላል። ከምግብ ከምናገኘው በተጨማሪ ጉበታችን ከፍተኛ ኮሌስትሮል ያመርታል።
ኮሌስትሮል ለማስተካከል የሚረዱ ተግባራዊ ምክሮች
ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ (Healthy Lifestyle)
ጤናማ የአኗኗር ዘይቤዎችን ማዘውተር ኮሌስትሮልና ከኮሌስትሮል ጋር የተያያዙ የልብና የደም ስር ህመሞችን ለማከም የማይተካ ሚና ይጫወታል። ጥሩነቱ አባዛኛዎቹ ለኮሌስትሮል ህክምና የሚመከሩ የአኗኗር ለውጥ መፍትሄዎች በቀላሉ ተግባራዊ ሊደረጉ የሚችሉ ናቸው።
ጤናማ የአኗኗር ዘዬ መከተል ሲባል የሚከተሉትን ያካትታል
• ጤናማ እና የተመጣጠነ አመጋገብ ማዘውተር፤ አትክልትና ፍራፍሬን የማእዳችን ግማሽ ያህል አድርገን መመገብ ይገባል። እህል እና ጥራጥሬም ስንጠቀም በፋብሪካ የተቀነባበረ ከሚሆን ሙሉ እህል ከነፋይበሩ ቢሆን ይመከራል። ገንቢ ምግቦችም ጮማ የሌላቸው እንዲሆን ማድረግ ይገባል። ጣፋጭ መጠጦችን እና ዲዘርቶችን ያስወግዱ።
• በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣
• ክብደትን ማስተካከል በተልይም ቦርጭ ማጥፋት፣
• አልኮል መጠጥ መቀነስ፣
• ጭንቀት መቀነስ፣
• በቂ እንቅልፍ መተኛት፣
• ጎጂ ሱሶችን ማስወገድ
የኮሌስትሮል መቀነሻ መድሃኒቶች
በተለይም የልብና ተያያዥ የደም ስር ህመም ያላቸው፣ ተደራራቢ አጋላጭ ህመም (multiple risk factors) ያላቸው ታካሚዎች እንዲሁም የኮሌስትሮል መጠን ከላይ በጠቀስናቸው የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ ካልተስተካከለ የኮሌስትሮል መቀነሻ መድሃኒት መውሰድ ያስፈልጋቸዋል። እነዚህ የኮለስትሮል መቀነሻ መድሃኒቶች የኮሌስትሮል ጉዳቱ ስር ሳይሰድ እና የማይመለስ ጠባሳ ሳይጥል በጊዜ መጀመር መልካም ነው።
ዋናዎቹ የኮሌስትሮል መቀነሻ መድሃኒቶች ስታቲን (statin) በመባል ይታወቃሉ። በርካታ የስታቲን መድሃኒት አይነቶች ቢኖሩም ኮሌስትሮልን በከፍተኛ ሁኔታ በማስተካከል ውጤታማነታቸው የተረጋገጠው ሮሱቫስታቲን (Rosuvastatin) እና አቶርቫስታቲን (Atorvastatin) የተባሉት የስታቲን መድሃኒቶች ናቸው።
ማጠቃለያ
አዎ! ከፍተኛ የደም ኮሌስትሮል ለጤና ጎጂ ነው። ምክንያቱስ ቢባል ኮሌስትሮል እንደማስቲካ የደም ስር ግድግዳ ላይ እየተለጠፈ የደም ስር ያጠባል፣ የደም ዝውውርን ይገታል፤ የደም ፍሰትን በመድፈን ድንገት ልብ እንዲደክም፣ አንጎል ታውኮ ፓራላይዝ እንዲሆን ሊያደርግ ይችላል።
በጊዜ ምርመራ በማድረግ ጤናዎትን አስቀድመው መጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራዊ እርምጃዎችን ዛሬዉኑ ይውሰዱ።
ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ።
በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ Blog, Telegram, YouTube & Tiktok ይከታተሉ።
ስለስቴሮይድ መድሃኒቶች ጥያቄ፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ካለዎት በዚህ አድራሻ ሊንክ ይጻፉልኝ።
ይህን መረጃ ጠቃሚ ሆኖ ካገኙት ለሌሎች ያጋሩ።