ስኳር ህመም ጋር የሚመጣ የኮሌስትሮል መዛባት (Diabetic Dyslipidemia)

ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለምከታተላቸው የስኳር ታካሚዎች የኮሌስትሮል መድሃኒት ሳዝዝ ከሚያጋጥሙኝ የታካሚዎች ምላሽ መካከል አንዱና ዋነኛው ‘ዶክተር፣ እኔ አልደላኝ፣ ጮማ አልቆርጥ፣ ቅቤ አልጠቀም፣ ያማረ አልበላ። እንዴት ነው እኔ ኮሌስትሮል የሚኖርብኝ? ኑሮን ሳላሸንፍ ኮሌስትሮል ከየት ይመጣል? ለምንድን ነው እንደሃብታም የኮሌስትሮል መድሃኒት የምወስደው? ደሞ ሰራተኛ የለኝ በየት እርፌ ስለፋ እኮ ነው የምወለው!’ የሚል ይገኝበታል። ይህ አስተሳሰብ የኮሌስትሮል ችግርን ጮማ የሚያዘወትሩ የባለሃብቶች በሽታ ብቻ አድርጎ የመቁጠር የተለምደ የተሳሳተ ግንዛቤ ነው። የኮሌስትሮል ችግር በተለይ የስኳር ህመም ያለባቸውን ሰዎች ዘር፣ ሃይማኖት፣ ጾታ፣ የኑሮ ደረጃ ሳይለይ ሁሉንም የሚያጠቃ ህመም ነው።


የስኳር ህመም ሲባል የደም ስኳር ከፍ ማለት ስለሆነ ስኳሩን ማስተካከል ብቻ በቂ ነው ብለው የሚያስቡ አሉ። ነገር ግን የስኳር ህመም ጋር ተያይዞ የሚከሰተው የኮሌስትሮል መዛባት ከስኳሩ እኩል ትኩረትና ህክምና ይፈልጋል። የስኳር ህመም ተጓዳኝ የጤና ችግሮችን ተጋላጭነት ለመቀነስ ኮሌስትሮልን ማከም ወሳኝ ነው።


ከስኳር ህመም ጋር የሚመጣ የኮሌስትሮል መዛባት (Diabetic Dyslipidemia) ምንነትና ጉዳት

ይህ የኮሌስትሮል ችግር የስኳር ህመም (diabetes mellitus)፣ ከመጠን በላይ ውፍረት (obesity) እና የኢንሱሊን ስራ መስተጓጎል (insulin resistance) ሲኖር የሚከሰት የደም ቅባት መዛባት ሲሆን የልብና የደም ሥር በሽታዎች ታጋላጭነትን በጣም ይጨምራል።


ይህ ከስኳር ህመም ጋር የሚመጣ የኮሌስትሮል መዛባት ዋነኛ መገለጫው

1.           የትራይግሊሲራይድ መጨመር (triglycerides ↑)፣

2.           የኤች ዲ ኤል (ጥሩ ኮሌስትሮል) መቀነስ (HDL-C ↓) እና

3.           የኤል ዲ ኤል (ጎጂ ኮሌስትሮል) መጠን እና ቅርጽ ለውጥ (small and dense LDL particles) ናቸው።


በደም ምርመራ ላይ የሚታየው የኮሌስትሮል ዉጤት በጣም ከፍ ባይል እንኳን የኮሌስትሮል መጠን (size)፣ እፍጋት (ጥቅጥቅ ማለት) እና ቅርጽ ለውጥ ስላለው የበለጠ መርዛማ እና ጎጂ ይሆናል። መጠናቸው ማነሱ እና ጥቅጥቅ ያሉ ስለሆኑ ኮሌስትሮል በቀላሉ የደም ስር ግድግዳ ዘልቆ በመግባት እንደማስቲካ ይጣበቃሉ።


ኮሌስትሮል ደማችን  ውስጥ ሲጠራቀም የደም ስር ግድግዳ ላይ እንደሙጫ ይጣበቃል። በጊዜ ሂደት እየደደረ የኮሌስትሮል ንጣፍ ይሰራል። ቀስ በቀስ የደም ቧንቧዎችን ያጠባል። ይህ ሂደት አቴሮስክሌሮሲስ (atherosclerosis) ይባላል። ውሎ አድሮ የደም ስር እያጠበበ የደም ዝውውርን ይገታል፤ የደም ፍሰትን ይቀንሳል። በሂደት የደም ቧንቧዎች መደፈን ያስከትላል። ይህ የደም ስር መጥበብ ልብ ላይ ሲከሰት ድንገተኛ የልብ ድካም (Heart attack) የሚባል ገዳይ የሆነ ከባድ ድንገተኛ አደጋ ይደርሳል። ወደ አንጎላችን የሚሄደው የደም ስር ሲጎዳ ደግሞ ድንገተኛ የአንጎል መታዎክ (ስትሮክ) ይባላል። ወደእግር የሚሄደው የደም ፍሰት ሲቋረጥ (peripheral arterial disease) ደግሞ ጋንግሪን (gangrene) ያመጣል። እነዚህ የደም ስር ህመሞች ሁሉም መንስኤቸውና ህክምናቸው ተመሳሳይነት ያለው ሲሆን በአንድ ላይ ስር የሰደደ የደም ስር ህመም (atherosclerotic cardiovascular diseases, ASCVD) ተብለው ይጠራሉ።


መንስኤው ዘረፈ ብዙ ሲሆን  በዋናነት ከስኳር ህመም እና ውፍረት ጋር የተያያዘው የኢንሱሊን ስራ መስተጓጎል (insulin resistance) ምክንያት የሚመጣ ነው። የአኗኗር ሁኔታዎች መዛባት ማለትም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማዘውተር፣ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ አልኮል መጠጣት እንዲሁም ሲጋራ ማጨስም ሌላኛው መንስኤዎች ናቸው።


የኮሌስትሮል ህመም ምልክቶች ምንድር ናቸው?

ከፍተኛ ኮሌስትሮል ለብዙ ሰዎች ምንም ዓይነት ምልክቶች አያሳይም። ከፍተኛ ኮሌስትሮል በሰውነትዎ ውስጥ ሌሎች ችግሮችን እስኪያመጣ ድረስ ምንም ዓይነት ምልክቶች አያሳይም። 


ምልክት አልባ ነው። ከፍተኛ ኮሌስትሮል እንዳለ ለማወቅ ብቸኛው መንገድ የደም ምርመራ በማድረግ ነው።


የኮሌስትሮል ህክምና ግብ (therapeutic targets of cholesterol treatment)

ኮሌስትሮልን በተገቢው ሁኔታ ማከም የልብን እና ተያያዥ የደም ስር ህመሞችን ተጋላጭነት ለመቀነስ ይረዳል። ከፍ ያለ የኮሌስትሮል መጠን በተለይም የጎጂ ኮሌስትሮል የሚፈለገውን ያክል ቁጥጥር ውስጥ አለመሆን ለልብ ድካም፣ ለስትሮክ እና ሌሎችም የደም ስር ህመሞች ተጋላጭነት በእጅጉ እንደሚጨምር ያለጥርጥር የተረጋገጠ ሳይንስ ነው።


የአብዛኛዎቹ የኮሌስትሮል ህክምና መመሪያዎች ዋናው የኮሌስትሮል ሕክምና ግብ ጎጂ ኮሌስትሮልን (LDL-C) መቀነስ ነው። የስኳር ህመም ላለባቸው ታካሚዎች የሚመከረው የኮሌስትሮል ህክምና ግብ እንደሚከተለው በሰንጠረዥ ተመላክቷል።

የልብ ህመም ተጋላጭነት ደረጃ              የስኳር ህመም ደረጃ የጎጂ ኮሌስትሮል (LDL-C) ግብ
የደም ስር ህመም ከተከሰተ በኋላ ድጋሜ እንዳይመጣ ለመከላከል – secondary prevention ከስኳር ህመም ጋር የተያያዙ የደም ስር ህመሞች ካሉ ለምሳሌ የልብ ድካም፣ ስትሮክ፣ ደረጃ 4 የኩላሊት ህመም <55 mg/dl
የደም ስር ህመም እንዳይከሰት አስቀድሞ ለመከላከል – primary prevention ከላይ የተጠቀሱት የስኳር ተጓዳኝ ህመም የሌላቸው <70 mg/dl
የኮሌስትሮል ህክምና ግቦች ለስኳር ታካሚዎች


የኮሌስትሮል መጠንን  የተቻለውን ያክል መቀነስ በተለይም ኮሌስትሮልን ከመጀመርያው መጠን ቢያንስ በ50% መቀነስ የልብ ሕመምን አደጋ ለመቀነስ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። በተቻለ መጠን እና ፍጥነት ኮሌስትሮልን በደንብ ዝቅ ማደረግ ይመከራል [faster and the lower, the better]።


መደበኛ የጤና ምርመራዎች፣ የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች (እንደ ጤናማ አመጋገብ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ) እና እንዳስፈላጊነቱ የኮሌስትሮል መድሃኒት መውሰድ እነዚህን ግቦች ለማሳካት የየራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ።


ከስኳር ህመም ጋር የሚመጣ የኮሌስትሮል መዛባት እንዴት ይታከማል?

የስኳር ህክምና ዘርፈ ብዙ የተቀናጀ የአደጋ ተጋላጭነት ቅነሳ ማድረግ ይፈልጋል። የስኳር ህመምን እና ተያያዥ የኮሌስትሮል ችግር ለማከም ሁሉን አቀፍ የሆነ፣ ታካሚውን ያማከለ ህክምና ይፈልጋል። በተናጥል ስኳሩን ብቻ ወይም ኮሌስትሮሉን ብቻ ስለታከመ ጤና በተፈለገው መጠን ላይስተካከል ይችላል። ስለዚህ ሁሉን አቀፍ ማስተካከያዎች ማድረግ ማለትም ስኳር ማስተካከል፣ ኮሌስትሮል ማከም፣ ግፊት መቆጣጠር፣ ቦርጭ ማጥፋት እንዲሁም መደበኛ የልብ፣ የአይን፣ የኩላሊት ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል።


የኮሌስትሮል መቀነሻ መድሃኒቶች

በተለይም የልብና ተያያዥ የደም ስር ህመም ያላቸው እንዲሁም ተደራራቢ አጋላጭ ህመም (multiple risk factors) ያላቸው የስኳር ታካሚዎች የኮሌስትሮል መቀነሻ መድሃኒት ያለማቋረጥ መውሰድ ያስፈልጋቸዋል።


ዋናዎቹ የኮሌስትሮል መቀነሻ መድሃኒቶች ስታቲን (statin)  በመባል ይታወቃሉ። በርካታ የስታቲን መድሃኒት አይነቶች ቢኖሩም ኮሌስትሮልን በከፍተኛ ሁኔታ በማስተካከል ውጤታማነታቸው የተረጋገጠው ሮሱቫስታቲን (Rosuvastatin) እና አቶርቫስታቲን (Atorvastatin) የተባሉት የስታቲን መድሃኒቶች ናቸው።


ስታቲን የልብና የደም ስር ሀመሞች ህክምና የጀርባ አጥንት ናቸው። የልብ ህመምን እንዲሁም ሌሎች የደም ስር ህመሞችን ተጋላጭነት በእጅጉ የሚቀንሱ፣ ዉጤታማ እና ደህንነታቸው የተጠበቀ እንደሆነ በበርካታ ጥናቶች እና ምርምሮች የተረጋገጠ ነው። ስታቲኖች ጎጂ ኮሌስትሮልን ከመቀነስ ባለፈ በበርካታ መንገዶች የደም ስር ጤናን ይጠብቃሉ። የልብ ድካምንን እና ሌሎችንም ስር የሰደዱ የደም ስር ህመሞች ከ25 እስከ 40 በመቶ ያህል ይቀንሳሉ።


ስለሆነም ስታቲን የልብ ህመም ላለባቸው እና እድሚያቸው ከ40 አመት በላይ ለሆነ ከፍተኛ ተጋላጭነት ላላቸው የስኳር ታካሚዎች ይታዘዛሉ።


ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ (Healthy Lifestyle)

ኮሌስትሮልን ለመቆጣጠር መድሃኒት መውሰድ ብቻ በቂ አይደለም። ይልቁንም ጤናማ የአኗኗር ዘይቤዎችን ማዘውተር ኮሌስትሮልና ከኮሌስትሮል ጋር የተያያዙ የልብና የደም ስር ህመሞችን ለማከም የማይተካ ሚና ይጫወታል። ጥሩነቱ አባዛኛዎቹ ለኮሌስትሮል ህክምና የሚመከሩ የአኗኗር ለውጥ መፍትሄዎች በቀላሉ ተግባራዊ ሊደረጉ የሚችሉ ናቸው።


ጤናማ የአኗኗር ዘዬ መከተል ሲባል ጤናማ እና የተመጣጠነ አመጋገብ ማዘውተር፣ በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እንዲሁም አልኮል መጠጥ መቀነስ ለኮሌስትሮል ህክምና መሰረታዊ ናቸው። በተጨማሪም ጭንቀት መቀነስ፣ በቂ እንቅልፍ መተኛት፣ ጎጂ ሱሶችን ማስወገድ እና ክብደትን ማስተካከል መልካም ነው።


ለሁሉም ሰው የሚሰራ የአመጋገብ ቀመር ማስቀመጥ ያስቸግራል። ዋናው በዘላቂነት መተግበር የሚችል ስልት መንደፍና በየጊዜው እያሻሻሉ መሄድ መልካም እንደሆነ አብዛኛውን የስነ ምግብ ባለሙያዎች የሚያስማማ ጉዳይ ነው።


ኮሌስትሮልን ለማስተካከል የሚረዱ አመጋገብ ልምዶች መካከል የሚከተሉትን ያካትታል።

  • አትክልትና ፍራፍሬ፡ በፋይበር፣ በቪታሚኖች እና በፀረ-ኦክሲዳንት የበለጸጉ ፍራፍሬዎች እና አትክልቶች መጥፎ ኮሌስትሮልን ለመቀነስ ይረዳሉ። ሁሌም ግማሹን የምግብ ሳህንዎትን ክፍል እንደ ኢትዮጵያ ባንዲራ በተ፤ለያዩ ቀለማት የአሸበረቁ ቅጠላ ቅጠሎች እና ፍራ ፍሬዎች ለመሙላት ይሞክሩ። ሲመገቡም እነዚህን በመጀመሪያ መብላት ጥሩ ነው።
  • አሰርነት ያላቸው የእህል ዘሮች፡- አሰርነታቸው ያልጠፋ ያልተፈተጉ ጥራጥሬና እህል ምግቦችም እንዲሁ የተሻሉ ናቸው።
  • ጤናማ ቅባት ያላቸው የቅባት እህሎች ለምሳሌ ለውዝ፣ አልሞንድና መሰል ዘሮች የጎጂ ኮሌስትሮል መጠንን ለማሻሻል ሊረዱ ይችላሉ። ከተጠባበሱ መቆያ ስናክ ምግቦች ይልቅ አንድ እፍኝ ለውዝ መመገብ በኮሌስትሮል ጤና ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል።
  • አሳ፡ የተለያዩ የአሳ ምግቦች ጠቃሚ የሆኑ ኦሜጋ -3 የቅባት አይነቶች የበለጸጉ ናቸው። እነዚህ የአሳ ቅባት ምግቦች ኮሌስትሮልን ለመቀነስና የደም ስር ህመምን ተጋላጨነት ይቀንሳሉ።
  • ጤናማ የዘይት አይነቶችን መጠቀም፤ ቅቤን ወይም ማርጋሪን ከመጠቀም ይልቅ በወይራ ዘይት በመተካት ጎጂ ኮሌስትሮልን መቀነስና ጥሩ ኮሌስትሮልን ከፍ እንዲል ይረዳል።
  • በፋብሪካ የተቀነባበሩና ያለቀላቸው ምግቦችን ይገድቡ። እንደ ቺፕስ፣ ኩኪስ፣ የታሸጉ ጣፋጭ ለስላሳ መጠጦችና ጁሶች፣ ለረጅም ሰአት ፍሪጅ የቀዘቀዙ ተጠባሽ ምግቦች መመገብ ይገድቡ። በሳቹሬትድ ፋት እና ትራንስ ፋት የበዛባቸው የተጠበሱ እና የተቃጠሉ ምግቦችን አይጠቀሙ። ቀይም ይሁን ጮማ ስጋ እና ቅቤ ከፍተኛ  ሳቹሬትድ ፋት መጠን ስላላቸው እነዚህን ምግቦች መገደብ የኮሌስትሮል ውጤትን ለማሻሻል ይረዳል።

ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ።


በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ  Blog, Telegram, YouTube & Tiktok ይከታተሉ።

ስለስቴሮይድ መድሃኒቶች ጥያቄ፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ካለዎት በዚህ አድራሻ ሊንክ ይጻፉልኝ።


ይህን መረጃ ጠቃሚ ሆኖ ካገኙት ለሌሎች ያጋሩ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top