የስቴሮይድ መድሃኒቶችን ካለአግባብ ለህመም ማስታገሻነት መጠቀም ጉዳቶች (Inappropriate glucocorticoid use)

ካለጤና ባለሙያ ትእዛዝ የስቴሮይድ መድሃኒቶችን (Glucocorticoids) ለህመም ማስታገሻነት በተደጋጋሚ መጠቀም አደገኛ የጤና ችግሮች ያስከትላል። ብዙ ሰው እነዚህን በሃኪም ማዘዣ ብቻ መታዘዝ ያለባቸውን መድሃኒቶች ከየፋርማሲው ለማንኛውም ህመም ማስታገሻነት እየገዛ በየወሩ ወይም አልፎ አልፎ መርፌ መወጋት የተለመደ ሆኗል።


በጣም የተለመደው Diclo-Dexa (diclofenac + dexamethasone) አደባልቆ መወጋት ነው። ለሪህ፣ ለጀርባ ህመም ወይም ሌላ ህመም ለማስታገስ ሃይለኛ ነው ስለሚባል ብዙ ሰው በየሰፈሩ መወጋት ተዘውትሯል። አንዳንዴ ‘እስኪ የብርዷን መርፌ ዉጋኝ?’ እያሉ በየጊዜው የሚጠቀጠቁ ሰዎችም አጋጥመዉኛል። እነዚህ መድሃኒቶች ከተረጋገጠ የህክምና ትእዛዝ ውጭ  በሚወሰዱበት ጊዜ ለከፋ የጤና ችግር ያጋልጣሉ። እውነት እውነት እላችኋለሁ እንዲህ ለህመም ማስተገሻ ተብሎ ቀላል መርፌ ተወግቶ በኋላ የጀርባ አጥንቱ ተሰብሮ ዊልቼር ላይ የዋለ ብዙ ሰው አለ። በዚህ ትምህርታዊ ጽሁፍ ካላአግባብ እና over-the-counter ስለሚወሰዱ የስቴሮይድ መድሃኒቶች  የሚያስከትሉትን የጤና ጠንቅ እናወራለን።


የስቴሮይድ መድሃኒቶች (Glucocorticoids) ምንድን ናቸው?

አድሬናል ግላንድ (Adrenal glands) ሰውነታችን ውስጥ በጣም ወሳኝ የሆኑ ሆርሞኖችን የሚያመነጩ የአካል ክፍላችን ናቸው። የሚገኙትም ከኩላሊት አናት ላይ እንደባርኔጣ ጉብ ብለው ነው። አድሬናል ግላንድ ከሚያመርታቸው ወሳኝ ሆርሞኖች ውስጥ ዋነኛው ኮርቲሶል (cortisol) ሲሆን ሰውነታችን ለጫና እና ውጥረት የሚሰጠውን ምላሽ፣ የደም ስኳርን፣ የደም ስኳር መጠንን እና ሌሎችም አጠቃላይ የሜታቦልዝም ሂደት በመቆጣጠር ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። በተፈጥሯዊ መጠን ውስጥ ያለ የኮርቲሶል መጠን ለጤና አስፈላጊ ነው። ነገር ግን ኮርቲሶል በተለያዬ ምክንያት ሲያንስ ወይም ሲበዛ የጤና ችግር ያመጣል። 


ግሉኮኮርቲኮይድ (Glucocorticoids) በመባል የሚጠሩት የስቴሮይድ መድሃኒቶች ሰው ሰራሽ የሆኑ ኮርቲሶል-መሰል መድሃኒቶች ናቸው። ተግባራቸውም እንደኮርቲሶል ነው። እንዚህ መድሃኒቶች ለብዙ አይነት ህመም ህክምና ጥቅም ላይ ሊዉሉ ይችላሉ። ግሉኮኮርቲኮይድ  መድሃኒቶች ዋነኛ ጸረ-ብግነት (anti-inflammatory) መድሃኒቶች ናቸው። ለአብነትም የተለያዩ የኢንፍላሜሽን፣ አለርጂ፣ አስም፣ አርትራይትስ፣ ሪህ፣ ካንሰር እና ሌሎች በርካታ ህመም አይነቶች ለማከም ጥቅም ላይ ይውላሉ። የሚዋጥ ታብሌቶች፣ አፍ ወይም አፍንጫ ወስጥ የሚነፋ፣ ቆዳ ላይ የሚቀቡ ቅባቶች፣ ጠብታ እና አንዲሁም በደም ስር የሚሰጡ መርፌዎችን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች ሊታዘዙ ይገኛሉ። እነዚህ መድሃኒቶች በሃኪም ሲታዘዙ እና በቂ ክትትል እየተደረገ ሲሰጥ ጠቀሜታቸው የላቀ ነው።


ነገር ግን አላግባብ ጥቅም ላይ ሲውሉ – በተለይም ያለሃኪም ትእዛዝ እና ተገቢ ክትትል ሳይደረግ ከተወሰደ – ከባድ እና የረጅም ጊዜ የጤና ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ።


ተገቢ ያልሆነ የግሉኮኮርቲኮይድ መድሃኒት አጠቃቀም ጠንቆች (Inappropriate Glucocorticoid Use)

በአለም አቀፍ ደረጃም ይሁን በኢትዮጵያ የግሉኮኮርቲኮይድ መድሃኒቶችን አለአግባብ መጠቀም እየተስፋፋ መጥቷል። ብዙ ሰዎች ካለሃኪም ትእዛዝ ለተለያዩ ህመም ማስታገሻነት ሲጠቀሙባቸው ይታያል። በተለይም እንደኮክቴል ዳይክሎፌናክ (diclofenac) እና ዴክሳሜታሶን (dexamethasone) ደባልቆ መወጋት እንደአቋራጭ ፈውስ ፍለጋ ተለምዷል። በኢትዮጵያ ያሉ ጥናቶች እንደሚያሳዩትም የጀርባ አጥንት ስብራት ወይም አጥንት መሳሳት ከሚያጋጥማቸው ሰዎች ውስጥ ወደ30 በመቶ የሚደርሱት እነዚህን የስቴሮይድ መድሃኒቶች ካለአግባብ በመጠቀም ምክንያት ጋር የተያያዘ እንደሆነ አረጋግጠዋል። 


 ተገቢ ያልሆነ የስቴሮይድ አጠቃቀም ሲባል ያለ አሳማኝ  የህክምና ተዛዝ ወይም ስፔሻሊስት ሃኪም ክትትል እነዚህን መድሃኒቶች መውሰድን ያመለክታል። እንዚህን መድሃኒቶች ለረዥም ጊዜ መውሰድ ከባድ የጤና እክል ያመጣል።


  • አደገኛ የሆርሞን መዛባት የሚያስከትል cushing syndrome ያጋልጣል።
  • ከመጠን ያልፈ ውፍረት ሊያመጣ ይችላል።
  • የደም ግፊት፣ የስኳር በሽታ ያጋልጣል።
  • የአጥንት መሳሳትና አደገኛ ስብራት ያስከትላል። በተለይም ለከፋ የጀርባ አጥንት እና የዳሌ ስብራት ይዳርጋል። በቀላል ጉዳት ወይም ካለምንም አደጋ ስብራቱ ሊከሰት ይችላል። አጥንቱ ከመሳሳቱ የተነሳ ትንሽ ነገር ለኮፍ ሲያደርገን ወይም ስናስነጥስ ሊሰበር ይችላል።
  • ጡንቻ ያሳሳል። ስቴሮይድ የሚወስዱ ሰዎች ቦርጫቸው እየጨመረ ጡንቻቸውእና አጥንታቸው እየሟሟ ነው የሚሄደው። በተለይም በምስራቁ የአገራችን ክፍል እንዲሁም መላ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢዎች ሰውነት ሞላ፣ ደንደን ሲል በባህል ስለሚዎደድ ሴቶች ለመወፈር እያሉ ሲወስዱት በተቃራኒው ቦርጭ ብቻ አድርጎ ለከፋ ችግር ይዳርጋቸዋል።
  • የቆዳ መሳሳትና ለኢንፌክሽን መጋለጥ፤ ስቴሮይድ በሽታ የመከላከል አቅምን ያዳክማል።

ከመሰል የጤና ችግሮች እራሳችንን እንዴት እንጠብቅ?

ዋነኛው መንገድ ከተረጋገጠ የህክምና ትእዛዝ ዉጭ እነዚህን መድሃኒቶች አለመውሰድ ነው። በአጋጣሚ ለህመም ማስታገሻ ህክምና ፈልገው ወደጤና ጣቢያ ወይም የግል ክሊኒክ ሲሄዱ የሚሰጥዎትን መርፌ ምንነት ያጣሩ።


ማጠቃለያ

ግሉኮኮርቲኮይድ መድሃኒቶች ለብዙ ህመም የሚታዘዙ መድሃኒቶች ቢሆኑም በጥበብ እና በተገቢው ክትትል ካልሆነ በርካታ መዘዝ ያመጣሉ። ለጊዜያዊ የህመም ማስታገሻ ካለአግባብ መጠቀም የረጅም ጊዜ የጤና ችግሮችን ያስከትላል። ስለሆነም እንዚህን መድሃኒቶች ከተረጋገጠ የህክምና ትእዛዝ ዉጭ የሚወስዱ ከሆነ አሁኑኑ ተገቢውን ምክር ያግኙ፤ ይመርመሩ።


ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ።


በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ  Blog, Telegram, YouTube & Tiktok ይከታተሉ።


ስለስቴሮይድ መድሃኒቶች ጥያቄ፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ካለዎት በዚህ አድራሻ ሊንክ ይጻፉልኝ።


ይህን መረጃ ጠቃሚ ሆኖ ካገኙት ለሌሎች ያጋሩ።

2 thoughts on “የስቴሮይድ መድሃኒቶችን ካለአግባብ ለህመም ማስታገሻነት መጠቀም ጉዳቶች (Inappropriate glucocorticoid use)”

  1. thank you for this informative article. my family has been affected by this non sense injections. we learned the hard way about it.

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top