ደም መፍሰስ ሊያስከትል የሚችሉ የቫይረስ ኢንፌክሽኖች የአር ኤን ኤ ቫይረስ ዝርያ ያለቸው ከባድ ሕመሞች ናቸው። በዋነኝነት የሚተላለፉት በአስተላላፊ ትንኞች ወይም በበሽታው በተያዙ ሰዎች የሰውነት ፈሳሽ ጋር በቀጥታ በመገናኘት ነው።
የበሽታው ዋና ምልክቶች ከፍተኛ ትኩሳት እና ደም መፍሰስ ያካትታል። ህክምናው በአብዛኛው የሚያካትተው የሰውነት ፈሳሽ በግሉኮስ መተካት፣ በባለሙያ ክትትል ማድረግ እና ተጓዳኝ ችግሮችን ማከም ላይ ያተኩራል።
ጥብቅ የኢንፌክሽን መከላከል እና ቁጥጥር ካልተደረገ በቀላሉ ሊስፋፉ የሚችሉ ናቸው። እነዚህ ቫይረሶች በከፍተኛ ሁኔታ ተዛማች ቢሆኑም መከላከል ግን ይቻላል። አንዳንዶቹ ክትባት ያላቸው ሲሆን በርካታ የመከላከል መንገዶች አሉ።
የቫይረሱ ዝርያዎች
እነዚህ ተዋህስያን የአር ኤን ኤ ቫይረስ ሲሆኑ የደም ስር እና የበሽታ ተከላካይ ህዋሶችን ያጠቃሉ።
| የቫይረስ ዝርያ አይነት | ቫይረስ | አስተላላፊ (Reservoirs & vectors) |
| ፍላቪቫይረስ (Flaviviridae) | ቢጫ ወባ (Yellow fever) ዴንጊ ትኩሳት (dengue fever) |
ኤደስ ትንኝ |
| ፊሎቫይረስ (Filoviridae) | ማርበርግ (Marburg virus) ኢቦላ (Ebola virus) |
የሌሊት ወፍ |
| አሬናቫይረስ (Arenaviridae) | ላሳ ቫይረስ (Lassa fever) | አይጥ |
| ናይሮቫይረስ (Nairoviridae) | ክራይሚያ-ኮንጎ ቫይረስ (Crimean-Congo hemorrhagic fever) | ክብቶች፣ መዥገር |
| ሃንታቫይረስ (Hantaviridae) | Hemorrhagic Fever with Renal Syndrome (HFRS) Hantavirus Pulmonary Syndrome (HPS) |
አይጥ |
መተላለፊያ መንገዶች
እነዚህ የቫይረስ ኢንፌክሽኖች ከሰው ወደ ሰው ወይም ከእንስሳት ወደሰው ሊተላልፉ ይችላሉ።
ከሰው ወደ ሰው፡ ከደም ሌሎች የሰውነት ፈሳሾች ጋር ቀጥተኛ ንክኪ በማድረግ ይተላለፋል። በተለይም በኢንፌክሽኑ የተያዘን ሰው በቅርበት መገናኘት፣ እንክብካቤ መስጠት አሊያም በቀብር ላይ ከፍተኛ የመተላለፍ አደጋ አለው። በቫይረሱ የተበከሉ መርፌ ወይም ሌሎች እቃዎች አስተላላፊ ናቸው።
ከአስተላላፊ እንስሳት ወደሰው (Zoonotic spillover): አይጦች፣ የሌሊት ወፍ፣ ከብቶች እና ኤደስ ትንኞች በሽታውን ወደሰው ሊያሰራጩ ይችላሉ።
የህመም ምልክቶች ምንድን ናቸው?
በቫይረስ የሚመጣ አደገኛ ትኩሳት ወምፍሳስ ደም የሰውነት የበሽታ ተከላካይ ህዋሶችን በማጥቃት የበሽታ መከላከል አቅማችንን ያዳክማሉ። የሰውነታችንን ጸረ-ቫይረስ ምላሽ ያመልጣሉ። የደም ስርን እንዲቆጣ በማድረግ ይጎዳሉ።
በቫይረሱ የተያዘ ሰው ምንም የበሽታው ምልክት ሳያሳይ እንደተዋህሲያኑ ዝርያ የሚለያይ ሆኖ ከጥቂት ቀናት እስከ ሶስት ሳምንታት ሊቆይ ይችላል።
የህመም ምልክታቸው የሚጀምረው እንደሌሎች ቫይረሶች ሁሉ ጉንፋን መሰል እንደ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የጡንቻና የመገጣጠሚያ ህመም እና ድካም ባሉ ቀላል ምልክቶች ነው። በተጨማሪም ከጊንፋን በተለየ ጠንከር ያለ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ እና የሆድ ህመም የመሳሰሉ የጨጓራና አንጀት ህመም ምልክቶች ያሳያሉ። በሽታው እየገፋ ሲሄድ ወደ ከባድ ምልክቶች ሊያድጉ ይችላሉ።በቆዳ ላይ፣ አፍና አፍንጫ ወይም የውስጥ የአካል ክፍል ላይ ደም መፍሰስ ያጋጥማል። ደም አፍስ ቫይረሶች የተባሉት ለዚያ ነው።
ህመሙ እየጸና ሲሄድ የደም ግፊት ከልክ በታች መቀነስ፣ የጉበት፣ ኩላሊት እና ሌሎችም የሰውነት ክፍሎቻችን ይጎዳሉ። ሲብስ የብዝሃ-አካል መድካም ያመጣል። ገዳይነታቸው ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው።
ከላይ የዘረዘርናቸው የቫይረሱ ምልክቶች ከሌሎች በርካታ አጣዳፊ ትኩሳት አምጭ ተላላፊ በሽታዎች ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። ለምሳሌ የወባ ህመም (ማንቀጥቀጥ የሚበረታ ሲሆን በቀላሉ የወባ ምርመራ በማድረግ ይለያል)፣ ታይፎይድ (የትኩሳቱ አጨማመር ለዬት ያለ ጸባይ አለው፣ የተበከለ ምግብ / መጠጥ መጋለጥ አጋጣሚ ይኖራል)፣ የማንጅራት ገትር ህመም፣ ኮቪድ-19 ወዘተ ተቀራራቢ ምልክቶች ሊኖራቸው ይችላል።
ምርመራዎች
አጠቃላይ የደም ምርመራ ላይ አማላክች የሆኑ የላብራቶሪዎች ሊኖሩ ይችላሉ ለምሳሌ የደም ህዋሳት ቁጥር መቀነስ፣ የጉበት ምርመራ ኖርማል አለመሆን፣ የኩላሊት ጉዳት ምልክት መኖር ወዘተ ሊገኝ ይችላል።
የቫይረስ ህመሙን ለማረጋገጥ የማረጋገጫ ምርመራ ያስፈልጋል። የቫይረሱን ዘረመል የሚለዩ ፕ ሲ አር ምርመራዎች፣ አንቲጂን ምርመራዎች፣ አንቲቦዲዎችን ያካትታሉ።
በሽታውን እንዴት መከላከል እንችላለን?
በሽታው እንዳይዛመት ዋና መከላከያ መንገዱ በቫይረሱ የተጠረጠረን ሰው መለየትና ኳራንቲን ማድረግ ነው። በበሽታው ከተያዙ ግለሰብ የሰውነት ፈሳሾች ጋር ንክኪን ማስወገድ ይገባል። እያንዳንዱ ሰው እጁን በአልኮል ወይም በሳሙና በደንብ በመታጠብ ንጽህና መጠበቅ አለበት። ከታማሚ ሰው ጋር ንክኪ ያላቸውን አልባሳት፣ እቃዎችና እና ምንጣፎችን በክሎሪን ዘፍዝፎ ማጽዳት ይገባል።
ከአስተላልፊ እንሣት ጋር ንክኪ ይቀነሱ። የትንኝ ንክሻዎችን መከላከል (ለምሳሌ ጸረ ነፍሳት፣ አጎበር መጠቀም፣ ዉሃ የሚያቁሩ እቃዎችን እና ኩሬዎችን ማጥፋት) ያስፈልጋል። ምግባችንን አይጥ እንዳይነካው በጥንቃቄ ከድኖ ማስቀመጥም ይመከራል። የተከማቹ እህሎችም ቢሆኑ ማከማቻ እቃውን በየጊዜ ማጽዳት ተገቢ ነው። የታመሙ ወይም የሞቱ እንስሳትን አይጠጉ። በከብቶች በረት እና ማረጃ ቄራዎች ሲገቡ ጓንት፣ ቦት ጫማ፣ ረጅም እጅጌ ልብሶች ይልበሱ።
በጤና ተቋማትም ከመደበኛ ጥንቃቄዎች ባሻገር የተለያዩ ኤሮሶል ብናኞችን የሚፈጥሩ የህክምና ፕሮሲጀሮች ሲሰሩ የአየር ወለድ ጥንቃቄዎች መተግበር አለባቸው። የመርፌ እና ሌሎች ቆሻሻ አወጋገድም ጥንቃቄ ይፈልጋል።
በማህበረሰብ ውስጥ ደህንነቱ የተጠበቀ የቀብር ሥነ ሥርዓቶች መተግበር አለባቸው። በበሽታው ምክንያት የሞተ ሰውን አስከሬን አለመንካትና በባለሙያ በሚገባ በአስከሬን መጠቅለያ እንዲሸፈን በማድረግ ወዲያውኑ በባለሙያ መቅበር ይመከራል።
ቢጫ ወባ መከላከያ ክትባት አላቸው። ዴንጊ ቫይረስ እና ኢቦላም ክትባት እየተሰራላቸው ነው።
ህክምና አለው?
ህክምናው በአብዛኛው የሚያካትተው የሰውነት ፈሳሽ በግሉኮስ መተካት፣ በባለሙያ ክትትል ማድረግ እና ተጓዳኝ ችግሮችን ማከም ላይ ያተኩራል። እንዳስፈላጊነቱ የትኩሳት ማብረጃ እና የህመም ማስታገሻ መስጠት ይገባል። በጣም ደም መፍሰስ ላጋጠማቸው የደም ልገሳ ሊፈልጉ ይችላሉ።
ከእነዚህ የህክምና ድጋፎች ባሻገር የሚሰጡ የጸረ-ቫይረስ ህክምናዎች እንደየቫይረሱ ዝርያ ይለያያል። እስካሁን የተረጋገጠ እና ፍቃድ ያገኘ መድሃኒት ያለ የኢቦላ ኢንፌክሽ ብቻ ነው። ሁለት መድሃኒቶች ያሉት ሲሆን ኢንማዜብ (Inmazeb) እና ኢባንጋ (Ebanga) ይባላሉ። እነዚህ መድሃኒቶች ቫይረሱ እንዳይራባ እና እንዳይፈለፈል ያደርጋሉ።
ሌሎቹ ቫይረሶች ከጥናትና ምርምር ያለፈ ጥቅም ላይ የዋለ ጸረ-ቫይረስ መድሃኒት የላቸውም።
ማጠቃለያ
በቫይረስ የሚመጣ አደገኛ ትኩሳት ወምፍሳስ ደም መከላከል የምንችለው ነገር ግን በአጭር ጊዜ ሊገድል የሚችል በሽታ ነው።
ተጨማሪ መረጃዎችን ወደ 8335 እና 952 በመደዎል ማግኘት ይችላሉ።
ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ።
በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ Blog, Telegram, YouTube & Tiktok ይከታተሉ።
ጥያቄ፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ካለዎት በዚህ አድራሻ ሊንክ ይጻፉልኝ።
ይህን መረጃ ጠቃሚ ሆኖ ካገኙት ለሌሎች ያጋሩ።